>

ለፖለቲካ ለውጥ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል - ሁለቱም በእጃችን ላይ ናቸው!  (አሰፋ ሀይሉ)

ለፖለቲካ ለውጥ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል – ሁለቱም በእጃችን ላይ ናቸው! 

አሰፋ ሀይሉ
(ጥቂት ማኬያቬሌያዊ ስልቶች ለፈጣን ለውጥ!) 

የህዝብን ኃይል በለውጥ አጀንዳዎች ዙሪያ ማደርጀት፡፡ እና ተገቢዋን የጫና ሰዓት ማወቅ፡፡ እነዚህ ሁለቱን የተካናቸው የፖለቲካ ኃይል የጠየቀውን አያጣም! ያለመውን አይስትም፡፡ ብዙዎች ለውጥን ለማምጣት ፅኑ ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን እንዴት ለለውጥ የሚሆን ኃይልን ማሰባሰብ እንደሚችሉ ግንዛቤው የላቸውም፡፡ እና ያን የለውጥ ኃይል መቼ ቢጠቀሙ እንደሆነ ውጤታማ ሊሆንላቸው እንደሚችል – ትክክለኛዋን ውጤታማ ቅጽበት የማወቅ – በቂ ግንዛቤው የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙዎች አጥብቀው የሚሹትን የፖለቲካ ለውጥ ሳያዩት ይቀራሉ፡፡
ብዙ ለውጥን ሊፈጥሩ የሚችሉ የነበሩ ብዙ ያገራችን የፖለቲካ ኃይሎች – ከፊትለፊታቸው የሕዝብን ጥያቄ አንግበው፣ ከጀርባቸው የህዝብን የድጋፍ ኃይል ይዘው፣ በገዢዎች ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር፣ አምባገነኖችን ሥጋት ውስጥ በሚጥል አኳኋን ከፍተኛ ግፊት ሊያደርጉ፣ እና መብት ነጣቂውን አጣብቂኝ ውስጥ ከትተው የመደራደር አቅም ብልጫውን ሊያገኙ ሲችሉ – ያን ማድረግ የሚችሉበትን ትክክለኛ ወቅት – ከገዢው ኃይል ጋር አጉል በመጓደድ – በከንቱ ሽንገላ በመዘናጋት – ገዢው የሚያድርበት ፍርሃት እነሱንም እንደ ተስቦ ተጋብቶባቸው በፍርሃት ተሸብበው – ያን ወርቃማ ዕድል ያባክኑታል፡፡ መብታቸውን በህዝብ ጫና ገፍተው ማስከበር ሲችሉ – ዘወትር ዘወትር መብትን በልመና ለማግኘት መከራቸውን ሲበሉ ይኖራሉ፡፡
የፖለቲካ ኃይል ማለት ጠብመንጃ ሳይተኩስ ገዢውን አካል በህዝብ ጩኸት ተጠቅሞ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት፣ እና የመደራደሪያ አቅም የሚያገኝ ንቁ የሠላማዊ ዜጎች ስብስብ ነው፡፡ የፖለቲካ ኃይል ብቸኛ መሳሪያው ‹‹ፕሬዠር›› ነው፡፡ ‹‹ፕሬዠር›› ወይም ‹‹ከባድ ተፅዕኖ›› በመፍጠር ኃይሉ ነው የፖለቲካ ኃይል መኖሩ የሚለካው፡፡ በተለይ ለተቃውሞ ፖለቲካው ጎራ – በገዢው ላይ የሚፈጥረው ፕሬዠር – ብቸኛው የህልውና ምንጩ ነው፡፡ ብቸኛው መብትን ማስከበሪያ መንገዱ ነው፡፡ ብቸኛው የመደራደሪያ አቅሙ ነው፡፡
ሥልጣን ላይ ያለው አካል – ለፖለቲካ ጥያቄው የይሁንታ መልስ ካልሰጠው የሚጠብቀውን ከፍተኛ ህዝባዊ ሰልፍ፣ ከፍተኛ የዜጎች ተቃውሞ፣ ከበድ ያለ አሉታዊ ውጤትን የሚያስከትል የመንግሥት ሥርዓት መናወጥ፣ የሥልጣኑ መቀመጫ መነቃነቅን፣ የሥርዓቱን ከመሠረቱ መናጋትን፣ አሊያም ከፍ ያለ ፋታ የማይሰጥ የህዝብ ጩኸትን ለማስተናገድ እንደሚገደድ፣ አሊያም ያንን ጩኸት አፍናለሁ ብሎ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ከፍ ያለ ህዝብን ለስቃይና ለእንግልት፣ ብሎም ለአካል ጉዳትና ለህልፈት ሊዳርግ በሚቃጣበት ወቅት ከባድ ጦስ ሊከተለው እንደሚችል ከወዲሁ ቀልቡን ገዝቶ እንዲገምት እና እንዲያውቅ – በሚገባው መልክ እና በተገቢው ሰዓት ማሳየት ያልቻለ የተቃውሞ ፖለቲካ ኃይል – ራሱን ተቃዋሚ ብሎ መጥራት የለበትም፡፡ ራሱን የዜጎች መብት አስከባሪ ብሎ መጥራት አይችልም፡፡ እስከጭራሹ ራሱን ‹‹የፖለቲካ ኃይል›› ብሎ ለመጥራትም ያልተገባ ፍዝ ስብስብ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበትና ትንሽ ኮሽታ እንኳ በሚያሰጋው ደረጃ ላይ በሚገኝበት ሰዓት የፖለቲካ ጫናን ለማሳደር ሕዝባዊ ተቃውሞን ማስነሳት፣ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ‹‹በተግባር ሊተገበሩ የሚችሉ ትክክለኛ ጥያቄዎችን አቅርቦ በተገቢው ሁኔታ መብቱ ሊከበርለት ካልቻለ›› የገዢውን ሥልጣን በህዝብ ቁጣ ማናጋት ያልቻለ የፖለቲካ ኃይል – ከቶውንም የተቃውሞ ፖለቲካ ኃይል ሊባል አይችልም! የገዢው ፓርቲ ተስፈኛና ተቀጥላ ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው! ይህ የፕሬዠር አቅምን የመፍጠርና፣ መቼ ላይ ይህን ፕሬዠር ኢፌክቲቭ ለውጥ ወይም ተሰሚነት እንዲያመጣለት አድርጎ መጠቀም እንዳለበት ያላወቀ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የስሜት እንጂ የስሌት ጸጋን ያልታደለ – ሩቅ የማይደርስ የስም ብቻ ፓርቲ ነው፡፡
በኛ ሀገር የሚታየው የተቃውሞ ፖለቲካው ዋና ችግርም ይሄው በስም ብቻ የመኖር እውነታ ነው፡፡ የኛ ሀገር የህዝብ እንባ ጠባቂ ነን የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች – ታላቅ ህዝባዊ ፖለቲካዊ ‹‹ሞመንተም›› መፍጠር በሚችሉበት፣ ወይም ተፈጥሮላቸው በተገኘበት፣ እና ገዢውን ኃይል በከፍተኛ የህዝብ ጫና አማራጭ አሳጥተው ብዙ ርቀት ሄደው ብዙ በሌላ ጊዜ ሊያሳኳቸው የማይችሏቸውን ‹‹ኮንሴሽኖችን›› መውሰድ በሚችሉበት ትክክለኛ ሰዓት ላይ – የገዢው አካል፣ ወይም የገዢው ፓርቲ፣ አሊያም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ‹‹አዛኝ ቅቤ አንጓች›› እና ፍፁም ዓይናፋር ሆነው ይገኛሉ፡፡ ግዴታቸውን ተወጥተው ትክክለኛ ውጤት በሚያገኙባት ሰዓት ላይ ሁለመናቸው ይዋልላል፡፡ እና ከደፈጣ እና ፈቀቅ ሳይሉ ዕድሜ እየቆጠሩ ከመቀመጥ፣ እና ከልመናና ከለቅሶ በቀር ሌላ ይህ ነው የሚሉትን ታሪክ ሳይሰሩ ገዢውን እያኗኗሩ ታሪካቸው ይደመደማል፡፡
ይህ ወቅቶች የሚፈጥሩትን የመደራደር አቅማቸውን በትክክለኛው ሰዓት ያለመጠቀም ህጸጽ ነው የኛን ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሽመድምዶ ያስቀራቸው፡፡ ይህን ትክክለኛውን ሞመንተም ሰብስበው ትክክለኛዋን ፕሬዠር የመፍጠሪያ ቅጽበት የተጠቀሙባት ፓርቲዎች ናቸው በኢትዮጵያ የቅርብም የሩቅም የፖለቲካ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበው – ታሪክ ሰርተው የምናገኛቸው፡፡ እና አሁን ይህን ሁሉ የምለው ለምንድነው?
አሁን ይህን ሁሉ የምለፈልፈው እስክንድር ነጋንና ሌሎችን ለእውነት በመቆማቸው ብቻ በገዢው አካል በእስር እየተሰቃዩ ያሉ የህሊና እስረኞችን በህዝባዊ ተቃውሞ ጫና ፈጥሮ ከእስር ለማስፈታት ትክክለኛ ጊዜው በልበ ሙሉነት አሁን መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ እርግጥ ነው፡፡ በአሁኗ ቅፅበት አሳሪው የአብይ መንግሥት በጦርነት እሳት ላይ ተጥዷል፡፡ ሆኖም ገዢው ብቻውን ዓየር ላይ የሚቆም አካል አይደለምና – ያው ብዙ ሺህ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግሥት ጎን በጦርነት እሳት ውስጥ ገብቶ ከተጠላችው ወያኔ (እና ከጎኗ ካሰለፈቻቸው ኢትዮጵያውያን ጋር) አንገት ለአንገት እየተናነቀ ነው፡፡ በትግራይ፣ በወለጋ፣ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅ፣ በምዕራብ -በሁሉም አቅጣጫ ብዙ የህልውና ስጋቶች የተጋረጡበትና – በብዙ ጫናዎችና ውጥረቶች ውስጥ የገባ መንግሥት ነው ያለው፡፡
ታዲያ በዚህ ቀውጢ ነፍስ-ግቢ ነፍስ-ውጪ ሰዓት ላይ – ብዙ ዓለማቀፍ ተቋማትንና ቆንሲሎችን በያዘችው የኃይልና የሥልጣኑ እምብርት – በአዲስ አበባ ላይ አንዲትም ኮሽታ እንድትሰማበት የማይፈልግባት የመጨረሻው ከባዱ የምጡ ሰዓት ይህች የአሁኗ ሰዓት ናት፡፡ ትንሽ የሕዝብ ጩኸት በመንግሥት ላይ ከፍተኛ አቶሚክ ንዝረት የምታደርስበት ሰዓት ብትኖር ይህች ቀውጢ ሰዓት ነች፡፡ ይህ ማለት በተቃውሞው ፖለቲካ ጎራ ላሉት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት – የእስክንድር ነጋን እና የሌሎችን ለህዝብ በመቆማቸው ብቻ በየከርቸሌው የታጎሩ – በእስር የመማቀቅ መከራ እንዲያበቃላቸው የመጠየቂያዋ ትክክለኛዋ ቅጽበት – አሁን ነች ማለት ነው፡፡
አሁን ላይ አብይ አህመድ በሥልጣኑ ተጠቅሞ ያለኃጢያቱ ያሰረውን እስክንድር ነጋን በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ አሊያ ግን በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሠላማዊ የተቃውሞ ጥሪዎችን በማቅረብ መሪውን ለማስፈታት ከፍተኛ ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ባልደራሱ እና ከባልደራሱ ጋር በአጋርነት የሚቆሙ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአብይ አህመድ ቁርጥ አድርገው መግለጽ አለባቸው፡፡
በዚህ ሂደት የሚመጣ በትር ካለ የሥርዓቱን ማንነት ለህዝብና ለዓለም ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ይሆናልና የተቃውሞ ፖለቲካው ራሱን እንደ ሻማ አብርቶ እውነቱን ለህዝብ አሳይቶ ለመቅለጥ ይቻለዋል ማለት ነው፡፡ ይህም በራሱ ታላቅ ስኬት ነው፡፡ 99 ፐርሰንት ሊሆን የሚችለው ግን – አሳሪው ኃይል – ማለትም ገዢው መንግሥት – ብዙ ጣጣና የህዝብ ተቃውሞ እንደ ዓይኑ ብሌን እየጠበቃት ባለችው በአዲስ አበባ ላይ ሳይከሰትበት በፊት- እስክንድር ነጋን ይፈታዋል፡፡ ምናልባት ግፋ ቢል – በለመደው ጮሌነት – በእስክንድር ነጋ ሰበብ – ከእነ እስክንድር መፈታት ጋርም – እነ ጃዋርንና በቀለ ገርባን የመሳሰሉትን የራሱን ኦሮሙማዎችም ለመፍታት አጋጣሚውን ቢጠቀምበት ነው፡፡ ህዝባዊ ጩኸት አዲስ አበባ ውስጥ ከተቀሰቀሰ የሚሆነው ይህ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ የግድ ጠንቋይ መሆን፣ አሊያም አንስታይንን መሆን አይጠይቅም፡፡ ግፋ ቢል ጥቂት ማኪያቬሌነትን ቢጠይቅ ነው፡፡
ጊዜው አሳሳቢ በመሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ ግርግር እንዲነሳበት ያልፈለገ አካል – ግርግር ከመነሳቱ በፊት አላግባብ በግፍ ያሰራቸውን ንጹሃን መፍታት አለበት፡፡ አሊያ ግን የሚመጣበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ፈልጎታል፣ ይሁን ብሎ ውጤቱን ተቀብሎታል ማለት ነው፡፡ እና እንደተመኛት ያወራርዳታል ማለት ነው፡፡ መብትን መጠየቅ በትክክለኛ ሰዓቷ ነው ስልም ይህን ማለቴ ነው፡፡ መብትህን የምትጠይቅባት ትክክለኛዋ ሰዓት ተቃውሞህ ገዢውን አጣብቂኝ ውስጥ ከትታ ሌላ መውጫ አማራጭ የምታሳጣባት፣ እና ከፍ ያለ የመደራደር አቅም የተላበስክባት ቅጽበት ነች፡፡ ያቺ ቅጽበት ከጨለሙ የአምባገነን ግድግዳዎች ጀርባ ቀናቸውን እየቆጠሩ የሕዝባቸውን ጩኸት በተስፋ ለሚጠባበቁት ለእነ እስክንድር አሁን ነች፡፡
የባልደራሱ ምክር ቤት፣ ሌሎችም የእስክንድር ነጋንና የሌሎችን የተቃውሞ ፖለቲከኞች አላግባብ መታሰር የምትቃወሙ የፖለቲካ ኃይሎች ተቃውሞአችሁን የምታሰሙባት ትክክለኛዋ ቅፅበት አሁን መሆኗን በሚገባ አስታውሱ፡፡ አሁን፣ አሁኑኑ፣ ለእስክንድር ቁሙ፡፡ አሁኑኑ ለእስክንድር ጩኹ፡፡ አሁን ለመጮህ ካፈገፈጋችሁ፣ አሁን ጩኸታችሁን ለማሰማት ሰበብ ከደረደራችሁ፣ ሁልጊዜ መብታችሁን ስትለምኗት ትኖራላችሁ፡፡ መብትን መለመን ወይም ማስከበር ምርጫው የፖለቲካው ኃይሎች ነው፡፡ ወይ በመንግሥት ላይ በትክክለኛዋ ቅፅበት ጫና አሳድሮ፣ መብታትን ማስከበር! አሊያ ግን ከገዢው ጋር አብሮ ሐዘን መቀመጥና – ሳልስቱ፣ አርባው፣ ሰማንያው ተዝካሩ እስኪወጣለት – ማስተዛዘን፡፡
ይህን በምናገርበት ሰዓት የብዙ የስድብ ሰራዊቶችን ድልብና ግልብ ቃላት እጠብቃለሁ፡፡ ስድብ የአላዋቂዎች ምርቃት ሆኗል፡፡ አዕምሮ ድፍንነት ያደባባይ ጀግንነት ሆኗል፡፡ ለገዢው ሥርዓት በአድርባይነት ጋሻጃግሬ ሆኖ መቆም – የጥበብ ሁሉ ከፍታ ሆኗል፡፡ መብትን አለመጠየቅ የዜግነት ትልቁ ስነምግባር መለኪያ ሆኗል፡፡ እና መቼም ሁለት ገጽ ሙሉ ጽሁፍ ችሎ አያነብምና፣ በስሜቱ በገባው ልክ. ለምን ተሳደበ ብዬ ሰውን አልኮንንም፡፡ ሰው ያለውን እና የሚችለውን ነው የሚሰጠው፡፡
ከአላዋቂ ሳሚው የስድብ ሰራዊት በላይ የሚገርሙኝ – በተሰለበ መንፈሳቸው ንጹሃንን በእስር እያማቀቀ ከሚገኘው ከገዢው መንግሥት ጋር በተሰለበ መንፈሳቸው ቁጭ ብለው – ማንኛውንም የተቃውሞ ሀሳብ የማጣጣያና የመፈረጃ ቅጽል ስም እያወጡ የሚውሉና የሚያድሩት አስተዛዛኞችና ኮናኞች ናቸው፡፡ ‹‹አንተ የወያኔ አሽከር!›› ‹‹አንተ የነፍጠኛ ልሳን!››፣ ‹‹አንተ የዘራፊ ጠበቃ!››፣ ‹‹አንተ የገዳዮች ተከላካይ!››፣ ‹‹አንተ የምናምን ምናምን…!›› በቃ ተቆጥረው የማያልቁ – በገዢው መንግሥት ላይ የተነሳችን እያንዳንዷን ተቃውሞ በሌላ ባልተነሳ አካልና ነገር እያስጠጉ – ተቃውሞ ማስተባበያ ቅጽሎች! ተቃውሞን መኮነኛ ቅጽሎች! በዝተዋል፡፡
እነዚህን አስተዛዛኞችና ኮናኞች እየሰማ – አንዲት ጋት ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ ኃይል ካለ – የለም እንጂ  – ከምላሴ ጸጉር.. – እላለሁ! ስለዚህ ለእነዚህ የስድብ፣ የእዝን፣ እና የኩነኔ ሠራዊቶች ለሚሰነዘሩ ‹‹አጉል›› ትርፍ ቃላት – ጆሮ-ዳባ ልበስ – ብሎ ከማለፍ ሌላ ምን የተሻለ ጥሩ መልስ እንደሚገኝ አልደረስኩበትምና – መልሴ – ዝምታ ነው! ጆሮ ዳባ ልበስ ብቻ!
በወታደራዊው አስተዳደር ደርግ ዘመን በሥርዓቱ ላይ ተቃውሞ ያነሱ የማይወጣላቸው ቅጽል አልነበረም፡፡ በዚያ ዘመን ነው ‹‹ተላላኪ›› የምትለዋ ወሳኝ የሀገራችን ገዢዎች ቃል የተፈጠረችላቸው፡፡ ደርግ ‹‹የኢምፔሪያሊስቶች ተላላኪ››፣ ‹‹የበዝባዦች ተላላኪ›› ‹‹የአድሃሪዎች ተላላኪ››፣ ‹‹የአረብ ተላላኪ››፣ ወዘተ እያለ ‹‹ተላላኪ›› የምትለዋን ቃል አባክኗት አለፈ፡፡ ወያኔ ደሞ ያንኑ ወርሳ ‹‹ተላላኪ›› የሚለውን ቃል ወደተለየ ታላቅ ከፍታ አደረሰችው፡፡ ‹‹የሻዕቢያ ተላላኪ!››፣ ‹‹የኦነግ ተላላኪ!››፣ ‹‹የውጪ ኃይሎች ተላላኪ›› ሌላ ቀርቶ ራሷን እንደ ጩሎ ሲልኳት የነበሩትን ግብፆች ረስታ ‹‹የግብጽ ተላላኪ›› ብላም ነበር ወያኔ፡፡ የሚልክ አካል ሲጠፋ መጨረሻ ላይ ‹‹የጥፋት ተላላኪዎች›› የሚልም መጥቶ ነበር፡፡ ወቸ ጉድ!!
አሁን ደሞ የአብይ አህመድም ሥርዓት ለላኪ-ተላላኪነት አቅመ ቃል በቅቶ – በአሁኑ ሰዓት ለመብቱ የተነሳ – ወይም በሥርዓቱ ላይ ተቃውሞ ያነሳ ሁሉ የሚሰጠው ቅጽል ከሁለት ‹‹ተላላኪነቶች›› አንዷን ነው፡- ወይ ‹‹የወያኔ ተላላኪ!›› ነው! አሊያ ደሞ ‹‹የሸኔ ተላላኪ!›› ነው! (ሀሀሀሀ…!!) ይቺኛዋን ግን ጥቅም ላይ ውላ አላየኋትም!! ግን መዋሏ አይቀርም! ታዲያ የጦርነት ልዩ ጥቅሙ ምንድነው? የሚቃወምህን ሁሉ – በጠላትህ ስም እየፈረጅክ ታዳፍንበታለህ!!
አዳፍኔውም አለ፡፡ ቅጽሉም አለ፡፡ ስድቡም ማንጓጠጡም አለ፡፡ እዝኑም ኩነኔውም፡፡ የፈሪውም መዓት ሺህ ሰበብ፡፡ ሁሉም አለ፡፡ ሁሉም የፈለገውን ይበል፡፡ የፈለገውን ነገር ተባሉና – ለቆማችሁለት ህዝብ ግን የተጨበጠ፣ የሚጨበጥ፣ ይህ ነው – ይህንን እኮ አድርገዋል – አስደርገዋል – የሚባልለት – አንድ ተጨባጭ ለውጥን አምጡ! ትክክለኛውን ጥያቄ አንስታችሁ፣ በትክክለኛዋ ሰዓት ከህዝብ ፊት ቁሙ! እና መብታችሁን በሠላማዊ ህዝባዊ ትግል አስከብሩ! አሊያ ግን ያላችሁ አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ከገዢው ጋር አብራችሁ ቅጽል እያወጣችሁ ለውጣችሁን ለምኑ! መብታችሁን በለቅሶ አስተዛዝናችሁ ጠይቁ! የሚቀራችሁ አማራጭ ይህ እና ይህ ብቻ ነው! ትክክለኛ ጊዜውን የተጠቀመባት ያሸንፋል! በጊዜዋ ያልተጠቀመባትን፣ ጊዜ ትቀልድበታለች!
ቸር ሁኑ!  
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic