>

የብልፅግና ጉዞ ላይ ፣ መሆናችንን ሳታውቂ ...!!! (በላይ በቀለ ወያ)

የብልፅግና ጉዞ ላይ ፣ መሆናችንን ሳታውቂ …!!!

በላይ በቀለ ወያ

* አንቺ እንደሌሎች ፣ ግፈኛን አትቃወሚ
ብልፅግና ነው እመኚ ፣ እንደጧፍ ነደሽ ስትከስሚ…!!!
የምስኪን መኖሪያ ፈርሶ ፣ መናፈሻ ቢገነባ
ነፍሰጡሮች በጭካኔ ፣ ሲሆኑ የቀስት ሰለባ
“ይህንን ግፍ ፣ ይህን ደባ
አልሰማሁም ሲል ቢሰማ ፣ ሙሴ ያልነው አሻጋሪ
ፍረድ ስንል ሚያስገርመን ፣ ምህረት ሰጥቶ ለአሸባሪ
በየቦታው በየመስኩ ፣ ህዝብ ሲረግፍ  እንደ ቅጠል
በሀይማኖተኞች ሀገር ላይ ፣ መስጅድ ቤተስኪያን ሲቃጠል
የብልፅግና ጉዞ ላይ ፣ መሆናችንን ሳታውቂ
“መንግስት የለም ወይ ?” በማለት ፣ እንደሞኞች አትጠይቂ
።።።
የሰው ልጅ በቀን በፀሐይ ፣ ምን  ቢሰቀል ተዘቅዝቆ
በድንጋይ ተወግሮ ቢሞት ፣ ነፍሱ እስክታልፍ ስጋው ደቆ
ሚሊዮን ህዝብ ሲፈናቀል ፣ በሀገሩ ላይ ሀገር ለቆ
የአባቶች ጩኸት ሲታፈን ፣ እናቶች እንባ ሲያፈልቁ
ዩንቨርስቲዎች በሞት ኮርስ ፣ ተማሪውን ሲያስመርቁ
ስርአት አልበኝነት ሲበራከት፣ ህገ መጥነት ሲስፋፋ
ግፈኞች ሲበራከቱ ፣ ” ፣ ሰውነት ከሰው ሲጠፋ
የብልፅግና መንገድ ላይ ፣ መሆናችንን ሳታዪ
“ኧረ ምን ጉድ ነው  ነገሩ?” መንግስት የለም ወይ አትበዪ
።።።።።
ሊነጋ ነው ባልነው ቀን ላይ ፣ድቅድቅ ጨለማ ተሰጥቶ
የቀን ጅቡ ሔደ ስንል ፣ የራበው ጅብ ተተክቶ
የጀግኖች ሀገር ሲጨልም ፣ ለፈሪዎች ፀሀይ ወጥቶ
ሥራው በሰው ተይዞበት ፣ ምስኪን ሰይጣን ስራ ፈትቶ
በሰዎች ዘንድ እየዞረ ፣ ሥራ ፍለጋ ሲባትል
ሰው ምስጥ ሆኖ ሰው ሲበላ ፣ ሰይጣን ደግሞ ከያሬድ ትል
ዛፍ ከሚሉት ከሰው ቢሮ
የሰው ፈተና ሲጥለው ፣ወድቆ መነሳት ተምሮ
በፅናት ሲፈልግ ስራ
እልፍ አንገቶች እንደ ዘበት ፣ ቢቆረጡ በገጀራ
ለፍርድ ይቅረብ ያልነው ገዳይ ፣ እንደጲላጦስ እጁን ታጥቦ
በንፁሐን ደም ሲቀልድ ፣ ከነ እድፉ ምርጫ ቀረቦ
የብልፅግና ጉዞ ላይ ፣ መሆናችንን ሳታዪ
“እዚህ ሀገር ህግ የለም ወይ?” ፣ ኧረ ምን ጉድ ነው አትበዪ
።።።
የመንጋ ፍርድ ሲጧጧፍ
የሰው ልጅ ፣ ሲቀልጥ እንደጧፍ
ተማሪዎች ሲገደሉ ፣ ተማሪዎች ሲታገቱ
መንገዶች እየተዘጉ ፣ መንገደኞች ሲንገላቱ
ካህኑ ክልል ስጡኝ ሲል ፣ ጠፍቶበት የሰማይ ቤቱ
“እግዚኦ ማረን አቤቱ “
የሚል ፀሎት አትፀልዪ
በብልፅግና ነው እመኚ ፣ ጥርጣሬሽን ተዪ
” ሳያይ የሚያምን ብፁህ ነው ” ፣ አንቺም እመኚ ሳታዪ
እንጂማ አንቺ እንደሌሎች ፣ ግፈኛን አትቃወሚ
ብልፅግና ነው እመኚ ፣ እንደጧፍ ነደሽ ስትከስሚ።
Filed in: Amharic