ኢትዮ ኤፍ ኤም
ከአንድ ወር በፊት ፓርቲያቸው በምርጫ ቦርድ የታገደባቸው አቶ ልደቱ አያሌው እና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ሕብር ኢትዮጵያ ፓርቲን መቀላቀላቸው ተገልጿል። ኢዴፓ፣ ኢሀንና ህብር ኢትዮጵያ ነገ በይፋ ሊዋሀዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ (ኢሀን) እና ህብር ኢትዮጵያ በይፋ ተዋህደው በአንድ ፓርቲ ስር ሊሰሩ ነው።
ኢሀንና ኢዴፓ በምርጫ ቦርድ ከምርጫው የተሰረዙ ሲሆን ህብር ኢትዮጵያ ግን በምርጫው ለመወዳደር ፍቃድ በማግኘቱ ተዋህደው በህብር ኢትዮጵያ ስም ሊሰሩ መሆኑን ሰምተናል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ (ኢሀን ) ሊቀ መንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ይሄንኑ ያረጋገጡ ሲሆን ነገ በዚሁ ውህደት ዙርያና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንሰጣለን ብለውናል።
ህብር ኢትዮጵያ፣ ኢሀንና ኢዴፓ ኢትዮጵያ ህልውናዋ አደጋ ስለተጋረጠበት ፓርቲዎቻችን በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል በሚል አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነትን መስርተው በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
አሁን ይሄ ስብስብ ከነገ ጀምሮ አንድ ፓርቲ ሆኖ እንደሚቀጥል ኢንጅነር ይልቃል ነገረውናል።
የኢዴፓው አቶ ልደቱ አያሌው እና የኢሀኑ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ በተነሳው ረብሻ ተጠርጥረው ለወራት ከታሰሩ በኋላ በዋስ ከእስር መፈታታቸው የሚታወስ ነው።