>

የሄርማን ኮህን የሰሞኑ የትዊተር መንጨርጨሮች - እና የሽንፈት ጥንቆላዎቹ! (አሰፋ ሀይሉ)

የሄርማን ኮህን የሰሞኑ የትዊተር መንጨርጨሮች – እና የሽንፈት ጥንቆላዎቹ!

አሰፋ ሀይሉ

የአሜሪካ ወኪል ሆኖ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ያገነጣጠለው የሲአይኤው የህይወት ዘመን ሠላይ፣ እና ባለፈው ‹‹ጄ/ል አሳምነው ፅጌ መፈንቅለ መንግሥት አደረገ›› ብለው እነ አብይ አህመድ መግለጫ በሰጡ ወቅት በማያገባውና በማያውቀው ጉዳይ ገብቶ ‹‹አማራ የሌሎች ብሔሮች የበላይ ለመሆን ነው እየተንደፋደፈ ያለው፣ ለዘለዓለሙ አይሳካለትም!›› የሚል አስተያየቱን በትዊተር ገፁ የለጠፈው ነውረኛ፣ እና አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን እንዲወጣ ለወቅቱ ወያኔ-ኢህአዴግ በትዊተር ትዕዛዝ (ምሪት) አስተላልፎ የነበረው ሄርማን ኮህን፣ አሁን ደግሞ በድጋሚ እንደ እርጎ ዝንብ ባልተጠራበት የሀገራችን ጉዳይ ጥልቅ ብሎ፣ በአብይ አህመድ ላይ የበቀል ሰይፉን በመምዘዝ፣ መርዙንና ለቅሶውን ከሟርት ጋር ቀላቅሎ ሀገር ይያዝልኝ እያለ ነው! ሄርማን ኮህን ለሶስት ተከታታይ ቀናት በትዊተር ገጹ የሚያስተላልፈው መልዕክት እየከረረ መጥቶ ወደ ጥንቆላ ተሸጋግሯል፡፡
ሄርማን ኮህን በትዊተር ሀዘን ተቀምጦ ያሰፈራቸው ሶስት መልዕክቶች ከቀን ወደ ቀን እዬዬአቸው ብሶ እንዲህ ይላል፡-
– 1)  የመጀመሪያው መልዕክቱ የአፍሪካ ሀገሮች ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን እያሰሩና ጭቆናን እያነገሱ ለወትሮም ኢንቬስተር ድርሽ የማይልባትን ምድራቸውን በኢኮኖሚ ድርቅ እያሽመደመዱ እንደሆነ ጻፈ፣
– 2)  ሁለተኛ ቀን ላይ ደግሞ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው አብይ አህመድ ከሀገሪቱ ብሔሮች ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር ሁሉም የሀገሪቱ ጎሳዎችና ብሔሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበትን የመጨረሻውን ከፍተኛ መብት የሚያቀዳጅ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚያነግሥ አዲስ ህገመንግሥት በመጻፍ ፈንታ፣ በትግራይ ላይ ጦርነት ለማካሄድ መነሳቱ እጅግ ጤናውን አንዳናጠበው ጻፈ፣
– 3)  በሶስተኛው ትዊተር መልዕክቱ ደሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የውጊያ ልምድ የሌለውን ሠራዊቱን ይዞ በውጊያ – ሌላ ቀርቶ የኤርትራንም ድጋፍ ራሱ ተጨምሮለት – ያካበተ ልምድ ያለውንና በውጊያ የደነደነውን የትግራይ ወታደራዊ ኃይል አሸንፋለሁ ብሎ ካመነ – ራሱን እያጃጃለ ነው ማለት ነው፣ ኢትዮጵያን ከመበታተን አድኖ አንድ አድርጎ ለማቆየት፣ ሥልጣን ከማዕከላዊው መንግሥት እጅ ወጥቶ ወደ ሁሉም መበተን አለበት፣ ያም የሚሆነው በፍጥነት ወደማያወላውል ውይይት በመግባት ነው – ሲል ጽሑፉን አስፍሯል – ሄርማን ኮኸን!
(ይሄኛውን የኖቬምበር 5 ትዊቱን ሳነብ፡- ‹‹አይ ሄርማን ኮህን? እኛ የማናውቀው፣ አንተ የምታውቀው፣ ከእኛና ከሻዕቢያ የተለየ የተሰማሩበት ውጊያ ነበር እንዴ ወያኔዎቹ? ወይስ በንዴት ጭራ ማብቀልና መጃጀት ያስቀባጥራል እንዲህ?›› ልለው ነሸጠኝ የገነፈለው የእርሱ ንዴት – እኔንም በንዴት አልብሶኝ! ወጊድ ሠይጣን!)
– 4)  ዛሬ በአራተኛው ቀን ምን ብሎ ስለኛ እንደፈተፈተ ግን ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም! ሣልስቱን ጨርሶ ድንኳኑን ነቃቅሎ ከለቅሶው ተነሳ መሰለኝ!
ጉዳዩን በሌላ ጊዜ የምመለስበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኔን ግን ይህ ነገር ሁልጊዜ የሚያሳዝነኝም የሚገርመኝም ነገር ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ሰዎች (ሀገሮች) – በተለይም አሜሪካ – በእኛ ሀገር አንድነት ላይ ሲመጣ – እኛ ላይ እንደ ነቀርሳ ተጣብቀው ህዝባችንን እያደሙና እርስ በእርሱ እየከፋፈሉ ዘላለም ተበታትነንላቸው እንድንቀር እንዲመኙ የሚገፋፋቸው ምን ዓይነት ሰይጣን እንደሆነ ብቻ አልገለጥልህ ይለኛል! ምን ዓይነት ክፋትና ምቀኝነት የተጸናወታቸው ሰዎች ናቸው? ለሀገራቸው ‹‹አንዲት የተባበረች አሜሪካ ብቻ ነው ያለችንም የምትኖረንም›› እያሉ ትውልዳቸውን እየሰበኩ፣ እኛን በብሔርና በዘረኝነት በታትነው ህልውናችንን የማክሰሚያ መንገድ ይጭኑብናል!
እንዴ!? ከኛም ባሱኮ አሁንስ! ወያኔም እንኳ የነሱን (በተለይ የዚህን ሄርማን ኮህን የተባለ ሃጠራው) ያህል ኢትዮጵያን በብሔር ከፋፍሎ ለመበታተን ያለመ አይመስለኝም! አንዴ ከ97 ምርጫ ማግስት የህወሀቱ ስዩም መስፍን በውጭ ጉዳይ መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችንና ከፍተኛ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ‹‹ስለተደቀኑብን የሥርዓቱ አደጋዎች›› ወዘተ እያለ ሰዉን ያስቀባጥራል፡፡ በመሐል አንዱ እጁን አውጥቶ ‹‹ቆይ ለምን ይሄን ብሔር ብሔረሰብ ምናምን የሚባለውን ነገር አንተወውም? ቢቀርብንስ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ግማሹ ሳቀ፡፡ ግማሹ ለእሱ ተሳቀቀ፡፡ ስዩም መስፍን ግን በሰከነና ዘና ባለ ፊት የመለሰለት መልስ፡-
‹‹እንዴ? ምነካህ ወንድም? ዋና መጫወቻ ካርዳችንን ልታሳጣን?
ብሔር-ብሔረሰብንኮ የተገበርነው እንደ አይዲዮሎጂ አምነንበት
ሳይሆን ዋናው የመጫወቻ ካርዳችን እሱ ስለሆነ ብቻ ነው!
ከጥቅሙ አንጻር ነው የገባንበት!››
የሚል ነበር፡፡ ሄርማን ኮህን ያንን የስዩም መስፍን ቃለህይወት ቢሰማ በንዴት ታንቆ ይሞት ነበር፡፡ ብዬ ነው የማስበው አሁን ሰውየውን እንዴት እንዴት እያደረገው እንደሆነ አኳኋኑን ሳየው! ሆሆ!! ይሄ ዘረኛ ነጫጭባ! ቆሽቱ አረረ! የታባቱ!
ሳስበው – ይመስለኛል – ሄርማን ኮህን – ያኔ አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አርጉት ሲል – እና እንዳለው አብይ ወደ ሥልጣን ሲመጣለት – አብይ ሥልጣን ላይ እንደወጣ – ሄርማን ኮህን በኤርትራ ሪፈረንደም ዘመን እንደለመደው –  የኦሮሚያን ሪፈረንደም ደሞ ያካሂድልኛል – ብሎ ተስፋ ጥሎበት ነበር መሰለኝ! የማነው ጅል ባካችሁ?! ድንጋይ ራስ!
የእርሱን ሸር እኮ ኢሳያስ አፈወርቂ ራሱ ባንኖበት – ባለፈው በኃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ – ‹‹ኤርትራንና ኢትዮጵያን የምታጣላው አሜሪካ ነች!›› የሚል መልዕክት ለዓለም ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች በሙሉ አሰራጭቶ ነበረ! በዚህ ድፍረቱ የተናደዱት አሜሪካኖች ለኢሳያስ ‹‹የአፍሪካው ኪም ጆንግ ኡን›› የሚል ቅጽል ሰጥተው የመጽሔት የፊት ገጽ ላይ እንዳወጡት ትዝ ይለኛል፡፡ የምመኘው – ሄርማን ኮህን ሳይሞት ዓይኑ እያየ – አንድ ቀን – እኛና ኤርትራ – ድሮ የተባበሩት መንግሥታት እንደወሰነልን – በፌዴሬሽን ተዋህደን – የምንገኝበትን ያን ቀን ነው! ያን ቀን – ሄርማን ኮህን በንዴት ሀሞቱን ተፍቶ ይሞታል!
(በነገራችን ላይ የሰውየው ዘረኝነትን የማስቀጠል ሴራ ነው እንጂ ያንገበገበኝ – ለምን አብይን አወገዘ፣ ወይ ለምን ጦርነቱን አወገዘ፣ ወይ ለምን ውይይት እንዲደረግ አሳሰበ… ብዬ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ! ለነገሩ ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና ማን አየ?! አሁን ማለት የምንችለው ፈጣሪ ከጠላቶቻችን ምኞት ይሰውረን ማለት ብቻ ነው! እና ለሰይጣን ጆሮ እንዲደፈን መመኘት ብቻ! እና ከቻልን ይዞ መደቆስ! (ሀሀሀ..!! አርጎት ነው?!)
ለማንኛውም ቆይ ስለ ሰውየው (ሄርማን ኮህን) ጉድ በሌላ ቀን ጊዜ ሲተርፈኝ እመለስበታለሁ! እሱ ስለ አፍሪካ ባሳተመው መጽሐፉ – ስንትና ስንት ዓመት የዘለቀውን የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ሁለቱን ወገኖች አስማምቼ ያስቆምኩት እኔ ነኝ!›› እያለ ነው ጉራውን የሚነፋው! ለሠራው እግዜር ይድፋው! ሌላን ሰው ብዬ አላውቅም! ለእሱ ግን እላለሁ! ክፉ ሰው ክፉ ያደርግሃል! ሌላውን ያሳሳተ ኃጢአቱ አይሰረይለትም! ዞሮ ዞሮ ጦሱ የራሱ ነው! ‹‹በስንቱ ተጠበስኩ – አለች ብረትምጣድ››! ላሁኑ አበቃሁ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ከጉልበታም የሩቅ ጠላቶቻችን የክፋት ሰይፍ ይሰውረን!
Filed in: Amharic