>

ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ከሜልበርን ኢትዮጵያዊ ጋር ተወያዩ፤ በቀጣይ እሁድ ከሲድኒ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመገናኘት ዛሬ ወደ ሲድኒ አመሩ! [ቋጠሮ]

profeser Mesfin Weldemariamእውቁ ኢትዮጵያዊ ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በሜልበርን የሚገኘው ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ቡድን ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት ባለፈው እሮብ ኦክተበር 15 ሜልበርን (አውስትራሊያ) ገብተዋል።

ድጋፍ ቡድኑ እኝህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር የህይወት ዘመናቸውን አብዛኛውን ክፍል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፤ በግል ህይወትን ምቾት ላይ ሳያተኩሩ፤ ለህዝባቸውና ለሃገራቸው ሁለንተናዊ ደህንነት ላደረጉት አስተዋጾና ውለታ ምስጋና ለማቅረብ በማሰብ ያደረገላቸውን ግብዣ በጸጋ ተቀብለው፤ ረዥምና አድካሚውን ጉዞ ተቋቁመው፤ ባለፈው እሮብ ምሽት ሜልበርን ሲገቡ የዝግጅቱ አስተባባሪዎችና በርካታ አዳናቂዎቻቸው በደስታና በእቅፍ አበባ ተቀብለዋቸዋል።

ፕ/ር መስፍን የጉዞው ድካም ከወጣላቸው በኋላ በመርሃ ግብሩ መሰረት አርብ እለት በሜልበርን ከተማ በዘዋወር ሙዚየምና ሌሎችም ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል።
ቅዳሜ ዕለት እንኳን ደህና መጡ ለማለት ወዳረፉበት ሆቴል የሄዱ ኢትዮጵያዊያንን እየተቀበሉ ሲናጋግሩ ውለዋል።

በማግስቱ እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሜልበርን ኢትዮጵያዊ በተገኘበት ታሪካዊ ስብሰባ ተገኝተው በተለመደው መልክ ትውልድ አናጭ፤ አነቃቂ፡ አስጠንቃቂና ከሁሉም በላይ አቅጣጫ አመላካች የሆነ ንግግር አድርገዋል።

የሜልበርን ኢትዮጵያዊ እኝህን፦ ባለፉት ሶስት መንግስታት ውስጥ አንጸባራቂና ጉልህ የታሪክ ስፍራ ይዘው የቆዩ ክቡር ሰው በግንባር አግኝቶ የሚሉትን ለመስማት በአዳራሹ የተሰየመው በከፍተኛ ጉጉትና ንቃት ነበር።

ፕ/ር መስፍን ወደ አዳራሹ ገብተው የተዘጋጀላቸውን ቦታ እስኪይዙ ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ አዳራሹ በጭብጨባ እያናጋ በፍቅር ተቀብሏቸዋል።
የዝግጅት አስተባባሪውን በመወከል አቶ ሳምሶን አስፋው አጠር ያለ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግግር አድርጎ ታዳሚው በጉጉት የሚጠብቃቸውን የክብር እንግዳ በመጋበዝ መድረኩን አስረከበ።

ፕ/ር መስፍን በተቀመጡበት ሆነው እንዲናገሩ ቢጠየቁም ለህዝብ ካላቸው አክብሮት ቆሞ መናገርን መርጠው የንግግር ማማውን ተረከቡ።

ከ40-45 ደቂቃ በላይ በዘለቀው ንግግራቸው የሃገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በርካታ ጉዳዮችን ዳሰዋል። ግልጽነትና እውነተኝነት፤ ያመኑበትን አውጥቶ ለመናገር ወደ ኋላ ያለማለት መለያዎቻቸው የሆኑት ፕ/ር መስፍን በዚሁ መንፈስ ያደረጉት ንግግር ታዳሚውን በአንክሮ ያስደመመ ነበር።(ሙሉ ይዘቱን ሰሞኑን በሚለቀቀው ቪዲዮ መከታተል ይችላሉ)

የፕ/ር መስፍን ንግግር እንዳበቃ፤ ለ20 ደቂቃ በተሰጠው የሻይ እረፍት ግዜም በስብሰባው የታደመው ኢትዮጵያዊ በየተራ እየቀረበ አብሯቸው የመታሰቢያ ፎቶ በመነሳት ክብርና ፍቅሩን ገልጾላቸዋል።

ከእረፍት መልስ በነበረው ለሁለት ሰአት ተኩል ያህል በዘለቀ የጥያቄና መልስ ክፍለ ግዜ እጅግ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው አንዳዴም ታዳሚውን እያሳቁ ምላሽ ሰጥተዋል።
የጥያቄና መልሱን መድረክ የመሩት የአስተባባሪው ኮሚቴ አባል አቶ አዳሙ ተፈራ ለአዳራሹ የተያዘው ሰአት እየተጠናቀቀ በመሆኑ የጥያቄና መልሱ ሂደት መቋጨት እንዳለበት እስኪገልጹ ድረስ ለጥያቄ የወጡ እጆች ችቦ መስለው ቆይተዋል።

አቶ አዳሙ የዕለቱ ዝግጅት ከመጠናቀቁ በፊት ለመጠየቅ እድል ላላገኘው በርካታ ኢትዮጵያዊ ከፕ/ር መስፍን ጋር የሚኖረን ቆይታ ይህ የመጨረሻ እንዳልሆነና የአውስትራሊያ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመመለሳቸው በፊት ሌላ ዝግጅት እንደሚኖር አስታውቀዋል።

የአስተባባሪው ኮሚቴ መርሃ ግብር እንደሚያመለክተው ያለፈው እሁድ ዝግጅት ከኢትዮጵያዊያን ጋር እንዲወያዩ ታቅዶ የተዘጋጀ ሲሆን ቀጣዩ ዝግጅት ደግሞ የፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም የምስጋናና የክብር ምሽት እንደሚሆን ታውቋል። በዚህ ዝግጅት የፕ/ር መስፍን የሶስት መንግስታት ስራ የሚወሳበትና የህይወት ዘመን አገልግሎት ሽልማት የሚሰጥበት እንደሚሆን ታውቋል።

የእለቱ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ በፕሮግራሙ መሰረት ለክብር እንግዳው የተዘጋጀው የእራት ግብዣ ተከናውኖ ጠቅላላ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ስለ ዕለቱ ስብስባና ስለ ፕሮፌሰር መስፍን መካከላችን መገኘት ምን እንደተሰማቸው የጠየቅናቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሰጡን አስተያየት ተመሳሳይ ነበር።

“እኛ ዕድለኞች ነን!” በማለት የጀመሩት አስተያየት ሰጭ ሲቀጥሉ፦ “በዝናና በዜና የምናውቃቸውን እኝህን ታላቅ ሰው በግንባር አግኝተን ከአንደበታቸው የሚወጣውን ቃል በጆሯችን መስማት መቻላችን እድለኞች ነን! ይህን የተቀደሰ ሃሳብ አፍልቀው እሳቸውን ጋብዘው ይህን መድረክ ያዘጋጁት ወገኖች ምስጋና ይገባቸዋል” ብለዋል።

በእለቱ የተገነዘብነው ሌላው ጉዳይ በዚህ መሰሉ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የማያውቁ ወጣቶች መገኘታቸው ሲሆን እነኚሁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑ ወጣቶች የፕ/ር መስፍንን አባታዊና ምሁራዊ ምክር በመሻት ልዩ ግዜ እንዲሰጣቸው አስተባባሪ ኮሚቴውን ጠይቀዋል።

ፕ/ር መስፍን ለአንድ ሳምንት ያህል በተመሳሳይ አላማና ፕሮግራም በሲድኒ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለሚኖራቸው ቆይታ ዛሬ ሃሙስ ኦክቶበር 23 ወደ ሲድኒ አምርተው ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ፕ/ር በቀጣይ እሁድ ማለትም ኦክቶበር 26 በስድኒ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚገናኙም ይጠበቃል።

ቀጣዩን የእንቅስቃሴ ሪፖርትና የቪዲዮ ዘገባ ሰሞኑን ይዘን እንቀርባለን ።
የቋጠሮ ሪፖርተር

Filed in: Amharic