አክቲቪስትና አርቲስት (ታማኝ በየነ በ2 ቀን ውስጥ ከ5 ሚልዮን ብር በላይ አሰባሰበ…!!!
* “የትግራይ ህዝብ ህውኃት በፈጠረው ችግር መከራ ላይ መውደቅ የለበትም”
መንግስት በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ህግ የማስከበር ስራ በሚሰራበት ወቅት በተለይም በትግራይና በመተከል በርካታ ዜጎች ለማህበራዊ ቀውስና ለችግር ተጋልጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ ምግብና ቁሳቁስ የሚያስፈልጋቸውም በርካቶች ናቸው። በዚህ ምክንያት እንደለመደው አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በሰብሳቢነት የሚመራቸው ማህበራትና በጎ ፈቃደኞች ማለትም ግሎባል አሊያንስ፣ ሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኛና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ማህበር፣ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የትግራይና የመተከል እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች በጋራ ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እርዳታ ማሰባሰብ ጀምረዋል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በእርዳታ አሰባሰቡ ጀምሮ፣ እርዳታ ማሰባሰቡን ተከትሎ ስለገጠመው ተቃውሞ፣ በአገሩ ስለላው ተስፋና ተያያዥ ጉዳዮች ከአርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች እነሆ።
የእርዳታ አሰባሰብ ጅማሮው ምን ይመስላል…አበረታች ነው?
አጀማመሩ ጥሩ ነው ግን፣ እኛ የምናስበው ምንድን ነው። የዚህ እርዳታ ዋና ዓላማ አራት አምስት ድንኳን ሙሉ እህል መሰብሰብ ወይም የተከፈተውን አካውንት የሚያጨናንቅ ገንዘብ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ ጉዳይ ሃላፊነት አለብኝ፤ የኔ ጉዳይ ነው እንዲል የማድረግ ስራ ነው የምንሰራው። ምክንያቱም እኛ እርዳታ አሰባሳቢ፤ የተወሰነ የተመቸው ሰው ብቻ እርዳታ የሚሰጥበት ፕሮግራም አይደለም። ፕሮግራሙ “ትግራይም መተከልም ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችህ አሉና ምን አድርገሃል ስትባል ምንድን ነው የምትመልሰው?” ወይስ አሁንም የካናዳና አሜሪካ መንግስት አለያም የካናዳ ስንዴና የአሜሪካ ዱቄት ነው የምትጠብቀው? አንተ እንደ ዜጋ ምንድን ነው ያደረግከው? የሚል መልዕክት ነው ማስተላለፍ የምንፈልገው። እና በዚህ ልክ ስንለካው ገና ነው። የምልሽ አገሪቱ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጋ ነው ያላት። ገጠር ያለውና አቅም የሌለው ይህን ማድረግ ባይችል እንኳን በቴሌቪዥንና በተለያየ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዜና የሚከታተለው ህዝብ በበቂ ደረጃ ምላሽ ሰጥቷል ብዬ አላስብም።
በዚህ በኩል ሚዲያውም ሊተባበረን ይገባል ብዬ አስባለሁ። በመግለጫው ላይ ለተገኙ ጋዜጠኞች “ጉዳዩ የራሳችን ነውና እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ ሌሎች እንዲሳተፉበት አድርጉ” ብለን ነግረናቸዋል። ነገር ግን ከአንድ ቀን የዘለለ ሽፋን የሰጠን የለም። በእኛ በኩል የምናስበውን ለማድረግ እየሞከርን ነው። ከተሳካልን ደስ ይለናል፤ ካልተሳካልንም የአቅማችንን አድርገናል ነው የምንለው።
ይህን እርዳታ ለመሰብሰብ ስትነሳ አክቲቪስቶች “አንተን ለትግራይ ህዝብ ምን አገባህ እኛ እንበቃለን” የሚል ተቃውሞ አስነስተውብሃል። አንተስ በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?
አዎ እውነት ነው። በደንብ በተጠናከረ መልክ “አንተ ምን አገባህና ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ትሰበስባለህ” ብለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመሩ አሉ። ይህን ማለት እንደ መብት ይችላሉ። እንደ እውነት ግን ማነው እነሱንስ ፈቃጅ ከልካይ ያደረጋቸው!?
በሁለተኛ ደረጃ ይሄ የ30 ዓመት የህገ-መንግስት አስተሳሰብ ነው። በዚች ምድር ላይ የሚደርስ ችግር፤ የሁሉም ዜጎች ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው። በ1966 እና 67 ዓ.ም በወሎና በትግራይ በተከሰተው ረሃብ ላይ ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ነው ያደረገው። ማይጨው ሲዘመት ሁሉም ዜጋ ያለው ቋጥሮ ነው የዘመተው፣ ሶማሊያ ስትወርረን ሁሉም ዜጋ ነው የተሳተፈው። አንተ ምን አገባህ ፣ ይሄ የሀረር ችግር ነው፣ ያኛው የኦጋዴን ችግር ነው ተብሏል? አልተባለም። በዚህ አይት አስተሳሰብ የታሰሩ፣ የዚህ ስርዓትና የዚህ ህገ-ምንግስት ጠባብ አእምሮ ባለቤቶች ናቸው ለመከልከልና ለመቃወም የሚሞክሩት።
እኔ እውነት ነው ያንን ክልል ያአስተዳድር የነበረውን ድርጅት ስቃወምና ሳጋልጥ ኖሬያለሁ። አላፍርበትም አምኜበት ነው ያደረግሁት። ህውሐት እና የትግራይ ህዝብም ፍፁም አይገናኙም። የህወሃት ቡድን ከትግራይ ህዝብ የበቀለ ቡድን መሆኑን አምናለሁ። ነገር ግን የትግራይ ህዝብ የጥፋት ተካፋይ ሊሆን አይገባውም። ህወሃት በፈጠረው ችግር መከራ ላይ መውደቅ የለበትም። እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ያሳስበኛል፤ ያገባኛል ብዬ ነው የማደርገው። በዚህ ሂደት ከዚህ መስመር ጀምሮ እዚህ ክልል ይሄ አጭር እስከታጠረበት እንዳትመጣ እንዳታስብ የሚለው ለእኔ አይሰራም።
ወደ ትግራይ ብቅ ብለሃል እንዴ?
ገና ነኝ አልሄድኩም።
የመሄድ ሀሳብ አለህ?
እንዴ! አገሬ አይደል እንዴት አልሄድም። እርግጥ የመጣሁት በግል ጉዳይ ነው። ነገር ግን ያየሁት ነገር ስላሳሰበኝና ስላስጨነቀኝ አመጣጤን ፈረንጆች ቫኬሽን (ቤተሰብ ጥየቃ) ቢሉትም፣ ከዚህ አይበልጥም በሚል ነው የገበዘሁበት። እንደው የሆነች ትንሽ አስተዋፅኦ ማድረግ ብችልና ምናልባት አፉ የደረቀ አንድ ህጻን ልጅ ትንሽ ውሃ አግኝቶ ቢጠጣና ትንሽዬ አልሚ ምግብ አግኝቶ ቢበላ፣ ለኔ ትልቅ ቁም ነገር ነው በሚል ነው እንጂ የመጣሁት በግል ጉዳይ ነው። ወደፊት ግን ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሄጄ ማድረግ የሚገባኝን ማድረግ እፈልጋለሁ።
የእርዳታ አሰባሰብ ሂደቱ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? በገንዘብ ደረጃስ ምን ያህል ገንዘብ ለማሰባሰብ ነው ያቀዳችሁት?
በቁሳቁስ ደረጃ ይሄው አሁንም እየተቀበልን ነው። አሁን የምታናግሪኝ ራሱ እዚሁ ጣይቱ ሆቴል ድንኳን ዘርግተን፣ ህዝቡ እየመጣ እየሰጠን እየተቀበልን ነው። መልዕክቱ በአግባቡ ደርሷል አልደረሰም አላውቅም። ምክንያቱም በምናስበው ደረጃ ብዙ ነው አልልም። አሁንም ግን በመኪናቸው ጭነው፣ በትከሻቸው ተሸክመው መኮሮኒና ፓስታ የመሳሰሉትን እያቀረቡልን ነው። በገንዘብ ደረጃ በውጭ አገር “ያን ያህል የአትርዱ” ዘመቻ እየተካሄደ፣ “እንዳትረዱ ለመሳሪያ መግዣ ነው” እየተባለ፣ “የታማኝ ቡድን ነው አትርዱ” እየተባለ እንኳን እግዚአብሔር ይመስገን በሁለት ቀን ውስጥ ወደ 117 ሺህ ዶላር ተሰብስቧል። በአገር ቤት ባንክ ውስጥ ወደ 400 ሺህ ብር ገብቷል። ገና የሚቀጥል ነው፤ ገደብ የለውም። ገደቡ እንደነገርኩሽ ይሄን መልዕክት የሚያገኘው እያንዳንዱ ዜጋ ምን አድርገሃል? ምን እያደረግክ ነው ሲባል፤ ምላሽ የሚሰጥበት ተሳትፎ እንዲያደርህ ነው የምንፈልገው እንጂ የብሩ ማነስና መብዛት አይደለም ዋናው አላማ፡፡ የሚመጣው ቁሳቁስ መብዛት ማነስ አይደለም ጉዳዩ። ነገር ግን እንደ ዜጋ እነዚህ ዜጎች ተጎድተው ስታይ ምን አድርገሃል ሲባል ዜጋ ምላሽ እንዲሰጥ ነው እንጂ በጊዜ ገደብ፣ በገንዘብ መጠንና በቁሳቁስ ልክ የሚለካ አይደለም።
የቀደመውን እንተወውና በቅርብ ጊዜ እንኳን ካሰባሰብካቸው እርዳታዎች ብንነሳ፣ የቡራዩው ቀውስ፣ የጉጂ ተፈናቃች፣ የአማራ ተፈናቃዮች፣ የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ ቀውስ በሻሸመኔ ለተፈጠረው ቀውስ ያደረግከው በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። አንተ ይህን ሁሉ ስታደርግ መቼም አንድ ቀን ይህቺ አገር ላይ ፍትህና ርትዕ መግሶ አያለሁ በሚል ተስፋ ይመስለኛል፡፡ ተሳስቼአለሁ?
(በግርምት እየሳቀ…) እንደው ለዚህ ጥያቄሽ እግዚአብሔር ይስጥሽ። በእውነቱ በጣም ልብ የሚያደማ ነገር ነው። ይሄ በየቀኑ የሚከሰተውና የሚታይው ችግር፣ ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ስትነሺ እንቅፋቱ ብዙ ነው። በዚሁ ሁሉ እንቅፋት፣ የሰው ፊት እንደ እሳት የሚገርፍበት ለማኝ እየተባልኩ በምሰደብበት ደጋግሜ ለድጋፍ ልመና ስወጣ፤ በጣም ያምማል ግን በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ቆይቼ የምሄድበት ጊዜ ይደርሳል። ሌላው አገር ደግ አያለሁ። እና በጣም ይከፋኛል። እንዴት ይህቺ አገር በገዛ ልጆቿ እኛው እራሳችን እናውድማት እያልኩ እቆጫለሁ አስባለሁ። ብቻ አንድ ቀን ማንም ዜጋ እኩል ሆኖ፣ በሰላም ገብተን እንወጣለን የሚለው ምኞቴ ነው። ያ ጊዜ እስኪመጣ ችግር እያየን ዝም ስለማባል በሌላውም መስክ ይሄንን ማረጋጋጥ የሚፈጥር ነገር ለመስራት እንደማንኛውም ዜጋ ያቅሜን አደርጋለሁ። በሌላ አቅጣጫ ማለቴ ነው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የተፈጠረው ችግር ተጎጂ የሆኑትን ዝም ብሎ ማለፍ ስለማይችል ድጋፍ ማሰባሰቡን በተቻለኝ መጠን አደርጋለሁ።