>
5:14 pm - Tuesday April 20, 2883

ጦሩ ያለው አፍንጫቸው ሥር ሮኬታቸውን የሚያስወነጭፉት ወደ ሕዝብ መንደር...!!! (አባይ ነህ ካሴ)

ጦሩ ያለው አፍንጫቸው ሥር ሮኬታቸውን የሚያስወነጭፉት ወደ ሕዝብ መንደር…!!!

አባይ ነህ ካሴ

 

ባሕር ዳር ከተማ ምሽቱን አሁንም ኹለተኛ ዙር የሮኬት ጥቃት ተሠንዝሮባታል፡፡  
የሮኬት ጥቃት በተደጋጋሚ ወደ ሕዝብ ማስወንጨፍ ፀረ ሕዝብነትን ከሚያጋልጥ በቀር ሌላ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ጦርነት ሕግ የለውም የሚባል አመለካከት እንዳለ ሁሉ ጦርነት ሕግ አለውም ይባላል፡፡ ኹለተኛው ስላመዘነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦር ወንጀለኞች የተባሉ ሁሉ ለፍርድ የሚቀርቡበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ሰላማዊ ሕዝብን ዒላማ ያደረገ ጦርነት ሰይጣናዊነት ነው፡፡
በሞት ጣር ላይ ያሉት የትህነግ አመራሮች አሁንም በመቃብር አፋፍ ላይ እየቃተቱ የሚጠማቸው የንጹሐን ደም ነው፡፡ ሦስቱ መሠረታዊ ድቀቶች እንዳይነሡ አድርጎ ይቀብሯቸዋል፡፡ በዐራት ታላላቅ ወንጀሎች የሚፈለጉት ሰዎች የተስፋ መቁረጥ ሒደት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በጦር ወንጀለኝነት፣ በዘር ፍጅት፣ በሌብነት እና በሀገር ክዳት፡፡  እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት ይዞ የመሞት መንጠራወዝ ይዟቸዋል፡፡
፩. የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የሠነዘሩት ራሳቸው መኾናቸውን በጉምቱው አባላቸው በሴኮ ቱሬ ጌታቸው አጋልጠዋል፡፡ የራስ ምሥክር በራስ ላይ ስለኾነ ሰውየውም ነገሩን ከተናገረ ወዲህ ደብዛው አልተገኘም፡፡ በዚህ የጦርነቱ ጀማሪዎች እኛ ነን ብለው በማያወላዳ ደረጃ ዐውጀዋል፡፡ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል ብሏል ሊቃቸው፡፡ ከዚያ ድንቅ ልፍለፋ በኋላ መብረቃዊ ጥቃት ይብላው ወይ እምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም አሉ፡፡
፪. በማይ ካድራ እስከ ፭፻ (500) የሚደርሱ ሰላማዊያን ዜጎች ላይ ያደረሱት የዘር ጭፍጨፋ፡፡ ለድርጅቴ እሟገታለሁ ብሎ ከቪኦኤ የተባረረው ሰውዬ በፍራንስ 24 ላይ ቀርቦ ስለማይ ካድራው ጭፍጨፋ የሰጠው ቃል ጭፍጨፋውን የአሮጊቶች ቡድን እንደፈጸመው ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ሰዎቹ የሞቱት እርስ በእርስ በነበረ የማኅበረሰቡ ግጭት ነው ብሏል፡፡ የአሮጊቶቹ ቡድን አላደረገውም ብሎ አፉን ሞልቶ ሊናገር አልቻለም፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ ሲያልቁ በከተማው የነበረው የታጠቀ ኃይል የአሮጊቶቹ ጦር መኾኑ ይታወቃል፡፡ አስተዳደሩም በእነርሱ ድርጅት ነበረ።  ሰዎቹን የኢትዮጵያ አምላክ ያስለፈልፋቸዋል፡፡
፫. ሮኬት በተደጋጋሚ ወደ ከተሞች ማስወንጨፋቸው፡፡ በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና በአስመራ ያደረጉት የሮኬት ጥቃት ማንን ለማጥቃት ነው? ጦርነቱ አፍንጫቸው ሥር ጥፋታቸው ወደ ሕዝብ መንደር፡፡ ፀረ ሕዝብነት እስከሞት ነው መፈክራቸው፡፡
Filed in: Amharic