ደረጀ ከበደ
“አዲስ አበባን እናድን” የሚለው የጥሪ ቃል በየፌስ ቡኩ በዩቲዩቡ ተሰራጭቶአል። እኔም ስለአዲስ አበባ ዝም አትበሉ ብዬ እንደአቅሜ ወትውቻለሁ። እንዲያውም የከተማዋን ዝነኛ አርቲስቶችንና ታዋቂ ሰዎችን በመልክቴ ሳስጠነቅቅ “ሰልቃጮችዋን እነታከለ ኡማን፣ እነ አዳነች አቤቤንና እነሽመልስ አብዲሳን እያጀባችሁ አትዙሩ ስል ከርሜአለሁ። ስለአዲስ አበባ የማይጨነቁ ቢኖሩ፣ ያው ፊንፊኔ ብለው የሚጠሩዋት፣ የእኛ ብቻ ናት፣ አናካፍልም፣ የሚሉን፣ ከሁዋላ የመጣ አይን አወጣዎቹ ዘመዶቻችን ናቸው።
አዲስ አበባን እናድን የሚሉ አብዛኛዎቹ፣ በምርጫው ወቅት ህዝቡ ሳይታለል ለአዲስ አበባ ወገንና አለኝታ ሆኖ የከረመውን ባልደራስንና እስክንድርን እንምረጥ ማለታቸው ነው። እስማማለሁ። እንዲያውም ደጋግሜ የምደልቀውን “ምርጫው የተበላ እቁብ ነው” “ብልፅግና ፓርቲ ኮሮጆ ገልብጦም ቢሆን የአዲስ አበባን ማጆሪቲ ለኢዜማ እንኩዋን አሳልፎ አይሰጥም” ማለቴን ለዚች ቅፅበት እገታለሁ።ምክንያቱም ሌላ አንድ ነገር አለ ያልተገነዘብነውና ልጠቁማችሁ የምፍልገው።
እንዲያው ለጨዋታ ያህል ባልደራስ አሸነፈ እንበል። ቀጥሎም ፓርቲው አብላጫ ድምፅ ይዞ ፓርላማ ከገባ በሁዋላ ለከተማዋ የሚበጃትን አይነት መመሪያዎችና ውሳኔዎች በድምፅ የበላይነት ያፀድቃል። ምንም ጥርጥር የለውም። ከሁሉ በላይ ግን አዲስ አበባ ራስዋን የቻለች ክልል ወይም ራስ ገዝ ግዛት እንድትሆን የማድረግም ሃይል ሊኖረው ይችላል።
በፓርላማ የፀደቁ ውሳኔዎችና ፖሊሲዎች ዶኩመንት ከተደረጉ በሁዋላ የሚቀጥለው እርምጃ ምንድነው? ወይም ምን ይቀራቸዋል?
ትክክል!! በተግባር፣ በመሬት ላይ በሚታይ መልኩ ስራ ላይ መዋል አለባቸው።
እዛ ላይ ነው ችግሩ!!! እዛ ላይ ነው ምርጫ ማሸነፍ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የሚገለጥልን።
እያችሁ ወገኖቼ ፖሊሲና ውሳኔን ማፅደቅና መመሪያ ማርቀቅ ላይ አይደለም ድሉ። የተፃፈውን ፖሊሲና የተላለፈውን ውሳኔ በተግባር ማስፈፀሙ ላይ እንጅ። እዛ ላይ ነው የባልደራስ አብላጫ ወንበር መያዝ ብቻውን በቂ የማይሆነውና ከተማዋን በተግባር የአንድ ብሄር መፈንጫ ከመሆን ሊታደጋት የማይችለው። ባልደራስ በፓርላማ ውስጥ የድምፅ ብልጫ ስለአለው በህግ የሚፃፉ መመሪያዎችን ማሳለፍ ይችላል። ነገርግን ውሳኔ በስራ ካልተተረጎመ የወረቀት ላይ ነብር ነው። ምክንያቱም በፀረዴሞክራሲው የአቢይ አህመድ መንግስት በፓርላማ የፀደቁ ፖሊሲዎችና ውስኔዎች የሱን ጥቅም የማያስጠብቁ ከሆኑ እንዳይፈፀሙ ያግዳቸዋል። ይህን የማድረግ ሃይሉም፣ ጠመንጃውም፣ እርሳሱና ልዩ ሃይሉም ያለው በባልደራስ እጅ ሳይሆን በአቢይና በጋንጎቹ እጅ ነው። የፓርላማ ውሳኔዎችን ጋርቤጅ ጥሎ የራሱን ተግባር ሲያከናውን ቢውል ማነው የሚያስቆመው???
ለማለት የፈለግሁት ነገር፣ ፓርላማ ከህግ አስፈፃሚ አካላት ትብብር ውጪ ብቻውን ሙት ነው። ዳኛ በወንጀለኛ ላይ የቅጣት ፍርድ ቢፈርድ ፍርዱን ተቀብሎ ለማስፈፅም ፈቃደኛና ዝግጁ የሆኑ የፖሊስ አካሎችና የእስርቤት ኦፊሰሮች ከሌሉ ምን ፋይዳ አለው? ትዝ ይላችሁዋል? ዳኛው አቶ ልደቱ አያሌውን ከእስር በዋስ ሲፈታቸው ፖሊሶች መጥተው ህግን ረግጠው፣ የዳኛውን ውስኔ ሽረው ሰውየውን በእስር ያቆዩዋቸው?
የአቢይ መንግስት የፈለገውን ነው የሚያደርገው።
ህግ የለም በምድሩ። ጥያቄው ፓርላማውስ በዚህ በስርአተ አልበኛ መንግስት ምን ይጠቅመን ይሆን የሚለው ነው??
አዲስ አበባ ነፃ የሆነች ከተማ የምትሆነው የራስዋ ህብረብሄር የፀጥታ መዋቅርና የሰለጠኑ ልዩ ሃይሎች ሲኖርዋት ነው። ከተለያዩ ብሄሮች የተውጣጡ የራሱዋ ፖሊሶች ሲኖሩዋት ነው። የአንድ ብሔር መንጎማለያ የሌሎች ግን መሸማቀቂያ መሆንዋ ሲቀር ነው። የራስዋ ዳኞች ፍርድቤቶችና መተዳደሪያ ፖሊሲዎች ሲኖርዋት ነው። ያን ለማድረግ በአሁኑዋ በአንድ ብሄር በተጨናነቀችዋ አዲስ አበባ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የተዘረጉት የአንድ ብሄር መዋቅሮችና ስርአቶች መፍረስ ግድ አለባቸው። የተረኛው ፓርቲ ነፀብራቅ የሆኑ እሰራሮችን በላጲስ ማጥፋት ያስፈልጋል ወዘተ!
ስለዚህ ምርጫው አዲስ አበባን በተግባር እያድናትም በወረቀት ላይ ብቻ እንጅ። ምናልባት በይፋ የኦሮሞ አካል መሆኑዋ አሁንም በወረቀት ይታገድ ይሆናል እንጅ በተግባር እኮ የኦሮሞ ክልል ከተማ ከሆነች ሰነበተች።
መፍትሄው– በመራር ትግል– በአዲስ አበባ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የየትኛውም አንድ ብሄር መዋቅሮች እንዲፈርሱ ማድረግ ወይም ለፌዴራሉ መንግስት በሽያጭ መልክ ማስተላለፍ። ምክንያቱም በኤትኒክ ፌዴራሊዝም በተበጣጠሰችዋ ሃገራችን ብሄርና ቁዋንቁዋ የማይጠየቅባት (ከይፋው የስራ ቁዋንቁዋ ውጭ) መዲናችን አዲስ አበባ፣ ተናጥል ብሄሮች የራሳቸውን የጎሳ ስርአት እንዳያስፋፉባትና ሌሎች ብሄሮች ላይ እንዳይጭኑ ማቀብ አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ሌላው አቢይና ሽመልስ ያፀደቁዋቸው አማራውንና ሌሎችን አዲስአበቤዎችን የሚያገሉ የቁዋንቁዋና የስራ እድል መሳተፊያ መስፈርቶችን መልሶ መፃፍ። ሁለት ቁዋምቁዋ የማያውቅ ለፌዴራል ስራ መወዳደር አይችልም የሚሉ መሰሪ ፖሊሲዎችን መቀየር ግድ ሊሆን ነው። እነኚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ብዙ ያልጠቅስኩዋቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ይኖራሉ በእርግጥ። አዲስ አበባችንን በተግባር የኢትዮጵያኖች ሁሉ ከተማ ለማድረግ በአይን የሚታዩና የማይታዩ ብዙ ጥገናዎች ያስፈልጉዋታል።
ይህን ሁሉ ማስፈፀሙ ላይ ግን ዴሞክራቲክ የሆነ፣ የህዝብን ድምፅና ፈቃድ የሚፈፅም መንግስት ሊያስፈልግ ነው። ያ በትግልና በመስዋእትነት የሚመጣ ነው!!!