>
2:46 pm - Thursday March 30, 2023

የአፄ ልብነ ድንግል እና የአሕመድ ግራኝ ጦርነት ከመሰረቱ ፖለቲካዊ እንጅ ሃይማኖታዊ አልነበረም...?!! (ተድላ መላኩ)

የአፄ ልብነ ድንግል እና የአሕመድ ግራኝ ጦርነት ከመሰረቱ ፖለቲካዊ እንጅ ሃይማኖታዊ አልነበረም…?!!

ተድላ መላኩ

ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም የሆነ አምሓራ ሁሉ ይህን በጥንቃቄ ሊመረምርና ሊገነዘብ ይገባል። 
 
ከታች በስክሪንሾት የተያያዙትን ምሑራዊ ማስረጃዎች በጥንቃቄ ከዚህ ጽሑፍ (ትንታኔ) ጋር እያነጻጸሩ ይመርምሩ።
ታሪክ ላይ አፄ ልብነ ድንግል እና የምስራቁ ወላሽማ/አደል ሱልጣኔት  ግዛት መሪ የነበረው ሃደሬ-ሶማሌው አሕመድ አል ግሀዚ (አሕመድ ግራኝ) ያካሄዱት ጦርነት ከመሰረቱ ፖለቲካዊ እንጅ ሃይማኖታዊ ጦርነት እንዳልነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ያትታሉ። የዚህም ማስረጃ አሕመድ ግራኝ አፄ ልብነ ድንግል ሴት ልጃቸውን ከዳሩለት ውጊያውን እንደሚተው የላከላቸው መልዕክት ነው – ከስር የተያያዘው ምሑራዊ ምንጭ (“The Historical Geography of Ethiopia: from the first century AD to 1704”) እንደሚነግረን አሕመድ አል ግሀዚ አፄ ልብነ ድንግልን “ሴት ልጅህን ከዳርከኝ ሰላም እሰጥሃለሁ፣ አልወጋህም” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።
ይህን በአግባቡ ለመረዳት ያፄ ልብነ ድንግል ቅም አያት የነበሩት አፄ ይኩኖ አምላክ በዘመናቸው ከነበረው የግብፅ ሡልጣን ጋር የተጻጻፉትን ደብዳቤ እና የምሥራቁ ሡልጣኔት (በኋላ አሐምድ ግራኝ የተነሳበትና የመራው) ከአምሓራ ሰሎሞናዊ ነገሥታት ጋር የነበረውን የጠላትነት ምክኒያትና መነሻ እና መሰረቱ ምን እንደነበረ (ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስለመሆኑ) የሚከተለውን ማስረጃ በጥንቃቄ መረዳትን ይጠይቃል።
 ከስር ባያያዝኩአቸው screenshots በምሑራዊ ሰነዶቹ ላይ (ሞርድካይ አቢር) እንደተገለጸው፣ የመካከለኛው ዘመን የሰሎሞናዊ ነገሥታት አባት የሆነው አፄ ይኩኖ አምላክ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር በጎ ግንኙነት እንደነበረው እንመለከታለን። ከታች እንደተጻፈው፣ በሞርድካይ አቢር በቀረበው የተጠና ታሪካዊ ሐተታ የሰሎሞናዊ ክርስቲያን ነገሥታት እንቅስቃሴ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የነበርና ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር በጎ ግንኙነትን የመሰረተ ነበር። ይህም ከሰባት መቶ ዘመን በፊት ነበር። አፄ ይኩኖ አምላክና እርሱን የተኩት ሰሎሞናዊ ነገሥታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የንግድ መስመሮችን እንዲቆጣጠሩ በማመቻቸታቸው በኢትዮጵያ ሰሎሞናዊ መንግሥት ሙስሊሞችና በምሥራቅ (ሶማሌ) ሡልጣኔት  ሙስሊሞች መካከል መቃቃር ተፈጥሮ ነበር ሲል ያስረዳል።
የዚህም ምክኒያት አምሓራ ሰሎሞናዊ ነገሥታት  የቀይ ባሕር የንግድ መስመሮች በአበሻ ሙስሊሞች እንዲያዙ በማድረጋቸው የምሥራቁ ሡልጣኔት ሙስሊሞች ከአበሻ ሙስሊሞች ጋር መቃቃር ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ይገልጻል። ከዚያም አልፎ አማራው አፄ ይኩኖ አምላክ ለግብጽ ሡልጣን በላከው ደብዳቤ አፄ ይኩኖ አምላክ በርሱ ሰሎሞናዊ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ሙስሊሞች ጠባቂ (ባለ አደራ) መሆኑን እና በርሱ መንግሥት ውስጥ አበሻ ሙስሊሞች ከአበሻ ክርስቲያኖች ጋር እኩል መብት ያላቸውና በሰሎሞናዊ መንግሥት ባለ አደራነት መብታቸው ተጠብቆ የሚኖሩ መሆኑን የሚገልጽ እንደሆነ ተዘግቧል።
 የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ሰሎሞናዊ ነገሥታት ያካሄዱአቸው ጦርነቶች በአበሻ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠሩ ሆነው አያውቁም። ያካሄዱአቸው ጦርነቶች  ለፖለቲካዊ የበላይነት ከተዋጉአቸው የምሥራቅ ግዛት ኃይሎች ጋር እንጅ በራሳቸው ግዛቶች ውስጥ ያለውን ሕዝበ ሙስሊም አልነበረም። እነርሱም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማ የነበራቸው፣ እንዲሁም በወረራና በጥቃት ምክኒያት የተካሄዱ መሆናቸው በታሪክ  መጻሕፍት  ይገለጻሉ። ክፉ ዓላማ ያላቸው አክራሪዎች ግን ሰሎሞናዊ (አማራ) ነገሥታት በራሳቸው ሕዝብ ላይ ጥቃት ያደረሱና ሙስሊም የሆኑን ኢትዮጵያዊያን ለይተው ያጠቁ አስመስለው በማቅረባቸው ሕዝባችን በገዛ ታሪኩ ላይ ጥያቄ እንዲያነሳና ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርገዋል። ከስብረዲን ጋር፣ ከሐቀዲን ጋር፣ እንዲሁም ከአሕመድ አል ግሐዚ (አሕመድ ግራኝ) ጋር የተደርጉ ጦርነቶች ከጎረቤት መንግሥት የምሥራቁ ሡልጣኔት ጋር የተደረጉ እንጂ የርስ በርስ የሃይማኖት ጦርነቶች አለመሆናቸው ይሚገለጽ ሐቅ ነው።
አፄ ልብነ ድንግልን የሙስሊም ጠላት አድርገው ማቅረብ የሚፈልጉ አንዳንድ ታሪክን በትክክል ያላዩ ሰዎች ብዙዎችን አሳስተዋል። አፄ ልብነ ድንግል ጦርነት የገጠመው በሃይማኖት አመካኝተው ከውጭ ኃይላት ጋር በማበር ያማራውን መንግሥት የወረሩን ጠላቶች ነው። ግራኝ አሕመድ ከምስራቅ ተነስቶ በቱርኮችና ዐረቦች እገዛ ቤተ አምሓራን ያጠቃ  በዘመኑ ግብር (tax)  ለማዕከላዊ መንግሥት ከመክፈል ውጭ ራስ-ገዝ ግዛት የነበረው የምሥራቁ ሡልጣኔት አደሬ-ሶማሌ መሪ ነበር። የግራኝ አህመድም ሠራዊት አረብና ቱርኮች እንጂ አማሮች አልነበሩም።  አፄ ልብነ ድንግል አማራ ንጉሠ ነገሥት ነበር። የአማራን መንግሥትና ሥልጣኔ ለማዳን ተጋድሎ አድርጎአል። የግራኝ ዜና መዋዕል መዝጋቢም የግራኝን አላማ “አማራን ቅኝ መግዛት”  (ፉቱህ አል ሐበሻ/ “Conquest of Abyssinia”) ብሎ ርዕስ ሰጥቶታል።
ልብነ ድንግል አምሓራን ከጥፋት እናድን አለ እንጂ ጠላት እንደሚለው “ሙስሊሞችን እናጥፋ” ፈጽሞ አላለም። እንዲያውም በራሱ ግዛቶች ውስጥ የነበሩን ሙስሊሞች የመጠበቅን ሃላፊነት ካያቶቹ ከነ አፄ ይኩኖ አምላክ የተቀበለ ንጉሠ ነገሥት ነበር። ለፖለቲካዊ የበላይነት የወጉአቸውን የምሥራቅ ግዛት ሙስሊም ኃይሎች እንጅ ሕዝበ ሙስሊሙን አልነበረም።   ውጊያው ሃይማኖታዊ ቅርፅ የያዘው በዐረብ ፋቂሕ ዜና መዋዕል እንደተዘገበው ቤተ ክርስቲያንን የማቃጠልና ክርስቲያኖችን የመጨፍጨፍ  ድርጊት የአሕመድ ግራኝ ሠራዊት በመፈጸሙ ነበር፤ ሆኖም ግን አሕመድ ግራኝ በእሳት አቃጥሎ ያወደመው ቤተ መንግሥቶችን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የግእዝ ብራና መጻሕፍትና የመሳሰሉትን ጭምር ነው። የአምሓራውን መንግሥት በዛሬ ትመና በቢሊዮኖች ዋጋ የነብረውን የወርቅ ሐብት በቱርኮቹና በዐረቦቹ አስዘርፎ አከፋፍሎአቸዋል (በዐረብኛ የተጻፈውን ፉቱሕ አል ሐበሻ ተመልከት)። ዓላማው የአምሓራን ሥልጣኔ አመድ ማድረግ እንጅ ሃይማኖታዊ ተጋድሎ አልነበረም።
አክራሪዎች በተለይ በውጭ ባዕድ መንግሥታት ወረራዎችና ጥቃቶች ምክኒያት ራሳቸውንና ሕዝባቸውን በመከላከል ሰሎሞናዊ ነገሥታት ያካሄዱአቸውን ጦርነቶች ሕዝበ ሙስሊሙ ላይ ያነጣጠሩ አድርገው በማቅረብ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በተለይ ሙስሊም አማራዎች የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ቅሬታና ቁጭት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ብዙ ሰርተዋል: እውነት ግን ነጻ ታወጣለችና እውነታውን በማስረጃ ልንናገር እንገደዳለን።
ምንጭ
George Wynn Brereton Huntingford, “The Historical Geography of Ethiopia: from the first century AD to 1704”
Mordechai Abir, “Ethiopia and the Red Sea: The rise and decline of the Solomonic dynasty and Muslim-European rivalry in the region”
Filed in: Amharic