የዘገየ ይቅርታ ለክቡር አቶ ልደቱ አያሌው!
መስፍን አረጋ
ይህ ደብዳቤ ክቡር አቶ ልደቱ አያሌውን በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡ ይቅርታው የዘገየ ነው፡፡ ይቅርታ ግን የዘገየውን ይዘግይ እንጅ መቅረት የለበትም፡፡
እንዳብዛኛው አገር ወዳድ ጦቢያዊ የ1997ቱ የቅንጅት አብዮት ግቡን ሳይመታ (ወያኔን ሳይነቅል) በመክሸፉ እጅጉን ተበሳጭቸ ነበር፡፡ እንዳብዛኛው አገር ወዳድ ጦቢያዊ፣ ለክሽፈቱ ዋናውን ተጠያቂ የኢዴፓውን አቶ ልደቱን አድርጌያቸው ነበር፡፡ ካብዛኛው አገር ወዳድ ጦቢያዊ በተለየ ሁኔታ ግን Lidetu Ayalew: the imposter (ልደቱ አያሌው፤ አስመሳዩ) በሚል ርዕስ በእንግልጣር ጦማር ጦምሬ፣ አቶ ልደቱን በብዕሬ ልደበድባቸው የምችለውን ያህል ደብድቤያቸው ነበር፡፡
ወያኔ በጦቢያና በጦቢያዊት ላይ በፈጸመው ወደር የለሽ ወንጀል ሳቢያ እጅግ አምርረን ስለምንጠላው፣ ወያኔን በምርጫም ሆነ በመርጫ የሚያስወግዱ የሚመስሉ የተቃዋሚ መሪወች በተከሰቱ ቁጥር እንደ መሲህ እየቆጠርናቸው፣ የወያኔን እድሜ ላንዲትም ቀን ቢሆን የሚያስረዝሙ የሚመስሉትን ደግሞ እንደ ይሁዳ እንመለከታቸው ነበር፡፡ ይህን እናደርግ የነበረው ደግሞ “ንጉሱ ይውረዱ እንጅ … “፣ “ደርግ ይውደቅ እንጅ … ” በምንልበት ዘይቤ፣ “ወያኔ ይውደቅ እንጅ … ” በማለት፣ የወያኔ ተቃዋሚወች ወያኔን ለመጣል የተነሳሱት እኛ በምንጠላው በምንነቱ (በወንጀሉ) ወይስ እነሱ በሚጠሉት በማንነቱ (በትግሬነቱ) መሆን አለመሆኑን አስቀድመን ሳናረጋግጥ ነበር፡፡
ነብታሚ (professor) መስፍን ወልደማርያም አበክረው እንዳስገነዘቡን፣ የኛ የጦቢያውያን ትልቁ ድክመት የምንረባረበው የምንጠላውን ለማስወገድ እንጅ በምንወደው ለመተካት አለመሆኑ ነው፡፡ አቶ ልደቱ አያሌውን ይቅርታ የምጠይቃቸው ደግሞ በዚህ ረገድ ለፈጸምኩት ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን አይዋረዱ ውርደት ስላዋረደ፣ ኢትዮጵያዊነትን በበጎ የሚያነሳሳ ማናቸውም ቡድን (የሩቅ ዓላማው ምንም ይሁን ምን) አገር ወዳዱን ጦቢያዊ በነቂስ አነሳስቶ እንደ በግ ሊነዳው እንደሚችል የቅንጅት አብዮት በግልጽ አሳይቷል፡፡ ለማ መገርሳና ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ዓላማቸውን ለማሳካት ባገር ወዳድ ጦቢያውያን ታዘለው ከስልጣን ኮርቻ ላይ ቂብ ለማለት የበቁት፣ ይህን እውነታ በደንብ ተረድተው በደንብ በመተግበር ነበር፡፡
እነ ዲባቶ (doctor) ብርሃኑ ደግሞ ወያኔን የሚጠሉት በማንነቱ (በትግሬነቱ) እንጅ በምንነቱ (በፀረጦቢያነቱ) እንዳልሆነ በጊዜ ሂደት ይበልጥና ይበልጥ ገልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ አማራውን የሚወዱ የሚመስሉት ደግሞ የስልጣን መወጣጫ መሰላል ለማድረግ ብቻና ብቻ እንደሆነ ቁልጭ ብሏል፡፡ በጥቅሉ ለመናገር፣ ዲባቶ ብርሃኑ እና መሰሎቹ ሰሜነኞች የሚሏቸውን አማራና ትግሬን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ደቡበኞች ናቸው፡፡ ያቶ ልደቱ ጥፋት ደግሞ በነ ዲባቶ ብርሃኑ ዓይን ሰሜነኛ መሆናቸው ነው፡፡
አቶ ልደቱ አንድ ለቅንጅቱ ነው (አጤ ቴድሮስ አንድ ለናቱ እንዲባሉ)፡፡ ቅንጅትን ቅንጀት ያስባለው የቅንጅት ኮኮብ አቶ ልደቱ እንደነበረና፣ ዲባቶ ብርሃኑና መሰሎቹ ግን የኮኮቡ ጭፍራወች እንደነበሩ አሌ የማይባል ሐቅ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ዲባቶ ብርሃኑና መሰሎቹ በኢሕአፓዊ ሤራ ደቁነው የቀሰሱ ሊቀሤራወች ፣ ለስልጣን ሲሉ ምንም ከማድረግ የማይመለሱ ስልጣን ሱሴወች መሆናቸው ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በአቶ ልደቱ ከሞላ ጎደል ብቸና ተጋድሎ ከስልጣን አፋፍ ሲደርሱ፣ አዶ (ወይዘሮ ወይም ወይዘሪት፣ Ms.) ቡርቱካን ሚዴቅሳን ከመሬት አንስተው ሰማይ የሰቀሏት፣ የቅንጅት አብዮት ሰማይ ያደረሰውን አቶ ልደቱን መሬት ለመፈጥፈጥ ሲሉና ሲሉ ብቻ እንደነበር ለማንም ግልጽ ነበር፡፡
እነዚህ ሁሉ የነ ዲባቶ ብርሃኑ ምሰራወች (የመሰሪ ሥራወቸ)፣ የማናቸውንም ሰው ደመ አፍልተው፣ ስሜታዊነት ውስጥ ከተው፣ ራስን ከመቆጣጠር አውጥተው፣ በረጋ መንፈስ የማያደርገውን እንዲያደርግ ማስገደዳቸው እሙን ነው፡፡
አቶ ልደቱ ግን ከማናቸውም ሰው በተለየ ሸካች (ፖለቲከኛ፣ politician) ነው፣ ለዚያውም አመራር ላይ የተቀመጠ ትልቅ ሸካች፡፡ ሽከታ (politics) ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የትዕግስት ብረትለበስ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ደግሞ ትልቅ ሸካች ትልቁን ስዕል ማየት እስከሚሳነው ድረስ በዝርዝሩ ታውሮ ለግልፍት ተጋላጭ መሆን የለበትም፡፡ በኔ በኩል አቶ ልደቱን ጥፋተኛ የማደርገው እዚህና እዚህ ላይ ብቻ ነው፡፡
የቅንጅት አብዮት ዋና ግብ የጦቢያን ነቀርሳ (ወያኔን) መንቀል ነበር፡፡ ስለዚህም አቶ ልደቱ የነ ዲባቱ ብርሃኑን ሸፍጥ ለጊዜው ችላ ብሎ፣ ወያኔን ለመንቀል ማድረግ የነበረበትን ሁሉ ማድረግ፣ መፈረም የነበረበትን ሁሉ መፈረም ነበረበት፡፡ ወያኔን ከነቀለ በኋላ ደግሞ እነ ዲባቶ ብርሃኑን ቀስ በቀስ በማራገፍ ቅንጅትን ከኢሕአፓ ሸፍጠኞች ሙሉ በሙሉ አጽድቶ፣ የራሱ የሆነውን ቅንጅትን በራሱ እጅ አስገብቶ፣ በራሱ መንገድ ሊቀርጸው ይችል ነበር፡፡ ይህን ማደረግ ባይችልም እንኳን ወያኔን ለመንቀል ያንበሳውን ሚና በመጫወቱ ብቻ የጦቢያና የጦቢያውያን ዘላለማዊ ጀግና ይሆን ነበር፡፡
እንዲህም ሆኖ፣ ወያኔ የወደቀው ያቶ ልደቱ ቅንጅት ስላንገዳገደው ብቻና ብቻ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ የወያኔ ውድቀት ሀ ብሎ የጀመረው ከ1997ቱ የቅንጅት አብዮት በኋላ ነበር፡፡ ስለዚህም በኋላይን (hindsight, retrospect) ስመለከተው፣ አቶ ልደቱን ከምወቅስባቸው ይልቅ የማወድስባቸው ይበልጡብኛል፡፡
ወያኔን ጣልን እያሉ የሚኮፈሱት የዘመናችን “ለውጠኞች”፣ ወያኔን ያዘመመላቸውን አቶ ልደቱን ማጎሳቆላቸው የሚያሳየው አንድ ነገር ቢኖር፣ የለውጠኞቹን ውለታቢስነት ብቻ ነው፡፡ ትልቁ ፌዝ ደግሞ አቶ ልደቱን በሐሳቡ የሚያጎሳቁለው የነ ዲባቶ ብርሃኑ ወዳጅ የኦሮሙማው ዐብይ አህመድ፣ ያቶ ልደቱን ሐሳብ እየሰረቀ እንዳሰኘው በማጣመም የራሱ ሐሳብ አስመስሎ የሚያቀርብ ዓይን ያወጣ ቾምሳኪ (መንታፊ፣ plagiarizer) መሆኑ ነው፡፡
መስፍን አረጋ:- EMAIL mesfin.arega@gmail.com