>
5:16 pm - Monday May 24, 1041

"በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም...!!!" (አቶ አብርሃም አለህኝ)

“በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም…!!!”

አቶ አብርሃም አለህኝ

 

* የአማራ ብልጽግና ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ስርአት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም !
ስናጠፋ የሚገስጸን ስናለማ የሚያግዘን ህዝብ እንዳለን እናምናለን። በህዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ስርአት በመነጨ ቅን ልቦናና  ፍላጎት የህዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል።  የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅና ድሪት አውልቆ የህዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም። ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሰረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
መደመርን መንገዳችን ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም።  ዛሬ በማይካድራ ፣ በዳንሻ ፣ በአላማጣ ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ አላማጣና ኮረም እንዲሁም በውልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የአማራ ነን ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ህብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው  የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።
ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።
በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።
ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።
በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።
ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ህዝባችንን ፣ መሬታችንን ፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 አመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ  እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ስነልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።
የወሰን ፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በህግና በስርአት አቀረብን እንጂ እንደ ትህነግ በማንአለብኝነት ዘራፍ አላልንም።
የተገፋን ፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግስቱም ሆነ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ አደጋ አልፈጠርንም።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰአት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር  መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ህዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ህዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።
በሰላማዊ መንገድ እጂ የሰጡና የተማረኩ  የትህነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን ፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ስርአት እልፍኛችንን ለቀን ፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ  አላሸማቀቅናቸውም።
እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰአት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ህዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም።  በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሀኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።
ይሁን እንጂ የአማራ ህዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትህነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።
1. ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ስርአት አቀንቃኙ ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰአት ውስጥ በምስራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ አላማውን ለማሳካት ከ3 አመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትህነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ህዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ህዝብ ሊያስመሰግነው  ሲገባ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ህግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 አመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ህዝብና መንግስት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢህገመንግስታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ህዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
2. እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ህዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ህዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በህዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ህዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው ፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተገደለባቸው ፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ስርአት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትህነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።
በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትህነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።
ስለሆነም የህግ የበላይነት ለማስከበር ፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ  ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች  (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በስርአቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትህነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scane) መፈተሽና መመርመር ፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ህዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-
2.1. ላለፉት 50 አመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (under ground Tourcoing caves) ለህዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
2.1. ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 አመታት እንደ ህዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ አለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
3. በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና  ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን በኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የህዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
4. በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የህግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን በቤንሻንጉል ክልል በህዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት አላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ህግ የማስበር ስራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሰረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የህዝባችንን እንቅፋት በህግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከቸረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።
በመጨረሻም በትህነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በህዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።
የህግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል ፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።
የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ህዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።
ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ህዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን !!!
ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ህዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን !!!
ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !!!
Filed in: Amharic