>

"አኖሌማ አይፈርስም! በፍጹም!" (መላኩ አላምረዉ)

“አኖሌማ አይፈርስም! በፍጹም!”

መላኩ አላምረዉ

*….አኖሌ ካልፈረሰ እያልህ ሀገር ይያዝልኝ የምትል አማራ ግን ምን ነክቶህ ነው? ተው እረፍ ትጣላኛለህ!!!
አልገባህም እንዴ? አኖሌ እኮ የአንተ ሐውልት ነው። ታሪክህ የማይመሰክረውን ባሕልህም ባሕርይህም የማይፈቅደውን… ያለ ስምህ ስም ያለ ግብርህ ግብር ተሰጥቶህና ተረት ተረት ተጽፎልህ የቆመልህን የበቀል ሐውልት ይፍረስ ስትል
ግን በጤናህ ነው? ይህ የተሰራብህ ሴራ በምን እንዲታወስልህ ነው አኖሌ ካልፈረሰ ብለህ ሀገር ይያዝልኝ የምትለው?
አኖሌማ አይፈርስም። በፍጹም አይፈርስም!!! (ለእኔ) አኖሌን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ አማራ የተሠራበትን ሴራና
የተፈበረከለትን የሐሰት ታሪክ አሻራ ለማጥፋት እየደከመ ነው። ይህ አኖሌ የሚባል ሐውልት እኮ “በአንድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር አንዲት ሀገርን
ለመመሥረት የሚደክመው መንግሥት ያቆመው ‹‹የማስተሳሰሪያ›› ሐውልት” ነው¡
ይህን ሐውልት ይፍረስ ማለት እኮ ሕወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ለአማራ ሕዝብ ውለታው ያቆመለትን ሐውልት ማፍረስ ነው፡፡ አንዳዴማ ገልብጠን እንጀምር እንጅ፡፡ ይህ እኮ የአማራ ሕዝብ ሀገራዊ ውለታ በሌላው ዘንድ እንዴት እንደሚመለስለት ማሳያ ነው፡፡
ልብ በል። “አኖሌ ሐውልት ቆሞ የሚመሰክረው ከአማራ ሕዝብ የተወለዱ ነገሥታትን ሆነ ሌላ አካልን ጡት ቆራጭነት ሳይሆን ለአማራ ሕዝብ ጥፋት በልብወለድ ተጽፎና ጠላትነት በሕግ ታውጆ ለሀገር የዋለው ውለታ የተከፈለበትን ጸያፍ መንግሥታዊ ተግባር ነው። አማራ ጠልነት ከመንፈስነት
አልፎ እንዴት በአካል እንደቆመ የሚያሳይ ቅርስ ነው”።
እናም አማራው አኖሌ ይፍረስ አትበል። የተሰራብህን ሴራና ተፈጸመብህን ግፍ ቆሞ ይመስክር እንጅ።
አኖሌ ካልፈረሰ የምትል አማራ ግን… ቆይ መሠረታዊ ስጋትህ ምንድነው? አኖሌ የበቀል ምልክት ሆኖ ከኦሮሞ ወንድም ሕዝብ ጋር ያጣላኛል ብለህ ከሆነ…
“ከአማራ ጋር ያጣላኛል፤ ያልተፈጠረ ታሪክ በሴራ ተሠርቶ ሐውልት መቆሙ ከወንድም የአማራ ሕዝብ ጋር ያጣላናልና ይፍረስልን” ማለት ያለበት ኦሮሞው እንጅ አንተ ምን ቤት ነህ? ያላቆምኸውን ሐውልት ካልፈረሰ ስትል ማን ይሰማኝ
ብለህ ነው?! ካልገባህ ልድገምልህ። አኖሌ የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ አበቃ።
ሐውልቱን ማፍረስም ሆነ በሌላ በጎ ምልክት መለወጥ ያንተ ጉዳይ አይደለም፡፡ አሮሞው ‹‹ከወንድም ሕዝባችን ከአማራ ጋር ለሚኖረን የጋራ ጉዞና አንድነት…›› ብሎ የሐውልቱን መቆም ሳይቃወም አንተ ምን ቤት ነህ? ለፍቅር ሲል፣ ከአንተ
ጋር በተለመደው አንድነት ለመኖር ሲል፣ ለጋራ ሀገርና ለዘላቂ ሕብረት ሲል… “ለጋራ ድልና ለፍቅር እንጅ ለጥል ሐውልት አያስፈልገንምና ላፍርሰው” ያላለውን አንተ ምነው አኖሌ አኖሌ አስባለህ?
ይወክለኛል ያለው ሕዝብ ካልፈለገ ግድ ነው? አንወድህም ሲሉህ በግድ ውደዱኝ ነው? በተግባር አቅፈኸው፣ ተጋብተህና ተዋልደኸው፣ ተዋሕደኸው በአንድነት አብረኸው እየኖርህ እያለ… በተንኮል ተሰልቶ የተጻፈን የእነ ተስፋየ ገ/አብን የልብወለድ ፈጠራ አምኖ ተቀብሎ ትውልድ ቂምን ፀንሶ በቀልን እንዲወልድ ከፈለገ አንተ ከፍላጎቱ ታስቆመው
ዘንድ ማን መብት ሰጠህ?
በአንተም በአባቶችህም ባልተፈጸመ፣ ክፉ ልብ በወለደው የፈጠራ ትርክት “አማራን በጥላቻ ሐውልት ነው ማስታወስ
የምንፈልገው” ካሉ በግድ የፍቅር ሐውልት አቁሙልኝ ብሎ ድርቅ ማለት ምን ይሉታል?
ምንአልባት… ይህ ሐውልት ይፈርስ ዘንድ የፈለግኸው በቀልን ፈርተህ ይሆን እንዴ? “ማርነትህ መርሮ ወተትነትህ ጠቁሮ” አማራ-ጠልነት የተሰበከላቸውና የጥላቻ ሐውልት የቆመላቸው ሁሉ ለበቀል ተነስተው ሕልውናህን እንዳያጠፉት ሰጋህ እንዴ? እና ይህን ሐውልት በማፍረስ የምታስቆመው ይመስልሃል?
…….ወዳጄ! የጥላቻ በቀልንም ሆነ ሌላ ተጽዕኖን ለመመከት በሚያስችል ቁመና ላይ ስትገኝ ብቻ ሕልውናህ ተረጋጦ በክብርና በእኩልነት እንደምትኖር ተረዳ። በሐሰት ትርክት ተፈጥሮላቸውም ሆነ እንዲሁ ከመሬት ተነስተው
ጠልተውህ በአንተ መኖር ሰላም አጥተው ሊያጠፉህ ቢዘምቱ፤ የበቀል ዘመቻውን የመመከት አቅምን ፈጥረህ በራስህ እስካልቆምህ ድረስ የጥላቻ ሐውልት ይፍረስልኝ ሙሾህም ሆነ የእባካችሁ አታፈናቅሉኝና አትግደሉኝ ልመናህ
ትርጉም የለውም። እናም አኖሌንም ሆነ ሌላውን ረስተህ ራስህን አስብ፡፡ በራስህ ተማምነህ ተደራጅተህና ደርጅተህ ቁም። ሌላ የሕልውና ማስቀጠያና የክብር ማስጠበቂያ ምድራዊ ሳይንስ የለም።
.
ማመን ያለብህ አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ማንም ለበቀል ይጭህ… አንተ በፍቅር ለመጋባት ብቻ ተዘጋጅ፡፡ ይቅር ባይ ልብ ያዝ፡፡ በበቀለኞች ልክ የሚያስብ ልብ አይኑርህ፡፡ ይህ ማለት ይቅር እያልህ ብቻ ተቀመጥ ማለት አይደለም፡፡
አትበቀል ማለት ጥፋ ማለት አይደለም፡፡ ሕልውናህን በራስህ ብቻ አረጋግጥ፡፡
አንተ ያላረጋገጥኸውን ሕልውና ማንም ሊያረጋግጥልህ አትጠብቅ፡፡ በራስ መተማመን እስከቆምህ ድረስ የሌላው አንተን መበቀልም ሆነ ማቀፍ አያሳስብህ፡፡ የሚያቅፍህን አቅፈህ ትስመዋለህ፡፡ ሊበቀልህ እጁን የሚዘረጋን
ደግሞ እጁን… ከተቻለ በፍቅርና በምክር ዳብሰህ ካልተቻለም ‹‹ቆንጥጠህ›› ታሳርፈዋለህ፡፡ ከፍ ብለህ በፍጹም የራስ መተማመን መንፈስ በፍቅርና በአንድነት ቁም፡፡ ፍቅርንና አንድነትን ያለ ሁሉ አብሮህ ይጓዛል። ሌላው ሁሉ ጉዳይህ
አይሁን፡፡ በግድ ስሙኝና እባካችሁ እመኑኝ እያልህ በመጮህ በራስህ ጸንተህ ለመቆም የሚያስችልህን ጉልበትህን አትጨርስ፤ ለሕልውናህ እጅግ የምታስፈልግህን ውድ ጊዜህንም አታባክን፡፡
የግርጌ ማስታወሻ፦
የሴት ልጅ ጡት የሕይወት ምንጭ የሆነ ክቡርና ተሸፋፍኖ መኖር ያለበት “የእናት ገላ” ነው። በሐውልት መቆሙ ግድ ቢል እንኳን በዚህ መልኩ ተገላልጦ መሆኑ
ሐውልት ከመሆኑም ባሻገር ሌላ ስህተት ይመስለኛል።
Filed in: Amharic