>

በኮሮና ሰበብ ተይዘው በሳዑዲ ወህኒ የሚማቅቁት ኢትዮጵያውያን "ስቃዩ በረታብን የወገን ያለህ?" እያሉ ነው...!!! (DW)

በኮሮና ሰበብ ተይዘው በሳዑዲ ወህኒ የሚማቅቁት ኢትዮጵያውያን “ስቃዩ በረታብን የወገን ያለህ?” እያሉ ነው…!!!

DW

“አምስት ወራችን ነው። ልብስ የለንም፤ ጫማ የለንም። ሽንት ቤት ባዶ እግራችንን ገብተን፤ ባዶ እግራችንን እንወጣለን። እግራችን ተመላልጧል። ሐሰሲያ የሚሉት በሽታም አለ። እከክ ማለት ነው። እንደ ፍየል በየግድግዳው እያሳከከን ነው የሚያድረው። ሕክምና ስንላቸው መጥተው እንደፈለጉት ይደበድቡናል” በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ግዑሽ ከትውልድ ቀዬው ተነስቶ የመንን በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲያመራ የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ ፍለጋ ነበር። “ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለኝም። ተሰድጄ፤ ሰርቼ ልጆቼን ለማሳደግ ነው የወጣሁት” የሚለው ግዑሽ ያለፉትን አምስት ገደማ ወራት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት እማቅቃለሁ ብሎ አላሰበም።
“ከታሰርን አምስተኛ ወር እያለቀ ነው። የምንተኛበት ስሚንቶ ነው። ብርድ ልብስ የለውም። ውኃ የምንጠጣበት እዚያው እንሸናል፤ እዚያው እንጠጣለን” የሚለው ግዑሽ “ብታየው እንዴት ተፈጠርኩ ብለህ ትናገራለህ። ያላየው ግን ማመን አይችልም” ሲል በአስከፊ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራል።
እንደ ግዑሽ ሁሉ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የሚገኘው ደስታ “ጠባብ” በሚለው አንድ ክፍል ውስጥ ብቻ 64 ገደማ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። ደስታ “እስር ቤቱ ጽዳት የለውም። ሽንት ቤቱ ፈንድቶ ወደ እኛ ይመለሳል። ጠባብ ነው። ከመጥበቡ ባሻገር እስከ 64 እንሆናለን። ተጨናንቀን ነው የምንተኛው። መንቀሳቀሻ የለውም። የሆነች መንቀሳቀሻ ትንሽ መስጊድ ነበረች እሷን በኤሌክትሪክ አድርገው ዘግተዋታል” ይላል።
“አምስት ወራችን ነው። ልብስ የለንም፤ ጫማ የለንም። ሽንት ቤት ባዶ እግራችንን ገብተን፤ ባዶ እግራችንን እንወጣለን። እግራችን ተመላልጧል። ሐሰሲያ የሚሉት በሽታም አለ። እከክ ማለት ነው። በጣም ነው የሚያሳክከው። እንደ ፍየል በየግድግዳው እያሳከከን ነው የሚያድረው። ሕክምና ስንላቸው መጥተው እንደፈለጉት ይደበድቡናል” የሚለው ደስታ ገና የ26 አመት ወጣት ነው።
ግዑሽ እና ደስታ በሳዑዲ አረቢያ መካ አቅራቢያ ታስረው ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ እንደሚሉት መጀመሪያ ከሚገኙበት የመን በሑቲ አማፂያን ለቀው እንዲወጡ በመገደዳቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲሻገሩ ነበር በድንበር ተቆጣጣሪዎች የተያዙት። ደስታ ከየመን በሑቲዎች ተገደው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲገቡ የተያዙ ኢትዮጵያውያን “በትንሹ 10 ሺሕ እንሆናለን” ሲል ግምቱን ተናግሯል።
“ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። ከድንበር ሁለት ሰዓት ያክል ሙሉ ለሊት እያጓዙን አደሩ። ከዚያ ጂዛን የሚባል እስር ቤት አስገቡን። ጂዛን አንድ አስር ቀን ቆይተናል። በጣም ጠባብ የሆነ ክፍል ሶስት መቶ አራት መቶ አጉረው ሊገድሉን ነበር ። በፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ወደ ጅዳ ለቀቁን። አገራችሁ ትገባላችሁ የሚል ምክንያት እየሰጡ ነው የለቀቁን” የሚለው ደስታ በወቅቱ በሑቲ አማፂያን የተገደሉ ጭምር እንዳሉ ያስረዳል።
“የሞቱ ጓደኞቻችን አሉ። ሳንቀብራቸው ወደ ቆሻሻ የተጣሉ በአይናችን እያየን ነው የመጣንው። አንዳንዶቹ በጭንቀት ነው አንዳንዶቹ ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት የተገደሉ አሉ። በአይኔ ያየኋቸው የማውቃቸው ጓደኞቼም አሉ። እኔ የተጎዱ እስከ አስራ ሰባት ሰዎች፤ የሞቱ ደግሞ ሶስት ሰዎች አይቻለሁ” ይላል ደስታ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ሪፖርት የኮሮና ወረርሽኝን እንደ ምክንያት በመጠቀም የሑቲ አማጽያን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማባረራቸውን እና በርካቶችን መግደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ከየመን ድንበር ያቋረጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ ድንበር ጠባቂዎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን ይኸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሪፖርት ይጠቁማል።
ሒውማን ራይትስ ዎች ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሑቲዎች “የኮሮና ቫይረስ ተሸካሚዎች” እያሉ ይዘልፏቸው እንደነበር ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ይፋ ያደረጋቸው ምስሎች እና ቪዲዮዎች አልዳየር ከተባለ ቦታ አቅራቢያ በሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ኢ-ሰብዓዊ ኹኔታ ያሳያሉ።
በአንዱ ቪዲዮ እንደሚታየው “የሰው ያለህ” የሚሉ ኢትዮጵያውያን የሚገኙበት እስር ቤት በውኃ ተጥለቅልቋል። በጂዛን በሚገኝ ሌላ እስር ቤት በጠባብ እና ንጽህናቸው ባልተጠበቀ ክፍሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ተፋፍገው ታስረው እንደሚገኙ ይታያል። ኢትዮጵያውያኑ ለቆዳ ሕመም ጭምር ተዳርገዋል። ይኸ ሕመም እነ ደስታ በሚገኙበት እስር ቤት ጭምር በበርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ተከስቷል።
“ልብሳችን አንዲት ናት። አንድ ፓንት፣ አንድ ሱሪ እና አንድ ቲ ሸርት። ይኸ ልብስ ደግሞ መቀየሪያ የለውም” የሚለው ደስታ እከክ ሲል የሚገልጸው እና በቆዳቸው ላይ የታየው ሕመም በአኗኗራቸው ምክንያት በተፈጠረ የንጽሕና ጉድለት እንደተከሰተ ያምናል።
“ሊቀጡን ከፈለጉ ማቀዝቀዣን ለሁለት እና ሶስት ቀን ያጠፉታል። ልብሳችንን አውልቀን ፓንት ብቻ ለብሰን እንቆማለን። ምክንያቱም የሳዑዲ አረቢያ ሙቀት በጣም ኃይለኛ ሙቀት ነው። አንዳንዴ ደግሞ ማቀዝቀዣን የመጨረሻ ያደርጉታል በብርድ ልናንልቅ ነው። ጉንፋን በጉንፋን እንሆናለን። ሕክምና ጠይቀን የሚሰማን አካል የለም። ከሶስት ሳምንት በፊት እዚህ የታመመ ልጅ ነበር። በሩን ደብድበን እንደምንም ብለን አስወጣንው። እስካሁን ድረስ አልተመለሰም። ሞቶ ይሁን ወይም የት እንዳስገቡት አላውቅም” የሚለው ደስታ ከእስር ቤት በማናቸውም ምክንያት የወጡ የት እንደገቡ እንደማይታወቅ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።
ባለፉት አመታት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ በኩል የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና የመንን በማቋረጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ያመራሉ። እንደ ግዑሽ እና ደስታ ሁሉ እግራቸውን ለአደገኛው ጉዞ የሚያነሱት የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ ፍለጋ ነው። ግዑሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲያመራ የሁለት ልጆቹን መፃኢ እጣ ፈንታ ለመታደግ ነበር።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የለኝም። ስለዚህ አማራጬ ተሰድጄ፤ ሰርቼ ልጆቼን ለማሳደግ ለማስተማር ብዬ ነው የወጣሁት። [ልጆቼ] አንዱ ስምንት ይሆናል፤ አንዷ አስራ ሁለት ትሆናለች። በድጎማ የሚያኖርልኝ መንግሥት የለም። ያለኝ አማራጭ ተሰድጄ ሰርቼ ልጆቼን ለማስተማር ነው። የእኔ ፋንታ እና የእኔ እጣ እንዳይደርስባቸው ማለት ነው” የሚለው ግዑሽ መቼ ከእስር እንደሚፈታ የሚያውቀው ነገር የለም።
የብሪታኒያው ዘ ሰንደይ ቴሌግራፍ ጋዜጣ የምርመራ ዘገባ ኢትዮጵያውያኑ በሳዑዲ አረቢያ ሁለት እስር ቤቶች እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል። አንዱ ሳዑዲ አረቢያ ከየመን በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በጂዛን ከተማ የሚገኝ ነው። ሁለተኛው በእስልምና እምነት ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣት የመካ ከተማ አቅራቢያ አል ሹማሲ ከተባለ ቦታ የሚገኝ ነው። ዶይቼ ቬለ ደስታ እና ግዑሽ የታሰሩበት አልሹማሲ ከሚገኘው እስር ቤት መሆኑን መረዳት ችሏል። በእስር ቤቶቹ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ማረጋገጥ አልተቻለም። የ26 አመቱ ወጣት ደስታ ግን በቦታው በጥበቃ ከተሰማሩ ወታደሮች መረጃ ጠይቆ ነበር።
“በሁለት ቡድን ነው የሚከፈለው አለኝ። አንደኛው ኤ፤ ሁለተኛው ደግሞ ቢ ይባላል። በኤ መቶ ክፍሎች፤ በቢ ደግሞ መቶ ክፍሎች አሉ። በጠቅላላ ሁለት መቶ ክፍሎች ነው ያሉ አለኝ። ስልሳ አራት ወይም ስልሳ ሶስት ሰዎች ናቸው በአንድ ክፍል ያሉት። እሱ [ወታደሩ] እንደነገረኝ ከሆነ ሁለት መቶ ክፍሎች ነው ያሉት። እኔ እርግጠኛ ልሆን አልችልም። ክፍሎቹ በሙሉ ሞልተዋል አለኝ። እስከ አስራ አምስት ወይም አስራ አራት ሺሕ የሚገመት ሰው አለ አለኝ” ብሏል ደስታ።
በአልሹማሲ እና በጂዛን በሚገኙ እስር ቤቶች በርካታ ሕንፃዎች መኖራቸውን በሳተላይት ምስሎች ያረጋገጠው ዘ ሰደንደይ ቴሌግራፍ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ሳይኖሩ አይቀሩም ብሏል።
የኮሮና ወረርሽኝን ሥርጭት ለመግታት ተብሎ በአሰቃቂ ኹኔታ የታሰሩት ኢትዮጵያውያን መቼ እንደሚፈቱ በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር የለም። ከመካከላቸው በጭንቀት ለሕመም የታደረጉ መኖራቸውን የሚናገረው ግዑሽ “አንዳንዴ በር ይሰበራል። አንዳንዴ የታሰረ ሰው ሰብሮ ለመውጣት ያስባል። ብዙ ችግር አለ” ይላል። ግዑሽ  ከሳዑዲ አረቢያ “ወታደሮች የምናገኘው መረጃ ግን መንግሥታችሁ አልቀበልም ስላለ እኛ የምናደርገው ጉዳይ የለም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  በጉዳዩ ላይ ሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ
Filed in: Amharic