ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት
አቻምየለህ ታምሩ
ሰው ሁሉ ልክ እንደ ቄሮ ለማሰብ ፍቃደኛ ያልሆነና የሚነግሩትን ሁሉ እንደወረደ ሳያጣራ የሚቀበል ጅል የሚመስላቸው ኦነጋውያን “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” እያሉ ለፋሽስት የገቡ የኤርትራ አስካሪሶች ጣሊያን ውስጥ ሞንቴ ሳክሮ በሚባል ቦታ ያቀረቡትን ትርዒት ከመሀሉ ቆርጠው በመለጠፍ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ሲወር አማሮች ፋሺስት ጣሊያንን ለመቀበል ያደረጉት “ሽለላ” አድርገው በፌስቡክ እያዳረሱት ይገኛሉ። አርበኛነትን በነገድ ወስነው የኛ አባቶች [ኦሮሞዎችን መሆኑ ነው] የሚሏቸውን ደግሞ ለፋሽስት ጣሊያን እየሸለሉ የክብር አቀባበል ያላደረጉ ብቸኛ አርበኞች አደርገው በማቅረብ ለማሰብ ፍቃደኛ ያልሆነውን ተከታያቸውን እንደልማዳቸው እያሳሳቱት ይገኛሉ። ቆርጠው ቀጥለው በፌስቡክ እያሰራጩት ያለውን ቅንብር ለማየት ይህንን ሊንክ ይጫኗል፤
የኦነጋውያን ፖለቲካ ለሕፃን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ እየፈጠሩ ወይም እንዲህ ከመሀል ቆርጠው በማውጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተደረገን ኢትዮጵያ ውስጥ ተደረገ እያሉ ሌላው መሳቂያ መሳለቂያ ቢያደርገን እንኳን ኦሮሞ ግን የምንነግረውን ሁሉ ያምነናል የሚል ንቅት የወለደው ድንቁርና ነው። ከፍ ሲል ባቀረብሁት ሊንክ ቆርጠው የለጠፉት ቪዲዮ ትክክለኛ ቅጂው [the original video] 3 ደቂቃ ከ3 ሴኮንዱ ያህል የሚረዝም ሲሆን እነሱ ግን ከዚህ ውስጥ ስለ ቪዲዮው መግቢያ የቀረበውን መግለጫ፣ በቪዲዮው ውስጥ የሚታየው ትርዒት የት ቦታ እንደተፈጸመ የቀረበውን ሀተታ ቆርጠው አውጥተው ትርዒቱ የቀረበበት ቋንቋ አማርኛ ስለመሰላቸው ብቻ አማራን ለመክሰስ ያስችለናል ያሉትን 1 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ የሚሆነውን ቆርጠው ለጠፉት። ከዋናው የጣሊያን ምንጭ ማለትም Istituto Luce Cinecittà ከሚባለው የጥሊያን ተቋም የተገኘውን ሙሉው ቪዲዮ ይህንን ሊንክ በመጫን ከተቋሙ ኦፊሻላዊ የዩቱብ አካውንት ማየት ይቻላል፤
ሊንኩን ስንጫን የምናገኘው የሙሉው ቪዲዮ ርዕስ በጣሊያንኛ “Mussolini visita l’accampamento eritreo di Monte Sacro” የሚል ሲሆን ወደ አማርኛ ስንመልሰው ደግሞ “ሙሶሎኒ ሞንቴ ሳችሮ የሚገኘውን የኤርትራውያን ካምፕ ሲጎበኝ” የሚል ነው። ልብ በሉ! ትዕይንቱ የቀረበው በጣሊያን አገር ውስጥ ሞንቴ ሳክሮ በሚትባል ከተማ ውስጥ ነው። ሙሶሎኒም ጉብኝቱን ያደረገው እ.ኤ.አ. ግንቦት 4 ቀን 1937 ዓ.ም. ነው። [ምንጭ፡ https://www.akg-images.com/ archive/-2UMDHUNGDRY3.html] ።
እንደሚታወቀው ፋሽስት ጣሊያን አዲስ አበባ የገባው እ.ኤ.አ. ግንቦት 5 ቀን 1936 ዓ.ም. ነው። ይህ ማለት ሙሶሎኒ ሞንቴ ሳችሮ የሚገኘውን የኤርትራ ካምፕ የጎበኘው ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያን ዋና ከተማ በተቆጣጠረ በአመቱ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኦነጋውያን ቆርጠው የለጠፉት ቪዲዮ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር ሲመጣ በ”ሽለላ” የተደረገለት የክብር አቀባበልን የሚያሳይ ቪዲዮ አይደለም ማለት ነው። ይህ ማለት አንድ ለአቅመ ማሰብ የደረሰ ሰው ትዕይንቱ የቀረበው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሎ ቢያስብ እንኳ ትዕይንቱ የቀረበው ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በያዘ በዓመቱ ስለሆነ ትዕይንቱ የቀረበው ፋሽስት ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ የተደረገ አቀባበል ነው ብሎ ሊያስብ አይችልም።
የሆነው ሆኖ “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” በሚል በቪዲዮው ውስጥ የሚሰማውን “ሽለላ” ኦነጋውያን በተካኑበት ቆርጦ መቀጠል ቆርጠው አውጥተው አማራ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ ያቀረበው “ሽለላ” አድርገው እያሰራጩ የሚገኙት ቅንብር የተቀዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ሙሶሎኑ ጣሊያን ውስጥ ሞንቴ ሳክሮ በሚባል ቦታ ይገኝ የነበረውን የኤርትራ አስካሪሶች ካምፕ በጎበኘበት ወቅት መሆኑን፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” የሚለውን ድምጽም የሚያሰሙት የኤርትራ አስካሪሶች ያቀረቡት “ሽለላ” እንጂ አማሮች አለመሆናቸውን በሙሉ ቪዲዮው መግቢያ ላይ የቀረበውን መግለጫ ባፍ ጢሙ ደፍተው ነው።
ባጭሩ “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” በሚል የሚሰማው ድምጽ አቅራቢዎች አማሮች ሳይሆኑ የኤርትራ አስካሪሶች ናቸው፤ ቪዲዮውም የተቀዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ጣሊያን ውስጥ ሞንቴ ሳክሮ በሚባል ከተማ የኤርትራ አስካሪሶች ካምፕ በሙሶሎኒ በተጎበኘበት ወቅት ነው።
ኦነጋውያኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተፈጸመን ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ እንደተፈጸመ አድርገው ተከታዮቻቸውን ለማሳሳት የሞከሩት “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” በሚል ጣሊያን ውስጥ ኤርትራውያን ያቀረቡትን “ሽለላ” አማርኛ አድርገው ኢትዮጵያ ውስጥ የቀረበ በማድረግ ነው። ሲጀመር አማርኛ የአማራ ቋንቋ ብቻ አይደለም። አማርኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አፋቸውን የሚፈቱበትና በሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ አፋቸውን የሚፈቱ ደግሞ በተደራቢነት የሚናገሩት የራሳቸው ቋንቋ ነው።
ሲቀጥል “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” የሚለው “ሽለላ” በአማርኛውም በትግርኛም ተመሳሳይ ሲሆን ጣሊያን ሞንቴ ሳክሮ ውስጥ በቀረበው ትዕይንት ላይ “ሲሸልሉ” የሚሰሙት የኤርትራ አስካሪሶች “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” የሚለውን ዜማ ከጨረሹ በኋላ ከአማርኛ በተለየ የትግርኛ ቋንቋ የሚያቀርቡትን ዜማ ማቅረብ ሲጀምሩ በቪዲዮው የምንሰማው ትዕይነት ይቋረጣል። ኦነጋውያኑ ግን በቪዲዮው መጨረሻ ላይ “ሽለላው” ከአማርኛ ወደተለየ ትግርኛ እንደተቀየረ ልብ አላሉትም።
የኦነግ አምበል የነበረው የዋናው ባንዳ ልጅ የአባ ቢያ አባ ጆቢር ልጆች ነን የሚሉት ግብዞች አርበኛነትን በነገድ ወስነው “ለፋሺስት ኢጣሊያን እንዲህ እየሸለሉ የክብር አቀባበል ያደረገለት የኔ አያቶች አይደሉም” ማለታቸውን ሳነብ መገረሜ አልቀረም።
ለማንኛውም የኛ አባቶች “ለፋሽስት ጣሊያን እየሸለሉ የክብር አቀባበል አላደረጉም” ለሚሉ የእውቀት ጾመኛ ኦነጋውያን የኦነግ ፈጣሪዎች የተወለዱበት የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ከ25 በላይ የሚሆኑ ባላባቶች “እኛ የወለጋ ሕዝብ. . . የኢጣልያን መንግሥት ተቀብለን በሠላም እንገባለን” ብለው ለሙሶሎኒ የጻፉትን ደብዳቤ ከታች ለጥፌላቸዋለሁ። ደብዳቤው የጣሊያንን ማሕደር ስበረብር ካገኘኋቸው በቶን የሚቆጠሩ የባንዶች ደብዳቤ መካከል አንዱ ነው።
በነገራችን ላይ ከላይ⇑ የታተመው የወለጋ ባላባቶች ለጣሊያን የገቡበት ደብዳቤ የተጻፈው በአማርኛ ነው። ጣሊያን ውስጥ ሞንቴ ሳክሮ በሚባል ቦታ ይገኝ በነበረው ካምፕ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራ አስካሪሶች “አይፈራም፥ አይፈራም ጎበዝ” ፤ “አይፈራም፥ አይፈራም ሞሶሎኒ” እያሉ ያቀረቡት “ሽለላ” በአማርኛ የቀረበ ስለመሰላቸው “አማሮች ፋሽስት ኢትዮጵያን ሲይዝ ያቀረቡት “ሽለላ” ነው” ብለው ተከታዮቻቸውን ያሳሳቱት ኦነጋውያን አባቶቻችን የሚሏቸው የወለጋ ባላባቶች በአማርኛ ለሙሶሎኒ የጻፉትን ደብዳቤስ አማሮች ለሙሶሎኒ የጻፉት አድርገው ያቀርቡት ይሆን?
መረራ ጉዲናም የዛሬን አያድርገውና በጦብያ መጽሔት በጥር 1988 ዓ.ም. «በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር በሌሎች ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወርዋሪ አይሆንም» በሚል በጻፈው ጽሑፍ ስለነዚህ ባንዳ የወለጋ ባላባቶች ጀግኖቹን እነ ራስ ጎበናን አጋሰስ እያሉ ሲሰድቧቸው ለነበሩ ኦነጋውያን በሰጠው ምላሽ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፤
“ለመሆኑ በትክክል የአጋሰስ ሥራ ሲሰሩ የኖሩ [የ]እነማን [አባቶች] ናቸው? የጎበናን ወደ አካባቢያቸው ወደ ወለጋ መሄድ በስም ብቻ ሰምተው እንደ አጋሰስ ወርቅ ሲሸከሙ የነበሩት የእነዚህ ሰዎች አባቶች አልነበሩምን? የእነሱ ጉድ ሲሆን እንዲነገርም እንዲነሳም አይፈልጉም እንጂ የአፍሪካ የነጻነት ትግል በተጀመረበት ታሪካዊ ወቅት መጀመሪያ እንግሊዝን «ነይና ግዥን» ብለው ማመልከቻ የጻፉ፣ እንግሊዝ እምቢ ስትል ለኢጣሊያን ፋሽስት አጋሰስ ሆነው እንቁላል ሲሸከሙ የነበሩ የእነሱ አባቶች የወለጋ ገዢዎች አልነበሩም? በጥቁር አንበሳ ሥር ተሰብስበው የነበሩትን የኢትዮጵያ አርበኞች ያስፈጀስ ማነው? የኦነጋውያን አባቶች የወለጋ ገዢዎች አልነበሩምን?”
መረራ ጉዲና ዛሬ ከሌንጮ ለታ በላይ ኦነግ ሆኜ ካልተገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ የሚለው ከ25 ዓመታት በፊት ያንን ሁሉ የኦነግ ጉድ ነግሮን ነው።
እንግዲህ! የኦነጋውያን ፈጠራ ሲጣራ፤ የተከደነው ውሸታቸው ሲገለጥና ዶሴው ሲወጣ እውነቱ ከፍ ሲል የቀረበውን ይመስላል። “ቢያንስ ለአዲሱ ትውልድ እውነትኛ ታሪክ እናስተምር፤ ለፋሺስት ኢጣሊያን እንዲህ እየሸለሉ የክብር አቀባበል ያደረገለት የኔ አያቶች አይደሉም” የሚሉን ኦነጋውያን ለቃላቸው ታማኝ በመሆን ከታች ባወጣሁት ዶሴ ስማቸውና ማኅተማቸው የሚታየውን አባቶቻችን የሚሏቸውን የወለጋ ባላባቶች በማውሳት “እኛ የወለጋ ሕዝብ. . . የኢጣልያን መንግሥት ተቀብለን በሠላም እንገባለን” የሚል ደብዳቤ ለሙሶሎኒ ጽፈው እንደሆነ የባንዳነት ታሪካቸውን ለአዲሱ ትውልዳቸው ታሪኩን ያስተምሩ።
በተረፈ ሳይመረምሩ፣ ያሳጣሩና ሳያረጋግጡ ሀሳብ የሌለበት የፈጠራ ወሬ እያዟዟሩ «ለፋሺስት ኢጣሊያን እንዲህ እየሸለሉ የክብር አቀባበል ያደረገለት የኔ አያቶች አይደሉም» ለሚሉ ወሬ ደጋሚዎች «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ ልሰናበት!