እነሆ ዛሬ የ ህ.ወ.ሓ.ት ፋሺዝም ያስከተለው የሲኦል ህይወት ተጀምሯል!!!
ጌታቸው ረዳ
ወደ ዋናው ርዕሰ ከመግባቴ በፊት መጀመሪያ የሐዘን መግለጫየን ላስቀምጥ። ሰሞኑን በወያኔ ፋሺሰት ነብሰገዳዮች ህይወቱን ባጭር ለተቀጨው የፈንቅል እንቅስቃሴ መሪ ለነበረው መምህር “የማነ ንጉሰ” ነብስ ይማር በማለት የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ ሐዘኑን ይገልጻል። ወያኔ ሲፈጠር “ፈሪ” ስለሆነ ባስተሳሰብ የሞገተውን በጥይት በመቅጨት የለመደበት ባህሪው ስለሆነ ብዙ ሺዎቹን የትግራ ተወላጆችና ኢትዮጵያዊያን ተቀናቃኞቹን ቀጭቷል። መስዋዕቱ የማነ ሲሰጣቸው በነበረው አንዳንድ ሃሳቦች ባይጥሙኝም፤ በመራራው ረዢም የትግል ጉዞ ካፈራናቸው የትግራይ ወጣቶች አንዱ የሆነ ይህ የትግራይ ወጣት ኮቴአችንን በመከተል “ወያኔ” በፍርሃት እንዲርበደበድ ያደረገው ጉልህ ሚና የማይረሳ የትግራይ ወጣት ታጋይ ስለነበር አድናቆቴን ልቸሮው አፈልጋለሁ። ነብስ ይማር! አምላክ ለቤተሰቡ መጽናናትን ይስጥ! ትግሉ ይቀጥላል!
አሁን ወደ ርዕሳችን ልግባ።
እንደምታውቁት ልክ እንደ ኦሮሞ ማሕበረሰብ 95% በሚያስብል ግምት ኦነግን እንደተከተለ ሁሉ በተመሳሳይነት ቁጥር ትግሬዎችም እንዲሁ በ1928 ዓ.ም ጣሊያኖች ለኢትዮጵያዊያን ትተውልን የሄዱት የቀየሱትን የፋሺዝም ርዕዮት “የአንጎል አጠባ” ተጠቂዎች ናቸው። የትግራይን ሕዝብ ከኢትጵያዊነት ስነ ልቦና ለማላቀቅ ረዢም ጊዜ ተወስዶ በርካታ የአእምሮ ማጠቢያ ቴክኒኮችን (ዘፈኖችን፤ተውኔቶችን፤መጽሐፍቶችን፤ንግግሮችን…. ወዘተ) ተካሂደዋል።
በሚገርመኝ ሁኔታ የፋሺሰት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ሳይቀር ደደቢት በረሃ ውስጥ ወያኔ የመሰረተው የየካቲቱ 11/1967 ዓ.ም የኢትዮጵያን የባሕር ወደቦችን ለጠላት ለመስጠት እና ፋሺዝም ለማንገስ የተመሰረተው የትግል ቀንና ወር መከበር አለበት ፤ ለዚያ መስዋዕት የሆኑትን እና ለነመለስ ዜናዊ ጭምር የቆመው የመቀሌው ሃውልትም በክብር መያዝ አለበት እያሉ “የወያኔ ፖለቲካ ተቃዋሚ ነን” እያሉ ነገር ግን የወያኔን “አርቲፋክት” (ቅርስ/አሻራ) የሚያከብሩ የፋሺዝም አሽቃባጮች ሳያፍሩ ዛሬም ችግሩ እንዲያብብ ድጋፍ እየሰጡ ነው።
በዚያ ወር እና አመተምህረት የትግራይ ብሔረተኞች የቀየሱትን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነው “የትግሬዎች የፋሺዝም ፖለቲካ” ትግራይ በረሃ ውስጥ ለዚህ ርዕዮት “መወለድና ማደግ” ለሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ስቃይ መነሾ የሆኑት ህይወታቸውን የሰው የወያኔ ታጋዮች ከተሰውትም መሃል የሰው ልጅ በእሳትና በፈላ ውሃ እየለበለቡ ሲመረምሩ የነበሩ ሰው መሳይ አራዊቶችም እንደ ቅዱሳን መላዕክት እንዲታዩ በክብር እንዲነሱ እያደረጉ ነው። በዚህ አሳዛኝ ታሪክ በላንበት ወቅት “የትግራይ ፋሺዝም” በሰፊው ሕዝብ ሕሊና ተቀባይነት እንዲኖሮው የሙታን ድርሳኖችን፤ ግጥሞችን እና ማስታወሻዎችን በየትምህርት ቤቶች እና በዓላት በማሰራጨት ሰፊ የሕሊና አጠባ በመደረጉ ወያኔ እና የትግራይ ሕዝብ ባስተሳሰብ አንድ ናቸው ስል የነበረውን በምክንያት እንደነበር ለበርካታ አመታት ጽሁፎቼን የተከታተላችሁ አንባቢዎቼ የምታውቁት ታሪክ ነው።
እነሆ ዛሬ ምንም በማያውቁ የትግራይ ህጻናት እና ሌላ ቀርቶ አስነዋሪ በሚባል ስነምግባር በውሾችና በፈረሶች “ወገብ” ላይ “ሽጉጥ” እያስታጠቁ በኬሚካል የተቀመመ ቀለም የወያኔ ባንዴራ በእንሰሰታቹ ቆዳ ላይ በመቀባት በወታደራዊ የሙዚቃ ማርሽ እያጀቡ ፋሺስታዊ አይበገሬነታቸውን (Invincibility) በሕዝቡ ጭንቅላት እንዲቀረጽ በማድረግ የትግራይ ማሕበረሰብ በማይወጣው ስቃይ ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል።
ቀደም ብየ በበርካታ ጽሁፎቼ እንደገለጽኩት ኤርትራኖች በተከተሉት የተሳሳተ የትግላቸው በመጨረሻ ያገኙት ትርፍ ቢኖር “የረገሙዋትን ኢትዮጵያን ተመልሳ እንድታኖራቸው በስደት መልክ መለመንን፤ ውርደትን ፤ ስቃይን ፤ አካለ ስንኩልነት…” ነው። ለዚህ ሁሉ ውርደት ኢሳያስ አፈወርቂ ነው ቢሉም መጀመሪያ ተጠያቂዎቹ ማንም ሳይሆን ኤርትራኖች በራሳቸው ያመጡት ስቃይ ተጠያቂዎቹ እራሳቸው እንደሆኑት ሁሉ” በትግራይ ሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ስቃይም ተጠያቂው ወያኔና እንዲሁም 99% የትግራይ ምሁራኖች እና እራሱ የትግራይ ሕዝብ እንዲሁም የወያኔ ዲቃላው “አብይ አሕመድ” እንደሆኑ ከሦስት ሳምንት በፊት በጻፍኩት ላይ መመልከት ይቻላል።
ኤርትራኖች ከ29 አመት በፊት ዘምባባ እና ከበሮ ይዘው እየዘለሉ ሲጨፍሩ የነበረውን የስካርና የትዕቢት መንፈስ ዛሬ እንዴት እንደበረደላቸውና ለስቃይ እንዴት እንደታደረጉ የታዘብነውን ያህል ትግሬዎችም የፋሺዝምን ምስረታ ያበሰረው የካቲት 11 በመጣ ቁጥር፤ ሕሊና ቢስ የኪነት ሰዎችን እየሰበሰቡ ሕዝቡን እያማለሉ ሲያስጨፍሩት “ትግራይ አሁን ላለቺው የሲኦል ህይወት” እንደሚዳርጓት ስንናገር ነበር። እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ኤርትራኖች “በስካራቸው ዘመን” ጆሮአቸው መስማት እንዳቃታቸው ሁሉ ፤ እኔ እንደ ትግሬነቴ አሁን ያለው እየመጣ የነበረው አደጋ ስለታየኝ እየተጓዛችሁበት ያለውን አደገኛ ጉዞ ተሎ ካልገታችሁት በትግራይ ሕዝብ (በራሴ ዘመዶችም ጭምር) ላይ መራራ ህይወትን ያስከትላል ብየ ሳስጠነቅቅ ማንም ሰሚ አልነበረም። በሚገርም ሁኔታ አሁን ወያኔዎች “ተከበብን” እያሉ ያሉትን ሁኔታ በ4 መዓዝን ተከብብው መውጫ በር እንደሚያጡ በቃለ መጠይቄ ገልጬ ነበር። ወቅቱም “ሕገምንግሥታችን ከተነካ በየመንደራችን እንከፋፈላለን ወይንም ወደ ሌላ ሁለተኛ የጦርንት አዙሪት እንገባለን” ሲል “ስብሓት ነጋ” በተናገረበት ወቅት” (በ1997 ምርጫ ይመስለኛል ፤ አመተምህረቱን በትክክል ባላስተውሰውም) አበበ ሃይሉ በሚያዘጋጀው ሳንሆዘ ዩኒቨርሲቲ ራዲዮ ጣቢያ ላይ ስብሓት ነጋ በሰነዘረው የግንጠላ አማራጭ እንዳብራራ ቃለመጠይቅ አድርጎልኝ አሁን እየታየ ያለው “በተለያዩ የጠላት ድምበሮች ተከብበናል” እያሉት ያለውን ኡኡታ እንደሚከሰት ተንበየ ነበር። እነሆ ዛሬ የ ህ.ወ.ሓ.ት ፋሺዝም ያስከተለው የሲኦል ህይወት ተጀምሯል።
በተደጋጋሚ እንደምታውቁት የትግራይ ምሁራን ራሳቸውን ለፋሺዝም አምልኮ ሸጠዋል። የወያኔ መሪዎች የትግራይ ምሁራንን በመያዝ ሕዝቡን በማሕበራት አደራጅቶ የሕዝቡን ሥነ-ልቦና ለራሱ በሚመች በመበዝበዝ በቁጥጥራቸው ሥር አድረገውታል። በቁጥጥር ስር ለማድረግ ዘገምተኛና ረቂቅ የትግራዋይነት “ኔትወርክ” በመዘርጋት ያከናወኑት ስልት የአእምሮ አጠባ የተከናወነበት የትግራይ ሕዘብ በፋሺዝም ትምህርት እንደታጠበ እንኳን ሕዝቡ እራሱ የተሸረበለት ሴራ አይገነዘበውም። ሌላ ቀርቶ በጣም ብሩህ ፣ በጣም ራሳቸውን የሚገነዘቡ ሰዎች የሚባሉት እንኳን በዚህ መሰሪ ወጥመድ ተይዘው ሊወድቁ ችለዋል፡፡ የወያኔ ፋሺቶች ያከናወኑት ተመሳሳይነቱ “ለብ/ሞቅ ባለው/ ባለው ድሰት የተጣደቺዋን የእንቁራሮቷ ታሪክ የተሰማት ደስታ እና መጨረሻ ውሃው ቀስ እያለ እየፈላ እንዴት ጠብሶ እንዳቃጠላት ሁሉ፤ የትግራይ ሕዝብም በጭፈራ ጦዞ የትዕቢት ሐረጎችን ያዘሉ ዘፈኖችን እያመነዠከ ቀስ እያለ በቀበኞቹ ተንኮል እራሱን ለማቃጠል በቅቷል።
እደኔ እንደምረዳው ለመፍትሄ አስቸጋሪ የሚያደርገው ነገር፡ ዛሬኢም እንደዚያ ችግር ውስጥ ገብቶ ፤ ለዕርዳታ የመጣለትን እህል “አዳኞቼ” የሚላቸውን ወያኔዎች መንገድ ላይ ጠብቀው እህልና መድሃኒት የጫኑ መኪኖችን ሲያጋዩዋቸው እያየ ተቃውሞ ያለማሰማቱ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር የትግራይ ሕዝብ የአንጎል አጣባው የተኮናወነው በወያኔ መሪዎች ምስል ስለተገነባ ወያኔን አስወግዶ በራሱ አስተሳሰብ መቆም እንደማይችል ስላሳመኑት በአሳዛኝ ሁኔታ ግማሽ ጎኑ ጭለማ ውስጥ እየገባ ነው። ከወያኔ አስተሳሰብ ተላቅቆ በእራሱ ምስል እንደገና ለመቆም የታጠበበትን ዘመን ያህል እንደገና ያን ያህል ብዙ አመታትን ይጠይቃል። እንደገባኝ ከሆነ “ሕዝቡ እራሱን ትንሽ አድርጎ ‘ወያኔን’ ትልቅ አድርጎ እንዲያምን ተደርጓል።
ዛሬ በየሚዲያው የምናደምጣቸው የወያኔ ጀሌዎች የበለጠ ሰብዓዊነት የጎደለው ነገሮችን ሲያደርጉና እየዋሹ መሆናቸውን እያወቁም ቢሆን ለነገ የሚባል ጭንቅላት አልተፈጠረባቸውም፡፡ በሚገርም ሁኔታ የወያኔ አጃቢዎች ያልበሩትም ጭምር እየተከናወነ ባለው ጦርነት የወያኔ መሪዎች በሚያሳፍርና በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተማረኩ አይተው ምክንያቱ በማናውቀው ሁኔታ “የቡድኑ አካል” ሆነው የወያኔ ቱልቱላ አዳማቂዎች ሆነው የተቀላቀሉ ብዙ ሰዎችን ታዝበናል።
ወያኔ በደረሰበት የማያንሰራራ ምት ምክንያት የወያኔ ሚዲያዎች “አልሞትንም” ለማለት ፋሺዝም ማራኪ ለማድረግ የሚያሰራጩዋቸውን ምስሎችን ተመልከቱ። መሳጭና የብሔረተኞችን ልብ የሚያማልሉ ሙዚቃዎችን በማስደመጥ የተከታዮቻውን የልብ ምት ለማረጋጋት ሌት ተቀን እየጣሩ ነው። የዚህ ቀቢሰ ተስፋ ዓላማ “ዓይነ ስውር ታዛዥነትን” ቀጣይነቱ እንዲኖሮው መግፋት ነው። ሆኖም የወያኔ ትግራይ ፋሺዝም ‘የትግራይ ሕዝብ ዛሬም የሙጥኝ ካለ’ ወደ ማይወጣው የገሃነብ ህይወት በራሱ ፈቃድ እየገባ መሆኑን ግንዛቤ እንዲይዝና ውጭ አገር በምቾት እየኖሩ ያሉት “የወያኔ ትግራይ” ጀሌዎች አሁን እየነደደ ከሚታየው ከሚንቀለቀለው እሳት የራቁ ስለሆኑ ጦርነት ለነሱ “እንደ ኳስ ጨዋታ” አድርገው ጦርነቱ እያበረታቱት ስለሆነ፤ እራሳቸው ወደ ጦርነቱ መክተት ያልፈቀዱ ከነዚህ “የሃሰት ቡድኖች” ራሳችሁን እንድታርቁ ምክሬን እለግሳለሁ።