>

ሰኞን በቃሊቲ [ከኤሊያስ ገብሩ-ጋዜጠኛ]

yenetsanet dimisoch‹‹መጽሐፉ በመውጣቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡
‹‹መጽሐፌን በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼም ቢያነቡት ደስ ይለኛል››
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
————–
ዛሬ ረፋድ ላይ ከወዳጄ አቤል አለማየሁ ጋር ቃሊቲ ሄደን የቀድሞ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ባልደረባችን የነበረውን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ለመጠየቅ ተቀጣጥረን ነበር፡፡ አቤል፣ ከቀጠሯችን 20 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ መስቀል አደባባይ ደረሰና ደወሎ ተገናኘኝ፡፡ ሁለታችንም በ2007 ዓ.ም በአካል የተገናኘነው ዛሬ ነበር፡፡ ‹‹በ2007 ም ቀጠሮ አታከብርም?›› ብዬ ቀለድኩበት፡፡ ….
ሚኒባስ ታክሲ ተሳፍረን ቃሊቲ ደረስን፡፡ የተለመደ ፍተሻውም ታለፈ፡፡ ነገር ግን፣ እስከዛሬ አጋጥሞኝ የማያውቀው አዲስ ፍተሻ መኖሩን አቤል ነገረኝ፡፡ በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ ማሽን ጫማ እና ቀበቶን አውልቆ በድጋሚ መፈተሽ ግድ ነበር፡፡ ይህም ታለፈና ‹‹ሸራተን›› ተብሎ ወደሚጠራው የቃሊቲ እስር ቤት አመራን፡፡ ይህንንም የእስረኛ መጠየቂያ ቦታ ስመለከተው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ በማያቸውን ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠቴ አልቀረም፡፡
አንድ ጥግ ላይ፣ በአጭር ርዝመት በእንጨት የተሰራች መጠየቂያ ጋር ደርሰን ቆምን፡፡ ለአንዱ ጥበቃ ፖሊስ ውብሸትን እንዲያሥጠራልን ነገርነው፡፡ ውብሸትም ከደቂቃዎች በኋላ ወደእኛ መጣ፡፡ ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶ ነበር፡፡ ብርቱካናማ ቲ-ሸርት አድርጓል፡፡ በቅድሚያ ያገኘሁት እኔ ነበርኩ፡፡ ተቃቅፈን ሰላምታ እየተለዋዋጥን እያለ ከለበሰው ልብስ አኳያ ‹‹የቀለም አብዮት ልትጀምር ነው እንዴ?›› አልኩትና ትንሽ ተሳሳቅን፡፡
ከአቤልም ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ የጋራ ወጋችንን ቀጠልን፡፡ ብዙ ሃሳቦች የተወያየነው በቅርቡ ለንባብ ስላበቃው ‹‹የነጻነት ድምጾች›› የሚል ርዕሥ ስላለው የመጽሐፍ ሁኔታ ነበር፡፡ በመጽሐፉ መውጣት በጣም ደስ ብሎታል፤ ይህም ፊቱ ላይ በግልጽ ይነበባል፡፡ ብዙ መከራን አሳልፎ ይህንን ማየት መቻሉ በጨለማ ውስጥ እንዳለች ሻማ ይቆጠራል፡፡ ለረዥም ወራት በኩላሊት ህመም እየተሰቃየ ከዝዋይ ወደቃሊቲ ለሕክምና መጥቶ እንኳን የረባ ሕክምና ሳይደረግለት ውሃ ጠጣ ነበር የተባለው፡፡ ልብ አድርጉ፣ የዝዋይ ውሃ ጠጠር ያለበት መሆኑ እየታወቀ ወደ ዝዋይ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ የወላጅ አባቱን የሞት መርዶ የሰማው በዘዋይ እስር ቤት ነው፡፡ ሌሎች አስቸጋሪ ነገሮች በውብሸት ሕይወት ውስጥ አልፈዋል፡፡ የሚቀየር ነገር ከሌለ ደግሞ 11 የእስር ዓመታቶች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ ይህቺን የተስፋ ብርሃን እንኳ በእስር ቤት ማየቱ ከምር ደስ ይላል – ለሞራሉ!
…ይህህ መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ አንብቦ የጨረሰው ዓቤል፣ አንዳንድ ጥያቄዎችን ከመጽሐፉ በመነሳት ሲያቀርብለት እሱም ሲያስረዳ እና ሲመልስለት እያለ ወዳጃችን ሰለሞን ሞገስ አጠገባችን ደረሠ፡፡ የውብሸት ጠያቂዎችም ሶስት ሆንን፡፡ …
‹‹አሁን ከማን ጋር ነው የታሰርከው?›› ስል ጥያቄዬን አቀረብኩለት፡፡ ከገብረዋድ (የቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኝ) እና ከአንድ ሌላ ልጅ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ ነኝ›› አለን፡፡ ገረመኝ፤ አብረው ይሆናሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡
‹‹ለአቶ ገብረዋድ አንድ ጥያቄ ጠይቅልኝ?›› አልኩት ለውብሸት፡፡
‹‹ምን?››
‹‹ከሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለፍርድ ቤቱ አንድ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ እኔም በችሎት ነበርኩ፡፡ ‹በማዕከላዊ ሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ሲናገሩ ገርሞኝ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ በእርግጥ ማንም ሰው በእስር ላይ እያለ ሰብዓዊ መብቱ መጣስ የለበትም፡፡ ነገር ግን፣ አቶ ገብረዋድ የመንግሥት ከፍተኛ ሹመኛ በነበሩበት ጊዜ የተቃውሞ ፓርቲ አመራሮች፣አባላት፣ ጋዜጠኞችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ዜጎች በተለያየ ምክንያት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ በማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት ሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ለፍርድ ቤት አቤቱታ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መስማታቸው አይርቀም፡፡ ያኔ ዝም ብለው አሁን በራሳቸው ላይ ሲደርስ ስለመብት ጥሰት መናገራቸው ተገቢ ነበር ወይ? የመብት ጥሰት በራስ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው ወይ ድምጽን ማሰማት የሚገባው?!›› አልኩት፡፡
ጥያቄዬን አድምጦ እጠይቅልሃለሁ አለኝ፡፡
የተለያዩ ነገሮችን እየተወያየን እያለ አንዲት ወጣት ልጅ ምግብ እና አነስተኛ ጥራቱን የጠበቀ ፍራሽ ይዛ በአቅራቢያችን መጣች፡፡ አቤል ‹‹ገብረዋድ ጋር ነች›› አለ፡፡ ወዲያው አቶ ገብረዋድ መጣ፡፡ ምቾት እና ነጻነት ባልተሰማው መንገድ ‹‹ሰላም ናችሁ›› የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣና ከውብሸት ጀርባ አልፎ ከምትጠይቀው ልጅ ጋር በትግርኛ ቋንቋ መነጋገራቸውን ቀጠሉ፡፡ ጠይቀን እንደተረዳነው ከሆነ ልጁ ነች፡፡ እኔም ጥያቄዬን ለአቶ ገብረዋድ ላቀርብለት አስቤ ከውስጤ ጋር አውርቼ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ከነበርንበት ቦታ አኳያ አመቺ ስላልነበረ ተውኩት፡፡ አቶ ገብረዋድም፣ ቀድሞን ወጣና ፍራሽ እና ምግቡን ይዞ ቻው ብሎን ሄደ፡፡ …
ውብሸትም መጽሐፉን አስመልክቶ እንዲህ አለን፡- ‹‹መጽሐፉ በመውጣቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ መጽሐፉን ሁሉም ሰው ቢያነበውም ደስ ይለኛል፡፡ ስለሀገራችን የእስር ቤት አስቸጋሪ ሁኔታ እና ስለሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች መጠነኛ መረጃ ያገኛል፡፡ መጽሐፌን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼም ቢያነቡት ደስ ይለኛል፡፡›› ካለ በኋላ የዳያስፖራ ማኅበረሰብን በተመለከተ ይህቺን ሃሳብ አከለ፡፡
‹‹ዳያስፖራዎች ስለሀገራችን ሁኔታ ያገባናል ስለሚሉ ነው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ድምጻቸውን በማሰማት ሰልፍ የሚወጡት፡፡ ይህን ባያስቡ ኖሮ በየካፌው ቡና እየተጠጣ ዝም ማለት ይቻላል፡፡ ከታሰርኩ በኋላ ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋዜጣን የማንበብ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ አንዲት ሴት የእኔን ፎቶግራፍ ደረቷ ላይ አድርጋ [የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ይፈቱ! የሚል] የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ድምጻን ያሰማችበትን ምስል ተመለከትኩና፡፡ ሴትየዋ እኔን አታውቀኝም፡፡ ግን የእኔን የእስር ጉዳት ለመቃወም አደባባይ ወጥታለች፡፡ ይህ ለሀገር ከመቆርቆር የሚመነጭ ነው››
…ባለኝ መረጃ መሰረት የውብሸት መጽሐፍ ጥሩ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ ዕትምም በቅርቡ ይገባል፡፡
…ከእኛ ራቅ ብሎ የሚገኘው ፖሊስ ከሌሎች ፖሊሶች ጋር ተነጋገረና ‹‹ሰዓት ሞልቷን፤ በቃችሁ›› አለን፡፡
እኛም ውቤን ‹‹አይዞን!›› በማለት አቀፈን የስንበት ሰላምታ ሰጥተነው ተለየነው፡፡ ‹‹አቶ ገብረዋድን ጠይቅልኝ ያልኩህን እንዳትረሳ›› በማለትም በድጋሚ አስታወስኩት፡፡
***FJ 2007****

Filed in: Amharic