>
5:13 pm - Sunday April 19, 2274

ሥልጣን እና ልጓም...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሥልጣን እና ልጓም…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

የሥልጣን ልጓሙ ሕግ ነው። ልጓሙን የሚይዘው ደግሞ ሕዝብ ነው። ይሄ ደግሞ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑን ማሳያ ነው። የወደደውን ይሾማል፣ ያልወደደውን ይሽራል፣ ያጠፋውን በድምጽ ይቀጣል፤ ያለማውን ሕይወቱን ጭምር ሰውቶ ድጋፉን ይለግሰዋል፣ ክፉም ሲመጣ ካንተ በፊት እኔን ይለዋል።
ኢትዬጲያ ውስጥ ሥልጣን ልጓም የለውም። ይልቅስ በተገላቢጦሽ ሥልጣን ሕዝብን መለጎሚያ ነው። ሕዝብ በስልጣን እና በባለሥልጣናት ተለጉሟል። ሹማምንት ሳይሆኑ ሕዝብን የሚፈሩት፤ ሕዝብ እነሱን ይፈራል። ባለሥልጣናት ከሕግ በላይ ለመሆናቸው አንድ ሺ አንድ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። በሕዝብ ሀብት እና ንብረት ፈላጭ ቆራጮቹ፣ አዛዦቹ፣ ለጋሾቹ፣ ነፋጊዎቹ፣ ነጣቂዎቹ ከቀበሌ እስከ ጠቅላዩ ያሉ ሹማምንትች ናቸው። ለወደዱት በሕዝብ ሀብት ለጋስነታቸውን ያሳያሉ። ያልተመቻቸውን የራሱን ሀብት ነጥቀው ደም እንባ ያስለቅሳሉ፣ ፍትህ ያጓድላሉ።
የሥልጣኑ ባለቤት ያልሆነ ሕዝብ ያገሩ ባዳ ነው። የሀገሩ ባለቤትም አይሆንም። በሀገሩ አይደለም በገዛ ንብረቱና ቤተሰቡ እንኳን በነጻነት እና በሙሉ ልብ ማዘዝ አይችልም። ሥልጣኑን የያዙ ሰዎች ልጓሙንም በጨመደዱበት አገር ተጠያቂ የሚሆን እና በመንግሥት ለሚፈጸሙ ጥፋቶች ጏላፊነት የሚወስድ ሹም ማግኘት መከራ ነው።
ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሆነባትን ኢትዬጲያን ለማየት ከሁሉም ብዙ ይጠበቃል። ለጊዜው እሩቅ ነች።
Filed in: Amharic