>

የዘንድሮው ምርጫ እጅግ ውድና ትልቁ ስጦታ! (ጌታቸው ሽፈራው)

የዘንድሮው ምርጫ እጅግ ውድና ትልቁ ስጦታ!

ጌታቸው ሽፈራው

አብንና ባልደራስ ኢትዮጵያን የገደለውን የፖለቲካ ባህል  አዲስ አበባ ላይ እንኩት አድርገው ሰብረውታል!
1) ምርጫ ኖረም አልኖረም፣ ከምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ታቃዋሚዎች እርስ በእርስ፣ ተቃዋሚዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ሲጓተቱ ነው የምናውቃቸው። ድርጅቶች “ይሄ የእኔ ነው፣ ከዚህ አትድረስ፣ ከዚህ አትለፍ” ሲባባሉ ነው የምናውቃቸው። በድርጅት ታጥረው፣ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ወዲያ አሽቀንጥረው ሲጥሉ ነው የምናውቃቸው። አንደኛው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያበላሸው፣ ይህ ስግብግብ፣ ግትር፣ ከድርጅት ቅጥር ግቢ ውጭ ማየት የተሳነው ደንባራ የፖለቲካ ባሕል ነው። አብንና ባልደራስ በአዲስ አበባ ጉዳይ ይህን የፖለቲካ ባሕል እንኩት አድርገው ሰብረውታል። አብን “የግድ እንደ ድርጅት መወዳደር አለብኝ” ብሎ የድርጅት ካማ ተከናንቦ አልመነቸከም።  የሕዝብ ጥቅም ከድርጅት ስምና አርማ፣ ጠባብ ድርጅታዊ ጥቅምና ዝና ያለፈ እንደሆነ በተግባር  አሳይቷል። ባልደራስም “እኔ የአዲስ አበባ ወኪል ነኝ፣ የእኔ አመራሮች ብቻ ይወዳደሩ” ብሎ አላስቸገረም። ሁለቱም የሕዝብን ጥቅም አስቀደሙ። ለድርጅት ጠባብ ጥቅም ሲራኮቱ ሕዝብ የሚደርስበትም ግፍ አስበው መሃል መንገድ ላይ ደረሱ። አብን እንደ ድርጅት አይወዳደርም። የአብን አመራሮች ግን በባልደራስ ምልክት ይወዳደራሉ። ድርድር ማለት እንዲህ ነው። ኢትዮጵያ ያጣችው ይህን ስልጡን የፖለቲካ ባሕል ነው። በዚህ ድርድር ወቅት ድንጋይ አልተወራወሩ፣ አልተሰዳደቡ፣  አልተዘላለፉ። የሞተም፣ የቆሰለም፣ ስሙ የጠፋም የለም። በሰላም ጨረሷት።
 ከምርጫ በፊት ተቃዋሚዎች እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከገዥው ጋር በጠባብ ድርጅታዊ ጥቅም ይጣሉና ምርጫው ሳይደረግ ችግር ይፈጠራል። አይደለም የአብንና የባልደራስን ያህል አቅምና እውቅና ያላቸው ድርጅቶች፣ ሁለት ሶስት ሰው ይዘውኮ ለድርድር ራሳቸውን የደጀን ተራራን ያህል ኮፍሰው ሌላውን ቋጥኝ አድርገው የሚያዩ  ግትሮች የሞሉበት ነው ፖለቲካው። ከካፖርት ኪስ የማትጠፋ ቀለም የተዝረዘረከባት ማሕተምና ሸረሪት የወረረው ቢሮ “ባለቤት” ሳይቀርኮ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቸ እገኛለሁ” የሚልበት የፖለቲካ ባሕል ውስጥ ነው ኢትዮጵያውያን የሚዋኙት።
በድርጅት እድሜ ለጋ የሆኑት አብንና ባልደራስ ግን ይህን ክፉ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መጋኛ የሆነ ባሕል እንክት አድርገው ሰብረው ወደ ስራ ገቡ። ከምርጫ በኋላ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዥዎች መግባባት ላይ የማይደርሱበት ጊዜ ብዙ ነው። አሸንፈው እንኳን መንግስት መመስረት ያቅታቸዋል። አብንና ባልደራስ አዲስ አበባ ላይ በወሰዱት ቁርጠኝነት ከምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት ነው የሰጡት። ለሕዝብ ጥቅም ከተቆመ ጫጫታ ፍትጊያ ሳይኖር ስምምነት መድረስ እንደሚቻል ነው ያሳዩት።  ኢትዮጵያ ሆይ! ልጆችሽ ሁሉ ከአብንና ባልደራስ ቢማሩ እንዴት እድለኛ ነበርሽ?
2)  እንደ ባልደራስና አብን የአዲስ አበባን ክብር የጠበቀ ማንም ፓርቲ የለም። ከእነሱ ውጭ ማንም የለም። ባልደራስ የአዲስ አበባን ጉዳይ በዋነኛነት የያዘ ፓርቲ ነው። እንደ ሌሎች ፓርቲዎች የተሳሳተ ፖሊሲ ቢከተልና ለሌሎቹ የእልህ መልስ ቢሰጥ አብንም ከልዩ ጥቅም በላይ አዲስ አበባ የአማራ ነች ብሎ መጠየቅ ይችል ነበር። አብን ግን “አዲስ አበባ የሁሉም ነች” የሚለውን የባልደራስን የአዲስ አበባ ወኪልነት ተቀብሎ ምልክትህ ከፊት ይሁን አለ። ባልደራስ አዲስ አበባ የሁሉም ነች ብሎ ያምናል። በዚህም የኦሮሞ ብልፅግናን ሳይቀር ጥሪ አቀረበለት። ኦነግን ጥሪ አቀረበለት። ኢዜማን ጥሪ አቀረበለት። የሶማሊ፣ የአፋር፣ ……የትኛውንም ድርጅት “አዲስ አበባ የሁላችን ነችና መፍትሄውን በጋራ እንፈልግ” ብሎ ጥሪ አቀረበ።  የኦሮሞ ብልፅግና፣ ኦነግ፣ ኢዜማ……አልተቀበሉም። እንደ ሌሎቹ ቢሆን ልዩ ጥቅም ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ የአማራ ነች ለማለት ትልቅ መከራከሪያ የነበረው አብን ሌላውን ጣል እርግፍ አድርጎ “አዲስ አበባ የሁላችንም ነች” የሚለውን የባልደራስን ጥሪ ሲቀበል፣ ባልደራስም ሌሎቹ እንደሚገፉት አልገፋውም። “አመራሮችህ አማራ ናቸው።” ብሎ የነውረኞችን መንገድ ሳይቀበል በምልክቱ እንዲወዳደር አደረገ። አዲስ አበባ እንዲህ ያለ ክብር ማንም ሰጥቷት አያውቅም።
 አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና ነች። የዓለም ተቋማት የሚገኙባት ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማ ነች። ለዚች ትልቅ ከተማ የኦሮሞ ድርጅቶች የሚከተሉት “ልዩ ጥቅም”  ያሳንሳታል። “አማራ መጣብህ” የሚለው የኢዜማ መንጋ መንገድ ያረክሳታል። ለአዲስ አበባ ልኳ የሰለጠነ ድርድር ነው። ታላቅነቷን አምኖ፣ የሁሉም መሆኗን አምኖ፣ ባልደራስ እሷን በቀዳሚነት የሚወክል መሆኑን አምኖ መቀበል ነው። ባልደራስም ሌሎችን የእናንተ ከተማ ነች ብሎ መቀበል ነው ክብሯ። አደረገው።  የአዲስ አበባን ክብር የሚመጥነው ባልደራስና አብን የወሰዱት አቋም ነው። አዲስ አበባን ትልቅ መሆኗን አይተው የድርጅት ጥቅም ጣል እርግፍ አድርገው ለክብሯ የገቡበት አቋም ነው።
የኢትዮጵያውያን ከተማ፣ የአባቶቻችን የአንድነትና ታላቅ አላማ ለማስቀጠል በሚያስችል ደረጃ ፖለቲካውን ከፍ ማለት እንደሚችል ያሳዩበት ነው። ለአዲስ አበባ፣ ለዘመኑ ብቻ ሳይሆን አባቶቻቸው የሰሯትን ከተማ እያሰቡ ለአባቶቻቸው ተግባር ጭምር እውቅና የሰጡበት ነው። ሌላው አንድ ወንበርም ላያገኝ፣ ሁለት ሶስትም ሰው ላያቀርብ የአዲስ አበባን ታላቅነት፣ አባቶቻችን በዓለም ደረጃ ከፍ ያደረጓትን ክብሯን ጥሎ “የእኔ ጥቅም ካልተጠበቀ” እያለ በሚበጠብጥበት ሁለቱ ግዙፍ ድርጅቶች ግን ለክብሯ በድርድር ጨረሱት። ዓለም አቀፍ ክብር፣ አባቶቻቸው በዓለም ደረጃ ያስቀመጡት ከፍታዋ፣  ከድርጅት ምናምን ክብርና ጥቅም እንደማይበልጥ አሳዩበት።
3) አብንና ባልደራስ ይህን ውሳኔ ሲወስኑ ለገዥዎችም፣ ለተቃዋሚዎችም፣ ለአዲስ አበባ ሕዝብም፣  እንደ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ  ሕዝብም አንድ ቁም ነገር በተግባር፣ ሰርተው አሳይተው አስተምረዋል። የአዲስ አበባ ጉዳይ በስግብግብነት፣ በብልጥነት፣ በማጭበርበር፣ በመናቆር ሳይሆን በሰለጠነ ድርድርና ውይይት ብቻ መፈታት እንደሚቻል አሳይተዋል። ተቃዋሚዎች፣ ገዥዎች ከዚህ ስልጡን መንገድ ተማሩ! አዲስ አበባ ሆይ! ማንም እየመጣ አካኪ ዘራፍ ስላለ ሳይሆን ይህኛውና ክብርሽን የሚጠብቀው መንገድ ብቻ ነው የሚያዋጣሽ! ኢትዮጵያውያን ሆይ! ለአዲስ አበባ ብቸኛው መፍትሔ ይህ ስልጡንና ዘመን የዋጀ መንገድ መሆኑን ተመልከቱ!
4) በዚህ ስምምነታችን ከምርጫ ወንበር ሳይሆን የፖለቲካ ባሕል ለውጥ እንደሚያስፈልግ፣ ይህን ለውጥም ከራሳቸው “ሀ” ብለው ጀምረው ያሳዩበት ነው። በዚህ ስምምነታችን ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ለሕዝብ ጥቅም መስራት እንደሚቻል ተምሳሌት ሆነው በተግባር ያሳዩበት ነው። በዚህ ስምምነታቸው ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ ችግሮች፣ ልዩነቶች በውይይና ድርድር ተፈትተው በጋራ መስራት፣ ለህዝብ መስራት እንደሚቻል ያሳዩበት በመሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ከዚህ አርዓያነት እንዲማሩበት የድርጅት ጥቅማቸውን አሽቀንጥረው ያሳዩበት ነው። ኢትዮጵያንና የሀገራችንን ወዝ የጠገብ ታሪክ ሳይዘነጉ፣ ሕዝባችንን የሚመጥን የፖለቲካ ባሕል እንድናዳብር፣ ምርጫውን ከወንበር ያለፈ ሀገርን የምናድንበት፣ ከጭቅጭቅና መጠላለፍ ወጥተን በሰለጠነ መንገድ ተደራድረንና ተስማምተን የሀገራችን አንድነት አጠናክረን ችግሮቿን እንድንፈታ በይፋ ያሳዩበት ነው። የዘንድሮው ምርጫ ብዙ ችግሮችን ጎትቶ ሊመጣ ይችላል። እንደ አብንና ባልደራስ ከድርጅት ጥቅም፣ ከግትርነት፣ ከስግብግብነት ይልቅ በቀናነት መደራደር ከተቻለ ለዘንድሮው ምርጫም ለቀጣይ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ፍቱን መፍትሄ ነው።
ተቃዋሚዎች፣ ገዥው ፓርቲ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያውያን አብንና ባልደራስ አዲስ አበባ ላይ የሳዩት አቋም በብዙ ችግር መሃል ለሚደረገው ምርጫ ያበረከቱት ምርጥ ገፀበረከት ነውና ተቀብላችሁ ተማሩበት! ሌሎች ተምሳሌታቸውን እንዲወስድ በማበረታታትና ግፊት በማድረግ ኢትዮጵያን ተጭኗት ከኖረው ገልቱ የፖለቲካ ባሕል እንላቀቅ!
አብንና ባልደራስ በጥምረታቸው አዲስ አበባ ላይ ትልቅ ድምፅ እንደሚያገኙ ከጅምራቸው መገመት ይቻላል። ግን ዋናው ወንበር ብቻ አይደለም። በወንበር ማሸነፍማ 97 ላይ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ አሸንፈው ነበር። ያኔ አሸንፈው ያላሳዩት የፖለቲካ ባሕልን ነበር። የፖለቲካ ባሕልን ስላላሸነፉት ያሸነፉት ወንበርም ብላሽ ቀረ። አዲስ አበባን አሸንፈውም ስምምነት አልነበራቸውም። አብንና ባልደራስ ግን ከምርጫ በፊት፣ ወንበር ሳያሸንፉ ተስማምተው፣ የፖለቲካ ባሕሉን አሸንፈው አሳዩን።
አብንና ባልደራስ ከምርጫ በፊት ያሳዩንን ስልጡን የፖለቲካ ባሕል እየተከተሉ በቀጣይም የበለጠ እንደሚያዳብሩት ተስፋ እናደርጋለን። ባይቀጥሉበት እንኳ፣ ዛሬ ያሳዩንን ስልጡንነት አይፍቀውም። አንድ አካል ሁሌም ላያስተምር ይችላል። ያስተማረበት፣ ታላቅና ስልጡን የሆነበትን አጋጣሚ  ለይተህ አርዓያነት ትወስዳለህ። አብንና ባልደራስ ለወደፊት ቢሳሳቱ እንኳን ይህኛውን ትክክለኛ አቋማቸውን እንማርበታለን። ቢሳሳቱ በሚሳሳቱበት  እንተቻቸዋለን፣ እንቃወማቸዋለን እንጅ የቆየውን ጎጅ የፖለቲካ ባሕል ያጠፉበትን ይህኛውን መልካም የፖለቲካ ባሕል ንቀን አንተወውም! ባልደራስና አብን በአዲስ አበባ ላይ የወሰዱት አቋምና ውሳኔ የዘንድሮው ምርጫ እጅግ ውድና ትልቁ ስጦታ ነው። አዲስ አበባ አመስግና፣ እጇን ዘርግታ መቀበል ያለበት  እጅጉን የከበረ ስጦታ ነው።
Filed in: Amharic