>

መተከል እና የጎጃም ዐማራ ሰሚ ያጡ ጩህቶች !  (ዘመድኩን በቀለ)

መተከል እና የጎጃም ዐማራ ሰሚ ያጡ ጩህቶች ! 

ዘመድኩን በቀለ

አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቶህ፣ 
ለብልቦ ለብልቦ አቃጥሎ ፈጀህ። አለ የሃገሬ ሰው።
•••
ኧረ ዘመዴ በመተከል በኩል እኮ አለቅነ፣ ህዝባችን አለቀ ይለኛል። እኔም ማን ነው የሚጨርሳችሁ እለዋለሁ። እርሱም መልሶ አይታወቁም። የመከላከያውን ሬንጀር ነው የለበሱት። ህዝቡን እየጨፈጨፉት ነው።  አሁን ደግሞ ከመከላከያው ጋር ገጥመዋል ይለኛል። እኔም መልሼ እጠይቀዋለሁ። ፋኖስ ምን አለ? የጎጃም ፋኖ፣ የዐማራ ልዩ ኃይል፣ የዐማራ ሚኒሻስ ምን ይጠብቃል? ወገኖቹን ከጥቃት መከላከል እኮ ሕጋዊ መብቱ ነው እለዋለሁ። እሱም መለሰልኝ፥ ግራ የገባን እሱ አይደል። መከላከያ ከለከለው። እንዳትዋጉ እረፉ አላቸው ይለኛል። ያነዜ የሆነ ነገር ሸከከኝ። መከላከያ ውስጥ የሆነ የሚሰነፍጥ ሴራም ያለ መሰለኝ። እናም ለደዋዬ እንዲህ አልኩት። ይኸውልህ ጎዶኛዬ፦
በጎንደር በኩል፦
… ህወሓት ትንኮሳ ስትጀምር፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ቀለበት ውስጥ ከትታ ልተደመስሰው ጦርነት ስትከፍትበት፣ ሮጦ ከተፍ ብሎ ደርሶ አፈር ከደቼ አብልቷት ያባረራት፣ ደምስሷትም መከላከያ ሠራዊቱን ከከበባና ከመደምሰስ ነጻ ያወጣው የዚያ የበጋው መብረቅ የትንቢት ተናጋሪው “ ዐማራ ተከበሃል” ያለው የአሳምነው ጽጌ የዐማራ ልዩ ኃይልና የጎንደር፣ የበለሳና የአርማጨሆ የዐማራ ፋኖ ነው። ጎንደር ነፃ የወጣችው፣ ወልቃይትና ጠገዴ ሁመራም ነፃ ወጥተው ወደ በጌምድር ወደ ጥንት ግዛታቸው የተመለሱት በዐማራ ፋኖና በዐማራ ልዩ ኃይል ጀግንነትና ተጋድሎ ነው። አንድ በል።
በወሎ በኩል፦
… በወሎ በራያ በኩል የሰፈረውን የህወሓት ጦርም እንዲሁ በላሊበላና በሰቆጣ በኩል አድርጎ ከታች ከአፋር ከተነሣው የአፋር ልዩ ኃይልና ከመከላከያ ሰራዊቱ ኃይል ጋር ተናብቦ መከላከያውን አጅቦ አላማጣን አልፎ በቆረጣ ኮረም የገባውና አሁን ራያ አላማጣ እና ኮረም ነፃ የወጡት በዐማራ ልዩ ኃይልና በፋኖ ድንቅ የተጋድሎ ውጤት ነው። ሁለት አልክልኝ።
በሸዋ በኩል፥
… የሸዋው ፋኖም ቢሆን በተጠንቀቅ ቆሞ በማንኛውም ጊዜ ከሕገወጡና ከሕጋዊው ኦነግ የሚመጣ ትንኮሳ ካለ በማለት በዓይነ ቀራኛ ዙሪያ ገባውን እየጠበቀ ነው። ሦስት አላችሁልኝ።
በጎጃም በኩል ግን፦
… እኔን አልገባህ ያለኝና እኔን እየገረመኝ ደግሞም እየደነቀኝ ያለ ጉዳይ ነው። በዚያ የጎጃም ዐማራ በበላይ ዘለቀ ልጆች መንደር ግን የሆነ ያለተገለጸ ነገር ይታየኛል። አልበራልኝም ማለት ይሆናል። በድባጤ፣ በመተከል የጎጃም አገው ዐማራ በሃለላል እየተጨፈጨፈ እንደሆነ እየተነገረ ነው። መከላከያ ሰራዊቱም ከቀስተኞቹና እስከ አፍንጫቸው ድረስ ከታጠቁት የኦነግ ሸኔ የህወሓት ቅልብ የጫካ ሠራዊት ጋር እየተተጋተገ መሆኑም እየተነገረ ነው። በዚህ ሁሉ መሃል ታዲያ የጎጃም የዐማራ ፋኖ ዝምታ አልገብቶኝም። ደግሞስ ከወዴት ነው ያለው? መንግሥትስ ከአቅሙ በላይ ከሆነ ለጎጃም ፋኖ እና ለዐማራ ልዩ ኃይል ለምን ፈቃድ አይሰጠውም። ህወሓት ላይ እኚኚ የሚለውን ያህል ኦነግ ላይ ምነው ጮጋ አለብኝሳ? ሁለት ጥይት ተኩሶ ሺ ዎችን ሱዳን ድረስ ለሚያሯሩጠው ዐማራ ለምን ወገኖቹን እንዲታደግ አይፈቅድለትም። ወይስ ይሄ ትንኮሳ ራሱ እንደሚባለው፣ እነደሚታማው ከህዳሴው ግድብ አካባቢ የዐማራውን ዘር የማጽዳት የፖሊሲው አንዱ አካል ነው? እኔ አልገብቶኝም።
… የጎጃም ዐማራውስ ቢሆን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ተብሎ የገዛ ርስቱ መተከልን ቆርሰው የወሰዱበት ሳያንስ አሁን ደግሞ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እንዲህ ቁም ስቅሉን ሲያይ ቆሞ የማየቱ ነገር ምን ይባላል? ይሄም አልገባኝም። መተከል አጎቱ እየታረደ ደብረ ማርቆስ ላይ ጤፍ ስንት ገባ? በቆሎስ? አዲስ አበባ ገበያው እንዴት ነው? የሲሚንቶና የብረት ዋጋ እንዴት ነው? ዶላር እንዴት ነው በየት ነው የማገኘው እያለ ሽቀላ ብቻ የሚያስብ ዐማራ አይቼም፣ ሰምቼም አላውቅ። ወይስ በመተከል ባለው የአገው ዐማራ የዘር ማጥፋት ተጠቃሚ የሆኑ ዐማሮች አሉ? አሁንም አልገባኝም።
… ለማንኛውም የቤንሻንጉል ክልሉ ሊቀ መንበር አፍቃሬ ህወሓት የመቀሌው አፈቀላጤ፣ የጀርባ ደጀን መሆኑን እወቁ። ሁመራ የሄደው የጎንደር ፋኖ፣ ኮረም የደረሰው የወሎ ዐማራ ፋኖ በስንት ጀግንነት ኘ እና ተጋድሎ የያዘውን ርስቱን ለቆ ደብረ ማርቆስ መጥቶ ነፃ ያወጣኛል ብለህ አትጠብቅ። አንተ የማንን ጎፈሬ ነው የምታበጥረው? ድግሞም “ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ይልም ነበር አጎቴ ሌኒን። ኢንዴዢያ ነው።
•••
… በመቀጠል “ አሐዱ ባንክን ” በተመለከተ መረጃው ወደ እናንተ ይደርሳል።
”  ጓ ”
Filed in: Amharic