>

አማራ የታገለው ግፍ ሲፈጽምበት የኖረውን የስብሃት ነጋን ቡድን አስወግዶ የሙሉ ነጋን ቀንበር ለመሸከም አይደለም!! (ህብር ራድዮ)

አማራ የታገለው ግፍ ሲፈጽምበት የኖረውን የስብሃት ነጋን ቡድን አስወግዶ የሙሉ ነጋን ቀንበር ለመሸከም አይደለም!!

ህብር ራድዮ

* ይሰማል አራት ኪሎ !?
በደሙ የነቀለውን ጭቆና በሴራ መልሶ ለመትከል ያሰበ የውድቀቱን ደውል ቀድሞ ደወለ ።የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመባል በህወሓት ችሮታ ሳይሆን  በዚህ መስዋዕትነት መሆኑን መዘንጋት ከምንም በላይ እንደ አዲስ አደራጅ በማይካድራ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ወደ ጎን አድርጎ በጉልበት የቀማነውን መልሰን እንውሰድ እና ህዝቡን መልሰን ባሪያ ላድርግ ብሎ የተነሳ ኃይል እየተንገዳገዱ ያሉ ፋሺስቶችን ምኞት ለማስቀጠል የቆረጠ ነው። ማንም ይደግፈው ማን ከዚህ ሴራ ጀርባ ያሉ መሰሪዎች የማይካድራውን ጭፍጨፋ የማውገዝ ሞራል የሌላቸው እኩያን ናቸው። ዶ/ር ሙሉ ነጋ ተጠርቶ ለተሰጠው ሥልጣን ለማጽናት የህወሓት እብሪት የወለደውን የመስፋፋት አጀንዳ ወደ ጎን በማድረግ በወልቃይት፣ጠገዴ”ጸገዴ(የተውሶ መጠሪያ) ፣ጸለምት(ጠለምትን ከፍለው የሰጡት ስያሜ)  እና ራያ ብቻ ሳይሆን በሕወሓት ዘረኛ እርምጃ እየሞተ ላለው የሽብር ቡድኑ በጠላትነት የፈረጀውን የአማራ ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ እና የሚገባቸውን እያስተዳደሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ቢሰሩ የተሻለ ነው። ይህን ለሾመዎትም አጀንዳ ለሰጡትም ቁማርተኞች በግልጽ ይንገሩ።
የጎረቤት ሌባ ባያዩኝ እሰርቅ ቢያዩኝ እስቅ  ያለፈበት ጨዋታ ወይስ!?
የትግራዩ ገዢ ሙሉ ነጋ(ዶ/ር) የትግራይን አደረጃጀት አስመልክቶ በማህበራዊ ገጻቸው ያወጡትን ጽሑፍ የፈጠረውን ጠንካራ ተቃውሞ አይተው እጅግ ዘግይተው “የኔ አይደለም’ ማለታቸውን አፈ ቀላጤዎቻቸው እየነገሩን ነው። ይህን ለማለት የተወሰደውን ጊዜ እና ለውትሮው አፈ ቀላጤዎቹ በብርሃን ፍጥነት ሲያደርጉት የነበረውን ለታዘበ አንድ ግልጽ ነገር አለ። ማህበራዊ ገጽ ሌላ ከተሾሙ በሁዋላ የላቸውም።ይሄም ይቅር። ለመሆኑ ይህን ሲናገሩ የመጀመሪያቸው ነው? ከጦርነቱ ማግስት በሰጡት ማግለጫ ያሉትን እኮ ነው የደገሙት።
በጊዜው ነገሩን ላለማራገብ ለስለስ አድርገን ጠቆም ለማድረግ ሞክረናል።ድብብቆሽ አይሰራም። በግልጽ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፋሺስቶቹን በወረራ የተያዘ ግዛት ለማስቀጠል ማለም ትርጉም የለውም። ዜጎች በገዛ አገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩበት የስም ፌደራሊዝም በሐይል ተይዘው በቆዩት ግዛቶች ብቻ ሳይሆን ወልቃይት፣ጸገዴ፣ጸለምት እና ራያ ( በጉልበት የተካለሉት እንደ መሐሪ፣ራያ አዘቦ፣ወፍላ እና አላማጣ) ከ1983 በነበሩበት ይዞታ ስር በጉልበት ከመነጠቃቸው ባሻገር ዜጎች በቋንቋቸው እንዳይናገሩ፣እንደ ዜጋ ተሸማቅው እንዲኖሩ ተደርገዋል። ይሄ ችግር ወያኔ እና ኦነግ ሰራሽ ሆኖ ዛሬ አማራ በገዛ አገሩ እየተሳደደ የሚገደልበትን የፋሺስቶቹን ስርወ መንግስት ጥቂት የሕወሓት መሪዎችን ብቻ በማስወገድ ግማሽ ሸክም ይቀላል በሚል እንጂ ማንም ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰራ የኖረው ደባ ጠፍቶት አይደለም። ቁማርተኞች እንደ ሕወሓት ጊዜ ሰጠኝ ብለው ለመንጠራራት መሬት ይጥበበን ማለታቸው ለሁሉም ግልጽ ነው። በህወሓት መቃብር ላይ የነገ ዕጣቸውን እና የዕብሪት እና ጥጋብ መጨረሻው ያለዝባቸው ከሆነ ማየት ነው። ተራራ የሚያክል ችግር ግን ከፊት እንዳለ  አውቆ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ባለ ሴራውንም ቁማርተኛውንም ነቅቶ መከታተል ይገባል።
ዜጎች የአገርን ህልውና ለማስከበር ያገኙትን ነጻነት ለማስከበር በሚዋደቁበት በዚህ ወቅት እኮ ነው ትላንት ራያ ብቅ ያለው ኦቢኤን የኦሮሚያ ይገባኛል ጥያቄ መስፋፋት አጀንዳን ይዞ ብቅ ያለው። ከእነ ሙሉ ነጋ ጀርባ የሚራወጠው እዚህ አጀንዳ ስር የተደበቀው ጭምር ነው።
ለዛሬ ረጅም ትንፋሽ ወስደው የፌስ ቡክ ገጹ የተሳሳተ ነው ያሉትን  ለምን ትክክለኛ አቁዋማቸው ከተጻፈው ይለይ እንደሁ አይነግሩንም!? አያደርጉትም። ከሆነ እናያለን። ለሁሉም የጎረቤት ሌባ ባያዩኝ እሰርቅ ቢያዩኝ እስቅ ማለቱን ለማስታወስ እንወዳለን።ይልቅ ሴራውንም ቁማሩንም ትታችሁ ተጋግዘን ሕወሓትን እንቅበረው።
Filed in: Amharic