«ኢትዮጵያ እሳት ያለበትን ሀገር ለመርዳት ትሄዳለች እንጂ የሰው ሀገር ገብታ ቆስቁሳ አታውቅም»
– ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺየጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የአምስቱ ዓመት ስመ ገናና አርበኛ የጀግናው የጦር መሪ በየዱር ገደሉ ለሀገራቸው አርበኞችን እየመሩ እያዋጉ የተዋደቁት የራስ መስፍን ስለሺ ልጅ ናቸው፡፡
የኢጣሊያ ፋሽስት ወራሪ ግራዚያኒ ሠራዊት በየካቲት 12 በአዲስ አበባ ከ33ሺህ በላይ ዜጎቻችንን በአካፋ፣ በዶማ እና በጥይት በጨፈጨፈበትና በእሳት ባጋየበት ብሔራዊ የኀዘን ቀናችን ፤ ስለአድዋው ጦርነት፤ ዛሬ ላይ ስለገጠሙን ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም ሀገራችንን ለማስቀጠል ከሕዝብና ከመንግሥት ምን እንደሚጠበቅ ከአዲስ ዘመን ጋር ልዩ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለመነሻ ያህል ስለውልደትና እድገትዎ ጥቂት ቢነግሩን?
ልጅ ዳንኤል፡- ስሜ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ ይባላል:: የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ነኝ:: የተወለድኩት ጎሬ ኢሉባቦር በ1936 ዓ.ም ነው:: ከጦርነቱ በኋላ አባቴ ራስ መስፍን ስለሺ የጎሬ ጠቅላይ ገዢ ተብለው በነበረበት ጊዜ ለእናቴ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ ለአባቴ ደግሞ ሁለተኛው ልጅ ሆኜ ነው የተወለድኩት::
እዚያ ሦስት ዓመት እንደተቀመጥን ጎሬ ላይ በተለይ በጠረፍ በኩል ከእንግሊዞች ጋር የነበረውን ችግር ከፈቱ በኋላ ያኔ ደጃዝማች ነበሩ የጅማ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ራስ ብሩን በመተካት ተሾሙ::
ጅማን እንዲያስተዳድሩ ተልከው እዚያው ጅማ አስር ዓመት ያህል ተቀምጠናል:: አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤታችን ጅማ ከተማ የሚገኘው ሚያዝያ 27 የሚባል ትምህርት ቤት ነበር:: ብዙውን የልጅነት ጊዜያችንን ያሳለፍነው ጅማ ነው::
በዚያን ዘመን በጅማ የነበሩት ትልልቆቹ ችግሮች ሽፍታዎች ቡና ነጋዴውን ገበሬውን ያሰቃዩ ስለነበረ ኮሎኔል ካርሊ ከሚባል የእንግሊዝ ፖሊስ አዛዥ ጋር ሆነው አብረው ያድኑ ነበረ ማለት ትችላለህ::
ጅማ በነበሩበት ጊዜ የጅማን ቡና ቡና ያሰኙት እሳቸው ናቸው:: ከአባ ጅፋር ቤተሰቦች ጋር በጣም በቅርብ በመገናኘት ሁለተኛ የኦሮምኛ ቋንቋ በደንብ አድርገው በመናገር ለኅብረተሰቡ በተለይ ቅርብ ነበሩ:: የራሳቸውም እርሻ ስለነበረ ከሠራተኛውም ከሁሉም ጋራ በቋንቋው ነው የሚናገሩት::
ያው እንደምታውቀው ጅማ የአባ ጅፋር ሀገር ከሚባለው ውጪ ኩሉኮንታ፤ ከፋ ሌሎችም ብሔረሰቦች አሉበት:: በቅርብ ከሁሉም ጋር ይገናኛሉ:: እንደ ሀገረ ገዢ አልነበረም የሚታዩት:: ይልቁንም አብሮአቸው እንደሚሰራ ሰው ነበር የሚያዩዋቸው:: እንደምታውቀው በድሮ ጊዜ ሥልጣን ሲሰጥህ ሥልጣንህን በትክክል ካልተጠቀምክ ንጉሠ ነገሥቱ አካኪ ዘራፍ የሚሉበት ጊዜ ነበር::
አዲስ ዘመን፡-የአባትዎት የራስ መስፍን ስለሺ የአርበኝነት ዘመን ተጋድሎ የት የት አካባቢ ነበር?
ልጅ ዳንኤል፡– በአጭሩ የእሳቸው የአርበኝነት ዘመን አንድ ቦታ ብቻ ተተክሎ የተዋጉበት የለም:: ብዙዎቹ አባት አርበኞች ጓደኞቻቸው ቀዬአቸው፤ አካባቢያቸው፤ የተወለዱበት ሰፈር ነው ሲዋጉ የነበሩት::
ራስ መስፍን ስለሺ ግን ሰባት ጠቅላይ ግዛት ነው የተዋጉት:: ሸዋ፣ ማይጨው፣ ወሎ፣ ትግሬ፣ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ፣ ጎንደር እና ጎጃም ላይ ተዋግተዋል:: ከዚያም አልፎ ቡኖ በደሌ ኢሉባቦር ላይ ተዋግተዋል:: በአጠቃላይ ታሪካቸው ሲታይና ሲነገር ሰባት ጠቅላይ ግዛት ነው የተዋጉት:: በሄዱበት ቦታ ሁሉ አሸናፊ ነበሩ::
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሠራዊት ነበራቸው?
ልጅ ዳንኤል፡– እሳቸው በጊዜው አዲሱን የጦር ስልት ከቤልጂጎች የተማሩ የክብር ዘበኛ ምሩቅ መኮንን ነበሩ:: በዚያን ጊዜ የሻምበልነት ማዕረግ ነበራቸው::
የሻለቅነት ማዕረግ ደርሰው ነው ጦርነቱ የመጣው:: ወደ ማይጨው ሲዘምቱም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ሆነው ነው:: ንጉሠ ነገሥቱ የተለየ ጦር በእሳቸው ስር ሆኖ ነው ማይጨው የዘመቱት:: አሁን ብዙ ጊዜ ማይጨው ላይ ተሸነፍን ነው የሚባለው:: በአባቴ አነጋገር አልተሸነፍንም ነው ይሉ የነበረው::
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
ልጅ ዳንኤል፡– በማይጨው አልተሸነፍንም የጦርነት፤ ስልት ስትራቴጂ ለወጥን ነው የሚሉት:: አንደኛ ያ ሁሉ ሕዝብ በቦምብ ጭስ በአውሮፕላን በመትረየስ ሲረፈረፍ በዚሁ ዓይነት የቀጠልን እንደሆነ ምንም ሰው አይተርፍም:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በዚህ ጊዜ አንድ ነገር ቢሆኑ ቢገደሉ ጦርነቱ እዚያ ላይ ያከትማል:: ለዚህ መድኃኒቱ ሰው ከማስጨረስ የስትራቴጂ ለውጥ ነው ያደረግነው እንጂ የመሸነፍ ጉዳይ አይደለም ነበር የሚሉት::
አዲስ ዘመን፡- ፋሽስት ኢጣሊያ ከ80 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ያደረሰው ጉዳት ምን ይመስላል?
ልጅ ዳንኤል፡– በአድዋ ጊዜ ስለነበረው ከሆነ የምናወራው የመጀመሪያው የኢጣሊያን ጦር ከኤርትራ ላይ ተወርውሮ ኢትዮጵያ ገብቶ ጦርነቱን በከፈተበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት አልነበረውም:: እንዳጋጣሚ ሆኖ በዚያን ጊዜ እንደሚታወቀው ረሀብ ነበረ:: የእርስ በእርስ ጦርነት፤ በሽታ የነበረበት ጊዜ ነው:: በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ደካማ ነች ተብሎ ነው የኢጣሊያን ጦር ሰተት ብሎ የመጣው::
ሆኖም ግን ዶጋሊ ላይ እነ ራስ አሉላ አባነጋ፤ መቀሌ ላይ እነ ራስ መኮንን፤ ሌሎችም እነ ራስ አባተ፤ ደጃዝማች ባልቻ፤ እነ ንጉሥ ሚካኤል ሁሉ ባሉበትና በተሳተፉበት ነው ጦርነቱ ሲካሄድ የነበረው:: በዚህን ጊዜ ነው እምዬ ምኒልክ ሀገራቸውን የውጭ ጦር እንደወረረ ያውቁ ነበር:: አጼ ምኒልክ በጊዜያቸው አስተዋይና ሩቅ የሚያዩ መሪ እንደነበሩ ታሪክም ይናገራል:: በሥራቸው ድል አድራጊነታቸው የታየበት የተገለጠበት ወቅት ነበር::
ይሄንን ልልህ የፈለኩት እሳቸው ይህ ጦርነት እንዲካሄድ ባደረጉበት ጊዜ የኦሮሞው ተወላጅ አማርኛ የማይችል፤ የአማራው ተወላጅ ኦሮምኛ የማይችል፤ የወላይታው፣ የሶማሌው፣ የኮንሶው፣ የትግሬው ሁሉ በቋንቋ ይህን ያህል ተግባብተው የሚነጋገሩበት ጊዜ አልነበረም::
ነገር ግን ሦስት ወር ሙሉ ከዚህ ወደ አድዋ በሚዘምቱበት ጊዜ በውስጣቸው ልክ ቋንቋ እንደሚችሉ እየተግባቡ የሄዱበት ጊዜ ነው:: ይህ ግልጽ የሆነ ታሪክ ነው:: ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረገው የተለያየ ባሕል ቋንቋ ያለው ኅብረተሰብ እነዛ ሦስት ትልልቅ ችግሮች ባሉበት ጊዜ በቂ ስንቅ ሳይዝ ለሀገሩ መስዋእት ለመሆን የተነሳበት 1988 ዓ.ም እንደዚህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ፋሽስት ኢጣሊያ አዲስ አበባ ላይ በየካቲት 12 ያደረሰውን ጭፍጨፋ በተመለከተ እንዴት እንደነበር ቢነግሩን?
ልጅ ዳንኤል፡– እኛ የካቲት 12ትን ስናከብር በዚያን ጊዜ የተጨፈጨፉትን ብቻ አይደለም:: 6ኪሎ ላይ ያለው ሐውልት በብሬዥኔቭ ቲቶ ለኢትዮጵያና ለንጉሠ ነገሥቷም በነበረው ፍቅር ሁለቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከኢጣሊያኖች ጋር ሲዋጉ ስለነበረ፤ የዩጎዝላቪያ መንግሥት ዛሬ ሰርቪያ የምንለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው ያቆመው የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ነው::
በዚያን ጊዜ እንደሚታወቀው ግራዚያኒ የአዲስ አበባ ገዢ ነበር:: የጨካኝ ጨካኝ አረመኔ ጥቁር ሕዝብ እንደ ሰው የማያይ በስም ካቶሊክ ነኝ ብሎ ሰው የሚያስጨፈጭፍ የሚጨፈጭፍ አልገዛም ያለውን ሁሉ የሚያጠፋ የጣሊያን ሀገረ ገዢ ነበረ:: ሆኖም ግን የሱ ሀገረ ገዢነት በዚያን ጊዜ ዋና ዋና ከተማዎችን ከመያዝ ባሻገር ከዚያ ውጪ ምንም ዓይነት ቁጥጥር እንደሌለው ያው በአምስት ዓመቱ የጦርነት ትግል ኢትዮጵያያረጋገጠችውና የተቀዳጀችው ድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም::
ግራዚያኒ በዚያን ጊዜ የንጉሳቸው ልደትና ልጅም ተወልዶ ስለነበር በጊዜው የነበሩ አንዳንድ መኳንንቶች፣ ራሶች፣ ደጃዝማቾች ለጣሊያን የገቡ የተገዙ የቤተክህነትም ሰዎች ባሉበት ስድስት ኪሎ ቤተመንግሥቱ ጋ ትልቅ በዓል አዘጋጅተው ነበር:: በዚሁ ጊዜ ሞገስ አስገዶምና አብርሀም ደቦጭ ከነደጃች ለጥይበሉ ገብሬ፤ ጀነራል መኮንን ደነቀ ነበሩ::
እነዚህ በወቅቱ እልፍኝ አስከልካይ ቢሆኑም የውስጥ አርበኛ ነበሩ ታሪክ እንደሚናገረው:: ብዙ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ:: ሲሞን አደፍርስ የሚባል ወጣት ሞገስ አስገዶምና አብርሀም ደቦጭን ታክሲ ስለነበረው ከግርግሩ ቦታ አሳፍሮ ወደ እንጦጦ ሱሉልታ አሻግሯቸዋል:: ምንድነው የሆነው እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ሲመካከሩበት የነበረ ነው:: ሞገስና አብርሀም የኤርትራ ተወላጆች ናቸው::
የተለያዩ ኤምባሲዎች ይሰሩ ነበር:: እንግዲህ በዚያን ጊዜ ምንአልባት ኤምባሲ ስለሚሰሩ በአርበኖች በኩል የመጠራጠር ነገር አለ:: ኢንፎርሜሽን ለማወቅ አርበኞቹ ያሉበትን ኃይላቸውን ሊናገሩ ይችላሉ በሚል መንፈስ ብዙዎች አርበኞች በጥንቃቄ ነበረ ሲጓዙ የነበረው::
ዋናው ነገር ምንድነው ሰዎቹ በተዘጋጀው በዓል ላይ አደጋ ለመጣል ስለወሰኑ የእጅ ቦምብ በመያዝ በሚቻላቸው ጠጋ ብለው ብዙ ኅብረተሰብ በነበረበት ጊዜ የእጅ ቦምብ ወደ ግራዚያኒ ይወረውራሉ:: ያው ግራዚያኒ እንደሚታወቀው እጁ ሁሉ ተመቷል:: ከአጠገቡ ያሉት የጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ኃላፊዎች ኮሎኔሎች ጀነራሎችም የተገደሉበት ሁኔታ ነው የነበረው:: በዚህ ሰዓት ከፍተኛ ግርግርና ትርምስ ተፈጠረ::
ግራዚያኒን ቶሎ ብለው ዛሬ ራስ ደስታ ሆስፒታል የተባለው ቦታ ወሰዱት:: እዚያው እያለ ነው የጣሊያን ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ እንደ ተኩላ ሰው እያሳደዱ ለሚገድሉት የጦር ወታደሮቹ የሚታይ የሚነቃነቅ ነገር ያለውን ሁሉ ጨርሱ ብሎ ትእዛዝ የሰጠው::
አዲስ ዘመን፡- ፋሽስቶች በመዲናችን ባደረጉት ጭፍጨፋ ምን ያህል ሕዝብ ነው ያለቀው?
ልጅ ዳንኤል፡-እንግዲህ ግማሹ ሰው ከ25 እስከ 35 ሺህ ሕዝብ ተገድሏል ይላል:: በተደጋጋሚ የሚነገረው ግን 33ሺህ ሕዝብ አዲስ አበባ ላይ አልቋል ነው
የሚባለው:: ይህ እንግዲህ ከተለያዩ ጸሐፊዎች ቦታው ላይ ከነበሩት ተውጣጥቶ አማካኝ ሆኖ የተገኘው 33ሺህ ሕዝብ አልቋል የሚለው ነው:: ያኔ በዚያ ድብልቅልቅና ጩኸት እልቂ እሳት መሀል ነፍሱን ለማዳን ሁሉም በየአቅጣጫው ከመሸሽ ከመሮጥ በስተቀር ማን ነው ቆሞስ የሞተውን ሰው የሚቆጥረው? ነፍሱን ለማዳን ወደቤቱ ሸሽቶ ሲገባም ናፍታና ቤንዚን እየተርከፈከፈ ከነቤቱ የተቃጠለ ሕዝብ ነው::
ከፊሉ እየሮጠ ሲሄድ ከኋላው በአካፋ አንገቱ እየተቆረጠ ወድቋል:: ግማሹ በጥይት ተመቷል:: እናቶች እኮ ሞተው ልጆቻቸው የእናቶቻቸውን ጡት እንደያዙ መሬት ላይ የተገኙበት ጊዜ አሰቃቂ ጊዜ ነበር:: በጊዜው የነበሩት ሰዎች ሲናገሩ ደርሼባቸዋለሁ:: ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ በተለይ የቤተመንግሥቱ ሰፈር አዲስ አበባ በሙሉ የክረምት ውሃ እንደሚጎርፈው ደም በደም ተጥለቅልቃ ነበረ፤ አሰቃቂም አሳዛኝም ነበር::
ምንም ጎበዝና ጀግና ብትሆን ደም እየረገጥክ በምትሄድበት ጊዜ መፍራትህ አይቀርም:: ነገም አንተም እንደዚያው እንደምትሆን ታውቃለህ:: ያለቀው አለቀ:: የተረፉት ተረፉ::
ያንን ካደረጉ በኋላ እነሞገስና አብርሀም ደቦጭ በዚያ ግርግር መሀል አምልጠው ወደ ሱልልታ ሄዱ:: ሲጓዙ ሻለቃ መስፍን ስለሺ (ራስ) ያሉበት ጦር ሰፈር ይደርሳሉ:: ሻለቃ መስፍን ስለሺ ጋ ሲደርሱ ቶሎ አልተቀበሏቸውም:: አንደኛ እንደዛሬ ስልክ የለም:: አዲስ አበባ የሆነውን ነገር ወዲያውኑ የሚሰሙበት ዕድል አልነበራቸውም::
እንደዚህ አድርገን ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለን አምልጠን ነው የመጣነው ብለው በሚናገሩበት ጊዜ ፈጥነው ለማመን አልቻሉም:: ይመስለኛል ወይ ሞገስ ወይ አብርሀም ከአባቴ ቤተሰብ ጋር ተጋብተዋል::
ቢያውቁትም በዚያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ኤምባሲ ውስጥ ይሰሩ ስለነበረ ደግሞ በድንገት እንዲህ አድርገን መጣን ሲሏቸው ለማመን ተቸገሩ:: መቼም የጦር ትምህርት የተማረ መስዋዕት ሆኖ በዚህ ቦታ ላይ እየታገለ ያለ ሰው በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእናቱም ልጅ ብትመጣ ቶሎ አይቀበልም::
ስለ ሞገስና አብርሀም የተጻፉ አንዳንድ መጽሐፍት ላይ ኤርትራዊ ስለሆኑ ጠርጥረዋቸው ነው ይላል:: አይደለም በዚያን ዘመን ኤርትራ፣ አማራ፣ ኦሮሞ የሚባል ነገር የለም:: ተቃቅፎ አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው::
ሀገሪቷም ድሀ ሀገር ነች:: ያለውን ተካፍሎ በሚኖርበት ጊዜ የዘር ነገር አልነበረም:: የዚህ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ ከመጣ በኋላ የምናውቃቸው ሳይሆን እነዚህ ጥራዝ ነጠቅ ጸሐፊዎች ትክክለኛውን ታሪክ እያዛቡ ዛሬ የምንጋጭበትን የፈጠሩ ቅጥረኞች በሚጽፉት በዚያ ተላከከ::
እነዚህ ሰዎች እሳቸው ጋ መጥተው ያለውን ኢንፎርሜሽንና አዲስ አበባ ላይ የተደረገውን ግራዝያኒ ላይ የደረሰውን በደምብ ሲረዱ ምንድነው የሆነው ሰዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ አስይዘው ከእሳቸው እንዲለዩ አደረጉ:: ማለፊያ ሰጧቸው:: ፈቀዱ::
ግዛቱ ያኔ የአርበኛ ግዛት ነው:: ትዝ ይልህ እንደሆነ በታሪካችን እንደሚታወቀው ፍቅረማርያም በቀበና፤ ደጃች ባልቻ እነደጃዝማች አበራ እነ ሻለቃ መስፍን የድሮ አሁን የነበርንበት ግቢ ድረስ መጥተው በየአቅጣጫው አዲስ አበባን ከበው ነበር::
ግንኙነትና መነጋገር አለመኖሩ ነው እንጂ አንድ ላይ ሆነው ማጥቃት የማድረግ ስልቱ ቢኖር ውጤት ይኖረው ነበር:: ለሁሉም አብርሀምና ሞገስን አሳለፏቸው:: ከዚያ በኋላ ወዴት እንደደረሱ አይታወቅም:: ሽፍቶች ገደሏቸው ነው የሚባለው:: ምንም የሚታወቅ ነገር የለም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለፋሽስት ጣሊያን አንበረከክም ብለው ሀገራቸውን በጀግንነት ጠብቀዋል:: ይህ ለሌሎች የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ያበረከተውን ሞራልና አስተዋጽኦ እንዴት ያዩታል?
ልጅ ዳንኤል፡– ያ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪክ በወርቅ የተቀባበት የተጻፈበት ወቅት ነው:: ባዶ እግሩን ባለው የተወሰነ ትምህርት ሀገር ምን እንደሆነ፤ ሕዝብ ምን እንደሆነ የሚያውቁት የኢትዮጵያ ጀግኖች ባደረጉት ድል ዓለም ተደንቋል::
እንኳን የዓለም ጥቁር ሕዝብ ይቅርና በኢምፔርያሊዝም ስር የነበሩት መላው ጭቁን ሕዝቦች በሙሉ የድል ማድረግን የይቻላልን መንፈስ የተጎናጸፉበት ነው::
አሜሪካን በየደሴቶቹ ያሉት እነ ጃማይካ እነ ኩባ እዛ ሰፈር ያለው በሙሉ ተነሳሽነትና ሞራል ለነፃነት የመዋጋት ድል ለማድረግ ይቻላል የሚለውን ታላቅ ትምህርት የቀሰሙት ከእኛ ጀግኖች ነው:: ኢትዮጵያን እስከ አሁን ድረስ ትልቅነቷን እያሳየ ጠላት ለተወሰነ
ጊዜ የነበረበት ታሪክ ነው ብዬ ነው እኔ የምወስደው:: ይሄን ደግሞ የእምልበት ምክንያት ምንድነው ብትለኝ አንበገርም የበላይ ነን ሲሉ የነበሩትን ነጮች ያወደመ ቅስማቸውን የሰበረ ታላቅ ታሪክ ነው::
በዚያን ጊዜ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን ዛሬ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ነገር የሚያንገበግባቸው ብዙ ነጮች አሉ:: አሁንም እየተከሰተ ያለውና ያለብን ትልቁ ችግር ከዚያ ጋር የተያያዘ ነው::
ሕዝቡ እየበዛ በሄደ ቁጥር ኢኮኖሚው እየተጣበበ ችግረኛ እየበዛ በሄደ ቁጥር ኢትዮጵያን ለማጥፋት ወይንም ለማዳከም በቀረጹት ፕሮግራም መሠረት ብዙ ቅጥረኞች ሀገራችን ውስጥም ውጭም እንዳሉ እንደሚያሰማሩ ግልጽ ሆኖ እያየነው ነው::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ በሠራዊታችን ላይ የተፈጸመውን ጥቃትና አረመኔያዊ ድርጊት እንዲሁም በማይካድራ ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ እንዴት ያዩታል?
ልጅ ዳንኤል፡– ሰዎች እኮ ነን:: ደካሞች ነን:: ዛሬ ያለነው እኮ ለሆዳችን ነው የምንኖረው:: ለሀገራችን ለሃይማኖታችን ለባሕላችን አይደለም:: ዛሬ ላይ እየተደረገ ያለው ጭፍጨፋ የሚያሳፍር ከኢትዮጵያውያን የማይጠበቅ ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት አንገቱን ቆርጦ የሚጥልበት ጊዜ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ነገር በድሮ ታሪካችን ላይ አልነበረም:: አማራና ኦሮሞ ሲዋጋ አልሰማንም::
ትግሬና ሌላውም እርስ በእርሱ በትናንሽ ነገር ይጋጭ እንደሆን እንጂ እንደዚህ ዓይነት ዘር የማጥፋት የእኔ ዘር ካልሆነ ብሎ የሚደረግ ነገር በሕልማችን አድርገነው ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አልነበረም:: ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም:: የተደረገው አሰቃቂ አሳፋሪ ድርጊት ነው::
ይህ ድርጊት ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ስም በዓለም ረሀብተኛ በሚል ሲነሳ የነበረውን አሁን ደግሞ ጨካኞች ገዳዮች የሚያሰኘውን ስም አሰጥቷል:: ዋናው ነገር ግን ዛሬ ያለው ዓለም እንደ ድሮው አይደለም:: ያነባል:: ያያል:: የተደረገውም የሥልጣን ሽኩቻ የበላይነትን ለማስጠበቅ እንጂ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ተሳትፏል ማለት አይደለም:: እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ቀደም ሲል ይሄንን ያደረጉት ቅጥረኞች ናቸው::
የኢትዮጵን ስም ለማጥፋት ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የተደረገ ነው:: ለምሳሌ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አስር ዓመት ሙሉ እንደምታየውና እንደምትከታተለው ጣሊያኖች እኛ የምንሰራውን አይወዱም:: ነጮች እኛ የምንሰራውን አይወዱም:: ለምንድነው ካልክ ታሪክ እያስታወስን፤ ትውልዱን እያነቃን ነው:: በዚያም መሠረት ሕዳሴ ግድብ እኮ እየተገደበ ነው::
በዓሎቻችንን በምናከብርበት ጊዜ ጠመንጃ እናንሳ አይደለም ያልነው:: የታሪክ ቤት ስለሆነ ቅጥረኞች ይሄንን ቤት ለማፍረስ ታጥቀው ተነስተዋል:: ይሄ ነው ሕዝቡ ያልገባው ነገር:: በየፍርድቤቱ በየጋዜጣው የሚደረገው በቅጥረኞች ኃይል ነው:: ማነው የሚከፍላቸው ካልን ግብጽ ሊከፍላቸው ይችላል:: የፋሽስት መንግሥት ሊከፍላቸው ይችላል::
አሜሪካ የዛሬ ስድስት ሰባት ወር የተደረገውን አይተናል:: ይታመናል እንዴ:: እነሱም ጋ እየተከፈለ ስለተደረገ አሁን የእኛ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ትልቁ ጸባችን ከቅጥረኞች ጋር ነው:: ለምንድነው ቢባል ታሪክ ይዘን ወጣን:: ፈረንጆች ምኒልክ እንዲህ አደረገ የሚባለውን መስማት አይፈልጉም::
የአድዋ በዓል ዛሬ እኔና አንተ የምናከብረው የጥቅምት 23 የሁለተኛውን የጣሊያን ጦርነት አባቶቻችን እንደገና ከ40 ዓመት በኋላ ጣሊያን ሰንቆ የመጣውን ባያሸንፉ ኖሮ የካቲት 23 አድዋ በዓል አይከበርም ነበር:: ስለዚህ አሁንም ቢሆን የካቲት 12፤ የካቲት 23፤ ሚያዝያ 27ን እያስታወስን እየዘከርን ስንሄድ ኢትዮጵያችንን ልጆቻችንን ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ለባሕላቸው የሚሞቱ የሰው የማይፈልጉ የራሳቸውን ተከራክረው የሚይዙ እንዲሆኑ አድርገን እየፈጠርን ነው:: ያ አልተፈለገም ለማለት ነው::
አዲስ ዘመን፡-በትግራይ ሕዝቡን ሰላም ለማሳጣት የሚንቀሳቀሱትን ኃይሎች በተመለከተ የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር እንዴት ያያቸዋል? የአድዋን ድል በተመለከተ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መሪነት ዘምቶ ያመጣው ድል ነው:: አስተያየትዎን ቢገልጹልን?
ልጅ ዳንኤል፡– አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ ሌሎችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ናቸው:: የየግላችንን የየብሔራችንን የሚያስታውሱን እንድንከፋፈል የሚፈልጉ የሌለውን ልዩነት እየፈጠሩ ጸጉር እየሰነጠቁ ከሚያጣሉን በስተቀር አንድ ነን:: እኔ ለምሳሌ ከሁለት ነው የተወለድኩት:: አንድ ቀን በሕይወቴ ከየት እንደመጣሁ አስታውሼው አላውቅም::
ኢትዮጵያዊነቴን ነው የማውቀው:: ሁላችንም በዚህ ነው ያደግነው:: ይሄንን ለማበላሸት በሚፈልጉበት ጊዜ አንተ አማራ ነህ፤ አንተ ኦሮሞ ነህ፤ አንተ ትግሬ ነህ እየተባለ በየትምህርት ቤቱ ሲሰበክ የነበረው? መጀመሪያ ፈረንጆች በየትምህርት ቤቱ ፒስ ኮር እየተባለ የመጡት በሙሉ አንዴ ፊውዳል፤ አንዴ አርስቶክራት አንዴ የመደብ ትግል እያሉ
ኢትዮጵያን በታተኗት:: ኢትዮጵያ አትበታተንም:: እኛ በጊዜያዊ መልኩ እንበታተን ይሆናል:: ኢትዮጵያ ግን መቼም አትበታተንም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ስትፈጠር ፈልጎ የተገናኘ ሕዝብ ነው:: ፈልጎ የተገናኘ ባሕል ነው::
የራሱ ቋንቋ ሃይማኖት ባሕል ያለው ሀገር፤ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ሳይባል እንደፈለገ ተጋብቶ የሚኖረውን ሀገር ውስጥ ገብተህ ልለያየው ብትል አንተ ራስህ በግል ተበጣጥሰህ ትቀራለህ እንጂ ኢትዮጵያ አትበጣጠስም:: በእኔ አስተሳሰብ በእርግጠኝነት ልናገር የምችለው ይሄ ነው::
አሁን ትግራይ ላይ እየተደረገና እየሆነ ያለው በተወሰኑ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ያለ ነገር ነው:: ይሄ ነገ በኦሮሞዎቹም በሶማሌዎቹም በሌላውም ሊኖር ይችላል:: ሕዝቡ ውስጥ ያለ ነገር ግን አይደለም:: ሕዝቡ ከድህነት የሚወጣበትን መንገድ ነው እየታገለ ያለው::
ሕዝቡ ከድህነቱ እንዳይወጣ የበላዮች ነን ብለን ሥልጣን የያዝን ክፍሎች ያንን ነው እያሸነው ሕዝቡ እንዳያድግ አንጎሉ እንዳያስብ እያደረግን ያለነው::
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት የወሰደውን እርምጃ እንዴት ያዩታል?
ልጅ ዳንኤል፡- ትክክል ነው:: ሕግ ማስከበር፤ ሕግ የበላይ መሆኑን በተግባር ማሳየት ማድረግ የማይችል መንግሥት መንግሥት መሆን አይችልም:: ስለዚህ ሕግና ሥርዓትን ማስከበሩን የግድ መቀጠል አለበት::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ ለውጭ ጠላት ተንበርክካ አታውቅም:: አሁን ደግሞ የውጭ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ቅጥረኞችና ተላላኪ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት እየተፈታተኗት ይገኛሉ:: መንግሥትን ወደ ጦርነት በግድ ለማስገባት እየተነኮሱ ይገኛሉ:: ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት? ለትውልዱስ ምን ይመክራሉ?
ልጅ ዳንኤል፡- በኢትዮጵያ ላይ ጦር ሲሰነዘር ዛሬ አይደለም:: ከ600 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረ ያለ ነው:: ለእኛ አዲስ ይሆናል እንጂ ለአባቶቻችን አዲስ አይደለም:: በአንድ መንፈስ በአንድ ኃይል ለሀገሪቷ መስዋእት ለመሆን መቆም ነው የሚበጀው:: ሱዳን ባለውለታችን የነበረች እንደ እህት ወንድም እንደ ጓደኛ ሆነን በመልክ እንኳን የማንለያይ ሕዝቦች ነን::
እኛም እነሱን ስንደግፍ እነሱም እኛን ሲደግፉ ኖረዋል:: እንግሊዝ እንዲወጣ ካደረግነው ክፍል አንዱ እኛ ነን:: የግብጽንም ተጽእኖ በተመለከተ እነቴዎድሮስ እነ ዮሐንስ አካኪ ዘራፍ ሲሉላት የነበሩት እኛው ኢትዮጵያውያን ነን:: ግን ዘመኑ ተለወጠና ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ቅጥረኛ የበዛበት፤ ሀገርን እንደ ሀገር ባሕሏን ክብሯን የማያውቅ ትውልድ ተፈጠረና ዛሬ ኢትዮጵያና ሱዳን ጠረፍ ላይ ተፋጠጡ ሲባል እኔ ግራ ነው የገባኝ::
አባቴ ራስ መስፍን ስለሺ ያኔ በጠላት ወረራ ዘመን ሻለቃ ማዕረግ በነበራቸው ጊዜ ሁለት ጊዜ ሱዳን በእግራቸው ሄደዋል:: ሱዳን የሄዱበት ምክንያት አንደኛው ሬድዮ ለማምጣት ነው:: ሁለተኛ በዚያው አጋጣሚ የአርበኞችን ወረቀት እየላኩ ለጃንሆይ የሚልኩበት ጊዜ ነበር:: ያ ወረቀት ነው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ላይ አርበኞች እየተዋጉ ናቸው ይኸው ወረቀቱ እነ እከሌ እነ እከሌ እነ እከሌ ብለው ተናግረው ኢትዮጵያ እንዳልተማረከች በጣሊያን ስር እንዳልሆነች የገለጹበት አንዱ እሱ ነው::
በሁለተኛው ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱን በሱዳን አድርገው ይዘው የመጡት ያኔ ሻለቃ የነበሩት ራስ መስፍን ስለሺ ነበሩ:: ስለዚህ ሱዳንን ያውቁታል:: ለሱዳን የነበራቸው
ፍቅር ቀላል አልነበረም:: ከነአርበኞቻቸው የተሰጣቸው ክብር የተደረገላቸው መስተንግዶ ቀላል አልነበረም:: ያንን እየሰማን ያደግን ሰዎች ነን:: እኔም በአጋጣሚ በደርግ ጊዜ ኢዲዩ ውስጥ ሆኜ ሱዳን ነበርኩ:: የሱዳንን ሕዝብ እንደአባቶቻችን ያህል ባላውቅም ኖሬበታለሁ:: አውቀዋለሁ:: በጣም ከልክ ያለፈ ደግና ጥሩ ሕዝብ ነው:: በሃይማኖታቸውም አክራሪ አይደሉም::
ኢትዮጵያውያንን ሲያዩ ፍቅር ነው:: አሁን ይሄ ተከስቶ ሳይ ቀደም ሲል የተኮተኮቱ በመጥፎ መልክ እንዲያዩን የተሰባሰቡት የተደራጁት ናቸው ዛሬ ይሄንን የሚያደርጉት እላለሁ:: በደቡብ፣ በሱዳን፣ በግብጽ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል:: ከሶማሌ ጋር ስንዋጋ ኖረናል:: ዛሬ እንዴት ነን? እኛ እኮ ጠላት የተባልነው ነን ሄደን የሶማሌን መንግሥት በእግሩ እንዲቆም ያደረግነው::
ኢትዮጵያ እሳት ያለበትን ሀገር ለመርዳት ትሄዳለች እንጂ የሰው ሀገር ገብታ ቆስቁሳ አታውቅም:: በመንግሥት በኩል ያለው ትእግስት ግሩም ነው:: አንደኛ የሱዳን ጦር ይሰለቸዋል:: የሰው ጠረፍ ውስጥ እንደገባ ያውቃል:: የኢትዮጵያ ጦር ትግራይ ላይ ያደረገው ሕግ ማስከበር አላዳከመውም:: አንድ ዕዝ ነው::
100 ሚሊዮን ሕዝብ ያለን ሕዝቦች ነን:: ጠመንጃ እኮ መያዝ የለብንም:: ከተፈጥሮአችን ሀገራችንን ማስነካት የማንፈልግ የማንፈቅድ ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ሆ ብሎ መነሳትም ይቻላል:: ይሄ የተደረገው ጨዋታ በቅጥረኞች የተፈጸመ ነው:: እኛን ለማዳከም እየተሞከረ ያለውም በዚህ መንገድ ነው::
አዲስ ዘመን፡-ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን::
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013