>

አማራ ሰንጋው ፕሬዝዳንት (አሳዬ ደርቤ)

አማራ ሰንጋው ፕሬዝዳንት

.አሳዬ ደርቤ

ከመስከረም አንድ ጀምሮ እስከ ሕዳር ድረስ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ ከ400 በላይ አማራዎችን/አገዎችን መግደልና፣ ስፍር ቁጥር የለሽ ሕዝብ ማፈናቀል የቻለ ሲሆን በቀጣይ ወራቶች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በርካታ ቀስትና ስለት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ፕሬዝዳንት ‹‹ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል አለበት›› የሚል ጥያቄ ከሚያነሱ ሃይሎች ጋር ስምምነት ባይኖረውም በእራሱ ግን ያስተካከላቸው አንዳንድ አንቀጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት›› የሚለውን አንቀጽ ‹‹ተንቀሳቅሶ የመሞት መብት›› ብሎ እንዳስተካከለው ተግባራቱን በማየት ማወቅ ይቻላል፡፡
ሲቀጥል ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ከሰው ነፍስ ይልቅ ለቁስ ከፍተኛ አክብሮት ያለው በመሆኑ፣ በባለፈው አንድ አውቶብስ ሙሉ ተሳፋሪ ክልሉ ውስጥ መታረዱን የሚገልጽ ሪፖርት ሲቀርብለት የጠየቀው ጥያቄ ‹‹በተሸከርካሪው ላይ የደረሰ ጉዳት አለ ወይ?›› የሚል ነበረ፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ ዜጎቹ በየቀኑ የሚገደሉበት የአማራ ክልል መንግሥት ‹‹የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ›› ሲወተውት ቢከርምም…. የአራት ኪሎው መንግሥት ግን አይነኬው እና አይተኬው ፕሬዝዳንት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቃ አሳማኝ ጥፋት ማግኘት አልቻለም፡፡
የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድም መንግሥት ባደረገው ግምገማ መተከል አካባቢ በቂ የኦነግ እና የትሕነግ ልዩ ሃይል መኖሩን ስላረጋገጠ ተጨማሪ የፌደራልም ሆነ የአማራ ልዩ ሃይል ወደ ስፍራው ማሰማራት አልፈለገም፡፡
ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ኮማንድ ፖስት አዋቅሮ ሳምንታዊ ሪፖርት እየተቀበለ ‹‹በመተከል ዙሪያ የአማራና የአገው ተወላጆችን ለመግደል ከታቀደው እቅድ ውስጥ ምን ያህሉ ተከናወነ?›› እያለ በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡
.
ማሳሰቢያ፡- የጻፍኩት ቁም-ነገር ቀልድ ከመሰላችሁ የችግሩ ምንጭ በዜጎች ነፍስ ላይ የሚቀልደው መንግሥት እንጂ የእኔ አለመሆኑ ይታወቅልኝ፡፡
Filed in: Amharic