>

ፕሮፌሰር መስፍንን ሳስታውሳቸው… (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ፕሮፌሰር መስፍንን ሳስታውሳቸው…

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

በአንድ ወቅት… ኢሰመጉ ከተቃዋሚ ድርጅቶች እና ከነጻው ፕሬስ ባልተናነሰ፤ ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ የኢህአዴግን አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን ያጋልጥ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ደግሞ የኢሰመጉ መስራች እና መሪ እንደመሆናቸው መጠን በሚዲያ ላይ እየወጡ መግለጫ ይሰጣሉ። እናም በዚያን ጊዜ ለነበርነው ወጣት የነጻው-ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ የፕሮፌሰር መስፍን እና እንደሳቸው በኢትዮጵያዊነት ልባቸው የነደዱ ዜጎች ንግግር፤ የድፍረት ምርኩዝ ሆኑን። በዚያ ላይ… ተናግረን ብንታሰር የሚጮሁልን፤ ፅፈን ብንከሰስ ጠበቃ የሚሆኑልን… ምንጊዜም የማንረሳቸው፤ የድፍረታችንም ምንጭ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በፊተኛው ረድፍ ላይ የሚጠቀሱ፤ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
*      *     *
የፕሮፌሰር መስፍን ንግግር… ብዙውን ጊዜ መሬት ጠብ አይልም!
ከአንዳንድ ንግግሮቻቸው መካከል አንዳንዶቹ ደግሞ፤ ልብ ውስጥ የሚቀሩ ናቸው። በተለይ አንድ ሰሞን… በመንግስት ሚዲያዎች አማካኝንነት፤ ኢህአዴግ – በፕሮፌሰር መስፍን ላይ ትልቅ የስም ማጥፋት እና የማስፈራራት ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። ይሄን ጊዜ ፕሮፌሰር እንዲህ አሉ። “ከምንም ነገር በላይ የምፈራው ፍርሃት መፍራት መሆኑን ቢያውቁ ኖሮ፤ ኢህአዴግ ሊያስፈራራኝ አይሞክርም ነበር!” በማለት የሰጡት የጀግና ምላሽ አንጀት የሚያርስ ነበር። ይህ የሆነው በኢህአዴግ የሽግግር ዘመን ነው።
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ “የኢህአዴግ መንግስት በኢሰመጉ ላይ ቂም ቋጥሮ ኖሮ፤ በኢሰመጉ ቢሮ ላይ በወቅቱ ለጆሮ የሚከብድ ባለብዙ ዲጂት፤ “ክፍያ እንዲፈጽም፤ ይህ ካልሆነ ግን ቢሮው ይዘጋል” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል  ደብዳቤ ለፕሮፌሰር መስፍን ደረሳቸው። ይህ ድርጊት ሆን ተብሎ ቢሮውን ለመዝጋት የተደረገ በመሆኑ፤ የድርጅቱን መስራች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ብቻ ሳይሆን፣ ሰራተኞቹንና የኢሰመጉ ደጋፊዎችን አሳዘነ። በወቅቱ ህዝቡ ከነበረበት የኢኮኖሚ አቅም አንጻር ይህን ያህል ገንዘብ አዋጥቶም ሆነ ሰብስቦ መክፈል አስቸጋሪ ነበር። ስለዚህ ፕሮፌሰር መስፍን ወደ ውጭ አገር ሄደው፤ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አቤቱታቸውን አቀረቡ።
ኢሰመጉ በዋሺንግተን ዲሲ በጠራው ስብሰባ ላይ፤ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል። የገንዘብ መዋጮም ተደረገ፤ ነገር ግን ኢሰመጉ የሚፈልገውን ያህል ገንዘብ ማዋጣት አልተቻለም። በዚህን ወቅት አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሰው፤ ሙሉውን የእዳ ወጪ የሚሸፍን መሆኑን ለፕሮፌሰር አሳወቀ። እናም የኢሰመጉ እዳ በዚህ አይነት ተከፍሎ ከእዳ ነጻ ሆኑና ቢሮው በድጋሚ ተከፈተ። በወቅቱ ኢህአዴጎች አፈሩ፤ እኛ ግን “እፎይ” አልን። እዳውን “የከፈለው ኢትዮጵያዊ ግን ዛሬም ድረስ ባናውቀውም፤ ባለበት “ክብረት ይስጥልን” ብለናል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በአካል ለማግኘት እድል ያገኘሁት፤ ይህ በኢሰመጉ ላይ የተቆለለው የሃሰት እዳ የሚከፈል መሆኑን ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው። ከመግለጫው በኋላ… ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተዋወቅን። ከአገር ቤት ከመውጣቴ በፊት፤ ከወጣሁ በኋላም በአሜሪካ፤ ባለፈውም አመት ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ፤ ቤታቸው ድረስ ሄጄ ለመጠየቅ ያበቃኝ፤ ኢሰመጉ ከተከፈተና ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ፤ አብረን ለነበርነው ወጣቶች የሰጡን የአደራ ቃል ነው። “እናንተ ወጣቶች ናቹህ። የኢትዮጵያ የወደፊት እድል ያለው በናንተ እጅ ላይ ነው። ይህችን አገር በታማኝነት እና በእውነት፤ ተስፋ ባለመቁረጥ አገልግሉ።” ይህ ቃል… ወላጅ አባቴ ከሰጡኝ ምክሮች በተጨማሪ፤ እንደህይወት መመሪያ አድርጌ የምከተለው፤ በደሜ ውስጥ የተዋሃደ ቃል ኪዳን ሆኖ ቀርቷል። ቃልን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚቻል ከሆነ፤ በዚህ አጋጣሚ ይህን የፕሮፌሰር አደራ ለመጪው ትውልድ እናስተላልፋለን። “…ይህችን አገር በታማኝነት እና በእውነት፤ ተስፋ ባለመቁረጥ አገልግሉ።”
ከዚህ በኋላ ፕሮፌሰር መስፍንን በተለያዩ አጋጣሚዎች አግኝቻቸዋለሁ። ከሁሉም ቀናቶች ግን ይሄኛው ቀን ልዩ ነበር። በአሰፋ ማሩ የቀብር ስነ-ስርአት ላይ የተናገሩት ንግግር በፍጹም የሚዘነጋ አይደለም። ስለአሰፋ ማሩ ጉዳይ የማታውቁ ብዙ ሰዎች ልትኖሩ ትችላላችሁና (ለቀድሞውም ሆነ ለአዲሱ ትውልድ የሆነውን ነገር እናጋራችሁ) ከዚያ በኋላ… የፕሮፌሰር መስፍንን ንግግር እና ሚና እናጫውታችኋለን።
ነገሩ የሆነው እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር፤ ሚያዝያ 30 ቀን፤ 1989 ዓ.ም ነው። አቶ አሰፋ ማሩ መምህር ነበር። ሆኖም የኢህአዴግ በትር ካረፈባቸው የመጀመሪያዎቹ መምህራን አንደኛው ሆነ። ስራውን ከለቀቀ በኋላ ለGood Shepherd በጎ አድራጎት ድርጅት መስራት ጀመረ። መስሪያ ቤቱ ከሚኖርበት ወረዳ 12፣ ቀበሌ 06 በአንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ሁሌ ጠዋት ጠዋት ይቺን አንድ ኪሎ ሜትር በእግሩ ነው የሚሄደው። እናም ዳገቱን እንደጨረሰ፤ ከፊት ለፊት 6 ፖሊሶችን የጫነ ቶዮታ ፒክ-አፕ ከፊት ለፊቱ መጣ። በመኪናው ላይ የተጫኑት ታጣቂዎች ክላሽንኮቭ መሳሪያ እና ቦንብ የታጠቁ የህወሃት ሰዎች ናቸው። መኪናው ከፊት ለፊቱ መጥቶ ሲቆም፤ መኪናውን አቋርጦ ከመሄዱ በፊት ከኋላው እየተከተለ ሲመጣ የነበረ… ሌላ ኦፔል የፖሊስ መኪና ለግድያው ተሰናዳ። ከዚያም ከኋላ በኩል የተቀመጠ ሰው አውቶማቲክ መሳሪያ አውጥቶ፤ አነጣጥሮ የአሰፋ ማሩን ጭንቅላት እና ደረት መትቶ፤ እንደአመጣጡ በፍጥነት እየበረረ ሄደ።
ታሪኩን እዚህ ላይ ማብቃት ይቻላል። ነገር ግን… በዚህ አጋጣሚ የደረሰውን ግፍ የማያውቁ እንዲያውቁ… የአቶ አሰፋ ማሩን የመጨረሻ መጨረሻ በአጭሩ እንግለጽላቹህ። ገዳዩን የያዘው ኦፔል መኪና ከሄደ በኋላ፤ ፒክ-አፑ ላይ የነበሩት 6 ፖሊሶች ከመኪናው ወርደው መንገዱን በሁለቱም አቅጣጫ ዘጉና፤ የሟቹን አሰፋ ማሩ ኪስ እና የያዘውን ቦርሳ ከፍተው ይበረብሩ ጀመር። ከዚያም…. ሌላ የፖሊስ መኪና መጥቶ የአሰፋ ማሩን አስከሬን ጭኖ በእንጦጦ ጀርባ በኩል፤ ወደ ስድስት ኪሎ አቅጣጫ ሄደ።  ይህ ከሆነ… ከአንድ ሰአት በኋላ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ ሰው ወደ ኢሰመጉ ቢሮ ደውሎ፤ “አሰፋ ማሩ አባላቹህ ነው?” ሲል ጠየቀ።
“አዎ አባላችን ናቸው” አሉ ስልኩን ያነሱት የኢሰመጉ አባል።
እናም ደዋዩ ሰውዬ “አሰፋ ማሩ በመኪና አደጋ ሞቷል። አስከሬኑን መውሰድ ከፈለጋቹህ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ታገኙታላቹህ” ተባሉ። እንደተባለውም የኢሰመጉ ሰዎች ዳግማዊ ሆስፒታል ሲሄዱ፤ አቶ አሰፋ ማሩ ጭንቅላቱንና ደረቱን በጥይት ተመትቶ መገደሉን አረጋገጡ።
(ታሪኩን ለማፍጠን ያህል) ከሰአት በኋላ… የሬዲዮ መገናኛ የያዙ ፖሊሶች ወደ አሰፋ ማሩ ቤት ሄደው፤ ቤታቸውን በርብረው የኢሰመጉ እና የኢመማ መግለጫዎች ያሉበትን ጽሁፍ ሰብስበው ወሰዱ። በንጋታው ወደ ኢመማ ቢሮ ሄደው ቢሮውን ፈትሸው፤ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ፋይሎች በመኪና ጭነው ወሰዱ። ከሰአት በኋላ የኢትዮጵያ ሬዲዮ “ፀረ ሰላም የሆኑ ሃይሎች…” ብሎ ከተነተነ በኋላ “ዋናው መሪ አሰፋ ማሩ ሊያመልጥ ሲል ተገደለ።” የሚል ዜና አቀረበ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተመሳሳይ ውሸት መናገር ብቻ ሳይሆን፤ በሳምሶናይቱ ውስጥ ቦንብ ይዞ እንደነበር በምስል አስደግፎ አቀረበ። (ታሪኩን ለመጨረስና ለታሪክ ለመተው ያህል) በንጋታው በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ 5ኛ አመት፣ እትም 201 ላይ… አቶ አሰፋ ማሩ የአርበኞች ግንባር መሪ እንደነበርና ሊያመልጥ ሲል መገደሉን ያትታል።
እኛ ደግሞ እንደጋዜጠኝነታችን ስፍራው ድረስ ተገኝተን፤ በቀሽም የኢህአዴግ ገዳዮች የተቀናበረ አሳፋሪ እና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ተግባር አጋለጥን። በኋላ ላይ ከባለቤቱም ሆነ ከጓደኞች እንደተረዳነው፤ አሰፋ ማሩ እንኳንስ ቦንብ ሊያፈነዳ ቀርቶ፤ አይቶትም እንደማያውቅ ነገሩን። ሁሉም ነገር ቀልድ ይመስል ነበር። (ሌላውን ዝርዝር እውነታ ለመረዳት በወቅቱ ኢሰመጉ ያወጣውን መግለጫ መመልከት ይበቃል) እናም ወደ አሰፋ ማሩ የቀብር ስነ ስርአት ልውሰዳቹህ። በዚህ የቀብር ስነ-ስርአት ላይ ለመገኘት ወደስፍራው የሄድኩት፤ ከአንድ ሌላ ጋዜጠኛ ጋር መሆኑን አስታውሳለሁ። (ከሲሳይ አጌና ወይም ከአክሊሉ ታደሰ ሊሆን ይችላል። አሁን ተዘነጋኝ።) የሆኖ ሆኖ በአሰፋ ማሩ የቀብር ስነ ስርአት ላይ ተገኘን። ወንድ ልጁ 2 አመት አልሞላውም፤ ሴቷም ገና የ2ወር አራስ ነበረች። የአሰፋ ማሩ ባለቤት እና ቤተሰቦቹ አምርረው ያለቅሳሉ። ሌላው ሃዘንተኛ ደግሞ… ንዴት እና ቁጭት ውስጡን ያበገነው፤ እንባውን ያተነነው ይመስላል። በዚያ ላይ ጸጉረ ልውጦች የሃዘኑን ድባብ እና እና የሃዘንተኞችን ተሳትፎ ለመሰለል፤ የደህንነት ሰራተኞች በለቀስተኛው መካከል ተገኝንተዋል። የቀጨኔ ሰዎች በሹክሹክታና በጥቅሻ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ እያደረጉ ነው።
የቀብር ስነ ስርአቱ ካለቀ በኋላ… ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ንግግር አደረጉ። ሙሉ የንግግራቸውን ቃል በወቅቱ በፊያሜታ ጋዜጣችን ላይ አውጥተነዋል። የንግግራቸው ፍሬ ቃል ግን እንዲህ የሚል ነበር። በቅድሚያ ስለአሰፋ ማሩ ታታሪነት እና ንጽህና ተናገሩ። ለባለቤቱ፣ ለቤተሰቡ እና እዚያ ለተሰበሰበው ህዝብ መጽናናትን ተመኙ። በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ግን እንዲህ አሉ፤ “ይህን ግድያ የፈጸማቹህ እና ያስፈጸማቹህ የኢህአዴግ ሰዎች ይህ መልዕክት ለናንተ ነው።” ሲሉ በዚያ የነበረው ሃዘንተኛ በሙሉ፤ ለቅሶውን አቁሞ ጸጥ አለ። ፕሮፌሰር በድፍረት እና በድንቅ ድምጸት ንግግራቸውን ቀጠሉ።
“…እዚህ መሃል ከመንግስት የተላካቹህ የደህንነት ሰላዮች መኖራችሁን እናውቃለን። ‘ማን ምን አደረገ፤ ምን ተናገረ?’ የሚለውን ለመሰለል ነው እዚህ የተገኛችሁት። እንግዲያውስ ይህን መልዕክት ለአለቆቻቹሁ እንድትነግሯቸው እንፈልጋለን።” ለወያኔ ሰላዮች አስጨናቂ፤ ለኛ ደግሞ አስደናቂ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን ንግግር ቀጠለ።
“…ይህን መልዕክት ለአለቆቻቹሁ ንገሯቸው። እናንተ የገደላችሁት የአሰፋ ማሩን ስጋ ነው። መንፈሰ ጠንካራነቱን እና መልካም ስሙን ግን ልትገድሉት አትችሉም። ዛሬ እዚህ ቦታ ላይ የቀበርነው የአሰፋ ማሩን አካል ነው። መልካም ስሙ እና ስራው ግን ከዚህ መቃብር በላይ ይሆናል። ትላንት አሰፋ ማሩን ገድላችኋል፤ ሆኖም በሺዎች የሚቆጠሩ አሰፋ ማሩዎች ይፈጠራሉ። ይልቁንስ ከመቃብር በታች እንጂ በላይ ለማይሆነው ስለናንተ አሟሟት አዝናለሁ…” ከዚህ የፕሮፌሰር ንግግር በኋላ ለቀስተኛው በመጽናናት ወደየመጣበት ተመለሰ። ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉትም፤ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ቆመን፤ ከመቃብር በላይ ስለሆነው አሰፋ ማሩ ለማውራት በቃን። የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።
ከዚህ በኋላ… ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር የተገናኘነው፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ፤ ከ15 አመታት በፊት – በአሜሪካ ኮለምበስ ኦሃዮ በጋበዝናቸው ወቅት ነበር። እለቱን ድንቅ የሆነ ትምህርታዊ ንግግር አደረጉ። ምሽቱን ደግሞ ከስብሰባው አስተባባሪዎች ጋር በአቢሲኒያ ሬስቶራንት ለእራት ግብዣ ተገናኘን። በዚህ እለት ከወጣቱ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን ከሰሙ በኋላ፤ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ያደረጉትን ንግግር፤ ዛሬም ድረስ እያነሳን የምናወጋው ጉዳይ ስለሆነ፤ በስፍራው የነበሩ በሙሉ ይህን አጭር ንግግር የሚያስታውሱት ይመስለናል። ፕሮፌሰር ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ፤ “ኧረ ይቀመጡ!” ያሏቸው ሰዎች ነበሩ። ፕሮፌሰር ግን… “ይቅርታ መጠየቅ ስለምፈልግ ነው የምነሳው። በባህላችን ደግሞ ይቅርታ ጠያቂ ቆሞ ወይም ተንበርክኮ ነው ይቅርታ የሚጠይቀው። ተቀምጬ ይቅርታ ልጠይቅ አልችልም…” በማለት የይቅርታ ንግግራቸውን ቀጠሉ።
“ጥያቄያቹህ ትክክል ነው። ለናንተ ያወረስናቹህ ኢትዮጵያዊነትን አይደለም። …ከኔ በፊት እና በኔ ትውልድ የነበሩ ምሁራን፤ ጓደኞቼ እና አጋሮቼ ዛሬ በህይወት የሉም። ከኔ በኋላ የመጣው ትውልድ በቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ጦስ እርስ በርሱ ተላልቋል። በጣም ያሳዝናል። እናንተ ወጣቶች ከዚያ ትውልድ በኋላ የመጣቹህ የኢትዮጵያ ልጆች ናቹህ። ለናንተ ያወረስነው እርስ በርስ መጠላለፍ እና መጠላላት መሆኑ በጣምም ያሳዝነኛል። ፍቅር እና አብሮ መስራትን አላወረስናችሁም። ለዚህ ደግሞ በተለይ ከኛ በኋላ የመጣው ትውልድ ተጠያቂ ነው። ሆኖም እነዚያ ሰዎች ዛሬ የሉም። አሁን እዚህ የቆምኩት በኔም ሆነ ከኔ በኋላ በመጣው ትውልድ ስላጠፋነው ጥፋት፤ ይቅርታ እንድታደርጉልን ነው።” የሚል ያልተጠበቀ ንግግር ሲያደርጉ፤ በምን አይነት መመለስ እንዳለብን የማናውቅ ወጣቶች እንባችንን እየጠረግን፤ ይቅርታቸውን ተቀበልን።
ከዚህ በኋላ… ፕሮፌሰር መስፍን በተደጋጋሚ ወደ አትላንታ ጆርጂያ ሲመጡ ለመገናኘት እድሉን አግኝተናል። በተለይም በቅንጅት ፓርቲ የጎላ እንቅስቃሴ ወቅት፤ በአሜሪካ አቆጣጠር በ2005 አትላንታ ሲመጡ፤ የተደረገላቸው የጀግና አቀባበል ከቶ አይዘነጋም። ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጓደኞች ጋር እንዲገናኙ ከመደረጉም በላይ ጁላይ 2 ቀን፣ 2005 ያደረጉት ንግግር ከሁላችንም ህሊና የሚጠፋ አይደለም። ፕሮፌሰር መስፍንን በብዙ ስራዎቻቸው ልናወድሳቸው እና ልናደንቃቸው ይገባናል። “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” የሚለው አባባል፤ ውስጣችን ገብቶ የሚዋሃደው፤ ፕሮፌሰር ለአገራቸው እና ለህዝቡ በድፍረት፣ በእውነት እና በታማኝነት ያደረጉትን መልካም ስራ ስናስብ ነው –  በተለይ በደርግ ማምሻ እና በኢህአዴግ የጭቆና ዘመናት ያደረጉትን ስራዎች ደግመን ደጋግመን ስንመረምር፤ እውነትም “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” ማለት ብቻ ሳይሆን፤ የቃሉም ትርጉም ይገባናል።
በመጨረሻም… ለመጨረሻ ጊዜ ፕሮፌሰርን ያገኘንበትን አጋጣሚ በማስታወስ እንለያያለን። ባለፈው አመት የመስቀል ዋዜማ አካባቢ ቤታቸው ለመሄድ ተዘጋጀን። እኔና ክንፉ… እነ ጋሽ ቸሩና ዶ/ር ሞገስ፣ እነየሺዋስና አንዷለም አራጌ፤ እነሼክስፒር ፈይሳ እና ሌሎችም ሰዎች ከፕሮፌሰር መስፍን ቤት ተገናኘን። በወቅቱ ፕሮፌሰር መስፍን፤ መንፈሳቸው እንጂ አካላቸው እየደከመ መምጣቱ በግልጽ ያስታውቃል። የሰው እርዳታ በታከለበት ሁኔታ ከአንድ ቦታ ወደሌላው ይሄዳሉ። እኛ የአመት በአል ክትፎ እና ጥብስ ስንበላ፤ ፕሮፌሰር መስፍን፤ የቀረበላቸውን ሾርባ በእርጋታ ይመገባሉ። መዋጥ የሚገባቸውን መድሃኒቶች በማከታተል ይወስዳሉ። እንዲያም ሆኖ በምናደርገው ጨዋታ እኩል ተሳታፊ እና መልስ ሰጪ፤ ብሎም ከክርክር ጨዋታችን በኋላ፤ የመጨረሻውን ዳኝነት ይሰጡ ነበር።
እናም ስለአገራችን ብቻ ሳይሆን፤ ስለመሪዎቿም አወራን። ስለዶ/ር አብይ፣ ስለእስክንድር ነጋ፣ ስለሌሎች ተቃዋሚዎች ተነጋገርን። አንዳንዶች ዶ/ር አብይ አህመድን በተመለከተ ያደረጉትን ወቀሳ፤ ፕሮፌሰር አልተቀበሉትም። ሆኖም አገሪቱ ያለችበትን የውድቀት አደጋ፤ ይልቁንም የወደፊት እጣ ፈንታዋ… እኛንም ሆነ እሳቸውን ክፉኛ አሳስቧቸዋል። ፕሮፌሰር የሁላችንንም አስተያየት ከሰሙ በኋላ… የሳቸውን ሃሳብ እንዲህ በማለት፤ በአጭር ቃል ገለጹልን። “ከጣሊያን ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፤ ከወደቀችበት ተነስታ ዳግም ተውለበለበች። አሁን ደግሞ ሰንደቋ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ እየወደቀች ነው። ከዚህ በኋላ የምትመጣው፤ አዲሷ ኢትዮጵያ ግን ወድቃ የምትነሳው ኢትዮጵያ ናት” አሉን።
ይህን የፕሮፌሰር መስፍን አነጋገር፤ እዚያ የነበርነው ሰዎች በሙሉ እናስታውሰዋለን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዛሬም ድረስ በውስጣችን እያላወስነው አለን። በእርግጥም ኢትዮጵያ መውደቅ የጀመረችው በብሔር እና በጠባብ የጎሰኝነት አስተሳሰብ መመራት ስትጀምር ነው። በጥላቻ ላይ የተመሰረተ የታሪክ ምዕራፍ እና አጻጻፍ ኢትዮጵያን ይገድላታል እንጂ፤ አያድናትም። ዛሬ ፕሮፌሰርን ስናስባቸው… ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ስላላቸው ክብር እናስባለን፤  በታማኝነት ስላገለገሏት አገራቸው እና ህዝባቸው ስንል… እኛም ክብር እንሰጣቸዋለን። ይህ ህዝብ እና አገር ዳግም ከፍ ወዳለው የክብር ሰገነት ይሸጋገራል። ፕሮፌሰር እንዳሉት ወድቀን እንነሳለን እንጂ፤ ወድቀን አንቀርም። ዳግም እንነሳለን፤ ለዚህም አምላክ ይርዳን።
Filed in: Amharic