>

የአምስት ወራት የግል ማስታወሻ

የአምስት ወራት የግል ማስታወሻ
አዘጋጅ Jomanex Kasaye
ያ ትውልድ ያመነበትን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ መስዋዕትነትን እንደከፈለው ሁሉ እህት በወንድም ላይ ጠቁማ ወደ ሞት የነዳችበትም አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል ወንድም ከወንድም ጋር የሚያፋጅ ግዜ ላይም ነበሩ፤ ዛሬ ላይ እንደቀልድ ምንሰማው ለመፍረድም ቀላል የሚመስሉትአስቀያሚ የታሪኮቻችን አጋጣሚዎች ዛሬም ላይ ይከሰታሉ እኛም ስህተቶችን የምንደግም እንጂ ከስህተቶቻችን የምንማር ዓይነቶች አይደለንም፡፡
ከኢህአዴግ ወገን ላልሆነው ፖለቲካ የሚወደድ ሆኖባይሆንም በአገር ጉዳይ ያገባኛል ያሉ ሰዎች የሚገናኙባቸው ቦታዎች የተለመዱ ናቸው እስር ቤት፣ ሰላማዊ ሰልፍ(እጥረት ቢኖርብንም)እንዲሁም ፌስቡክ የመጀመሪያውን ተርታ ይይዛሉ፡፡ እንደውም Journalist Edom Kassayeማህበረሰብ ሚዲያው እርስ በርስ ለመግባባት ለመገማገምና ለመተዋወቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በኤዶም ካሳዬ እና በእኔ መካከልም ትውውቅምክንያት የሆነውና በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ለመሄድ ከተሰባሰቡት የዞን ዘጠኝ አባላት ጋር ተሰባስበን በነበረበት ወቅት ነበር ወዲያውም ኤዲ ጆማ ተባብለን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ሞቅ ወዳለው የፖለቲካ ጨዋታ ስንገባ አይተውን የተጠራጠሩት ጓደኞቻችን ከዛሬ በፊትም ሳትገናኙ አልቀራችሁም አይነት ትንኮሳ ጀምረው ነበር የምንታጨቅበት ታክሲ ሲመጣ ወሬያችን ቢቋረጥም፡፡

ከቂሊንጦው እስር ቤት የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ጥየቃ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገናኝተን ተጨዋውተናል፣ እንደውም በአንድ ወቅት በጨዋታችን ውስጥ ደጋፊና ተቃዋሚ ጥግ እና ጥግ (አንዳንዴም ጽንፍ) የያዙ ፍረጃዎች ኑሮ ፈተና ለሆነባቸው የቤተሰብ ሃላፊዎች ስራቸው አስተማማኝ ይሆን ዘንድ አባልነት ግዴታ ሆኖባቸው አባል የሆኑትንና ያልሆኑት ግን ውሳኔዎችን ለማስቀየር ምንም ዓይነት አቅም እና ስልጣን የሌላቸው ነገር ግን በተቃውሞ ጎራ በካድሬነት የመፈረጅና የመዘለፍ አጋጣሚዎችን ያስተናገዱ ሰዎች ስለመኖራቸውና አንዳንዶች በብሔር ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ተቸንክረው ወደ መከላከልና ጽንፍ የያዙ ደጋፊ ሆነው ስለመገኘታቸው እንዲሁም በኑሮ ውድነት ምክንያት መቃወም እየፈለገ ቤተሰቡን ማስተዳደር ፈተና ሆኖበት ከቤት ኪራይና ከሌሎች ወጪዎች የሚናጡ ባልና ሚስቶች ብሶትን መሰረት አድርገን መሃከል ላይ ስለምንገናኝበት አልያም የእነኚህን ሰዎች ስሜት ሌሎች እንዲረዱ ለማድረግ አንድ ጽሁፍ በጋራ ለመጻፍ ሁሉ ተመካክረን ነበር፡፡

በጋዜጠኛነት በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችውስጥ ያሳለፈችው ኤዶም ከዞን ዘጠኞችና ከእነ አስማማውና ተስፋለም ጋር ስትከሰስ የግድ ዞን ዘጠኝ ነሽ እያሉ ነበር በሕግ የሚቀልዱትፖሊሶች የከሰሷት፡፡

ከዛ በፊት ግን ዞን ዘጠኝ ባትሆኚም ከእነሱ ጋርስለምትቀራረቢ መረጃ ስጪን እያሉ የገባችበት የሚገቡ በስልክ ፋታ የሚያሳጧት “ደህንነቶች” ነበሩ፤ ኤዲ በአንድ ወቅት የሆነ መስሪያ ቤት ስራ ለማመልከት ጎራ ብላ ስትወጣ አፍታም ሳይቆይ ይደወልላታል በዚህ ወቅት የደወለው ደህንነቱ ነበር የመስሪያ ቤቱን ባለቤትስም ጠርቶ “ ሥራ እንዳመለከትሽ ሰምቼያለሁ ከእኛ ጋር እኮ ብትተባበሪ የተሻለ ደረጃ በተሻለ ደሞዝ አስቀጥርሻለሁ” ብሏት ነበር፤በተደጋጋሚ ወቅትም “ዞን ዘጠኞች ለምን መጻፍ አቆሙ የተደበቀ ህቡህ ሥራ ስለጀመሩ ነውና መረጃ እንድትሰጪኝ እፈልጋለሁ አለበለዚያ ውጪ አገር ስብሰባ ላይ መንግስትን ለማሳጣት የተናገርሻቸውን ምክንያት አድርገን ልናስርሽ እንችላለን አንቺ ብቻ ተባበሪን እንጂ ወደ ውጪም መሄድ ከፈለግሽ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ምንም ችግር የለውም ትሄጃለሽ አንቺ ብቻ ተባበሪን “ የሚሉ ማስፈራሪያዎችና ማግባቢያዎች ይቀርቡላት ነበር ፡፡ ኤዶም በመልሷ “እኔ እስከማውቀው ልጆቹ ምንም እየሰሩ አይደለም ትልልቅ ሆቴል ውስጥ ኢንተርኔት ነጻ ስለሆነ እና ሰውም ስለማይበዛ ማኪያቶ እየጠጡ የሚጨዋወቱናቸው መጻፍ ስላቆሙ ጓደኝታቸው ተቋረጠ ማለት ስላልሆነ ይገናኛሉ ከመንግስት ጫና ስላበዛችሁባቸው እንዲሁም በግል ምክንያቶቻቸውእንጂ ሌላ ነገር ስላሰቡ አይደለም” ብላ መልሳላቸው ነበር፡፡ የደህንነቶች ክትትል አሁንም የተባበሪና መረጃ አምጪ ትዕዛዝ ለረጅም ጊዜ ፋታ አልሰጣትም ነበር ፡፡በአንድ ወቅት ስብሰባ ላይ ሆና ስልክ ባለማንሳቷ የገባችበት እንደሚገባ እና እንደማታመልጣቸው ከዛቻ ጋር የጽሁፍ መልዕክት ተልኮላት እነደነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ደህንነቱና አለቆቹ የሆነ ነገር እየተካሄደ ነው የሚል ስጋት መስከራቸው ምንም የሚያጠያይቅ አልነበረም፡፡ ( እኛም እነደ ቡድን አውነቱን ሲያውቁ ይተውታል የሚል የዋህነት ነበረብን) እናም ኤዶም የምታቀርበው እውነተኛ መረጃ ከሌለ በፈጠራም ቢሆን እንድትተባበራቸው ግፊት ሲደርጉባት የቆየ ቢሆንምለእንደዚህ አይነት ርካሽ ተግባር ተባባሪ ባለመሆኗ የጅምላ እስሩ ተቋዳሽ ሆናለች፡፡ የእኔም መትረፍ ያለኤዶም እና ናትናኤል ፈለቀ(ናቲ) የሚቻል አልነበረም፡፡ “freedom of expression ትሰራላችሁ ወንጀል አንደሆነ አታውቁም?” የሚሉ የእውቀት ደረጃቸው ለመግባባት አንኳን የሚያስቸግሩ ሰዎቸን እነ ኤዲ ለወራት ለማሳመን ሲጥሩ ከርመዋል፡፡
በታሰሩ ቀን ማግስት በነበረው ቅዳሜ ጠዋት ላይ በቅርቡ የልጅ አባት የሆኑትን ወዳጆቼንለመጠየቅ ከሰአት በኋላ ከዞን ዘጠኞች ጋር ቴስት ኦፍ አዲስ የምግብ ፌስቲቫልን ለመታደም ማታ ላይ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመታደምአስቀድሜ አቅጄ የነበረ ቢሆንም ሰው ያስባል ኢህአዴግ ያስራል ሆነና የሕይወቴ አንዱ እና ትልቁ የምለው ብዙ ወንድሞቼንና እህቶቼን በእስር ያጣሁበት ማግስት ሆነ፡፡
ጊዜው አምስት ወራት ተቆጥረዋል ቢልም ለብዙዎቻችን እንደቆመ ነው፣ ንጹህ ኅሊና ያላቸው ለትውልድ ምሳሌ የሚሆኑ ጓደኞቼን ህገ መንግስታዊ መብት ባልተከበረበት፣ የህግ የበላይነት እና የህግ ስርአት መመራት ቀልድ በሆነበት በስርአቱ አገልጋዩች መነካታቸው ያንገበግበኛል፣ ለኔ ጊዜው አሁንም እንደቆመ ነው ሻንጣዬ ውስጥ ያለውን እቃ አውጥቼ ቁምሳጥን ውስጥ ለመጨመር አዲስ ሕይወት ከጀመርኩ እነሱን የምረሳ እየመሰለኝ እንዳለ አለ ተመልሶ እነሱን እንደሚያገኝ ለጉዞ እነደተሰናዳ ሰው ልቤ እንደተሰቀለ እስካሁን አለሁ፡፡ ይህ እኔም ሆነ የተረፍነው ወዳጆቼ የምንጋራው ስሜት ነው፡፡
ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚያኮራ መከራን ለመጋፈጥ የቆረጡ እውነተኛና ሃቀኛ ሰዎች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፤ እነሱንም የወለዱ እናትና አባቶች ሊኮሩ እንጂ ሊያዝኑ አይገባም፡፡

ኤዲ ያንቺ ጓደኛ ስለሆንኩ ኩራት ይሰማኛል፡፡

Filed in: Amharic