ጀግኖችን ማስታወስ ጀግንነት ነው!!
ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን
በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ታሪክ፤ ወደር የሌለው የጀግና ሜዳሊያ ከተሸለሙት ሁለት ጀግኖች አንዱ ናቸው፦ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሀ/ማርያም። ሌላኛው ወደር የሌለው ዋናውን የኢትዮጵያ ጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጦር አይሮፕላን አብራሪው ፤ ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ናቸው።
.
እኚህ ሰው በተለይ በምስራቅ ጦር ግንባር ከተገኘው ከካራማራን ድል ጋር አብረው ይነሳሉ። በዚያ ወቅት (የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም) የኮሎኔል ማዕረግ የነበራቸው ተስፋዬ ሀብተማሪያም፣ በጭናክሰን ግንባር አስደናቂ ጥቃት የፈፀመውና ለታላቁ የካራማራ ድል መንገድ የከፈተው የኢትዮጵያ የፓራኮማንዶ ኅይል አዛዥ ነበሩ። በዚህም ጀግንነታቸው የተነሳ የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳሊያ ለመሸለም የበቁ ናቸው።
.
ይህም ብቻ አይደለም፤ ወደሰሜን ጦር ግንባር ኤርትራ ተጉዘው አስደናቂ ገድል የፈፀሙ የጦር መሪ ናቸው። ይህም ጀግንነታቸው በናቅፋ ሰማይ ጠቀስ ተራሮች ሥር ጎልቶ የታየው በ1960ዎቹ መጨረሻ ነበር።
በዚያ ወቅት በተዋጊነቱ እጅግ በጣም ዝነኛ የነበረው 15ኛ ሻለቃ በናቅፋ ተራሮች መሃል ሳለ ከሻዕቢያ ጋር ብርቱ ፍልሚያ ላይ ነበር። ዕርዳታም ያሻዋል። ይኼኔ ነበር በተስፋዬ ኃ/ማርያም የሚመራው 91 የሚሆኑ የአየር ወለድ አባላትን የያዘው ጦር ወደ ናቅፋ የተላከው።
.
የጦርነት ወረዳው ፈታኝ ነው። እጅግ በጣም ከፍታ ያለው ተራራማ ቦታ ላይ ነው የሚደረገው። በኮሎኔል ተስፋዬ መሪነት ከአውሮፕላን ነበር በፓራሹት የወርደው፦ ውጊያ መሃል። ወዲያውኑ ነበር በሻቢያን ጦር የተከበበው።
በዚህ ከበባ መሃል ገብቶ ነበር ለሰባት (7) ወር ከጠላት ጋር የተፋለመው። ቀለብ፤ ጥይት፤ አስፈላጊ ቁሳቁስ ወዘተ በአየር ፓራሹት (ዣንጥላ) እየተጣለለት ነበር የሚዋጋው። ያውም፤ ከአየር የሚወረወርለት ቀለብ እና ጥይት ግማሹ በንፋስ ኃይል እየተገፋ ወደጠላት ወረዳ እየወደቀበት ነበር የተፋለመው።
በሰባተኛው ወር ላይ፣ ሻዕቢያ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ በ15ኛ ሻለቃና ኮሎኔል ተስፋዬ በሚመሩት አየር ወለድ ጦር ምሽግ ላይ ጥቃት ከፈተ።
በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረቱ 750 ኪሎ ሜትር ዘልቆ በገባው የሶማሊያ ወረራ (በምስራቅ ጦር ግንባር) ላይ ነበር። ይህም፤ ናቅፋ ለነበረው ጦር ተጨማሪ ረዳት ጦር ለመላክ አላስቻለውም። ይህንን ሁኔታ የተረዳውና በሰው ኃይልም ሆነ በጦር መሳሪያ ብዛት የበላይነት የነበረው ሻዕቢያ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ጥቃት ከፈተ።
ከ6 ወራት በላይ በከበባ ውስጥ ሆነው ሲዋጉ የከረሙት በጀግናው የ 15ኛ ሻለቃ አዛዥ ሻለቃ ማሞ ተምትም እና በኮሎኔል ተስፋዬ ኃ/ማርያም የሚመራው ሰራዊት አንድ አማራጭ ነበራቸው። እሱም የተቃጣባቸውን ኃይለኛ የማጥቃት ዘመቻ መክተው በመልሶ ማጥቃት መውጣት ነው። እናም በርግደው ለመውጣት መልሶ ማጥቃትን ተያያዙት። በዚህ ጊዜ 5 ጊዜ የደፈጣ ውጊያ ገጠማቸው። ለዚህም ደፈጣን በደፈጣ በመጋፈጥ ምላሽ እየሰጡ ወደፊት ገፉ። በመጨረሻም የሻዕቢያን ጠንካራ ከበባ በርግደው ወጡ። ጠላት (ሻዕቢያ) ም ያንን ቦታ ሳይወድ በግዱ “ተስፋዬ በር ” ብሎ ሰየመው።
.
ይህ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሀ/ማርያም የጦር ሜዳ ገድል እጅግ በጣም ጥቂቱ ነው።
.
እኚህ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል፤ እኚህ ታላቅ ጀግና ጀነራል ለተጋድሎአቸው ውለታ ክብር ይገባቸዋል ያሉ ሀገር ወዳድ ባለሀብቶች በትላንትናው ዕለት (ነሐሴ25/2012 ዓም) አዲስ የሃዩንዳይ መኪና ሸልመዋቸዋል። ለብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሀ/ማርያም ሽልማቱ የተበረከተላቸው በቶቶት የባሕል አዳራሽ በተሰናዳ ዝግጅት ነው።
.
_