>

ገዳና  እሬቻ ....!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ገዳና  እሬቻ ….!!!

አቻምየለህ ታምሩ

ዐቢይ አሕመድና የዘረጋው የአፓርታይድ አገዛዝ ባላደራዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥንታዊቱን በራራን፤ ዘመናዊቱን አዲስ አበባን አፍርሰው በኦነጋውያን የደነዘዘ አእምሮ ውስጥ በተፈጠረችው ፊንፊኔ ለመተካት ያላፈረሱት የቆየ አሻራና የከተማይቱን ጥንታዊነት የሚመሰክር ምልክት የለም። የከተማ አስተዳደሩን የፖሊስ ሠራዊት ኦሮሚያ ከሚባለው ክልል በመለመሏቸው ለከተማው ከባሕር የወጣ አሳ በሆኑ የፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ቄሮዎች ተክተውታል። ደብረ ዘይት በሚገኘው ሆራ ሐይቅ ከመስቀል በኋላ ይከበር የነበረውን እሬቻን “ሸገርን ለማስዋብ” በሚል ዐቢይ አሕመድ ግለሰቦችን [አብዛኛዎቹ አማሮች ናቸው] አምስት አምስት ሚሊዮን ብር እንዲያወጡ አድርጎ ባስቋረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ  እንዲከበር አዳነች አበቤ በዐቢይ አሕመድ በተሾመች ሳምንት ሳይሞላት አባገዳ ለሚባሉቱ የይዞታ ካርታ ሰጥታለች።
ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አበባን  ይፋዊ ስም  ወደ ሸገር  ቀይሮ “ሸገርን ማስዋብ” የሚል የማፈናቀያና የጥንቱን የአዲስ አበባ ኗሪ የማጽጃ ፕሮጀክት የቀረጸው  የሁላችንም የሆነችን አዲስ ስበባን ለማስዋብ ሳይሆን የኦሮሙማዋን ፊንፊኔ ለመፍጠር ነው።  አዲስ አበባ ውስጥ ዐቢይ ባቋረው ሰው ሰራሽ ኩሬ እንዲከበር  ቋሚ የይዞታ ካርታ የተሰጠው እሬቻ ዐቢይ አሕመድ  “ሸገርን ማስዋብ” የሚል የዳቦ ስም  ሰጥቶ እየፈጠራት  ላለቸው የኦሮሙማዋ ፊንፊኔ አንድ ማሳያ ነው። ዐቢይ አሕመድም ሆነ ወራሪዎቹ አባገዳዎች  አዲስ አበባ ውስጥ ተከብሮ የማያውቀውን እሬቻን አዲስ አበባ ለማክበር ሽርጉድ እያሉ ያሉት የበዓሉ ፍቅር ፈጥርቋቸው ሳይሆን አዲስ አበባ በመውረር የኦሮሞማዋን  ፊንፊኔ ለመመስረት  በሚያደርጉት እንቅስቃሴ  ከ150 ዓመት በፊት እዚህ ነበርን ብለው ለፈጠሩት ተረት  እንድ “ማስረጃ”  የኦሮሞ ባሕል  አድርገው  የሚያቀርቡትን  እሬቻን አዲስ አበባ ውስጥ እንደነበር አድርገው ማቅረብ የግድ ስለሚያስፈልጋቸው ነው።
ከዚህ ውጭ  አዲስ አበባ ውስጥ ተከብሮ የማያውቀውን እሬቻን አዲስ አበባ ውስጥ  ለማክበር የሚነሱበት አንዳች ምድራዊ  ምክንያት የለም።  ሆኖም ግን  እሬቻም ልክ እንደ ገዳ ሁሉ በታሪክ የኦሮሞ አይደሉም። ኦሮሞ  ገዳን የተማረው ከባንቱ ነው። የከባንቱ ሥርዓት የነበረውን ገዳን የወረሰውም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ነበር። ስለዚህ የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ሥርዓት ተብሎ በዩኔስኮ ሊመዘገብ ከቶ አይቻለውም። ገዳ እንደ ሥርዓት በዩኔስኮ መመዝገብ ካለበት የኦሮሞ ተብሎ ሳይሆን የባለቤቶቹ የባንቱዎች ተብሎ ነው። ገዳ የኦሮሞ ሥርዓት እንዳልነበር፤ ኦሮሞ ገዳን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከባንቱ እንደተማረው ታሪኩን አጣርቶ  የነገረን ከአባ ባሕርይ ቀጥሎ በኦሮሞ ታሪክ ጥናት ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነው ጣሊያናዊው  ምሑር ፕሮፈሰር ኢኔርኮ ቸሩሊ ነው።
ፕሮፈሰር ኢኔሪኮ ቸሩሊ ስለ አካባቢው ታሪክ የተጻፈውን የጥንቱን የዜንጅ መጽሐፍ ዋቢ በማድረግ እ.ኤ.አ. በ1957 ዓ.ም.  Somalia: Scritti Vari editi ed Inediti I እና እ.ኤ.አ. በ1959 ዓ.ም. Somalia: Scritti Vari editi ed Inediti II በሚል በጣሊያንኛ ቋንቋ ባሳተማቸው መጽሐፍቱ  የመዛገበውን ታሪክ ጠቅሶ ጂን ዶሬስ እ.ኤ.አ. በ1971 ዓ.ም.  “ Histoire Sommaire de la Corne Orientale de l’Afrique”  በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ባሳተመው መጽሐፉ ላይ ታሪኩን እንዲህ ያስቀምጠዋል፤
“ዛሬ ሱማሊያ በሚባለው ምድር ሱማሌ ጋላን ተካ። መጀርቲን በሚባለው አካባቢ አንድ መዘክር ወይም የጥንት መጽሐፍ ይገኛል። ይህም ሰነድ ዑባያ በተባለ አካባቢ በሱማሊኛ Galka’yo (ጋል ካ አዮ) የተባለ ቦታ እንዳለ ይጠቅሳል። የቦታው ትርጉም “ጋሎች የለቀቁት [ቦታ] ማለት ነው።. . . ከሰሜን ምስራቅ የመጣው የጋላ ሕዝብ ከመቶ ዓመት በላይ ከዘለቀ ትግል በኋላ  ባንቱን ከማዕከላዊ ሶማሊያ አስወጣ፤ [ጋላ] የገዳ ሥርዓትን የወረሰውም ከባንቱ ነው። [በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን] ሱማሌ ጋላን ወግቶ ከሲማሊያ አስወጣ። ጋላ በገዳ ሥርዓት በመጠቀም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ከፍተኛ ለምለም መሬቶች ወረረ” [1]
ይህ  የቼሩሊ ጥናት በግልጽ እንደሚያሳየው ኦሮሞ የገዳ ሥርዓትን የወረሰው ከባንቱ ሲሆን ሥርዓቱንም ከባንቱ የተዋሰው ኢትዮጵያን ለመውረር ነበር።
 እሬቻም  የኦሮሞ ገዢ መደብ በየስምንት አመቱ ሲያደርግ የኖረውን ወረራ ገና ሳያካሂድ፤ የእርሻ ስራና ሰብል ማምረት ሳይጀምርና ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ምድር ሳይስፋፋ መስከረም በገባ መስቀል በተከበረ በሳምንቱ ሲከበር የኖረው ደብረ ዘይት የአቡዬ የጸበል ሥፍራ በነበረው በሆራ ሐይቅ ነበር። እሬቻ  ቃሉ ጭምር  የአማርኛ ቃል እንጂ የኦሮምኛ ቃል አይደለም። እሬቻ ኦሮምኛ ነው የሚል ቢኖር የቃሉን የኦሮምኛ ግንድና ቃሉ በኦሮምኛ እንዴት አንደሚረባ ማስረዳት ይጠበቅበታል። የግዕዙ ሊቅ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” በሚል ባሰናዱት መዝገበ ቃላት ውስጥ እንደጻፉት እሬቻ ዋናው ሰብል ደርቆ ከመታጨዱና በአውድማ ተወቅቶ ወደ ጎተራ ከመግባቱ በፊት ቀድሞ የደረሰው ተቆርጦ በበትር በመወቃት ወይም በእጅ ታሽቶ የሚቀመሰው እህል ይሉታል። ለላው ሊቅ ከሣቴ ብርሃን ተሰማም በ1951 ዓ.ም ባሳተሙት “የአማርኛ መዝገበ ቃላት” መጽሐፋቸው የአማርኛ ቃል ስለሆነው እሬቻ የሚነግሩን ትርጉም ተመሳሳይ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም. ባሳተመው “የኣማርኛ መዝገበ ቃላት” ገጽ 101 ላይ እሬቻ የአማርኛ ቃል መሆኑን በመበየን ተመሳሳይ ትርጉም ይሰጠዋል። ታዋቂው አሜሪካዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አጥኚ ቶማስ ኬንም ባዘጋጀው የአማርኛ – እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ቅጽ አንድ ገጽ 397 ላይ ስለ እሬቻ የአማርኛ ቃልነትና ትርጉም የሚነግረን ተመሳሳይ ነው።
በመሆኑም የእሬቻ በዓልን የሚያከበረው አራሹ ገበሬ ክረምቱን በሰላም እንዲያልፍ፤ ያዘመረው እህል ለፍሬ እንዲበቃና እሸት እንዲቀምስ ያስቻለውን ፈጣሪውን ለማክበር ነው። ባጭሩ የእሬቻ በዓል እህል የሚያበቅል አራሽ ገበሬ የሚያከብረው አመታዊ ዝክር ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞቹ እነ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን፣ ዶክተር ነገሶ ጊዳዳ፤ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፤ አቶ ይልማ ደረሳ፤ ፕሮፈሰር ተሰማ ታዓ፤ ወዘተ እንደነገሩን ደግሞ ኦሮሞ ከብት በማርባት የሚተዳደር የነበረ ሲሆን የእርሻ ስራ የጀመረው ዛሬ በሰፈረበት አካባቢ ከረጋ በኋላ ከ17ኛውና ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ነው። ይህ ማለት የተሰማራበት የስራ መስክ ከብት ማርባት፤ እምነቱ ደግሞ ዋቄ ፈና ነው የተባለው ኦሮሞ የማያበቅለው እህል የሚሽትበትን ወቅት ጠብቆ ሃይማኖቱ አይደለም የተባለውን መስቀልን አሳልፎ መስቀል በሆነ በሳምንቱ እህል እንዲያበቅል፤ እሸት እንዲቀምስ ለሚያስችል ፈጣሪ ምስጋና ሊያቀርብ ይችላል ካልተባለ በስቀር ከብት አርቢ የነበረው ኦሮሞ እሬቻን ማክበር የጀመረው ሸዋን ሲወር ያገኛቸው አራሽና እህል አብቃይ የአማራ ገበሬዎች ያመረቱት ሰብል ለፍሬ እንዲበቃና እሬቻ [እሼት] እንዲቀምሱ ላስቻላቸው ፈጣሪያቸው ያቀርቡት የነበረውን የምስጋና ባሕል በመውረስ ነው። ስለዚህ እሬቻ ከብት አርቢ የነበረው ኦሮሞ ከነ ቃሉ ከሰብል አምራች የአማራ አርሶ አደሮች የወረሰው የምስጋና በዓል ሲሆን ኦሮሞ አካባቢውን ከመውረሩ በፊት ጀምሮ ይከበር የነበረው ደብረ ዘይት በሚገኘው ሆራ ሐይቅ እንጂ አዲስ አበባ ውስጥ አልነበረም።
ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ እሬቻ  የሚከበርበት የሸዋ ምድር ኦሮሞ አካባቢውን ከውረሩ በፊት በግብርና ሥራ እየተዳደረ ይኖርበት የነበረው አማራ ነበር። ይህን ታሪክ የሚነግረን ኦነጋውያን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱት የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊ ጀርመናዊው አይኬ ሐበርላንድ ነው። አይኬ ሐበርላንድ እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም.  “Galla Süd-Äthiopiens ”  በሚል  በጀርመንኛ ባሳተመው መጽሐፉ ገጽ 786 ላይ እንዲህ ይላል፤
“Im Herzen Äthiopiens, in Regionen, die einst von den Amhara besetzt waren, lebt die Shoah Galla, die oft als Tullema bezeichnet wird.”
የእንግሊዝኛ ትርጉም፤
“In the heart of Ethiopia, in regions once occupied by the Amhara, live the Shoa Galla, often referred to as the Tullema” [2]
የአማርኛ ትርጉም፤
“በማዕከላዊ ኢትዮጵያ  የአማራ ይዞታዎች በነበሩ አውራጃዎች ውስጥ ቱለማ የሚባሉ የሸዋ ኦሮሞዎች ይኖራሉ”
እንግዲህ! የኦሮሞ ብሔርተኞች በሙሉ  በፈጠሩት ተረት እየተመሩ   “ እሬቻን  ከ150 ዓመታት በፊት ይከበር ወደነበረበት ወደ ፊንፊኔ መልሰነዋል” የሚሉን  በታሪክ የነሱ ወዳልነበረው  ቦታና  ኦሮሞ አካባቢውን ከመውረሩ በፊት ባላርሥት የነበረው አማራ ያከብረው የነበረውን  የሰብል ክብረ በዓል ወርሰው ነው።  እሬቻ በእውነት የኦሮሞ ባሕል ቢሆን ኖሮ  [ከወያኔና ኦነግ ዘመን በፊት] ክብረ በዓሉን  ከሁሉ በፊት  መከበር የነበረበት  የኦሮሞ አባት የሆነውና ዛሬም ድረስ  ከብት በማርባት የሚተዳደረው ቦረን  በሚኖርበት ቦረና ውስጥ እንጂ  ኦሮሞ ወደ  ማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ከገባ በኋላ ያገኛቸው የኢትዮጵያ ነገዶች የሚተዳደሩበት የእርሻ ስራ በሚዘወተርበት አካባቢ መሆን አልነበረበትም። በዓሉንም ማክበር የነበረበት የዘላን ኑሮውን በመተው በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች የእርሻ ስራ ተምሮ  የኢኮኖሚ ባሕል በመቀየር በተማረው የእርሻ ስራ  ኑሮውን በመሰረተው  ልጁ ቱለማ ሳይሆን የኢኮኖሚ ባሕሉን ሳይቀይር ዛሬም ድረስ  ኑሮውን ከብት በማርባት የሚገፋው አባቱ ቦረን መሆን ነበረበት።
በዚህ ላይ ከቱለማም ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ ኦሮሞ አይደለም። ከቦረና ውጭ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ኦሮሞዎቹ ወራሪዎቹ አባገዳዎቹና የነሱ ዘመዶች ብቻ ናቸው።  የተቀረው ኦሮምኛ እንዲናገር የተደረገው ተገዶ  እንጂ  ኦሮሞ አይደለም። ኦሮምኛ የሚናገረው ሁሉ ኦሮምኛ እንዳልሆነ እውነተኞቹ ኦሮሞዎቹ ራሳቸው ምስክር ናቸው። በእውነተኞቹ ኦሮሞዎች ትውፊት ውስጥ «Salgan Borana, sagaltamman gabra» የሚል አባባል አለ። ይህ ወደ አማርኛ ሲተረጎም «ዘጠኙ ኦሮሞ ነው፤ ዘጠናው ገርበ ነው» ማለት ነው። ገርባ ኦሮሞ ሲስፋፋ ያስገበራቸውንና ባርያ ያደረጋቸውን ነገዶች የሚጠራበት ስያሜ ነው። በኦሮሞ በራሱ ትውፊት መሰረት ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ከሚኖረው ኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝበ መካከል ትክክለኛው ኦሮሞ ከአስሩ አንዱ ብቻ ነው ማለት ነው። ከአስሩ ዘጠኙ ገርበ ወይም በአባገዳዎች በወረራ የተያዘና በኃይል ኦሮሞ የተደረገ ሕዝብ ነው። ባጭሩ እሬቻ የኦሮሞ ባሕል ቢሆን ኖሮ ከሁሉ በፊት መከበር የነበረበት “Salgan Borana” የተባሉት በሚኖሩበት አካባቢ እንጂ “sagaltamman gabra” በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ መሆን አልነበረበትም። እንዴውም እሬቻ ከዘመነ ወያኔና ኦነግ በፊት “Salgan Borana”  በተባሉት እውነተኞቹ ኦሮሞዎች ዘንድ አይታወቅም።
_________
የግርሜ ማስታወሻ
[1] ትርጉም፡ ግርማ በሻህ  in [አምሃ ዳኘው (2012)፥ ሐገራዊ ብሔርተኝነት እና ዘውጋዊ ብሔርተኛነት በኢትዮጵያ፥ ገጽ 118]
[2] ዝኒ ከማሁ፥ ገጽ 171.
Filed in: Amharic