>

‹‹ሉሉ›› አነጋጋሪዋ የጃንሆይ ድንክ ውሻ...,!!! (መስፍን ተፈራ)

‹‹ሉሉ›› አነጋጋሪዋ የጃንሆይ ድንክ ውሻ…,!!!

መስፍን ተፈራ

* …. ጀነራል መንግስቱ ነዋይ ለገሃር በነበረው የጦር ካምፕ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ለጠባቂያቸው ሻምበል ” እኔ እዚህ ችግር ላይ የገባሁት ያንተን ደምወዝ ከአንድ የውሻ ደሞዝ እንዲሻል ለማድረግ ብዬ ነበር ” ማለታቸው በታሪክ ማህደር ተመዝግቦ ይገኛል
 
ጃንሆይ ይቺ ድንክ ውሻ ሳያስከትሉ የሚሄዱበት ቦታ ቤተክርስቲያን ብቻ ነበር ይባላል። የውጭ ሀገር ጉብኝት ሲደረጉ ሁሉ ሉሉ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር አብራ ትሄዳለች፡፡ … ጃንሆይ ከአውሮፓላን ከመውረዳቸው በፊት ሉሉ ትወርድና የራሷን ጉብኝት ታደርጋለች። ውድድር ለመመልከት ወደ ስታዲየም ሲመጡም ኳስ ሜዳው ላይ ተዘዋውራ ተመልሣ እስራቸው ትተኛለች ።
ሉሉን የሚወዷት ሰዋች የመኖራቸውን ያህል የሚጠሏትም ብዙዋች ነበሩ፤ በተለይ የዮኒቨርቲቱ ተማሪዎች ጃንሆይ ለምርቃት በዓል ሲመጡ የእሷ አብሮ መምጣት አይጥማቸውም ነበር። እሷም ከመካከላቸው እየገባች ታነፈንፍ ስለነበር አንድ አመት ላይ አንድ ምሩቅ ሰው ረገጣትና ጮህች፤ በዚህ ጊዜ አጃቢዎች ረጋጩን ተማሪ ለመለየት ብዙ ቢሞክሩም ሌሎች ተማሪዎች ስለሸፈኑለት ተማሪው ሳይለይ ነገሩ እንዲሁ በቅሬታ ታለፈ፤ ”ባለቤቱን ካልናቁ ውሻውን አይነኩም ” እንደሚባለው ጃንሆይን ካልናቁ ወይም ካልጠሉ ውሻውን አይነኩም በሚል ውሻዎን ሁሉ ሰው ያከብር ነበር።
አንድ ጊዜ ኮሎኔል ተክሉ ገብሩ ሻምበል በነበሩበት ወቅት ተግባረዕድ ትምህርት ቤት የራዲዮ ኮሙኒኬሽን ትምህርት ሲማሩ ጃንሄይ ትምህርት ቤቱን ለመጉብኘት ሲመጡ መኮንኑ እግር ስር ሉሉ መጥታ ስላስቸገረቻቸውና ጃንሆይም በቅርቡ ስለነበር ውሻዋን ”ወይጅ ” ማለት ስለፈሩ “ወይዱ” ስላሉ ጔደኛቻቸው ”ወይዱ” የሚል ቅፅል ስም ሰጥተዋቸው ነበር ።
ሉሉ የወር ደሞዝ ተቆርጦላት በወር የአንድ ሻምበል ደምወዝ ብር 175 ታገኝ እንደነበር የታወቀው ጀነራል መንግስቱ ነዋይ ለገሃር በነበረው የጦር ካምፕ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት ለአንድ ሻንበል ” እኔ እዚህ ችግር ላይ የገባሁት ያንተን ደምወዝ ከአንድ የውሻ ደሞዝ እንዲሻል ለማረግ ብዬ ነበር ” ማለታቸው በታሪክ ማህደር ተመዝግቦ ይገኛል።
ሞት አይቀርምና ሉሉ ስትሞት ቤተመንግስት ውስጥ ተቀብራ መቃብሯም በእብነበረድ ስለተሠራ ጃንሆይ ከተወቀሱበት ነገር አንዱ ሆኗል።
ምንጭ ፦ የአቶ ጥላሁን ብርሃነስላሴ ”የ20ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጲያ ” የተሰኘው መጽሀፍ
Mesafint Sci-tech
Filed in: Amharic