>

ከዋናዎቹ የአድዋ አዝማቾች መካከል...!!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ከዋናዎቹ የአድዋ አዝማቾች መካከል…!!! 

አቻምየለህ ታምሩ

ከጎንደር ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር በሁለት ዐቢይ ዋና ዋና  ጀግና መሪዎች ስር የተሰለፈ ነበር። የመጀመሪያውና ቀዳሚው የአድዋ ደጀን ጦር በራስ ወሌ ብጡል የሚመራው የበጌምድር ጦር ነበር። ራስ ወሌ የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ሲሆኑ ደጀኑን ጦር ከደብረ ታቦር ተነስተው እየመሩ በቅድሚያ የዘመቱት በአምባላጌ ግንባር ነበር። በነገራችን ላይ ራስ ወሌ የስሜን ባላባቱ የደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ገብሬ ልጅ ናቸው። የደጃዝማች ብጡል ታላቅ ወንድም ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ደራስጌ ላይ ድል ያደረጓቸው ስሜን ለ45 ዓመታት የገዙት የዝነኛው የደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም ታናሽ ወንድም ናቸው።
በሁለተኛ ምድብ የተስለፈው የጎንደር ጦር የሰሜንን ጦር እየመሩ ተከዜን በማቋረጥ ወደ ትግራይ ተሻግረው ወደ አድዋ በዘመቱት በደጃዝማች ገሠሠ ወልደሐና የተመራው ጦር ነው። ደጃዝማች ገሠሠ ወልደ ሐና ከአባታቸው ከመላከ ገነት ወልደ ሐና እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ብጡል የተወለዱ ሲሆን እቴጌ ጣይቱ ታናሽ እኅት ልጅ ናቸው። ይህ ማለት ከጎንደር የዘመተውን የኢትዮጵያ ጦር እየመሩ ወደ አድዋ የዘመቱት  የበጌምድር ገዡ ራስ ወሌና የስሜኑ ገዢ  ደጃዝማች ገሠሠ ወልደሐና ዘመዳሞች ናቸው።
ደጃዝማች ገሠሠ ከአድዋ በኋላ ስሜንን ከ1892 ዓ.ም. -1902 ዓ.ም. ለአስር ዓመታት  አስተዳድረዋል። ስሜን የሚባለው ታሪካዊው የኢትዮጵያ ክፍል ከባምብሎ እስከ ተከዜ ወንዝ የተዘረጋውን ምድር ነው። ይህን የኢትዮጵያ ክፍል ከደጃዝማች ገሠሠ በኋላ ልጃቸው ደጃዝማች አምባቸው ገሠሠና የልጅ ልጃቸው ደጃዝማች ከበደ አምባቸው አስተዳድረውታል

ራስ ወሌና ደጃዝማች ገሠሠ ወልደ ሐና በድምሩ  ከ20ሺ በላይ የጎንደር ጦር እየመሩ አድዋ ዘምተዋል!
ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉ የአድዋ ጀግኖች ሁሉ ይኹን!
Filed in: Amharic