>

አክቲቪስት ሽመልስ ምን እያለ ነው? (ሙሉአለም ገብረመድህን)

አክቲቪስት ሽመልስ ምን እያለ ነው?

ሙሉአለም ገብረመድህን

የኢሬቻን በዐል ምክንያት በማድረግ ሽመልስ አብዲሳ ያስተላለፈውን መልዕክት አነበብኩት፡፡ የመልዕክቱ ፖለቲካዊ እንድምታ ብዙ ሊያስብል የሚችል ቢሆንም በመዝጊያው ላይ ማተኮር መርጫለሁ፡፡
‹‹ኦሮሚያን እንገነባለን›› ሲባል…
ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ግዛት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዞን በታች ያለው መንግሥታዊ መዋቅሩ ፈርሷል፡፡ ሰው ከሕግ ቁጥጥር በላይ ሆኖ ከርሟል፡፡ የሀገር ዳር ድንበር የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መከላከያ ሠራዊት የፖሊስ ስራ ሲሰራ ከርሟል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል የሚገኙ የወለጋ አራት ዞኖች፣ ጉጅና ቦረና የደፈጣ ውጊያ ቀጠና ከሆኑ ሁለት ክረምት ተቆጥሯል፡፡  መንግሥት የማይቆጣጠራቸው ነጻ መሬቶች ሁሉ የተፈጠሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ የዞን አመራሮችና የጸጥታ ኃላፊዎች ላይ የ’ነጭ ሽብር’ እርምጃ ሲወስድ የከረመው አባቶርቤ በግብር ክልሉን መንግሥት አልባ የፉኮይስቶች መርመስመሻ አድርጎታል፡፡
በየትኛውም አካል አስተባባሪነት ይሁን፣ በኦሮሚያ ጭፍጨፋና ግድያ ያልተፈፀመበት ህዝብ እና አካባቢ የለም። ኦሮሚያ የደም ምድር፤ የመከራ ቀዬ ሆኗል። ኦሮሚያ ደም የተጠሙ ወጣቶች ደም ለማፍሰስ የሚክለፈለፉበት የሞት ቀጠና ነው ስንል ወደ እውነታው መቅረብ እንጅ መራቅ አይደለም።
በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ የዘር ማጽዳት ወንጀል የተፈጸመበት ክልል ነው፡፡ የጥቅምቱ እና የሰኔው ጭፍጨፋ አፍሪካ ውስጥ በ2019/20 በአህጉሪቱ አባል አገራት ውስጥ ያልተከሰተ በኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ ተብሎ በተከለለው የኢትዮጵያ ግዛት ብቻ የደረሰ የጥፋት ድግግሞሽ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ አሮሚያ የመከራ ምድር መሆኗን የሚያብሰው ጭፍጨፋ በውጭ ዜጎች ላይም ተፈፅሟል። የናይጀሪያዊው ከበርቴ ዳንጎቴ ስሚንቶ ስራ አስኪያጅ (ዜግነት ህንዳዊ)፣ በዱከም ቻይናውያን፣ በወለጋ ጃፓናውያን፣ በደብረዘይት ህንዳዊ ህይወታቸው ጠፍቷል። የጠፋውንና የተዘረፈውን ንብረት አይነትና ብዛት፣ የተቃጠለውን ፋብሪካ፣ በዚህ የደረሰውን ውድመትና ማህበራዊ ቀውስ ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አይደለም።
ሽመልስ አብዲሳ ‹‹ኦሮሚያን እንገነባለን›› ሲል ከዚህና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሆነ ተቀባይነት አለው፡፡ ሽብርተኝነትን ማጽዳት ከራስ ይጀምራል።
**
‹‹ኢትዮጵያን እንደግፋን›› ሲባል…
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ለሀገረ-መንግሥቱ ህልውና ስጋት ከሆኑትና መንግሥታዊ ሽርተኝነትን ከሚያራምዱ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች አንዱ ኦሮሚያ ነው፡፡ ‹‹ተረኛ ነን በአገሩ እንዘዝበት›› በሚል የእብሪት ፖለቲካ የሚንቀሳቀሰው ይኄ ኃይል፡- አንድ ሚሊዮን ጌዲዮን ከማፈናቀል፣ ቤኒሻንጉል ካማሽ ዞንና አሶሳን ከመውረር፣ አዲስ አበባ ላይ የቀጠለውን የመሬትና የመዋቅር ወረራ በማስቆም፣ ድሬዳዋና ሐረርን ለመዋጥ እያዛጋ ያለውን የፈሽስት ፖለቲካ መስመሩን በማረም ከተሞቹ የነዋሪዎቻቸው እንዲሆኑ በማድረግ፣ በክልሉ የሚኖሩ አማሮችን የፖለቲካ ውክልና ጥያቄ የሚቀበል፣  … ከሆነ በርግጥም ‹‹ኢትዮጵያን እንደግፋለን›› የሚለው ሃሳብ ራሱ የሚደገፍ ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ከፋሽስታዊ ፖለቲካቸው ታቀቡ ማለት ኢትዮጵያ በአንድ ጎኗ ሰላሟን አገኘች ማለት ነው፡፡
***
‹‹የአፍሪቃ ቀንድን እናረጋጋለን›› ሲባል…
የአፍሪቃ ቀንድ አገራት የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣  ጅቡቲ ና ኤርትራ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ከሆነ አንድ የክልል መንግሥት ከሌሎች አገራት ጋር የቀጥታ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችል ‘የፌዴሬሽኑ ሀ ሁ’ ነው፡፡ ኦሮሚያ ተብሎ የተከለለው የኢትዮጵያ ግዛት  363.375 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው፡፡ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር ይዋሰናል፡፡ ቀላል የጂኦግራፊ ዕውቀት ነውና ደቡብ ሱዳን ምስራቅ አፍሪቃ እንጅ የአፍሪቃ ቀንድ ውስጥ የምትካተት አገር አይደለችም፡፡
አስቂኙ ነገር በሁለቱም አዋሳኝ አገራት የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ ጠንካራ ይዞታ ያለው መሆኑ ነው፡፡ ወለጋን ተንርሶ የሚዋሰነው የደቡብ ሱዳን መስመር ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ ዝውውርና የማዕድን ኮንትሮባንድ የሚከናወንበት አካባቢ ነው፡፡ የኦነግ ሸኔ አባላት አንጻራዊ ነጻ ይዞታቸው ሆኖ የከረመበት ቀጠናም ነው፡፡ እንኳንስ ለሽመልስ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ከቅኝት በስተቀር በአካባቢው ውሎ ለማደር አስቸጋሪ ቦታ ነው፡፡ በኬንያ በኩል ያለው የድንበር ተዋሳኝነት እንደ ደቡብ ሱዳኑ የከፋም ባይሆን የኦነግ ሸኔ አባላት ከጉጅና ከቦረና ዞኖች ጥቃት አድርሰው የሚሸሸጉበት ቀጠና ነው፡፡ በነሐሴ/2012  የኬንያ የሰሌዳ ቁጥር ባላት አንዲት ፒክ አፕ ደብል ጋቢና መኪና የኦነግ ሸኔ አባላት ጥቃት አድርሰው ወደ ኬንያ ሲመለሱ በመከላያ ሰራዊት ተመተው መውደቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ በየጊዜው መሰል ክስተቶች የሚያጋጥሙበት ቀጠና ነው፡፡ ሞያሌ በጸጥታ ስጋቷ ከአፍጋኗ ካቡል ለይተን የምናያት አይደለችም፡፡
አፍሪቃ ቀንድን ቀርቶ በታሪክ አጋጣሚ ‘ምራው’ ተብሎ የተሰጠውን ክልል በአግባቡ መያዝ አልቻለም፡፡ የወለጋን ደም ያፋሰሰ ፖለቲካዊ ቅራኔ መዋቅራዊ ለውጥ (ክልልነት) እንጅ ሌላ ምንም ነገር ሊፈታው እንደማይችል ሰዎቹ ከገባቸው ቆይቷል፡፡ አርሲ፣ ባሌና ሐረርጌ ለሽመልስ መንግሥት ሳይሆን ለመካከለኛው ምስራቅ ዓላማ ወራሾች ልባቸው ቅርብ ነው፡፡ በክርስትና ማንነቱ እየተገፋ ያለው የሸዋ ኦሮሞ አማራጭ ፍለጋ እያማተረ ነው፡፡ ጅማ ከዐቢይ የሚያፈነግጥ ሁሉ ‹ የሰኚ ጠላት ነው› በሚል ፈርጇል፡፡ ቦረናና ጉጅ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም መንግሥት ዘንግቶናል በሚል ቅሬታ ራሳቸውን በራሳቸው ለመጠበቅ የጦር መሳሪያ ይዞታቸውን አጥብቀዋል፡፡  ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው  የክልሉ መንግሥት መኖሩን እያስረገጠ ያለው በሚዲያ ፕሮፖጋንዳና አዲስ አበባ ላይ በሚያሳርፈው መዋቅራዊ ጫናና ወረራ እንጅ በተግባር 363.375 ስኩዌር ኪሎ ሜትር  ያካለለ መንግሥታዊ ይዞታ የለውም፡፡
ትላንት ለምለሙ የወለጋ መሬት ላይ ሦስት ነገር ይለቀም ነበር፡- ዶላር፣ ዮሮና ፓውንድ፤ ዛሬ በሠላም እጦት የተነሳ የጥይት ቀልሃ፣ ቁስለኛና ሙት ከመልቀም በዘለለ በተፈጥሮ የታደለውን ቡናና ሰሊጥ በወጉ ማምረት አቁሟል፡፡
ሽመልስ አብዲሳ እንዲህ ባለ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቆ ነው እንግዲህ ‹‹ ኦሮሚያን እንገነባለን፤ ኢትዮጵያን እንደግፋለን፤ የአፍሪቃ ቀንድን እናረጋጋለን›› የሚለው? Bravado !
****
ሰውዬውን ‘አክቲቪስት ሽመልስ’ እያልን ስንጠራ በምክንያት ነው።
Filed in: Amharic