>
5:18 pm - Sunday June 15, 7586

ለለውጥ ዝግጁ የሚያደርግ ቀላል ውሳኔ...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ለለውጥ ዝግጁ የሚያደርግ ቀላል ውሳኔ…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

በለውጡ ጅማሮ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተፈትነው ከሚወድቁባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች የአዲስ አበባ ጉዳይ መሆኑን ደጋግመን ገልፀን ነበር። እንደጠበቅነውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅቡልነት ተሸርሽሮ ጥያቄ ውስጥ የገባው ባለቤቶቿን ባይተዋር ባደረገችው አዲስ አበባ መሆኑ የቅድሚያ መስመር ይዟል።
ይህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገቡበት ቅርቃር መውጣት የሚችሉበት እድሎች አሁንም ተሟጠው አላለቁም። ከእነዚህ እድሎች ውስጥ አዲስ አበባን እና አዲስአበቤን በተመለከተ የሚከተሉት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ቀላል ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ምክራችንን እንለግሳለን።
፩:- ከሁለት አመት በፊት የስራ ዘመኑን የጨረሰው የእንቶ-ፈንቶዎች ስብስብ የሆነውን “የአዲስ አበባ ክልል ምክር-ቤት” አዲሱ አመት ከመግባቱ አንድ ቀን በፊት(በዋዜማው) ያሰናብቱ።
፪:- የአዲስ አበባ ካቢኔ ምድብተኛ ከንቲባዋን (“ሲም ካርድ”) ጨምሮ በአዲሱ አመት ዋዜማ ያሰናብቱ።
፫:- እስከሚቀጥለው የበጀት አመት የሚቆይ “የአዲስ አበባ የሙያተኞች ገለልተኛ ባለአደራ ክልላዊ መንግስት” ይመስርቱ።
 ( የግል ጥቆማ አቶ ክቡር ገና፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ የህግ ምሁሩ ዶክተር ደረጄ ዘለቀ፣ አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ አቶ አቡበከር፣ ወ/ሮ አስቴር በዴኔ፣ አቶ ማቲዎስ(የቀድሞ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጽህፈት-ቤት ኃላፊ))
፬:- የአዲስ አበባ ቻርተር በአዲሱ አመት ዋዜማ መሻሩን ይፋ ያድርጉ። የአዲስ አበባ ፓሊስ ተጠሪነት ሙሉ ለሙሉ ለባላደራ ምክር-ቤት ያድርጉ። ተጠሪነቱ ለባላደራ ምክርቤቱ የሆነ ” የተደራጀ ሌብነትና ዝርፊያ አጣሪ ኮሚሽን” ያደራጁ።
፭:- በቀጣዩ ግንቦት ወር የአዲስ አበባ ክልል ምክርቤት ምርጫ እንደሚካሄድ ይወስኑ። የክልል ምክርቤት የምርጫ ህጉን ያሻሽሉ።
(የግሌ ምክር-ሃሳብ: የአዲስ አበባ ክልል ፕሬዝዳንት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስአበቤ በጠቅላላ የሚመረጥ ሆኖ የሚያገኘው ድምጽ ከአጠቃላይ መራጩ ከ50 በመቶ በላይ መሆን ይኖርበታል።)
፮:- ለአዲስ አበባ በመቆርቆራቸው ምክንያት ግልጽ ጦርነት አውጀውባቸው እግረ-ሙቅ ያጠለቁባቸውን የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቅርታ ጠይቀውና የሞራል ካሳ ከፍለው በአዲሱ አመት ዋዜማ ከእስር ይፍቷቸው። ይህን በማድረግ እርሶም ከአምላኮትና ህሊናዎ ይታረቁ።
አዲስ-አበባ-ከስር-ትፈታ!
አዲስአበቤነት-ይለምልም!
ግዛት-የማስመለስ-ንቅናቄ!
Filed in: Amharic