>
5:01 pm - Friday December 2, 4664

የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም! (አሰፋ ሀይሉ)

የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም!

አሰፋ ሀይሉ

ሁሌ ይሄን ሰውዬ ባሰብኩት ቁጥር የሚመጣብኝ በመጨረሻ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በሚዲያ ላይ ቀርቦ የተናገረው የውርደት ቃሉ ነው፡- ‹‹ሱሪዬን አውልቀው ነው የገረፉኝ፣ አሁን ስማቸውን መጥራት የማልፈልጋቸው የፓርቲው ሰዎች ፊት አቅርበው ነው የገረፉኝ..!››፡፡ እያለ ሲያላዝን፡፡ ሙትቻ! ይበሉህ እንጂ አንተን አስወልቀው ያልገረፉ ማንን ይግረፉ! ከእነሱም ብሶ – በሥልጣንና በጥቅም ታውሮ – የወለደውን፣ ያሳደገውን፣ አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ያበቃውን የገዛ ወገኑን፣ የገዛ ህዝቡን ‹‹ነፍጠኛ፣ ነፍጠኛ›› ከሚሉት ጋር ተደርቦ ‹‹ነፍጠኛን በለው፣ ማንነትህን አሳየው!›› ሲል እንዳልነበር – ሥልጣናቸውን አደላድለው ሲያበቁ – በመጨረሻ እንደ ሸንኮራ ምጥጥ አርገው ወደ ከርቸሌ ተፉት! ይበለው ነው የምለው በበኩሌ!
ያኔ ታምራት ለፍርድ ሲቀርብ – በአዲስ አበባ የህግ ት/ቤት ተማሪ እያለሁ – የጠቅላይ ፍርድቤቱ ምክትል ፕሬዚደንትና የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የነበረው – መንበረፀሐይ – በትርፍ ጊዜ መምህራችን ሆኖ የተወሰኑ ኮርሶችን ሰጥቶን ነበር፡፡ እና በታምራት ላይኔ ችሎት ተሰይሞ ሲፈርድ – ፍላጎት ላላችሁ ተማሪዎች ወደ ችሎት አዳራሹ መግቢያ ካርድ በነፃ ማግኘት ትችላላችሁ – ሲለን ተሽቀዳድሜ ነበር የገባሁት፡፡ የመጨረሻዋን የፍርድ ቃል፣ መንበረፀሐይ እንዲያውም በሁለተኛው ክስ ጥፋተኛ ሊሆን አይገባውም ብሎ የተከራከረለትን የልዩነት ሀሳብ – ሁሏንም ነገር በቦታው ላይ ተገኝቼ የታምራትን ዓይን እያየሁት ነው የተከታተልኩት፡፡ በወቅቱ ሌላው ሳይጠየቅ የእሱ ዝርፊያ ብቻ ነው ወይ ለፍርድ የሚቀርበው ብዬ በማሰብ – ችሎቱ በእውነት ላይ ተመሥርቶ ፍርድ ቢሰጥም – ግን የቂም መወጫ ነው ብዬ አስቤ – እንዲያ ቆሌዋን እንደተቀማች ጠንቋይ – ያ ሁሉ ካዳሚውና ሥልጣኑ ግርማሞገሱ ሁሉ ርቆት – በችሎቱ ፊት ከጠበቃ ዮሴፍ ገብረእግዚአብሔር ጎን ቆሞ ሲቁለጨለጭ – በወጣት ልቤ በተወሰነች መልኩ አዝኜለት እንደነበር አልክድም፡፡
አሁን ግን ብዙ ነገሮችን አውጥቼ አውርጄ – የማስበው – ‹‹ዋጋው ነው!›› እያልኩ ነው፡፡ እግዜሩ ቅርብ እንደሆነ በጊዜ የተማርኩት በዚህ ሰው ነው! ፈጣሪ የእጅህን ዋጋ እዚህችው ምድር ላይ ሳትቀበላት እንደማይሸኝህ ነው ከዚህ ሰው የተገርፌያለሁ ስሞታ የተረዳሁት፡፡ ብዙዎቻችን እንደምንገምተው ሟቹ መለስ ዜናዊ መሠለኝ ታምራትን ፊቱ አስቀርቦ ‹‹ገልብጣችሁ ግረፉልኝ›› ብሎ ሱሪውን አስወልቆ ያዠለጠው፡፡ ዋነው ትኩረቴ ማን ገረፈው፣ ማን አስገረፈው አይደለም፡፡ ማንም ይሁን ማን መጨረሻው ነው የሚመስጠኝ፡፡ የሚገርመኝም፡፡ ያኔ በሥልጣን ላይ እያለ ለተዘባበተበት የአማራ ደም፣ ነፍጠኞች እያለ በገደል ተጥለው ለሞቱት ኢትዮጵያውያን ደም – የገዛ አለቃው – ደስ የሚል ዋጋውን ሰጥቶታል፡፡ በዚህስ መለስን ስሙን በበጎ ማንሳት ይገባኛል፡፡ በእውነት የሚያስመሰገን ውለታ ነው የዋለለት ለአማራ ሕዝብ፡፡
አሁን ላይ ካለፈ ከስንት ጊዜ በኋላ የታምራትን ስምና አስከፊ ዕጣ ፈንታ የማነሳው ለምንድነው? – ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ የማያቸው የብአዴን እንከፎች ደግመው ደጋግመው ታምራትን እያስታወሱኝ ነው፡፡ ዛሬም ላይ በነፍጠኛ ጥላቻ ከሰከሩት የቄሮው ባለጊዜዎች ጋር አብረው – ተሰፍሮ በተሰጣቸው የሥልጣን ወንበር ላይ ጉብ ብለው የሚያጫፍሩት፣ ‹‹የለውጥ ዘመን መጥቷል›› በሚል የጅል ስብከታቸው በወገናቸው በአማራው ደም ላይ እየተዘባበቱ ያሉት፣ ከራሱ ከቄሮው በላይ የቄሮው መንግሥት እንባ ጠባቂ ሆነው የተገኙት የጊዜያችን የብአዴን አቸፍቻፊዎች – ገዱዎቹ፣ ደመቀዎቹ፣ ተመስገኖቹ፣ ንጉሡዎቹ… – መጨረሻቸው ካሁኑ ወለል ብሎ እየታየኝ ነው ታምራትን የማነሳው፡፡ ዕድሜ ይስጠንና መጨረሻቸውን ለማየት ያብቃን፡፡
መጨረሻቸው ከቀደመው የበኩር አምሳያቸው – ከታምራት ላይኔ መጨረሻ የተለየ እንደማይሆን ብርቱ ተስፋ አለኝ! በፍጹም የተለየ አይሆንም! በነፍጠኛ ልክፍት አቅላቸውን ያጡት ተረኞች ጊዜ ገዝተው መንበራቸውን ሲያደላድሉ – እንከፎቹን የአማራ አሸንክላዎች እንደ ሸንኮራ መጥጠው የትም ይጥሏቸዋል! እግዜሩ ቅርብ ነው! ከተገረፍኩ ባዩ ታምራትም፣ ከአስገራፊው አለቃውም አጨራረስ እንዳየነው… ዘንድሮ እግዜሩ ሠማይ እስክትደርስም አይታገስህ፡፡ እዚችው በምድር ላይ የሠራሃትን አወራርደህ ነው የምትሰናበተው፡፡ ከታሪክ የማይማሩ፣ ያቺኑ ራሷኑ ታሪክ መልሰው ይደግሟታል!
ከታምራት ወዲህ – ዳግም ሱሪያቸውን አስወልቀው የገረፏቸውን እንከፎች፣ ከከርቸሌ ባህታዊና ኡስታዝ አድርገው ሲያወጧቸው – ‹‹ጉድ! ጉድ!›› እያልን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም! እንወክለዋለን ከሚለው ሕዝብ በልብም፣ በስነልቦናም፣ በፍላጎትም፣ በከንፈርም፣ በሁሉም ነገሩ የተፋታ መሪ – ሁልጊዜም መጨረሻው ከታምራት የተለየ አይሆንም፡፡ ሱሪውን አስወልቀው ያስገርፉታል፡፡ የሚጮህለትም፣ የሚያዝንለትም፣ የሚደርስለትም፣ የሚነሳለትም አያገኝም፡፡ ታምራትን ያየ – የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና እንደሌለው አይስተውም! ጊዜ ያሳየን – ብዬ ተውኩ፡፡ ይኸው ነው!
አልፋና ኦሜጋ፣ በተዓምራቱ የሚገለጥ፣ የኢትዮጵያ አምላክ፣ ስለ ድንቅ ሥራው፣ ለዘለዓለም፣ የተመሰገነ ይሁን!
የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic