>

በዐቢይና በአስተዳደር ሥር ላለፉት 3 ዓመታት የተፈጸሙ ዘግናኝ ፍጅት መፈናቀልና ውድመት ህወሀትን መወንጀሉ ፌዝ ነው...!!! (ጌራወርቅ ጌታሁን)

በዐቢይና በአስተዳደር ሥር ላለፉት 3 ዓመታት የተፈጸሙ ዘግናኝ ፍጅት መፈናቀልና ውድመት ህወሀትን መወንጀሉ ፌዝ ነው…!!!
 
ጌራወርቅ ጌታሁን

 

* የአእምሮ አጠባው እንደቀጠለ ነው፤ ሕዝቤም በተቀደደለት ቦይ ዝም ብሎ እያፈሰሰ  ነው።
* በአኬልዳማዋ ኦሮሚያ ምድር የተፈጸመውን ያንን ኹሉ የሆረር ፊልም የሚመስል አሠቃቂ ግድያና የዘር ፍጅት ኹሉ ለሕወሓት ሰጥቶ ዐቢይንና አስተዳደሩን ንጹሕ አድርጎ ማሰብ ለእኔ የአእምሮ በሽተኛነት ነው። 
ወደጄ በንጹሐን ደም በጨቀየችው በኦሮሚያ ምድር የተፈጸመችውን እያንዳንዷን ድርጊት የኦሮሚያ ልዩ ኀይል ጠንቅቆ ያውቀዋል፣ ለማ መገርሳ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ ዐቢይ አህመድ ጠንቅቀው ያውቁታል፣ ማወቅ ብቻም አይደለም የድርጊቶቹ አጋፋሪዎች እነርሱው ናቸው።
ሻሸመኔ ላይ  አሰቀድሞ መረጃው ሲደርሰው “አርፈህ ተኛ” ብሎ የስልክ ትእዛዝ የሰጠው ሽመልስ አብዲሳና ዐቢይ አህመድ አቋማቸውም ሆነ ዓላማቸው አንድ ነው። በዐቢይና በእርሱ አስተዳደር ሥር ላለፉት 3 ዓመታት የተፈጸሙ ዘግናኝ ግድያዎችን፣ ዘረፋዎችን፣ መፈናቀሎችን እና ያንን ሁሉ ግፍ በሕወሓት/ትሕነግ ላይ ለጥፎ ራሱን ነጻ ለማድረግ ሲሞክር አምነህ የተቀበልክ ኦርቶዶክሳዊ ካለህ በእውነት ወደ ጠበል ሂድ።
1. በግልጽ “ሰብረናቸዋል” ብሎ የዘር ፍጅትን በአደባባይ ያወጀውን ገዳይና አስገዳይ የሾሙትና አሁንም የበላይ አድርገው እያሠሩት ያሉት ሕወሓቶች ሳይሆኑ ዐቢይ ነው-ይኽም ተረሳ።
2. በመሐል ሀገር “እንዳትታረድ ተደራጅተህ ራስህን ጠብቅ” ብሎ አዲስ አበባን ከውድመት ሕዝቧን ከመታረድ የታደገው ጀግናው እስክንድር ነጋን ያሠሩት ሕወሓቶች ሳይሆኑ ዐቢይና ጀሌዎቹ ናቸው-ነገር ግን ረሳነው።
2. ወለጋ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አርሲ፣ ቤንሻንጉል… በኦርቶዶክሳዊነታቸውና በብሔራቸው እየተመረጡ የታረዱት ወገኖቻችንን እንደዘበት ተረሱ በቃ? እነርሱንስ ያሳረዳቸው ያስገዳለቸው ሕወሓት ነው?
3. ኦነግ የሚባለውን አራጅ ቡድን ከነትጥቁ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው ሕወሓቶች ሳይሆኑ ራሱ ዐቢይ ነው። አሁንም ድረስ በኦነግ አማካኝነት ኦሮሚያ ላይ ንጹሐን እየታረዱ ነው።
4. ባልደራስን እና መሪዎቹን መሰብሰቢያ ቦታ እንኳን እንዳያገኙ በኦሮሚያ ልዩ ኀይል ፍዳቸውን ሲያሳያቸው የከረመው ዐቢይና አስተዳዳሩ ነው እንጂ ሕወሓቶች አይደሉም-ይህም ተረሳ።
5. በምርጫው የበላይነቱን ይወስድብኛል ብሎ ልደቱ አያሌውንም (እርሱንም ባላምነውም) ያሠሩትና ፍርድቤት የሰጠውን ዋስትና እየከለከሉት ሕወሓቶች ሳይሆኑ ዐቢይና አስተዳደሩ ነው-ግን ይኽም ተረሳ።
6. የአዲስ አበባን ኮንዶሚኒየምና መሬት ለብሔሩ በነፍስ ወከፍ ያከፋፈለውን ታከለን በሕግ ከመጠየቅ ይልቅ አቅፎ የያዘው ጩጬው ዐቢይ ነው እንጂ ሕወሓቶች አይደሉም-ይህንንም ረሳነው።
7. ኹለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 27 የኦሮሚኛ ማስተማሪያ ት/ቤቶችን በአዲስ አበባ ሕዝብ በጀት ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የከፈቱት ሕወሓቶች ሳይሆኑ ባለጊዜዎቹ እነ ሁሉ ኬኛ ናቸው-ነገር ግን ይኽም ተረሳ።
8. አዲስ አበባ ላይ የከተማዋንና የስልጡን የሕዝቧን ስነልቦና የማይወክሉ ታሪኩንና ልምዱን የማይጋሩ ኦሮሞ ከንቲባዎች ከአምቦ እና ከአሰላ እያመጣ ከሕግ ውጪ በራሱ አምባገነናዊ መንገድ የሾመው ዐቢይ ነው እንጂ ሕወሓቶች አይደሉም-ነገር ግን ረሳነው።
9. የአዲስ አበባን ከተማ ለመሰልቀጥ ቀን ከሌሊት የሚለፋው፣ ዴሞግራፊ ለመቀየር ብሔሬን አምጥቼ አሰፍራለሁ የሚለው፣ የኮንዲሚንየምና የመሬት ወረራን ሲያጧጡፍ የከረመው መቀሌ የተደበቀው ሕወሓት ሳይሆን ዐቢይና የእርሱ አስተዳደር ነው-ግን ተረሳ።
10. ኦርቶዶክሳውያኑ እነ ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ እነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን፣ እነ ጀነራል ገዛኢ፣  እነ ዶ/ር አምባቸው፣ እነ እዘዝ ዋሴን፣ እነ ምግባሩ…በተመሳሳይ ወቅት በጩጬው ሤራ ነው የተገደሉት እንጂ በሕወሓት አይደለም። እኛ ግን ይህንንም እረስተነዋል። ”እኔ ጠቅላይ ሚንስትር ሳልሆን በፊት የተፈታውን ጄነራል አሳምነውን ያስፈታሁት እኔ ነኝ” እያለ ያላጋጠመው ዐበይ ነው እንጂ ሕወሓት አይደለችም-ነገር ግን ተረሳ። ሕወሓት ለ27 ዓመት የኢ/ኦ/ተ ቤ/ክንን እና ኢትዮጵያን ከጎዳቻት በላይ የዐቢይ አስተዳደር በ2 ዓመት ውስጥ ይበልጥ ጎድቶናልና ዋናው ፈተና ገና ከፊታችን እንደሚጠብቀን ተረሳ።
11. ኦሮሚያ ላይ እስከ 40ኛ ዙር ድረስ ልዩ ኀይል እያሰለጠነ፣ ትግራይ 250 ሺ ኮማንዶ ሰልጥኖ ሲያስታጥቅ እያየሁ እንዳላየ እንዳልሰማ አልፎ የአማራን ክልል ልዩ ኀይል ግን ግማሹን በትኖ የተረፈውንም ለማዳከም ብዙ የሠራው ዐበይ ነው እንጂ ሕወሓት አይደለችም-ነገር ግን ተረሳ። (ዐቢይ ማታለል እንጂ ከስሕተቱ መማር የማይችል ሰው ስለሆነ ነው እንጂ ከሕወሓት ያስጣለው የአማራ ልዩ ኀይልና የገበሬ ሚኒሻ መሆኑ ለእርሱ ትልቅ ትምህርት ነበር። ነገር ግን ሳይውል ሳያድር አስቀድሞ ራሱ ዐቢይ ያመነውን አማራው የሠራውን ገድል ዛሬ በአደባባይ ክዶታል።)
12. ያ ሁሉ አማራ በኦሮሚያ ምድር እንደበግ እየታረደ ሲያልቅ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ያለው ንጹሐንን በብሔራቸውና በሀይማኖታቸው ምክንያት ተለይተው መገደላቸውን እንኳ በወጉ ለመናገር ካለመፈለጉ በተጨማሪ ሬሳህን በብሔር እየከፋፈለ የነገረህና “ኦሮሞዎችም እየተገደሉ ነው” ብሎ ሊያካክስና ሊሸፋፍን የሞከረው ዐቢይ ነው እንጂ ሕወሓት አይደለችም-ምን ዋጋ አለው ይኽም ከተረሳ ቆየ። ለነገሩ ራሱ ዐቢይ ጨርሶታልኮ- “ሾርት ሚሞሪ” ነው ያላችሁ ያለው እንዲህ የትናንቱን እየረሱለት ዛሬ ላይ የሚያሽቃብጡለትን ነው።
13. ኦነግንና ሕወሓትን አሸባሪ ብሎ ላለመፈረጅ የፈለገው ዐቢይ ነው እንጂ ሌላ አካል አይደለም።
14. ከምዕራብ ኦሮሚያ ከደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት ታግተው ታፍነው የጠፉት 17 እኅቶቻችን ይኸው አንድ ዓመት ሞላቸው-ዛሬ ተረሱ፤ መቼም ሕወሓት ወለጋ ደምቢዶሎ ድረስ ሄዶ አፈናቸው አትለኝም።  የዐቢይ አስተዳደር በንጉሡ ጥላሁን አማካኝነት ተማሪዎቹን አንዴ “አስፈትቻቸዋለሁ” በሌላ ጊዜ ደግሞ ዐቢይ ራሱ “እኔ ነኝ ያገትኳቸው ብሎ ሐላፊነቱን የወሰደ አካል አልተገኘም” እያለ ነበር ያላገጠው። ልጆቹን በሕይወት መመለስ ባይችል እንኳን እውነተኛ መረጃ ለሕዝብ ይፋ አለማድረግና ለቤተሰቦቻቸውም እርማቸውን እንዳያወጡ አንድ ዓመት ሙሉ ድኀ ወላጆቻቸውን ሲያስለቅስ የኖረው ዐቢይ ነው እንጂ ሕወሓት አይደለችም። ነገር ግን እኛም ይህንንም በአንድ ሰሞን የፌስቡክ ጫጫታ ብቻ አለፍነውና ዛሬ ረስተነው መልሰን የመሠሪው ዐቢይ አጨብጫቢዎች ሆንን።
15. መንግሥት ባመነውና በነገረን መረጃ መሠረት
“ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል በኦሮሚያ ውስጥ 37 ግጭቶች ነበሩ” ብሎናል። ወዳጄ በሃይማኖታቸውና በብሔራቸው ምክንያት ብቻ ተለይተው የታረዱትን ወገኖችና አራጁን ኦነግን አንድላይ ደምሮ “ግጭት” እያለ የሚያላግጥብህ ዐቢይ እንጂ ሕወሓት አይደለችም። በመተከል፣ በምዕራብ ወለጋና በጉራ ፈርዳ የተፈጸመው እጅግ ዘግናኝ እልቂት ግጭት ሳይሆን የሚባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል/genocide ነው። ዐቢይ ግን እንዳደነዘዘህና አእምሮህን እንደሰለበህ ስለሚያውቅ “ግጭት” እያለ ያላግጥብሃል።
ዐቢይ ጃዋር ላይም ሆነ ሕወሓት ላይ የዘመተው በሥልጣኑ ስለመጡበት ብቻ ነው እንጂ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ስለደረሰው በደል አስቦ አይደለም።
ዐቢይ አእምሮአቸውን የሰለባቸውን መንጋ ተከታዮቹን ይበልጥ ለማታለል አሁን ላይ በመላው ኦሮሚያ እስካሁን ለተፈጠለው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ሕወሐት ነው እያለ ነው። እነዚህን ስልብ የዐቢይ መንጋዎች አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ-ከዚህ በኋላስ የሌላውን ቦታ ትተን በደሟ ምድር በኦሮሚያ ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ዐቢይ ሐላፊነቱን ይወስድላችኋል??? ልብ በሉ “ሕወሓት/ትህነግ ተደምስሳለች መቀሌንም ተቆጣጥሬአለሁ” ብሎ ካስጨፈረህ በኃላ አሁን እኔ ይህን ጽሑፍ እየጻፍኩ ባለሁበት ሰዓት እንኳን 9 አማራዎች በኦሮሚያ ምድር በኦነግ በግፍ ተገድለዋል።
የዋሁ አማራ ሆይ! መሠሪውን ዐብይን ተማምነህ ድጋሚ ለ3ኛና ለ4ኛ ጊዜ ሿሿ እንዳትሠራ አስብበት። ከተኛህበት የአዚም እንቅልፍ ንቃና ወገንህን ጠብቅ። ዐቢይ ማለት ያ ሁሉ አማራ በኦሮሚያ ክልል ሲታረድ ሲገደል ሲፈናቀል አንድ ቀን እንኳን ተሳስቶ መግለጫ ያልሰጠ የገዳይህ ተባባሪ ነው። “አትግደሉን” ብለህ በከንቱ መሞት መገደል እንደሌለብህ ለመናገር ወደ አደባባይ እንኳን እንዳትወጣ የከለከለህ ጨካኝ ሰው ነው። ሞኙ አማራ ግን ዛሬ ላይ ሕወሓትን ያጠፋልህ መስሎህ፣ የበላህን ሲያክልህ እውነት መስሎህ ዛሬም ተሸወድክ።
ኹለተኛ ጥያቄ ልቀጥል-ንጹሐን በየቦታው የሚታረዱት በተለይም ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ተደርጎ ዜጎች በግፍ ይገደሉ ይፈናቀሉ የነበሩት ሕወሓት በቀረጸው ሕገ መንግስት መነሻነት መሆኑ ግልጽ ነው። እና ዜጎችን በብሔር፣ በቋንቋ ከፋፍሎ በክልል ወስኖ በልዩ ኀይል ተወጥሮ የሚያገዳድለውን ሀገርም የሚያፈራርሰውን የሕወሓትን ሕገ መንግሥት አሁንስ ዐቢይ እንዲቀየር ያደርገዋል???
3ኛ ጥያቄ፤ ለመሆኑ “ሕወሓት እና ኦነግ ሽኔ ለምንድነው በሽብርተኝነት የማይፈርረጁት? ምንድነው የቀረው? ሽብርተኝነት ከዚህ በላይ ምንድነው?” ተብሎ ዐቢይ ትናንት በፓርላማ ለተጠየቀው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ለምን መስጠት እንዳልፈለገ የሚነግረን ኦርቶዶክሳዊ አለ???
ምሳሌ 26፡23-28 “ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ እቃ ነው። ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል። በልቡ ሰባት ርኵሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው። ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል። ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል።”
ላለፉት 3 ዓመታት የተፈጸሙ ዘግናኝ ግድያዎችን፣ ዘረፋዎችን፣ መፈናቀሎችንና ያንን ሁሉ ግፍ በሕወሓት/ትሕነግ ላይ ለጥፎ ራሱን ነጻ ለማድረግ የሞከረውን መሠሪውን ዐቢይን በዐቢይ ስም የተቀበልክ ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ በእውነት እግዚአብሔር የዐቢይን ዋጋ ይስጥህ!!!
ማጠቃለያ፦ እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም-ስለፖለቲካውም አያገባኝም፣ ነገር ግን በሃይማኖቴና በቅድስት ሀገሬ በኢትዮጵያ ላይ ስለመጣው መከራ ስናገር ኹለት ዓመት አለፈኝ። ይህን ሁሉ ያናገረኝ ለሃይማኖቴና ለሀገሬ ያለኝ ፍቅር ነው። ከየትኛውም ብሔር ይምጣ ዜጎች በሃይማኖታቸውና በብሔራቸው ተለይተው የማይገደሉበትን ሥርዓት ዘርግቶ መግዛት የሚችል መሪ ከተገኘ እርሱን ለመቃወም ሞራሉም ብቃቱም አይኖረኝም። ነገር አሁን ላይ ያሉት ብልጽግናዎች፣ ቀደም ብለው የነበሩት ሕወሓቶች እና ትናንት የነበረው ደርግ ሦስቱም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና የኢትዮጵያ ጠላቶች ስለሆኑ ኹሉንም እጅግ አድርጌ እጸየፋቸዋለሁ። ሦስቱም ከኢትዮጵያ ምድር እንደአቧራ በነው እንደጢስ ተነው ከነስም አጠራራቸው እንዲጠፉም ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ስለፖለቲካ ዓለም አንዳች ነገር ትንፍሽ አልልም። ምንም ቢፈጠር አንዲት ነገር ላለመጻፍ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ። የቅዱሳኑን ገድልና ታሪክ ከመጻፍ ውጪ ስለፖለቲካው ምንም ነገር ቢፈጠር አልጽፍም። እስካሁንም ድረስ ከሃይማኖታችሁ ብሔራችሁ በልጦባችሁ “ሕወሓትን አትንካ” ዐቢይን አትናገር” እያላችሁ በስድብም ጭምር ትመልሱልኝ የነበራችሁ እኅት ወንድሞቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይቅርታ የምጠይቃችሁ እኔ አጥፍቼ ሳይሆን ከሃይማኖታችሁ ይልቅ የብሔራችሁን ስሜት ልጠብቅላችሁ ባለመቻሌ ነው። የክህነትን ሥልጣን ተቀብለናል ያሉ ዲያስፖራ ካህናት ሳይቀሩ ከሃይማኖታቸው ይልቅ ብሔራቸው የበለጠባቸው ሰዎችን ከማየት በላይ ምን የሚቀፍ ነገር አለ!!!
የቅዱሳን አምላክ የቅድስት ኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማየት ያብቃን!
Filed in: Amharic