>
5:28 pm - Sunday October 10, 2117

በኢትዮጵያ 1.8 ሚሊዮን ዜጐች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል...! (ዓለማቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM)

በኢትዮጵያ 1.8 ሚሊዮን ዜጐች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል…!!!

ዓለማቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM)

 

በኢትዮጵያ 1.8 ሚሊዮን ዜጐች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ያስታወቀው ዓለማቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM)፤ ከእነዚህም ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት በግጭት የተፈናቀሉ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ባለፈው ዓመት (2012) ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የተፈናቃዮችን ሁኔታ በተመለከተ ከመላ ሀገሪቱ መረጃ ማሰባሰቡን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 1.8 ሚሊዮን ያህል ዜጐች በረሃብ በግጭትና በጐርፍ ሳቢያ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
የስተደኞች ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ሪፖርቱ፤ ከተፈናቃዮቹ መካከል 1 ሚሊዮን 557ሺህ የሚሆኑት በግጭት፣ 351ሺህ 062 ያህሉ በድርቅና ምግብ እጥረት እንዲሁም 154ሺህ 789 የሚሆኑት በጐርፍ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ነው የተመለከተው፡፡
እነዚህ ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ተጠቃሽ ሲሆኑ ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 1200 መጠለያ ጣቢያዎችና 1200 ተፈናቅለው የነበሩ ዜጐች የተመለሱባቸውን መንደሮች ቃኝቶ ሪፖርቱን ማውጣቱን አመልክቷል፡፡
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ያለውና አሃዞቹ በመንግስት የተረጋገጡ መሆኑንም አይኦኤም ጠቁሟል።
በሌላ በኩል፤ ከኮቪድ 19 የበረሃ አንበጣና ከጐርፍ ጋር በተያያዘ 15.1 ሚሊዮን ዜጐች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበር ድርጅት አስታውቋል፡፡
በሀገሪቱ በመጋቢት ወር የተሰማራው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ 330ሺህ የስራ እድሎችን ማሳጣቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህም በመቶ ሺህ የሚባሉ ቤተሰቦች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል ብሏል፡፡

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎችን ለመድረስም 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
Filed in: Amharic