>

በፖለቲከኞች ክሽፈት አበሳዋን የምትበላ አገር፤ ኢትዮጵያ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

በፖለቲከኞች ክሽፈት አበሳዋን የምትበላ አገር፤ ኢትዮጵያ….!!!

_ያሬድ ሀይለማርያም

ሙስና፣ በዘር ላይ ያተኮረ ጥቃት እና ግጭት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ጦርነት፣ መረን የለቀቁ ካድሬዎች፣ የሕግ የበላይነት መጓደል፣ ወዘተ…። ሁሉም የፖለቲከኞች ክሽፈት መገለጫዎች ናቸው።
አብዛኛዎቹ ችግሮቻችን በፖለቲከኞች ብልግና እና እውቀት ማጣት የመጡ ናቸው። በላዩ ላይ ግፍና ግፈኞችን ለመሸከም ትከሻውን ያደነደነ እና ሁሉን ቻይ ሰፊ ሕዝብ አለ። የከሸፉ ፖለቲከኛች እና ግፍ ቻይ ሕዝብ መገጣጠም ነገረ ሥራችንን ሁሉ የእምቧይ ካብ፣ የእምቧይ ካብ እንዲሆን አድርጎታል።
ለማንኛውም መቀሌ መሽገው የነበሩ ተጋዳላዮችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል በሚል በተከፈተው ጦርነት ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ እና የአገር ሀብት መውደም ማነው ተጠያቂው? ከዚህ ሁሉ ኪሳራ በኋላ ተፈላጊዎቹ አልተያዙም እና አፋልጉን ከተባለ የሕግ ማስከበሩ ተልዕኮ ከሽፏል ማለት ነው? የወያኔ አመራሮች ለፈጸሙት ተነግሮ የማያልቅ ወንጀል በተያዙ ጊዜ ይጠየቁ ይሆናል። እነሱን ለመያዝ በተወሰደው እርምጃ በሰው ህይወት እና ንብረትስ ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂው ማነው?
በአብይ አስተዳደር በኩል ብዙ መልስ የሚፈልጉ ነገሮች ይታዩኛል፤
+ የደረሰው የጉዳት መጠን፣ ምን ያህል ሰው በዚህ ጦርነት አለቀ? የማይካድራውን ጨምሮ በግራና በቀኝ በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች፣
+ ምን ያህል ሰዎች ጦርነቱን ሸሽተው በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ተሰደዱ፣ ተፈናቀሉ?
+ ምን ያህል ተቋማቶች እና ምን ያህል ግምት ያለው የአገር ሀብት ወደመ?
+ ጦርነቱ ምን ያህል የአገር በጀት አናጋ፣
+ በጦርነቱ ትግራይ ክልልን ስንት አመት ወደኋላ ሳባት?
+ ጦርነቱ በተካሄደባቸው፣ በተለይም የአየር ጀቶች እና ከፍተኛ መሳሪያ ባጓራባቸው መንደሮች እና ከተሞች የሚኖሩ እና ከጥቃቱ የተረፉ ህጻናት አይምሯቸው በምን ሁኔታ ላይ ይሆን? ስለ አገራቸውስ ምን ያስቡ ይሆን?
ለማንኛውም እንደ ሀገር ከዚህ ጦርነት ያተረፍነው እና ያጣነውን ነገር ከስሜት እና ከበቀል መንፈስ እርቀን ቁጭ ብሎ መመርመር የግድ ይላል።
ከወያኔ መሳደድ፣ መዋረድ እና መወገድ በላይ ምን ትርፍ ፈለግህ?  የሚል ሙግት ሊነሳ ይችላል። እንዲያ ከሆነ የፖለቲካችንን ከርሞ ጥጃነት ያሳይ ይሆናል እንጂ ለእኔ ትርፍ አያሳየኝም። ደርግ በተሸኘበት መንገድ ወያኔም በድምሰሳ መልክ መወገዷ ከ30 አመት በኋላም ፖለቲካችን ባለበት እየረገጠ ነው ማለት ነው። ወደ ፊት ፈቅ አላልንም።
ሰሞኑን የአገሪቱን መገናኛ ብዙሃን፤ ነጻ ተብዮዎቹንም ጨምሮ የሚያስተላልፉትን ዘገባ ከሰማችሁ ልክ ደርግ በተገረሰሰ ማግስ በወታደራዊ አስተዳደሩ ላይ ይዘንብ ከነበረው ውርጅብኝ እና ፕሮፖጋንዳ በይዘትም ሆነ በአዘጋገብ ዘዮ አንድ ነው። ደርግን ሲያቆለፖፕሱ የነበሩ ጋዜጠኞች እርግማን አውራጅ እንደሆኑት ሁሉ፤ ወያኔን የነካ ምን እንደነካ ስንጥር አድርገው ያወግዙ የነበሩ ሚዲያዎችና ካድሬዎች፤ አንዳንድ ምሁር መሳይ ተንታኞችም ጭምር ጁንታ በሚል ነጠላ ዜማ ሲያደነቁሩን ይውላሉ።
ዙሩን አሁንም እየተሽከረከርነው ይመስላል።
Filed in: Amharic