>
5:18 pm - Tuesday June 15, 4371

ሰሞኑን በደቦ ጥቃት ህይወቱን ያጣው የሞራል ማማ ላይ የደረሰዉ ባዮ ቴክኖሎጂስቱ ካሳ ጌጡ ....

ሰሞኑን በደቦ ጥቃት ህይወቱን ያጣው የሞራል ማማ ላይ የደረሰዉ ባዮ ቴክኖሎጂስቱ ካሳ ጌጡ ….


ካሳ ጌጡ የተወለደዉ ላሊበላ ሲሆን  የዲምፕሎማ  ትምህርቱን ከጅማ እርሻ ኮሌጅ ከአመቱ ተመራቂዎች አንደኛ በመዉጣት በመጨረስ በጅማ እርሻ ምርምር ቴፔ የቅመማ ቅመም ምርምር ማዕከል ስራዉን ጀመር። ካስ ትምህርቱን በመቀጠል ከአለማያ ዩኒቨርስቲ ዲግሪዉን ያዘ። ከዚያም  በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል እንደተቀጠረ ቁልፍ የሀላፊነት ሚና ያደረገዉ ቤተሰቡን ለመርዳት ወሳኝ ርምጃ መዉሰድ ነበር:: በዚህም ወንድም እህቶቹን በራሱ ስር አምጥቶ አስተማረ::
በሆለታ ምርምር ማዕከለም በተመራማሪነት እየሰራ ሳለ ወደ ጀርመን ሀገር በመሄድ በባዮ ቴክኖሎጅ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪዉን በከፍተኛ ዉጤት አጠናቀቅ::በከፍተኛ ዉጤቱ  የተደሰቱት መምህሮቹ የፒኤችዲ ትምህርቱን እንዲቀጥል ቢጠይቁትም መጀመሪያ ሀገሬን ጥቂት ጊዜ ማገልገል አለብኝ በማለት ወደ ሀገሩ ተመልሶ የምርምር ስራዉን ቀጠለ::
ለተወሰነ ጊዜ ሀገሩን ካገለገለ ብኋላ የሶስተኛ ድርግሪዉን ለመቀጠል የስኮላርሽፕ እድል ስላገኘ ወደ ሀገረ እንግሊዝ  አቅንቶ ነበር። በተመሳሳይም  በሀገረ ካናዳ ሌላ የሶስተኛ ዲግሪ እድል እግኝቶ ትምህርቱን ካጠናቀቀ ብኋላ መምህሮቹ አንድ ከሀገራት ህግ ያፈነገጠ ጥያቄ ይጠይቁታል። ይሄዉም የተልባ ዘርን ወደ ካናዳ እንዲልክ ይጠይቁታል። ሆኖም ካሳ ከፈለጋችሁ ፒ ኤችዲዬ ይቅርብኝ እንጂ ከመርህ ባፈነገጠ መልክ የሀገሬን ዘር /Genetic Resource/ ወደ  ካናዳ አልክም ብሎ አቋም ይወስዳል::ካሳ ይሄ ነዉ።
በራሱ ጥቅም ላይ ጨክኖ ለመርህ ይቆማል::ስንት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪዎች ወይም የታዳጊ ሀገራት ተመራማሪዎች እንዲህ አይነት በራስ ጥቅም ላይ ጨክኖ ለመርህ የመቆም ዉሳኔ  እንደሚወስኑ ቤት ይቁጠረዉ። ይሄዉ የካሳ የመርህ ሰዉነት እና የሞራል ማማ ላይ የደረሰ ሰዉ መሆኑን ያስመሰከረ ሌላ ክስተትም በቅርቡ እንደተከሰተ በቅርብ የሚያዉቁት ጓደኞቹ ይመሰክራሉ።
ይሄዉም ካሳ በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ለማከናወን  የኢንቨስትመንት ቦታ ጥያቄ ለክልሉ መንግስት ያቀርባል::ሆኖም እንደሚታወቀዉ በእጅ መሄድ የለመዱ አንዳንድ ባለስልጣናት የካሳን የኢንቨስትመንት ጥያቄ ማጓተት እና አፍነዉ መያዝ ቀጠሉ::አንዳንድ የካሳ የቅርብ  ወዳጆችም በእጅ ካልሄደ ያቀረበዉ ጥያቄ እንደማይሳካለት ሁኔታዎችን እያገናዘቡ አሳሰቡት።
በተለይም ካሳ ያቀረባቸዉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀችቶች ለሀገር በጣም ጠቃሚ መሆናቸዉን እና ለአጠቃላይ የሀገሪቱም ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆናቸዉን የተረዱ ጓደኞቹ የካሳ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተሰናክለዉ እንዳይቀሩ በማሰብ ካሳን እንደ ዘመኑ የኢንቨስትመንት ባህል እና አካሂያድ የሚደረገዉን አድርጎ ስራዉን እንዲጀምር መጎትጎት ጀመሩ::
ሆኖም ካሳ ግን “በሀገሬ ኢንቨስት ማድረግ መብቴ ነው። የኢንቨስትመንት ቦታዎችንም ማግኘት መብቴ ነው። ቦታዎቹንም አገኛቸዋለሁ። የፈጀዉን ያህል ጊዜ ይፍጅ እንጂ አምስት ሳንቲም ለባለስልጣናት ጉቦ አልሰጥም። ፕሮፕጀክቴ ግን እዉን ይሆናል” ሲል በአቋሙ ይጸናል። ከብዙ ዉጣ ዉረድም ብኋላ የተወሰኑት የኢንቨስትመንት የቦታ ጥያቄዎቹ ተቀባይነት አግኝተዉ ወደ ስራ መግባት ችሎ ነበር።
ከካሳ ባህሪ ዉስጥ ልዩዉ እና አስገራሚዉ አለምን የሚያይበት እይታዉ ሁል ጊዜም አዎንታዊ እና ደፋር መሆኑ ነዉ:: ሲናገር ትሁት ነዉ::ሰዉ አያስቀይምም::ንግግር ዉስጥ ቁጥብነት:መርህ እና ብሩህነት ግን ሁሌም አሉ::ስለ ኢትዮጵያ ያለዉ ብሩህነት ልዩ ነዉ:: ተግዳሮትን እና ችግርን ሳይሆን የሚያዬዉ ከችግሩ አድማስ ብኋላ ያለዉን ተስፋ ነበር። ለስለስ ብሎ በትህትና ሲናገር አድማጭ ንግግሩን እንዲያምነዉ የማድረግ ጉልበት አለው።
ሆለታ ምርምር በሚሰራበት ጊዜ ኦሮሚያ ዉስጥ ጀልዱ በሚባል ወረዳ የሚኖር አንድን አርሶ አደር ስለ ድንች ዘር ሲመክረዉ “ይሄን ድንቺ ዘር ምርምሩ በሚያዝህ ቀመር መሰረት ካመረትህ ከአምስት አመታት ብኋላ የተዋጣለት የድንች ዘር ኢንቨስተር ይወጣሃል” ሲል እንደ ጓደኛ ይነግረዋል::ይሄዉ አርሶ አደር የድንች ዘር አምራች ኢንቨስተር ሆኖ የኦሮሚያ ክልል ባዘጋጀዉ ትልቅ  ስብሰባ ላይ ሲናገር “ከዛሬ አምስት አመት በፊት ካሳ የተባለ የሆለታ ምርምር ተመራማሪ የድንች ኢንቨስተር እንደምሆን ሲነግረኝ ሙሉ ለሙሉ አመንኩት። ምርምሩ የሰጠኝንም ምክሮች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ወሰንኩ።
ከሌሎች ባለሞያዎች በተለዬ መልክ ለምን እንዳመንኩት ግን እርግጠኛ አይደለሁም” ሲል በመድረክ ላይ ምስክርነቱን መስጠቱን በእለቱ በስብሰባ ላይ የተሳተፉ ተመራማሪዎች መዝገብው መያዛቸዉን ይናገራሉ። ካሳ በሞያዉ ታላላቅ ሀገራዊ እቅዶችን እያከናወነ ነበረ:: ከተለምዶ ዘር የማዳቀል ምርምር  እስከ ባዮቴክኖሎጅ  ያጠና እና ተግባራዊ ያደረገ ባለሞያ ነበር:: በካናዳ በጀርመን በእንግሊዝ በኢትዮጵያ ብዙ እዉቀቶችን የቀሰመዉ ካሳ  ከሳይንቲስት ተመራማሪነት ወደ ኮንሰልታንትነት በመዛወር የተገባራዊ እዉቀቱን እያሰፋ ታላላቅ አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ ያበረከተ  ታላቅ  የሀገር ተስፋ ነበር።
ካሳ ጌጡ ጣናን የወረሰዉን እንቦጭ ወደ ማዳበሪያነት ለመለወጥ ታላቅ ፕሮጀክት ነድፎ በማቅረብ ተወዳድሮ በራሱ የኮንትራት ድርጅት አሸንፎ እንደነበረና ይሄንኑ ተግባራዊ ለማድረግ  ደፋ ቀና እያለ ነዉ ድንገት ህይወቱ በሰዉ እጅ ማለፉ የተሰማዉ:: የሚያዉቁት ሁሉ የካሳ ሞት የእግር እሳት የሆነባቸዉ በብዙ ምክንያት ነዉ::እሰዉ ጥግ የማይደርሰዉ ካሳ በሰዉ እጅ ሊሞት ከቶም የማይገባዉ የሀገሪቱ ድንቅ ባለ አዕምሮ ነበር በማለትም ጓደኞቹ በጸጸት ይናገራሉ::
ካሳን በቅርብ ከሚያዉቁት ተመራማሪዎች አንዱ አማረ ሀይለስላሴ(Dr.) ስለ ከሳ የሚከተለዉን ምስክርነት ሰጥቷል::
“Kassa is a great thinker. He picked up a small idea of hybrid tomato planting media preparation I and Amenti Chali developed and converted it to business. He supplied the hybrid tomato planting media to upper awash producers and proofed his concept of making a business out of it. his recent effort was to use the water hyacinth extracted from lake Tana as an input to this and develop a big supply chain … very sad to hear his death and I am struggling with myself to accept his death.”
እንደ ካሳ ጌጡ አይነት ድንቃ ድንቅ ዜጎችን ሀገር ስታጣ የእግር እሳት ነዉ !ለወዳጅ ዘመድም ህመም። ለቤትሰብ እማ ምንኛ የልብ ቁርጥማት ይሆን? ካሳ ጌጡ ያባታቸዉን ፍቅር ያልጠገቡ ከአስር አመታት በታች የሆኑ ሶስት ትንንሽ ልጆቹን እና ባለቤቱን ትቶ ገንቦሬ በሚባል ቦታ በተፈፀመበት የደቦ ጥቃት ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
ነፍስህን ፈጣሪ ይማራት
ቤተሰቡን ለመርዳት እንዲሁም በአሟሟቱ ጉዳይ የፍትህ ጥያቄ ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ይሄ የእርዳታ ማሰባሰቢያ GoFundMe ተዘጋጅቷል፤ የቻላችሁ እርዱት። https://gofund.me/dec4035d
Filed in: Amharic