>

ትህነግ በወረራ የያዘቻቸውን የአማራ ታሪካዊ ግዛቶች አጥብቃ ያሰረችባቸው "አምስት ገመዶች"  (መስከረም አበራ)

ትህነግ በወረራ የያዘቻቸውን የአማራ ታሪካዊ ግዛቶች አጥብቃ ያሰረችባቸው “አምስት ገመዶች”  

 

መስከረም አበራ


በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባን የተቆጣጠረው ህወሃት ቀጣይ ሥራ ያደረገው የትግራይን ግዛት ማስፋፋት ነበር፡፡ ይህ የረዥም አመት ፕሮጀክት የተጀመረው ከጎንደር ወልቃይትን የመሰሉ፣ ከወሎ ራያን የመሰሉ ለም መሬቶችን ልምላሜ ወደ ሚያጥራት ትግራይ ክልል በማካለል ነው፡፡ ይህ ህወሃት በአማራው ህዝብ ላይ ከሰራቸው በርካታ ግፎች ውስጥ በከፍተኛ በጥንቃቄ የተሰራው ነው፡፡
ቀን እንደዞረለት የተረዳው ህወሃት ግዛቶቹን ወደ ትግራይ የማካለሉን ስራ ሲሰራ ተገን ያደረገው መሳሪያውን ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ የኢትዮጵያ ጌታ መሆኑ የሰጠውን ቱርፋት ሁሉ ተጠቅሞ ጉዳዩን በተለያዩ ገመዶች አጥብቆ ሲያስር ኖሯል፡፡ ህወሃት ኮስተር ብሎ የያዘው ከአማራ ክልል ግዛቶችን እየወሰዱ ትግራይን ለም፣ ግዙፍ እና ሃያል ግዛት የማድረጉን ነገር አጥብቆ ከማሰሩ የተነሳ ይህን በተመለከተ ጥያቄ ሲነሳበት ፈርጠም ብሎ “ሪፈረንደም ይደረግ” እስከ ማለት አድርሶታል፡፡Tigray region after 1991
ምንጭ፦ Ethioforum.com
በአንፃሩ የመሬቱ እውነተኛ ባለቤት የአማራ ክልል እንደሆነ፣ እነሱም አማራ እንደሆኑ የሚያነሱ ወገኖች ሪፈረንደሙን አጥብቀው የሚቃወሙት ብቻ ሳይሆን በሰላም ለመኖር ያለመፈለግ ዝንባሌ አድርገውም ያዩታል፡፡ ለመሆኑ ህወሃት ሪፈረንደም እስከመጠየቅ ድረስ ያስደፈረው፣ ጉዳዩ ወደራሱ ፍላጎት እንዲያዘነብል አድርጎ አጥብቆ ያሰረበት ገመድ ምንድን ነው? ብዛቱ እና ጥብቀቱስ እንዴት ነው? የሚለውን መመርመሩ አስፈላጊ ነው፡፡
 
ገመድ አንድ- የጎሳ ፖለቲካ ተረክ:-
 
ህወሃት የተፈጠረለት አላማ ትግራይን ከአማራ አገዛዝ ነፃ ማድረግ ነበር፡፡ በተፈጥሮ ሃብት ድህነቷ ሳይቀር የመጣውን የትግራይ ጉስቁልና ምክንያቱ አማራ ነው ሲል ኖሯል-ህወሃት በማኒፌስቶው፡፡ የትግራይ ችግር ሁሉ በአማራ ምክንያት የመጣ እንደሆነ በደመ-ነፍስ ሲያስብ የኖረው ህወሃት የትግራይ ጉስቁልና የሚከላውም የአማራውን ሃብት በመዝረፍ፣ ግዛቱን በመቀማት፣ አከርካሪውን በመስበር እንደሆነ አምኖ ታጥቆ ሰርቶበታል፡፡ የዚሁን ቅጅ ለሌሎች ብሄረሰቦች ሲያዛምት፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ችግሮች ሁሉ ባለቤት አማራው እንደሆነ ሃፍረቱን ጥሎ በአደባባይ ሲሰብክ ኖሯል፡፡
ይህንኑ ዕምነቱን በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ለማስረፅ ብዙ አልተቸገረም ነበር፡፡ በዚህ ላይ በአማራው ላይ የተጋረጠውን ትልቅ አደጋ በሚመጥን ቅንብር እና ፍጥነት የአማራው ብሄርተኝነት መብቀል አለመቻሉ ህወሃትን ከልካይ አልቦ የአማራው ቀጭ አድርጎታል፡፡ አማራው መተንፈስ ያለበት ትምክህተኛ፣ መቀጣት ያለበት ወንጀለኛ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ይህ እሳቤ በሃገሪቱ አለቅጥ የገዘፈው የጎሳ ፖለቲካ የሚሽከረከርበት ሃዲድ ሆኖ ኖሯል፡፡የአማራው መበደል፣ መሸማቀቅ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት መረጋገጥ ምልክት መስሏል፡፡ አማራውን መግደል፣ ማሳደድ፣ በአደባባይ ማሸማቀቅ፣ ማክፋፋት ለታሪክ ስህተቶች የሚሰጥ እርምት ሆኖ ተቆጠረ፡፡ የአማራ መሞት፣ መብት መገፈፍ ለጆሮ የማያስደነግጥ፣ ለዘገባም የማያስቸኩል፣ ቢዘገብም ጉድ የማያስብል ነገር ሆነ፡፡
በዚህ መሃል ህወሃት ገበያው ደራለት! በአንድ በኩል አማራውን የመግደል የማሳደዱን ነገር በመላ ሃገሪቱ ከተነሱ በአማራ ተበደልኩ ባይ የጎሳ ፖለቲከኞች ጋር እየተጋገዘ እየከወነ በሌላ በኩል የአማራውን መሬት ወደ እናት ምድሩ ትግራይ የማዳበሉን ነገር ለብቻው ተያዘው፡፡ ተጠንቅቆ ያበጃጀው የጎሳ ፖለቲካ ከባቢ አማራውን ያለጠያቂ እንደፈለገ እንዲያደርግ የፈቀደለት ህወሃት ገመዶቹን እያነባባረ የመሬት ዘረፋወን አጥብቆ ማሰሩን ቀጠለ፡፡
ገመድ ሁለት- ረዥሙ የሽግግር ወቅት:-
 
ህወሃት አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ያወጀው አራት ዓመት የሽግግር ወቅት በሽግግር መንግስት እድሜ ከተሰላ ረዥም የሚባል ነው፡፡ እውነተኛ አላማው እንደስሙ ለመሸጋገር ከሆነ ሁለት አመት ለሽግግር በቂ ጊዜ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ጉዞው ላይ የራሱ የሆነ ድብቅ አጀንዳ ለማያጣው ህወሃት ግን የሽግግር ወቅቱ የሃገሪቱን የፖለቲካ ልጓም በህዝብ ወደተመረጠ መንግስት እጅ ማሸጋገር ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ የሽግግሩ ጊዜ ለህወሃት የሃገር ጌትነት ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ባላነሰ እጅግ አስፈላጊ ወቅት ነበር፡፡ ስለዚህ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ለወደፊት የገዥ ነጅነት ዘመኑ ስምረት መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን መከወን ነበረበት፡፡
ከነዚህ ጉዳዮች አንዱ ከአማራው ግዛት ላይ እጁ የቻለለትን፣ ልቡ የወደደውን ያህል መሬት መቦጨቅ የሚያስችለውን ቅድመ-ሁኔታ ማመቻቸት ነበር፡፡ ይህ ስራ ወደፊት (የሽግግሩ ወቅት ሲያልቅ) በህገ-መንግስት ሊፀና የታሰበው የጎሳ ፌደራሊዝም ህወሃት የሊበላቸው ያሰባቸውን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ የተባሉ አሞሮች ጅግራ የሚያደርግ መሆን ነበረበት፡፡ ስለዚህ በነዚህ ቦታዎች እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በጠመንጃ የታገዘ የህዝብ ስብጥር ለውጥ (Artificial Demographic Reengineering) መደረግ ነበረበት፡፡
ይህ ፈጣን እርምጃ አሃዱ የተባለው መለስ ዜናዊን ቤተ-መንግስት ያስገቡ በሽዎች ሚቆጠሩ የህወሃት እግረኛ ወታደሮችን መሳሪያቸውን አስፈትቶ ወልቃይት ላይ በማስፈር ከሸማቂነት ወደ ዘመናዊ ገበሬነት በማሸጋገር ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከህወሃት የጌትነት ወራት በፊት በተፈጥሯዊው የጎረቤት ህዝቦች የመሄድ መምጣት መስተጋብር ከትግራይ ወደ ወልቃይት ካቀኑ ትግሬዎችም በተጨማሪ ሲቪል ትግሬዎችን በፍጥነት ወደ ወልቃይት ማስፈሩ ለነገ የማይባል አልቸኳይ ስራ ሆነ፡፡
ይህን ለማድረግ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎችን ማቋቋሙ ወደፊት ሊመጣ ያለውን ለማያውቀው አማራ አፍዝ አደንግዝ ነበር፡፡ የተደገሰለትን የማያውቀው የአካባቢው ህዝብ ህወሃት በሽግግሩ ወቅት ከተከዜ ማዶ ህዝብ በገፍ እያመጣ የማስፈሩን ነገር ለእርሻ ሥራው ሰራተኛ ከማምጣት ያለፈ አድርጎ ለማሰብ እንደ ህወሃት ከተንኮል መቦካትን ይጠይቃል፡፡
ጥድፍ ያለው ሰፈራ ህወሃት የወልቃይትን ጉዳይ አጥብቆ ካሰረባቸው ገመዶች እጅግ ጠባቃው ነው፡፡ህወሃት በዚህ ስራው መሬት ከመቀማቱ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት ሳይቀር በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቁትን ከባድ ወንጀሎች በወልቃይት ህዝብ ላይ ሰርቷል፡፡ ከገብሩ አስራት ጀምሮ በዚህ ወንጄል የማይጠየቅ የህወሃት አመራር ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፡፡
ወልቃይትን በግድ ትግሬ ለማድረግ የሽግግሩ ወቅት ሳያልቅ በሚል እሽቅድምድም በሚመስል ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምድሯ የበቀለው አማራ በጅምላ ተገድሏል፣ ታስሯል፣ ተፈናቅሏም፡፡በምትኩ የባለጊዜ በአንድ ሌሊት እንደ ጅብ ጥላ በቅሎ እንዲያድር ተደርጓል፡፡
ይህ ግልጥልጥ ብሎ ሳይመረመር፣ለተሰራውን አሰቃቂ የኢ-ሰብዓዊነትና የመብት ረገጣ ግዙፍ ወንጀል ተጠያቂነት ሳይመጣ የወልቃይትን ነገር በአራት ዓመት ውስጥ በተፈበረኩ አርቲፊሻል ብቃዮች የሪፈረንደም ድምፀ-ውሳኔ ልፍታ ማለት ሲበደል በኖረው ህዝብ ላይ መቀለድ፣ሰሜን ኢትዮጵያንም የሁከት ምድር ማድረግ ነው፡፡
ገመድ ሶስት- ህገ-መንግስቱ እና አሰራሩ:-
 
ህወሃት በ1987 ያወጣው ህገ-መንግስት በረዥሙ የሽግግር ወቅት በጠመንጃ ታግዞ ለጀመረው ትግራይን በአማራው ኪሳራ ማስፋፋት ፕሮጄክት ህጋዊ ሽፋን የሰጠበት ነው፡፡
ወልቃይትን በተጣደፈ፣ጤናማ ያልሆነ ሰፈራ በትግሬ የመሙላቱን ስራ አማራውን አሳዶ ከመግደል ማሰሩ ጋር አሰናስሎ ወልቃይትን “አፍላ ትግሬ” ማድረጉን ከ1987 በፊት አስረገጠ፡፡ አሁን ተራው ህገ-ወጡን ብቻ ሳይሆን ወንጀሉን ህጋዊ ለማድረግ ህገ-መንግስቱን በስራ ላይ የማዋል ነው፡፡
ፅንሰት ውልደቱ ከህወሃት መሃል እጅ የማይወጣው የሃገራችን ህገ-መንግስት ያዋቀረው ዘጠኝ ክልል ቋንቋቸው ተመሳሳይ የሆኑ ህዝቦችን በአንድ ግዛት ያዋስናል፡፡ “አፍላዋ ትግሬ” ወልቃይትም ቀድሞ በህወሃት የልብ ፅላት ወደ ተፃፈላት ወደ ትግራይ ክልል ከመካለል ውጭ አማራጭ አልነበራትም፡፡
ማራጭ የለኝም ብላ ግን ዝም ብላ ወደ ነዷት አልነጎደችም፡፡ ከግድያ፣ ከባዶ ስድስት ሲኦል የተረፉት ሰላላ ድምፆቿን ሰብስባ፣ መፈናቀል የበታተናቸውን ጉልበቶቿን እንደምንም አቀናጅታ አማራነቷን እያወጀች ትገኛለች፡፡ ጩኽቱ የሚጎርፈው ግን ህወሃት እንዲመቼው አድርጎ በሰራው ቦይ ስለሆነ ጠመንጃ ይገላግለኝ ከሚለው የቢቸግር መፍትሄ የተለየ ጠብ የሚል ሁነኛ መፍትሄ ሊገኝ አልቻልም፡፡
የሽግግር መንግስቱ የጀማመረውን የጎሳ አከላላል ያፀናው ህገ-መንግስት ወልቃይትን ከነጩኽቷ ለትግራይ ክልል ምክርቤት በመሸለም የግፍ ጉዞዋን እንድትቀጥል አደረገ፡፡ ወልቃይትን በተመለከተ ህገ-መንግስቱ ያደረገው ነገር ቢኖር በሽግግሩ ወቅት የተደረገውን ወንጄል፣ የተሰራውን ደባ ህጋዊ ማድረግን ነው፡፡ ህጋዊ የሆነ ነገር ሁሉ ተገቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡
ለዚህ ከወልቃይት ጉዳይ በላይ ማሳያ የለም፡፡ከአራት አመት በኋላ የሚፃፈው ህገ-መንግስት ትግሬ ብሎ እንዲጠራው በተፈለገ የአማራ መሬት ላይ የሚኖርን ህዝብ በፍጥነት ገድሎ፣ አስሮ፣ አሰድዶ፣ የገባበትን አጥፍቶ፣ የቀረውን ደግሞ ማንነቱን አስክዶ በምትኩ ከአንድ ዘር ብቻ የተቀዳን ህዝብ በመኪና እየሞሉ በገፍ ማስፈር ሃገሩ ኢትዮጵያ ባይሆን ብዙ አመት ፍርድ ቤት የሚያመላልስ ወንጀል እንጅ ሆድ ሲያውቅ በሆነ ሁኔታ ህገ-መንግስቱን እየጠሩ የሚመፃደቁበት፤ ጭራሽ ለሪፈረንደም የሚጋበዙበት ሰው ፊት የሚያቆም ሥራ አልነበረም፡፡
ህገ-መንግስቱን ለገደብ የለሽ ምኞቱ ማስፈፀሚያ እና ለይሉኝታ ቢስ ክርክሩ ማገር ብቻ የሚጠቀመው ህወሃት ታዲያ ፍትህ ተነፍገው፣ ሳይወዱ በግድ በግፍ ወደ ትግራይ የተካለሉ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ቦታዎችን የትግራይ ህጋዊ ግዛቶች ናቸው ሲል በእማኝነት የሚጠራው ራሱ በጠመንጃው የከተበውን ህገ-መንግስት ነው፡፡
ከእርሱ ህልውና በፊት በወልቃት አካባቢ በጉልበተኛው ህወሃት እጅ የተደረጉ ወንጀሎችን ያይ ዘንድ አፈጣጠሩ የማይፈቅድለት ህገ-መንግስትም የተፈጠረለትን አላማ ከማስፈፀም በቀር ፍትህ ርትዕ ሳያሰፍን የህወሃት ማኒፌስቶ ቅጅ ሆኖ ብቻ ሃያ ሰባት አመት ዘልቋል፡፡ በህወሃት ሳቢያ በጥንድ አይኑ የሚያለቅሰውን የወልቃይት ህዝብ የሚያስለቅሰውን ጉዳይ ይዞ ወደ ችግሩ አባት ወደ ወህወሃት ፓርላማ እንዲሄድ ያዛል፡፡ ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ህገ-መንግስቱን ራሱን ህወሃት የወልቃይትን ነገር አጥብቆ ያሰረበት ሶስተኛ ገመድ ያደርገዋል፡፡
ገመድ አራት- የህወሃት “ሁለት-ነፍስ”:-
 
ወልቃት በፍጥነት ትግሬ ሆና ህገ-መንግስቱን እንድትጠብቅ ወንጀል ሲሰራ የኖረው ህወሃት ምንም እንዳልሰራ ሰው የወልቃይት ነገር መታየት ያለበት በህገ-ንግስቱ እንደሆነ ይወተውታል፡፡ ከብዙ አመት በኋላ የወልቃየትን ጉዳይ በአደባባይ ይዘው መከራከር የጀመሩት አባላትም ይህንኑ በደባ የተሞላ መንገድም ቢሆን እንሞክረው ብለው ሲደክሙ ኖረዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለደከሙት ድካም እና ላሳዩት ቆራጠነት ትልቅ ክብርም አድናቆትም ያለኝ ቢሆንም በመንገዱ አዋጭነት ላይ ግን ወደተስፋቢስነት የተጠጋ ትልቅ ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡
የወልቃይት ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ሲሄድበት የነበረው መንገድ የሚያመራው ህወሃት ነገሩ እንዲሄድ ፈልጎ ባስተካከለው፣ እሱን ከነወንጀሉ እውነተኛም፣ ህጋዊም፣በስተመጨረሻም በስመ-ሪፈረንደም አሸናፊ በሚያደርገው አቅጣጫ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ መጀመሪያው አቤቱታ የሚቀርበው ምናልባትም የወልቃትን ህዝብ በአራት አመት ውስጥ በማጥፋቱ ላይ ተግተው የሰሩ የህወሃት ወንጀለኛ ባለስልጣናት በሞሉት የክልላቸው ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክርቤት ነገሩን በፈለገው የጊዜ ርቀት ሲያሸው ኖሮ ከላከው የሚልከው ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት ነው፡፡
ህወሃት በሃገሪቱ የፖለቲካ አየር ሞልቶ እንደመኖሩ ጉዳዩ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በሚያደርገው ሽግግር ላይ ባለ ሁለት ነፍስ ሆኖ በየደረጃው ጥቅሙን የሚያስከብር ስራ ሲሰራ ኖሯል፡፡በፌደሬሽን ምክርቤት ውሳኔ ጉዳዩ በትግራይ ክልል ፓርላማ ብቻ እልባት ይሰጥበት የሚል አስቂኝ ይሉኝታ ቢስ ውሳኔ ተወስኖ የነበረው በህወሃት ሁለት ነፍስ ምክንያት ነበር፡፡
ምስጋና ለጊዜ ይግባውና ህወሃት ሁለት ነፍስ መሆን ቀርቶ አንዱን ይዞ መኖሩ አጠራጣሪ መሆኑን ሲያውቅ፣ በሞት አፋፉ ላይ ሆኖም ወ/ሮ ኬሪያ የተባሉ ህወሃት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እንዲሆኑ ያደረገው የወልቃይት ጉዳይ እንቅልፍ የማይሰጥ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡
አምስተኛው ገመድ- የገለልተኛ ወገን ዜማ:-
 
ውሉ ሲወሳሰብ የኖረው የወልቃት ችግር አሁን አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ የገባው የዶ/ር አብይ ኢህአዴግ ቢቸግረው ነገሩን የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄ ሲል እውነትን መሸሽን ሲመርጥ ተስተውሏል፡፡ ህወሃትም በበኩሉ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ እልባት አግኝቷል ሲል እሳትን በጋቢ ሊያዳፍን ሲሞክር ኖሯል፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬ ላይ የወልቃይት ጉዳይ ቢሸሹት የማይሆን ጉዳይ በመሆኑ መንግስትም የማንነት ጥያቄ መሆኑን ተቀብሏል፡፡ ሆኖም ችግሩን ሊፈታ የተነሳበት መንገድ ፍቱንነት አሁንም አጠራጣሪ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የማንነትን ጥያቄ ለመፍታት ቆርጠናል ሲሉ በቴሌቭዥን ብቅ ብለው ተናግረዋል- የፌደሬሽን ምክርቤት አፈ-ጉባኤዋ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ያመጣል ያሉትን አካሄድ ሲያስረዱም ገለልተኛ ቡድን አዋቅረን ወደ ህዝቡ ወርደን ችግሩን እንፈታለን የሚል የተለመደውን የህወሃት ዘይቤ ነው ይዘው የመጡት፡፡ገለልተኛ የተባለው ደግሞ ብዙ የማንነት ጥያቄን የፈታው ደቡብ ክልል ነው ሲሉ አክለው ከዩኒቨርሲቲም ሰዎችን ጨምረው ጉዳዩን እንደሚያዩት ተናግረዋል ወይዘሮዋ፡፡
ይህ አካሄድ ከላይ የተጠቀሱትን የህወሃት ገመዶች ይመግብ ይሆናል እንጅ አዲስ እና ሁነኛ መፍትሄ የሚያመጣ አይመስልም፡፡ ቀድሞ ነገር ይቋቋማል የተባለው አካልም ሆነ የራሳቸው የወይዘሮ ኬሪያ ገለልተኝነት ማንን ያስማማል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በመቀጠል የማንነት ጥያቄን የመመለስ ብዙ ልምድ ስላለው ተመረጠ የተባለው የደቡብ ክልል በወልቃይት ደረጃ የተወሳሰበ ችግር ገጥሞት ፈቶያውቃል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
በዚህ ላይ ህወሃት በጌትነት ዘመኑ የደቡብ ክልልን ካድሬዎችን እንደ ሁለተኛ ነፍሱ የሚቆጥራቸው መሆኑ ግልፅ በመሆኑ ከደቡብ ይመጣሉ ለተባሉት ሰዎች ገለልተኝነት ጥብቅ ጥያቄ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ ህወሃት አማራውን የሌሎች ብሄሮች ሁሉ ጨቋኝ አድርጎ ሲያቀርብ እንደመኖሩ የአማራውን የማንነት ጥያቄ በሌሎች ብሄረሰቦች ዘንድ በገለልተኝነት የመስተናገዱ ነገር ምንያህል አስተማማኝ ነው የሚለው ሁሉ ያጠያይቃል፡፡
በአጠቃላይ የወልቃይት ጉዳይ ሁሉም ሰው ወደ ማይፈልገው የአመፅ ውስጥ እንዳይገባ ከተፈለገ የችግሩ አቀራረብም ሆነ የአፈታት መንገድ ከዚህ ቀደም ከታየበት እይታ በተለየ መታየት አለበት፡፡ እንዴት መታየት አለበት በሚለው ላይ የታየኝን ለማለት ሳምንት ልመለስ፡
Filed in: Amharic