>

የሀበሻው ልዑል ዓለማየሁ...!!!   (በስንታየሁ ሀይሉ)

የሀበሻው ልዑል ዓለማየሁ…!!!

(በስንታየሁ ሀይሉ)

“ምስኪኑ ልጅ ፍርሀቱ አለቀቀውም፡፡ የመቅደላው እልቂት እና የአፄ ቴዎድሮስ ሞት ስላየ በአዕምሮው ይመጣበታል፡፡ “ 
ንግስት ቪክቶሪያ
ከዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ እና ከወይዘሮ ጥሩወርቅ ውቤ በሚያዚያ 5 ቀን 1853 ዓ.ም ደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ ተወለደ በልዑሉ መወለድ የተደሰቱት አፄ ቴዎድሮስ በእለቱ መድፍ ከማስተኮሳቸው በተጨማሪ ብዙ እስረኞችንም ፈትተዋል፡፡
በ1860 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ጦርነት ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ገባ። በጊዜው ልዑል አለማየሁ እድሜው ሠባት ዓመት በመሆኑ ከእናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ፣ ከመምህሩ አለቃ ዛራት እና ከእናቱ አጃቢ ገብረመድህን ጋር ሆኖ ከሃገሩ እንዲወጣ አደረጉ፡፡
ይሁን እንጂ በጉዞ ላይ እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ በፀና ታመው ለካፒቴን ስፒዲ ልጃቸውን ልዑል አለማየሁን እንደ አባት ሆኖ እንዲያሳድገው የአደራ ቃል ሰጥተውት በሞት ተለዩት። በአጭር ጊዜ ልዑል አለማየሁ አባቱንም እናቱንም በሞት ተነጠቀ፡፡
አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገረው ባለአደራው ካፒቴን ስፒዲ እና ልዑል አለማየሁ የጠበቀ ወዳጅነትና ፍቅር ስለነበራቸው ካፒቴን ስፒዲ በሚሄድበት ሁሉ ልዑሉ ተከትሎት ይገኝ ነበር።
የስዊዝ ካናልን እንደተሸገሩ የልዑል አለማየሁ አጃቢ መምህር ገብረመድህንና አለቃ ዛራት ጠፉ፡፡ በተለያዩ የታሪክ መረጃዎች የሚጠቀሰው ጄኔራል ናፒር  የተባሉት የጦር ምርኮ መሪ የልዑል አለማየሁ እና የካፒቴን ስፒዲን ፍቅር በማየታቸው የልዑሉን ሀላፊነት ሙሉ ለካፒቴን ስፒዲ  እንዲረከብ ወስኖ ኢትዮጵያውያን ሞግዚቶቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ሳያደርግ አልቀረም ይባላል።
 ልዑል አለማየሁ ከጠባቂው ካፒቴን ስፒዲ ጋር ፌሬዝ በተባለችው መርከብ ተሳፍሮ ከሶስት ወራት የመርከብ ላይ ጉዞ በኃላ እንግሊዝ ሀገር ደረሰ፡፡
አጤ ቴዎድሮስ ከመሞታቸው አስቀድሞ ልጃቸው እንግሊዝን እንዲጎበኝና ስልጣኔን ተምሮ ሀገሩን እንዲያሳድግ ከፍተኛ ምኞት እንደነበራቸው ቢጠቀስም ከካፒቴን ስፒዲ ሌላ አንድም የሚያውቀው ሰው በአጠገቡ ያልነበረው ልዑል አለማየሁ ከፍተኛ ሀዘን እና ጭንቀት ነበረበት። የጭንቀቱ ምክንያት ከብቸኝነቱ በተጨማሪ በመቅደላ የተመለከተው ጦርነትና የወላጆቹ ሞት ሀዘኑም እጅጉን ጎድቶታል፡፡
በእንግሊዝ ሀገር ንግስት ከነበረችው ንግስት ቪክቶሪያ ልዑል አለማየሁን በፍጥነት የጎበኘችው ሲሆን የእድሜው ለጋነት፣ የደረሰበት ሀዘንና የልዑልነት ግርማሞገሱ አይታ ልቧ ስለተነካ ልዑሉ የፈለገው እና ያሻው ይደረግለት ዘንድ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡
ልዑሉ በመቅደላ የነበረውን እልቂት በመጠኑም ቢሆን በማየቱ እና የአባቱ እና የእናቱ ተከታታይ ሞትም በልጅ አዕምሮው ሊቀበለው ከሚችው በላይ ስለነበር እጅግ ታውኮ እንደነበር በተደጋጋሚ ተፅፎ እናገኛለን፡፡ አንድ እንግሊዝ ሀገር ውስጥ በሚገኝ ሙዚየም ውስጥ ባለ የንግስት ቪክቶሪያ የእለት ማስታወሻ ላይም ንግስቲቱ፡ “ምስኪኑ ልጅ አሁንም ፍርሀቱ አለቀቀውም፡፡ መቅደላ የነበረው እልቂት እና የአባቱን ሞት ስላየ በአዕምሮው ይመጣበታል፡፡ “ የሚል ቃል ፅፋ እናገኛለን፡፡
የልዑሉ ጠባቂ የነበረው ካፕቴን ስፒዲ ልዑሉን እንዳይጎዳው በሚል በንግስቲቱ የቅርብ ክትትል ውስጥ ሆኖ የእንግሊዘኛ ቋንቋን ያስተምረው ጀመር። ንግስቲቱ ለልዑሉ የተለየ አክብሮት እና ፍቅር ፤ ልዩ ትኩረትም እንደነበራት በግል ማስታወሻዎቿ ከማስፈሯ በተጨማሪ በተደጋጋሚ “ለዚህ እናት ለሌለው ልጅ እናቱ እኔ ነኝ” ስትል ትደመጣለች፡፡
ልዑል አለማየሁ  ከንግስቲቱ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት ከግዜ ወደ ግዜ እየበረታ ቢመጣም ከሀገሩ ሲወጣ አብሮት የነበረውን ካፕቴን ስፒዲን ግን ለአፍታም አልዘነጋውም ነበር፡፡ በየትኘውም ስፍራ ሲሄድ ስፒዲ አብሮት እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ግብዣም ሲሄድ ሆነ ከልዑላን ልጆች ጋር እንዲጫወት ሲጋበዝ ስፒዲን ትቶ መሄድ አይሆንለትም፡ ፡ ቤተ-መንግስት ሲገባ እንኳን ስፒዲን አስከትሎ ነው፡፡ ስፒዲ እና አለማየሁ አብረው ይበላሉ አብረውም ደግሞ ይተኛሉ፡፡ አለማየሁን ለብቻው ማሳደግ የከበደው ስፒዲ ልጁን በማሳደግ ትረዳው ዘንድ ሚስት ለማግባት ወሰነ፡፡ ከዛም ወ/ሮ ኮታንን አገኘ እና አገባት፡፡ አለማየሁ እና ወ/ሮ ኮታንም ለመዋደድ ግዜ አልወሰደባቸውም ነበር፡፡
 በ1861 ዓ.ም ካፒቴን ስፒዲ ህንድ ሀገር በምትገኝ አንዲት ከተማ አዛዥ ሆኖ ስለተሾመ የ8 ዓመቱን አለማየሁን እና ሚስቱን ይዞ ወደዛው አቀና፡፡ በሄዱበት ሀገርም አለማየሁ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጥሎ የነበረ ሲሆን ከመደበኛው ትምህርት በዘለለም ፈረስ ግልቢያ እና ሌሎች ስፖርቶችንም ያዘወትር ነበር፡፡ ልዑሉ በዚህ አይነት ከቆየ በኃላ ቻንስለር ሮበርት ሉዊ ልዑሉ የቀለም ትምህርት ላይ ከሚያዘወትር ይልቅ የወታደር ትምህርት ቤት ገብቶ የፈረስ ውትድርናን እንዲማር መደረግ አለበት ሲሉ ያቀረቡት ሀሳብ የልዑሉን ህይወት እስከወዲያኛው የለወጠ ነበር፡፡
 ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ተነጥሎ በመንግስት ቁጥጥር ስር በማድረግ እና የውትድርና ትምህርቱን እንዲከታተል ተወሰነ፡፡ ይህ ውሳኔ ግን ለአለማየሁም ሆነ ለስፒዲ ከባድ ግዜ ነበር፡፡ ስፒዲ እና ሚስቱ አለማየሁን ላለመስጠት ከባድ ትግልን አደረጉ፡፡ ነገር ግን ትግላቸው ውጤትን አላስገኘላቸውም፡፡ ይልቁኑም አለማየሁ ወደ እንግሊዝ ሀገር እንዲመለስ ተወሰነ፡፡ ስፒዲም አለማየሁን ይዞ ወደ እንግሊዝ መጣ፡፡ የአለማየሁ አዲሱ አስተማሪ እና ጠባቂ እንዲሁኑ የተመረጡትም በአስተማሪነታቸው የተመሰከረላቸው እና በደግነታቸው የታወቁት ቄስ ብሌክ ነበሩ፡፡
ንግስት ቪክቶሪያም የአለማየሁን እና የስፒዲን ፍቅር ያውቁ ስለነበር ሁለቱን ቶሎ መነጣጠል አልፈለጉም፡፡ ይልቁኑም አለማየሁ ከቄስ ብሌክ ጋር እስኪላመድ ድረስ ስፒዲ አብሮት ይቆይ ስትል ፈቀደች፡፡ አዲሶቹ የአለማየሁ ጠባቂዎች አለማየሁ ስራ እንዲሰራ ወሰኑ፡፡ በወጣለትም ፈረቃ መሰረት በሳምንት ለ 31 ሰዓት ተኩል ያህል ማንኛውንም አይነት ስራ እንዲሰራ ተወሰነ፡ ፡
የስፒዲ ሚስትም ይህንን በመቃወም ጠባቂው ለነበሩት ለቢዶልፍ ደብዳቤ በመላኳ አንዳንድ ግዜ ልዑሉ እሷ ጋር እንዲያሳልፍ ተፈቀደለት። እሷም  አብሯት እያለ ያየችውን በደብዳቤ አስፍራዋለች።
“ልዑሉ ማደጉን ቁመቱ አድጓል፡፡ መልኩ ግን ገርጥቷል፡፡ አካላቱም ከስቷል፡፡ ዝምተኛ እና ጭምትም ሆኗል፡፡ ከወንዶች ልጆች ጋር እንዳይገናኝ እና ከእኩዮቹም ጋር እንዳይገናኝ ተደርጓል። ውጪ እየወጣም እንዳይዘል ታግዷል፡፡ እየደጋገመም ‘አብረውኝ የሚጫወቱ ልጆች አጣሁ ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ ከሁለት ልጆች ጋር አንድጫወት ይፈቀድልኛል፡፡ ሊያጫውቱኝ የሚመጡትም እነዚህ ልጆች ሁልግዜ እነሱ ብቻ በመሆናቸው ተሰላችተናል፡፡ በሌላ ቀን ግን የሌሎች ልጆችን እጅ አንኳን ጨብጬ አላውቅም’ ብሎኛል፡ ፡ ይህንን የመሰሉት ነገሮች ያበሳጩታል፡፡ እኔም ብሆን ይህን የሚበሳጭበትን ጉዳይ ለማስተው ጓደኛ ልፈጥርለት አልቻልኩም፡፡ እየደጋገመ የነገረኝም ‘ወንዶች ልጆች እፈልጋለሁ፡፡ የበለጠ እንድንዛመድም እፈልጋለሁ’ ብሎ መለሰልኝ፡፡ እኔ እንደማስበው አለማየሁ ደስተኛ እና በሚደረግለት የረካ ልጅ አይደለም፡፡”
የስፒዲ ሚስት የፃፈችው ይህ ደብዳቤ ከንግስት ቪክቶሪያ ዘንድ ደረሰ፡፡ ንግስቲቱም ትንሹ ልዑል አብሮአቸው ሊጫወት የሚችሉ ጓደኞች እንዲፈለጉለት አዘዘች፡፡ እንደተባለውም ተደረገ፡፡ በ1867 ዓ.ም አለማየሁ ወደ ራግቢ ትምህርት ቤት ተዛወረ፡፡ በዚህም ከቄስ ብሌክ ቤት ወጥቶ ወደ ሊው ዋርነር ቤት እንዲገባ ተደረገ፡፡ በዚህ ግን ደስተኛ ስላልነበር በቀጣዩ አመት ሚስተር ድራፐር ቤት እንዲኖር ተደረገ፡፡ ቄስ ብሌክም ካዩት የልዑሉ ባህሪ በመነሳት ልዑሉ ወታደርነት ላይ ቢያተኩር የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ተናገሩ፡፡ በዚህም ንግግር መሰረት የወታደር ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ፡፡
ልዑል አለማየሁ በእንግሊዝ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩ መምህራን ሁሉ መልካም ወዳጆች ሆነውለታል፡፡ እርሱ ግን ከትምህርት ይልቅ ለስፖርት የተሻለ ፍቅር ነበረው፡፡እግር ኳስ እና ራግቢም ይጫወት ነበር፡፡ መምህራኑ ወታደራዊ ሳይንስ እንዲያጠናም ግፊት አድርገዋል፡፡ እናም እ.ኤ.አ. በመስከረም 1878 ወደ ሳንድረስት ወታደራዊ ትምህርት ቤት ካለ ፈተና እንዲገባ ተደረገ፡፡
በወታደራዊ ትምህርት ቤት ደስተኛም ሆነ ውጤታማ አልነበረም፡፡እናም ለእረፍት እንደወጣ አልተመለሰም፡፡
ልዑል አለማየሁ ወደ ሀገሩ መመለሱን የሚናፍቁ ሁለት ደብዳቤዎች ከኢትዮጵያ ደርሰውት ነበር፡፡ አንዱ ከአያቱ (ከእናቱ እናት) የተላከ ሲሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ላኪ ማንነት አይታወቅም፡፡
በመጨረሻም ልዑል አለማየሁ ወደ ሊድስ በመሄድ በሰር ራምሰን ቤት ተቀምጦ በነበረበት ወቅት በምግብ ተመረዘ። እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 14 1879 (ህዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም) በተወለደ በ19 ዓመቱ በጥቂት ቀናት ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
በንግስቷ ፈቃድ በዊንድሶር የቅዱስ ጊዮርጊስ የነገስታት መቀበርያ ቤተመቅደስ በክብር የቀብር ስነስርዓቱ ተፈፀመ፡፡ በመቃብሩም ላይ “የሀበሻው ልዑል አለማየሁ” የሚል ፅሁፍ ሰፍሮበት እስካሁን በእንግሊዝ ሀገር ይገኛል፡፡
የልዑል አለማየሁን አፅም ወደ ኢትዮጵያ ለማስመጣት በተለያየ ጊዜ ጥረት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡
Filed in: Amharic