>

ቀበሮ ገዳይ ...!!! ( በእውቀቱ ስዩም)

ቀበሮ ገዳይ …!!!

በእውቀቱ ስዩም

ድሮ ልጅ እያለን ደብረማርቆስ ውስጥ ቀበሮ ገዳይ የሚባል የመቶ ሜትር  ሩዋጭ ነበር፤እናቱ ያወጣችለትን ስም  የሚያውቅ የለም፤  ከለታት አንድ ቀን ፤ቀበሮ በሩጫ አባርሮ ጅራቱን ይዞ በርግጫ ደቅድቆ ገድሉዋል እየተባለ ይወራለት ነበር፤
ደብረማርቆስ ስቴድየም ውስጥ ውድድር ላይ የሚያደርገው ነገር ትዝ ይለኛል፤ ገና ሩጫው ሊጀመር ሲል  ከጎረቤት አውራጃ ከመጡ ተወዳዳሪዎች  ተነጥሎ  ወደ ደጋፊዎቹ ዞሮ   እጁን ያውለበልባል!  ረጅም ስለነበረ የምስራቅ ጎጃምን ሰማይ  በፎጣ የሚወለውል ነው እሚመስል!  ከዚያ ፤በአክሮባት   ወደ ሁዋላ ይገለባበጣል !  ያባ ታምሩ ወፍጮ  መዘውር ራሱ እንደዛ አይገላበጥም፤ ይቀጥልና ወደ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ዞሮ ይገረምማቸዋል፤ “ አሁን ቢቸግር እንጂ እናንተን ከመሰለ ውርጋጦች ጋር  መሽቀዳደም ነበረብኝ “  የሚል ይመስላል፤
  ልክ ሩጫ ሲጀመር ቀድሞ ይወጣና ይፈተለካል፤ በጣም ከመፍጠኑ የተነሳ ፎቶግራፍ ለማንሳት እንኩዋን   አይመችም! ሁለት ካሜራማኖች ከጎ ከጎኑ  ተከትለን ፎቶ እናነሳለን ብለው በልብ ድካም ሞተዋል   ባጭሩ፤ ልጁ  ቀበሮ ገዳይ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኛ ገዳይም ነበር!  ግን ችግሩ ምን መሰላችሁ?  ቀበሮ ገዳይ  ሩጫውን ለማጠናቀቀ አስር ሜትር ሲቀረው  አቁዋርጦ   ይወጣና ተመልካቹን ከሩዋጮች እሚለየውን   የሽቦው  አጥር ተደግፎ ያስመልሳል!
እና አሁን ሳየው በህይወታችን ውስጥ ያሉት ብዙ ነገሮች እንደ ቀበሮ ገዳይ እንጂ እንደ ሃይሌ አይደሉም  ፤ ነገሮችን ስንጀምርና ያለን ጉልበት እስከመጨረሻው አይቆየንም ፤  ኮረና የጀመረ  ሰሞን፤  የዳንቴል ማስክ ሰርቼ  በነፍስ ወከፍ ለህዝብ ካላዳረስኩ  ብላ ስትገለገል የነበረች ሴትዮ፤   ዛሬ ዶክተር ሊያ ገፅ ስር  “ ይሄ ነገር ዛሬም አለ  እንዴ ?’ የሚል ኮመንት ታስቀምጣለች፤
 ጦርነትም እንዲሁ ነው፤  ውጊያ የተጀመረ  ሰሞን የወኔ ችግር አይኖርም   ባንድ ቀን ውጊያ ሁለት የጠላት ወታደር  ገድለህ ፤ አምስት ማርከህ ሶስቱን ደግሞ እንዳይለመዳችሁ ብለህ ራሳቸውን ዳብሰህ ታሰናብታለህ፤ ጦርነቱ ካመት በላይ የሚቀጥል ከሆነ ግን  ሌላ ጣጣ ይመጣል ፤   ወኔ  በወይኔ ይተካል፤    በጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ቀርቶ፤  ቂጥህን ራሱ በሳንጃ ብትወጋ ወደፊት መንቀሳቀስ ታቆማለህ፤  በሳንጃ የተወጋ ቂጥህን  እንደ ሃብሃብ ፈንክተህ ጥለህ  ፤ የተረፈ ቂጥህን  አስከትለህ፤  ወደ ቤትህ መመለስ ነው የምትፈልገው!
የፍቅርም ነገር እንደዚያ ይመስለኛል፤ ሲጀምር በነበረው ጉልበት የሚቀጥል  ፍቅር ያለን ሰዎች የታደልን ነን
ንዋይ ደበበ አፍላ ሳለ፤ ባንድ ብርጌድ ማሲንቆ መቺ ታጅቦ የሚዘፍነው ዘፈን ነበር” ያላንቺ እኖራለሁ እኔ መች ወጣኝ’ ይላል፤ መላው የሰው ዘር ለኦክስጂን ሲጠቀምበት የኖረውን አገላለፅ ነው ንዋይ ለፍቅረኛው የሰጠው፤
ንዋይ በሌላ ዘፈን
“አትጥፊ በብዙ ከልቤ እንዳትወጭ
እንደዛም ስላልኩሽ ቶሎ ቶሎ አትምጭ”
ብሎ አረፈ፤
የመጀመርያው አገላለፅ ፍቅር የተጀመረ ሰሞን የነበረውን ስሜት ሲያንፀባርቅ ፤ ሁለተኛው ግጥም የሰነበተ ፍቅርን ይወክላል
Filed in: Amharic