>
11:59 am - Wednesday December 1, 2021

ለዓላማዋው እንደብረት ጠንከሮ፣ረዥም ርቀት ከሚያልመው ኡስታዝ አቡበከር እና በተስፋ ከተሞሉት የዞን 9 ልጆች ጋር በቂሊኒጦ የነበረኝ ቆይታ

‹‹ለመብታችን መከበር እኛ ዋጋ ካልከፈልን ማን መጥቶ ይከፍልልናል?››
‹‹የሙስሊሙ መብት ካልተከበረ ክርስትያኑ አይመቸውም፤
የክርስትያኑ መብት ካልተከበረ ሙስሊሙ አይመቸውም››
ኡስታዝ አቡበከር አሐመድ
‹‹ቤት ሰሪ ደም የለውም፤ ግድብ ሰሪ ደግሞ መብት የለውም››
ጦማሪ ዘላለም ክብረት
‹‹ይሄ ትውልድ ምን አጠፋ?››
ጦማሪ አቤል ዋበላ

በኤሊያስ ገብሩ-ጋዜጠኛ
ትናንት በቃሊቲ እስር ቤት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ከወዳጆቼ አቤል አለማየሁ እና ሰለሞን ሞገስ ጋር ጠይቀነው ያወጋነውን ሃሰብ አካፍያችሁ ነበር፡፡ የምሳ ሰዓት ደርሶ ከቃሊቲ እንደወጣን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለመጠየቅ ብናስብም ‹‹በአንዴ ሁለት ሰው መጠየቅ አይቻልም›› በተባለው አዲሱ ‹‹መመሪያ›› መሰረት እስክንድርን ለመጠየቅ ዕድሉ አልነበረንም፡፡
ከአቤል ጋር ሰዓት በኋላ ‹‹ወደቂሊኒጦ ሄደን የታሰሩትን እንጠይቃለን›› ተባብለን ስለነበረ ወዲያው ወደቃሊቲ መናሃሪያ ታክሲ ያዝን፡፡ ምሳ ከበላንም በኋላ ጉዞ ወደቂሊንጦ እስር ቤት!
በቂሊንጦ ዞን አንድ፣ ሁለትና ሶስት የተለያዩ እስረኞች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በዞን አንድ ጦማሪያኑ ዘላለም ክብረት እና አቤል ዋበላ፣ እንዲሁም የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል የሆነው ኡስታዝ አቡበከር አሐመድ ይገኛሉ፡፡ በዞን ሁለት፣ ጦማሪያኑ በፍቃዱ ሐይሉ እና አጥናፍ ብርሃኔ የሚገኙ ሲሆን በዞን ሶስት ደግሞ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል አሕመዲን ጀበል ታስረውበታል፡፡
አንድ ሰው ከእነዚህ መካከል መጠየቅ ከፈለገ በአንዱ ዞን ያሉትን ብቻ ነው መጠየቅ የሚችለው፡፡ ባለፈው ቂሊንጦ በመጣሁ ጊዜ መጠየቅ የቻልኩት ዞን ሶስት የነበሩትን በመሆኑ እነአቤልን ‹‹ዛሬ መጠየቅ ያለብኝ እነበፍቄን ነው›› አልኳቸው፡፡ እነአቤል ደግሞ እነተስፋለም ወዳሉበት ዞን ሶስት ሊሄዱ አሰቡ፡፡
መግቢያ በር ላይ ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ መዝጋቢዋ በእድሜ ገፋ ያለች ፖሊስ ድምጿን ከፍ በማድረግ ‹‹ቶሎ ቶሎ ኑ›› በማለት የወንድ ረድፍ ጠያቂዎችን ታጣድፋለች፡፡ አጠገቧ ለምዝገባ የደረሰን ጠያቂ ‹‹ቁጭ በል›› የሚል ትዕዛዝ አዘል ቃልም ስትሰጥ ነበር፡፡ ሁኔታዋ ብዙም አላማረኝም፡፡ አንዲት የሴት ጠያቂ ወጣትን ‹‹መታወቂያሽ አልታደሰም›› በሚል ከቦታው እንድትሄድ አደረገቻት፡፡ የእኔ ተራ ደረሰ፡፡ መታወቂያ ሰጠኋት፡፡ አገላብጣ አየችውና ‹‹2004 ነው የሚለው፡፡ የአገልግሎት ዘመኑ አልፏል፡፡ በዚህ መግባት አትችልም›› አለችኝ፡፡ መታወቂያዬ 2005 ዓ.ም ላይ መታደሱን ነግሬያት እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ እንደሚያገለግልም አስረዳኋት፡፡ ‹‹ቁጥሩን ተመልተው ይህ ‹‹4›› ወይስ ‹‹7›› ነው የሚመስለው?›› አለችኝ›› ‹‹7›› ቄጥር ላይ የፊርማ ጭረት ቢያርፍበትም ‹‹2007 ዓ.ም ነው የሚለው›› አልኳት፡፡ ፊቷ እንደተኮሳተረ ነው፡፡
ይህንን ጉዳይ ማንሳት የፈለኩት አንዳንዴ በጥሩ ሥነ ምግባር ጠያቂን ከተጠያቂ እስረኞች ጋር የሚያገናኙ ፖሊሶች እንዳሉ ሁሉ ደስ በማይል እና ሥነ-ምግባር በጎደለው መንገድ የሚያስተናግዱ ፖሊሶች መኖራቸውን ለማስገንዘብ ነው፡፡
…እዚህም እንደቃሊቲ ዘመናዊ የፍተሻ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ገብቷል፡፡ ፍተሻውን ካለፍኩ በኋላ ‹‹አንገትህ ላይ የጠመጠምከውን ውጪ አስቀምጥ›› ተባልኩ፡፡ ‹‹ለምን?›› ስል ‹‹አይቻልም›› የሚል ምላሽ ተሰጠኝና ለማውለቅ ተገደድኩ፡፡ ይህ ሲገጥመኝ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ …በአጋጣሚ አንገቴ ላይ ያደረኩት እስከርፍ የሙስሊሞች ነበር፡፡ (ስሙ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ግን አላውቀውም)
ወደዞን አንድ አመራሁ፡፡ አራቱ ጦማሪያኖች አንድ ላይ መስለውኝ ስማቸውን አስመዘገብኩኝ፡፡ በግምት ከአምስት ደቂቃ በኋላ ተጠያቂ እስረኞች መምጣት ጀመሩ፡፡ ከአንድ እስረኛ ጋር በድንገት ተያየን፤ እሱም እኔም ፈገግ አልን፡፡ በመልከ መልካም ፊቱ ላይ ጺሙ በመጠኑ ሙልት ብሎ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል፡፡ ፊቱ ላይ ፍጹም እርጋታ ይነበብበታል፡፡ ይህ ሰው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል በመሆን እየተንቀሳቀሰ ሳለ ከጥቂት ዓመት በፊት ለእስር የተዳረገ ኢትዮጵያዊ ነው – ኡስታዝ አቡበከር አሐመድ፡፡
‹‹ኤልያስ እንዴት ነህ?›› በማለት ለሰላምታ እጆቹን በሽቦ ውስጥ አሾለከ፡፡ እኔም ደስ ብሎኝ አጸፋውን መለስኩለት፡፡ ከአቡበከር ጋር በአጭር ደቂቃ ውስጥ ስላለፉትና ስለአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ሁነቶች በመጠኑም ለማውጋት ቻልን፡፡ አቡበከር አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ አልፎ አልፎ ይጽፍልን ነበር፡፡ ጽሑፉን የሚቀበለው አቤል አለማየሁ ነበር፡፡ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ከመታሰራቸው አንድ ቀን በፊት ለእኔ እና ለኃይለመስቀል በሸዋምየለህ የመጨረሻ ቃለ ምልልስ ከነአሕመዲን ጋር ሰጥቶን ነበር፡፡
አቡበከር እንደእስክንድር ነጋ ያመነበትን ነገር ፊትለፊት የሚናገር ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ስለወቅቱ የኢትዮጵያ የፕሬስ ሁኔታ የሚያምንበትንና መሆን ያለበትን በግልጽ በአጭር ቃል ነገረኝ፡፡ በሃሳቡ እኔም እስማማበት ነበር፡፡
አቡበከርን ሊጠይቁ የመጡ ብዙ ጠያቂዎች ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ እኔ እና እሱ ያለንበት ቦታ ድረስ እየመጡ ሰላምታ ሰጥተውት እንዲመጣ ጠይቀውት ነበር፡፡ እኔ እና አቡበከር ግን ሳናስበው በተወስጦ ውስጥ ሆነን ሃሳብ መቀያየራችንን ቀጥለናል፤ በእርግጥ ደስ የሚሉ ሃሳቦችን እያወጋን ነበር፡፡
…በመጨረሻም ስለታሩበት ጉዳይ፣ ስለፍርድ ሂደቱና ስለፍርድ ሂደታቸው መዘግየት ከነምክንያቱ አጫወተኝ፡፡
‹‹ያነሳነው የመብት ጥያቄ ሰላማዊና ትክክለኛ ነው፡፡ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንደትጥቅ ትግል አይደለም፡፡ ሊረዝም ይችላል፡፡ በመጨረሻ ግን ይሳካል፡፡ ለመብታችን መከበር እኛ ዋጋ ካልከፈልን ማን መጥቶ ይከፍልልናል? እኛ በቦታውና በጊዜው ላይ ተገኘተናል፡፡ መክፈል የሚገባንን ዋጋ እንከፍላለን፡፡ እየከፈልንም ነው፡፡ አሳሪዎቻችን የታገሉትን ዓላማ ዘንግተዋል፡፡ ለትግል ያነሳሳቸው ጭቆና እና የመብት ረገጣ ነበር፡፡ በትግል ወቅት ጓዶቻችው ሲሰው፣ ሲቆስሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩ …ይበልጥ በርትተው ትግላቸው ላይ ቀጠሉበት እንጂ ተስፋ ቆርጠው ትግላቸውን አላቋረጡም፡፡ አሁን ግን ይሄንን የዘነጉት ይመስለኛል፡፡ እኛም ለእምነት መብታችን በምናደርገው ትግል ላይ ታስረናል፡፡ ይህ ይበልጥ ያበረታናል እንጂ ከዓላማችን ፈቀቅ አንልም፡፡ አረቦች ‹ምንጩ ከቆሸሸ ወንዙም ይቆሽሻል› የሚል አባባል አላቸው፡፡ እውነት ነው፣ የእምነት ነጻነታችንን በትክክል አረጋገጠን ወንዙን ንጹህ ለማድረግ በቅድሚያ ምንጩን ነጻ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የሙስሊሙ መብት ካልተከበረ ክርስትያኑ አይመቸውም፤ የክርስትያኑ መብት ካልተከበረ ሙስሊሙ አይመቸውም፡፡ የአንዱ ሰላም አለመሆን ለአንዱ ሰላም አይሰጥም፡፡ ወረቅት ላይ ያለውን የዕምነት ነጻነት መብት መሬት ላይ በተግባር ማውረድ ይገባናል፡፡››
[እዚህ ጋር፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ማሰቤ ግድ ነበር፡፡ በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሁሉም መስክ እስካልተፈጠረ ድረስ የሰላማዊ መብት ትግል መቀጠል እንዳለበት አበክሮ ያምናል፡፡ ዛሬ በእስር ሆነ በስደት እየተከፈለ ያለው ዋጋ ነገ ላይ ፍሬ እንደሚያፈራ ሲናገርም በእውነተኛ ተስፋ ተሞልቶ ነው]
አብበከር፣ ‹‹ኤልያስ አንድ የፈረሱን ምሳሌ ልንገርህ›› አለኝና ምሳሌውን አስከተለ፡፡ ‹‹ሰዎች አንድን ፈረስ ጥለው ጉድጓድ ውስጥ ከተቱት፡፡ እዚያም ጉድጓድ ውስጥ ቆሻሻ በየጊዜው ይጥሉበት ጀመር፡፡ ፈረሱም ቆሻሻውን ከእግሩ ስር እየረገጠ ወደላይ ከፍ ማለትን ተያያዘው፡፡ ፈረሱ ላይ ቆሻሻ ሲጥሉበት እሱም ቆሻሻውን ከእግሩ ስር በማድረግ ሂደት መጨረሻ ላይ ከጉድጓዱ ወጣና እና በነጻነት መኖሩን ቀጠለ፡፡ የእኛም ታሪክ በዚህ ይመሰላል፡፡ ጉድጓዱ እስር ቤታችን ነው፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ ነገር እንደቆሻሻው ቢጨመርብንም ቆሻሻውን ከእግራችን ስር በማድረግ አንድ ቀን እንደ ፈረሱ ነጻ እንወጣለን፡፡ መብታችንም በትክክል ይከበራል›› አለኝ፡፡
የአቡበከር ጥንካሬ፣ ትህትና፣ ጽናት፣ ዓላማ ላለው ነገር የመቆሙ ወኔ አስደማሚ ነበር፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ይሄን የፈረሱን ታሪክ ‹‹አዲስ ጉዳይ›› መጽሔት ላይ በአስተማሪ ብዕሩ ከትቦት አንብቤያለሁ፡፡ የሁለት ትልልቅ ኃይማኖት ልጆች አንድ ምሳሌን መጋራታቸው ይበልጥ ደስ አለኝ፡፡ አብበከርን በትህትና፣ በመርህ፣ በሃይማኖት ቃል፣ በእውቀት በድፍረትና በእምነት ተሞልቶ ለቆመለት እና ዋጋ እየከፈለለት ላለው የመብት ጥያቄ ረዥም ርቀት የሚያልም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ብየዋለሁ፡፡
የአቡበከር ጠያቂዎች ጨዋታችንን ሊያስቀጥሉን አልቻሉምና ከወንድሜ አቡበከር ጋር ደስ በሚል ስሜት ቻው ተባብለን ልንለያይ ስንል የዞን 9 ጦማሪያኑ ዘላለም ክብረት እና አቤል ዋበላ ወደእኔ መጡ፡፡ የተለመደ ሰላምታ ተቀያየርን፡፡ ሁለቱም በመምጣቴ ደስ ብሏቸዋል፡፡ ፈገግታቸው ፊታቸው ላይ ይታያል፡፡ ከአቤል ጋር በአካል ስንገኛን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ከወላጅ አባቱ ጋር ጥቂት ደቂቃዎች በአካል ተነጋግረን እናውቃለን፡፡ አቤልን በአራዳ ፍ/ቤት እጆቹ በካቴና ታስረው ሲገባና ሲወጣ አይቸው ነበር፡፡ ማዕከላዊ ምርመራ ከጨረሱ በኋላ ሌሎቹን መጠየቅ ስችል በወቅቱ አቤል ከጨለማ ክፍል ስላልወጣ አላገኘሁትም ነበር፡፡
ዘላለም ተረድቶን ነው መሰለኝ ‹‹በአካል አትተዋወቁም እንዴ?›› ሲል ጠየቀን፡፡ አቤል ‹‹በፎቶ ነው የማውቀው፡፡ ባለፈው ማዕከላዊ በታሰርክበት ጊዜ ያደረስከን ሰላምታ ደርሶኛል፡፡›› አለኝ፡፡ ዘላለም ሰማያዊ ፓርቲ ባደረገው ትልቁ ሰልፍ ላይ አብረን እንደነበረን በማስታወስ ከእሱ እና ከበዕውቀቱ ስዩም ጋር በዕለቱ የተነሳነውን ፎቶግራፍ አስታውሶ ነገረኝ፡፡ ረስቼው ነበር፡፡ …
‹‹እንዴት ናችሁ? ጠነከራችሁ?›› በማለት ጥያቄዬን አስከተልኩ፡፡ ‹‹ደህና ነን፤ ለምደነዋል›› አሉኝ፡፡ ሁለቱም ውጪ ስላለው ሀገራዊ ጉዳዮች ጥያቄ መጠየቅ ይወዳሉ፡፡ ስለተለያዩ ነገሮች ሃሳቦችን ተለዋወጥን፡፡ ስለወቅቱ የፕሬስ ሁኔታ፣ ስለአንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲዎች፣ በምርመራ ወቅት ስላጋጠማቸው፣ ስላስገረማቸውና ስላዘኑባቸው ሁነቶች፣ ስለሶሻል ሚዲያው፣ ስለቀጣዩ ምርጫ … አውግተናል፡፡ [በመጠቂያው ቦታ እኔ፣ዘላለምና አቤል አናጺዎች የጥገና ሥራ እየሰሩ የሚሰማውን የቆርቆሮ እና የሚስማር ግንኙነት ድምጽ በክላሲካል ሙዚቃነት ተጠቅመንበታል]
ዘላለም እንደናትናኤል ፈለቀ ሳቅ ቅርቡ ነው፡፡ ያወራል፣ ያዳምጣል፤ ይሥቃል፡፡ ቁምነገሮችን ደስ በሚል ለዛ ባለው ቀልድ አዋዝቶ ነበር የሚናገረው፡፡ አቤልም ፈገግ ቢልም ንግግሮቹ አጠር አጠር ያሉ ግን፣ ከባዶች ናቸው፡፡
‹‹እነበፍቄስ?›› አልኳቸው፡፡ መዘግየታቸውን አይቼ፡፡ ‹‹ዞን ሁለት ነው ያሉት፡፡ እኛም ያገኘናቸው አምና ነው፡፡ ካገኘሃቸው በጣም ሰላም በልልን›› አለኝ ዘሌ! በሌላ ዞን መሆናቸውን ያወኩት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡
በጋራ ያወጋናችን ቁምነገሮች በሙሉ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ማከታት አይቻልም፡፡ ጥቂቱን ግን እንዲህ ላካፍላችሁ፡፡ ከዘላለም ጀመርኩ፡-
‹‹ኢቴቪ (ኢቢሲ) ግድብ …ግድብ …ግድብ በሚሉ ዘገባዎች ተጠምዳለች፡፡ ቤት ሰሪ ደም የለውም፤ ግድም ሰሪ ደግሞ መብት የለውም›› አለኝ በቀልድ እያዋዛ፡፡
‹‹ምን ማለት ነው?›› አልኩት፡፡
‹‹ያው ለግድቡ ግንባታ ተብሎ ብዙ ህዝቡ በተለያየ መንገድ ገንዘብ እያዋጣ ነው፡፡ ‹ቤት ሰሪ ደም የለውም› ሲባል ይለፋል፣ ይደክማል ማለት ነው፡፡ ግድብ ሰሪ ደግሞ ዋና ዓላማው ግድቡን መገንባት ስለሆነ መብቱን መጠየቅ አይችልም፡፡ ልጠይቅም ቢል በአንከሮ የሚሰማው የለም፡፡ ‹ልማት ላይ ነን›› ይባላል፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ‹ግድቡን ሰርተን ለማጠናቅ የተወሰነ ዓመት ሊሰጠን ይገባል› ያሉትን አትዘንጋ›› አለኝ፡፡
በዘሌ ንግግር ውስጥ ትልቅ ቁም ነገር በቅኔ ውስጥ አለ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!
አቤልም ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን›› ብሎ ካሳቀን በኋላ ‹‹ባቡሯ እንደት ነች?›› አለኝ፡፡ ‹‹ሃዲዷ እየተሰራላት ነው›› አልኩት፡፡ ‹‹ያው ምርጫ መጥቷል፡፡ ግድቧን፣ ባቡሯን፣ ኮንዶሚኒየሟን …ሰራን ብለው ይቀርባሉ›› አለ እየሳቀ፡፡
አስከትሎም ‹‹ይሄ ትውልድ ባልነበረበት፣ ባልኖበረበት፣ ባለሰራው ታሪክ ለምን ተጎጂ ይሆናል? እኛ በማናውቀው እየተቀጣን ነው፡፡ ይህ ትውልድ ምን አጠፋ? ትውልዱ ያሳዝነናል›› ሲልም ከልቡ ተናገረ፡፡ ትውልዱን በተለመከተም የሚመሰለንን እና የምናምንበትን ሃሳብ ተካፈልን፡፡ ስለነገ ተስፋም አወጋን፡፡ ሁለቱም ተስፈኞች ናቸው፡፡ ‹‹እኛ ገና ወጣቶች ነን፡፡ እዚህ በእድሜ የገፉ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ሕይወት አንዳንዴ እንዲህ መሆኗም ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ነገር በእርጋታ ታገናዝባለህ፡፡ ትጠይቃለህ፤ ትመልሳለህ፡፡ እንዲሁ ኖሮ ሞተ መባሉም አንዳንዴ ትርጉም የለውም›› አሉኝ፡፡ ዘላለም ‹‹በዚህ ዞን ደግሞ ኮኮቦች (ሰታሮች) ነን›› በማለት አስፈገገን፡፡
‹‹እስኪ ከቻልክ፣ ፖሊሶች ምንም ካላሉህ እነበፍቄን እና አጥናፍን ጠይቃቸው፤ ለእኛም የናፍቀት ሰላምታ አድርስልን›› አሉኝ፡፡
‹‹አይዟችሁ፣ ብርታትና የመንፈስ ጥንካሬ ይኑራችሁ፤ ሁሉም ያልፋል፡፡ ከእስር የምትወጡበት ጊዜ አለ፡፡ ተስፈኛ ናችሁ፤ ይበልጥ ተስፈኛ ሁኑ!›› ብዬ ዘሌንና አቤልን ተሰናበትኳቸው፡፡ ወደዞን ሁለት መግቢያ ተጠግቼ ጠባቂ ፖሊሱን ጠየኩት፡፡ ‹‹በዞን አንድ ስትጠይቅ ነበር፤ ነገ ተመለስ!›› የሚል ቃል አጠንክሮ ነገረኝ፡፡ ድግሚ ብጠይቀውም ‹‹ሂድ ብየሃለሁ›› የሚል የቁጣ ምላሽ ነበር ያገኘሁት፡፡
አቤል እና ሰለሞን በግምት ከ30 ደቂቃ በኋላ መጡ፡፡ እነተስፋለም ሰላም መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ ጉዞ ወደመሀል አዲስ በአበባ ሆነ፡፡ ሰለሞን ወደሰፈሩ ቦሌ ሚካኤል ሲሄድ እና እና አቤል ረፋድ ላይ በተገናኝነት መስቀል አደባባይ አለመሻሽ አቅራቢያ ደረስንና ‹‹ቻው›› ተባብለን ተለያየን፡፡
እስረኞችን መጠየቅ ለተጠያቂው ውስጣዊ ደስታን፣ ለጠያቂው ደግሞ ውስጣዊ ሰላምን፣ ለጠያቂም ሆነ ለተጠያቂ ደግሞ የጋራ ተስፋን ይሰጣል!

Filed in: Amharic