>
7:10 am - Thursday March 23, 2023

ካራማራና ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ቢገባን ? ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ካራማራና ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ቢገባን ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

የካራማራ ድል እና የኢትዮጵያ ሰራዊት መስእዋትነትና ትውስታ 


 የካራማራ የኢትዮጵያውያን ድል የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ/ም እንደሚከበር ከተሪክ እንማራለን። ስለካራማራ ድል ብዙ ተጽፎለታል፤ ብዙ ተነግሮለታል። በአገራችን አለመታደል ሆኖ ስለድል እንጂ ስለውድቀት ብዙ ጊዜ አይወራም። የችግሩ ምንጭ ተዳፍኖ ይቀራል፤ ዳግም ስህተት ይሰራል። ጦርነት እንደማንኛውም የሥራ መስክ ሁሉ የጦርነትን መርሆዎች ተግባራዊ የሚያደርጉ በመስኩ የተካኑ ሞያተኞች ይጠይቃል። እነዚህ ሞያተኞች ወደጦርነት ሲገቡ የትኞቹ መርሆዎች ለድል እንደሚያበቋቸው ገምግመው ይገባሉ። በጂጂጋው ውጊያ የሶማሊያው ማጥቃት ለድል በቅቷል፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ጦር ያደረገው የመከላከል ውጊያ የሶማሊያን ጦር መቋቋም እንዳላስቻለ በኢትዮጵና ሶማሊ ጦርነት ታሪክ ላይ አተኩረው በተጻፉ የታሪክ መጽሐፍት ላይ ተጠቅሷል። የሶማሊያ ማጥቃት ስኬታማ የሆነበትን ለሌላ ጊዜ አቆይተን የኢትዮጵያ ጦር ለውድቀት የተዳረገበትን ምክንያቶች ሁሉንም ባይሆን እንኳን ዋና ዋናዎቹን መጥቀሱ ተከታዩ ትውልድ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደግም ይማርባቸዋል። ውድቀቱን የማነሳው የበዓሉን ስሜት ለማደብዘዝ አይደለም። በዚያን ጊዜ በዚያ ግንባር የነበሩ የጦሩ መሪዎችን ወይም ከበላይ ሆነው መመሪያ ይሰጡ የነበሩ የደርግ አባሎችን የሞያ ብቃት ላይ ጥያቄ ለማንሳት ወይም ለመወንጀል ሳይሆን ከነሱ ስህተት ሌላው እንዲማርበት ለማድረግ ነው።

ካራማራ ከጂጂጋ ከተማ በስተምዕራብ 5 ኪ/ሜትር ላይ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከጭናክሰን እስከ ደጋሃቡር መዳረሻ ድረስ ተዘርግቶ እንደአጥር የቆመ ተራራ ነው። ይህን ተራራ በተሽከርካሪ ለማለፍ አንድ ብቻ በር አለ፤ ስያሜውንም የአገኘው ከዚሁ የማለፊያ በር እንደሆነ ይነገራል። ካራማራ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን “ካራ“ የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው አንዱ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው በማጥበቅ ሲነበብ በር ማለት ሲሆን፣ “ማራ” ማለት ደግሞ ጥምዝ፤ ጠመዝማዛ መንገድ ሲሆን የሁለቱ ቃል ማለትም ካራማራ የሁሉም መንገድ መግቢያና መውጫ ጠመዝማዛ ማለፊያ በር እንደሆነ ከቋንቋው ባለሞያዎች ጠይቀው መረዳታቸውን  አደፍርስ የተባሉ የጦር አዋቂ ካሰፈሩት ጽሁፍ ላይ ተረድቻለሁ። ( ማእረጋቸውን ለግዜው ማወቅ ባለመቻሌ መትቀስ አልቻልኩም፡፡ ለዚሁም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ከፍተኛ የመከላከል ውጊያ ከተደረገባቸው ቦታዎች አንዱ ካራማራ ነው፤ ሆኖም በሶማሊያ ማጥቃት ጊዜ ለመከላከል ቁልፍ የሆነውን ካራማራ የወታደራዊ መሪዎቻችን ሳይጠቀሙበት ቀርተው የደረሰው ጉዳት ካራማራን በድል ብቻ ሳይሆን በውድቀት እንዲታሰብ ያደርገዋል። 

ካራማራ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ አንዱ የጦር ሜዳ የሆነበትን የኋላ ታሪክ ተመልሶ ማየቱ ለግንዛቤ ይረዳል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የኃይል አሰላለፍ በአንድ በኩል የአሜሪክ፤ የእንግሊዝና የሶቪየት ሕብረት ጦር የሕብረት ጦር(Allied Forces) ተብለው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጀርመን፤ ኢጣሊያ፤ ጃፓንና ቱርክ አብረው (Axis Power) ተብለው ፍልሚያ ሲያደርጉ ኢጣሊያና ጀርመን በአፍሪካ ውስጥ በቅኝ ግዛትነት ይዘዋቸው ከነበሩት አገሮች ለማስወጣት ተወስኖ ጦርነት ተጀመረ። ኢጣሊያ የአውሮፓ አገሮች አፍሪካን ሲቀራመቱ ደቡብ ሶማሊያን የኢጣሊያ ሶማሌላንድ በማለት ቀደም ሲል ይዛለች።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከሰሜንና ከምሥራቅ አቅጣጫዎች ዳግም ወረራ ሠንዝራለች። ከሰሜን አቅጣጫ የተሰነዘረውን ጥቃት በማይጨው ጦርነት ማገድ ባለመቻሉ አዲስ አበባ ሚያዝያ 27 ቀን ገብቶ 1929 ሲቆጣጠር፤ በምሥራቅ በኩል ደግሞ ከሞቃዲሾ ከተማ የተነሳው በማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ የተመራው ጦር በኦጋድዴን ውስጥ በፈርፈር፤ ቀብሪደሃር፤ ደጋሃቡር፤ ጂጂጋ አድርጎ በካራማራ በር አልፎ ሐረር ከተማ ሚያዝያ 30 ቀን 1929 ገብቷል። 

ከላይ እንደተጠቀሰው ኢጣሊያ በእንግሊዝና በፈረንሳይ መልካም ፈቃድ በዓለም የተከለከለ የጋዝ መርዝ ተጠቅማ ኢትዮጵያ የገባች ቢሆንም አሁን በተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ፤ እንግሊዝ ጣሊያንን ከአፍሪካው ቀንድ የማስወጣት ኃላፊነት ወሰደች። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ለመውጋት እንግሊዝ በሦስት አቅጣጫ ኃይሏን አሰለፈች። 1ኛ በሱዳን በኩል ንጉሠ ነገሥቱም በዚሁ ግንባር ነበሩ፤ 2ኛ ከኬንያ አቅጣጫና 3ኛ የእንግሊዝ ሶማሌላንድ ትባል ከነበረችው በሐርጌሣ ግንባር ነበር። በሦስቱም ግንባሮች እንግሊዝ ያሰለፈችው ጦር ከቅኝ ግዛቶቿ የተመለመሉ ነበሩ። የሐርጌሣው ግንባር ጦር የአካተተው የናይጀሪያ እግረኛ ተዋጊ ጦር፤ የደቡብ አፍሪካ ብረት ለበስ ጦርና በደቡብ አፍሪካውያን የሚበር የአየር ኃይል ነበር። 

የኢጣሊያ ጦር የሐረርን ከተማ ለ4 ዓመታት በማስተዳደር ላይ እንዳለ እሱን ለማስወጣት የእንግሊዝ ጦር ከሐርጌሳ ወደ ጂጂጋ ጉዞውን ቀጠለ። የኢጣሊያ ጦርም የእንግሊዝ ጦርን ለመግታት ካራማራ ላይ ከፍተኛ የሆነ የመከላከያ ምሽግ አዘጋጅቶ ቦታውን ይዞ የእንግሊዝን ጦር መቃረብ መጠባበቅ ጀመረ። የእንግሊዝ ጦር ጂጂጋ ደርሶ በግንባር የናይጀሪያ እግረኛ ጦር አሰልፎ በመድፍ ተኩስ እየተረዳ የካራማራን ማለፊያ በር ለመያዝ ያደረገው እንቅስቃሴ ካራማራና በስተጀርባው የተጠመዱት የኢጣሊያ መድፎች ተኩስና የተቀበሩ ፈንጂዎች እግረኛውን የናይጀሪያ ጦር ሊያቀርበው ባለመቻሉ፤ በሚቀጥለው ዙር የደቡብ አፍሪካ ብረት ለበስ ጦር ማጥቃት ሰንዝሮ በተመሳሳይ ችግር የተነሳ ካራማራን መያዝ ቀርቶ መጠጋትም አልሆነለት። በተለያየ ዘዴና በተለያየ አቅጣጫ የተደረጉ የማጥቃት ሙከራዎች አልተሳኩም። የካራማራን ተራራ በምድር ጦር አጥቅቶ መያዝ አስቸጋሪ መሆኑን የተረዳው የእንግሊዝ ጦር መሪ በደቡብ አፍሪካውያን የሚበሩ በርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖችን አሰልፎ ከሐርጌሳ እየተነሱ በካራማራ ላይ ባለው የኢጣሊያ የጦር ምሽግ ላይ የቦንብ በረዶ ማዝነብ ጀመሩ። የኢጣሊያ ጦር ሊቋቋመው ባለመቻሉ ጨለማን ተገን በማድረግ በሌሊት ካራማራን ለቆ ወደ ሐረር አፈገፈገ።

የእንግሊዝ ጦር ካራማራን ከተቆጣጠረ በኋላ ማለፊዋን በር (Marda Pass) ብሎ ሰይሟል። ይህ ስያሜ በግለሰብ ስም ይሁን ወይም በጦር ክፍል ማወቅ አልቻልኩም፤ የምታውቁ ጠቁሙ። የእንግሊዝ ጦር የሚያፈገፍገውን የኢጣሊያንን ጦር እግር በእግር እየተከተለ ጉዞውን ወደ ሐረር ቀጠለ። በግንባር የተሰለፈው የናይጀሪያ ጦር መጋቢት 29 ቀን 1941 ሐረር ከተማ ገባ ። 

ወደ ኋላ ሄጄ ይህን ሁሉ ታሪክ ያነሳሁት ካራማራ ለመከላከል ውጊያ የነበረውን ጠቀሜታ ለማሳየት ነው። ሌላም ምሳሌ ላክል፤ በሀገራችን የመከላከያ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የወታደራዊ ትምህርት የሚሰጥንበት በሆሎታ እስታፍ ኮሌጅ ትምህርት ቤት ነበር። አሁን ባለው ሠራዊት ውስጥ እስታፍ ኮሌጅ ያለ ይመስለኛል። ቀደም ሲል በነበረው እስታፍ ኮሌጅ የመከላከል ውጊያን በተመለከት በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ በክፍል ውስጥ የሚሰጠው በተግባር ልምምድ የሚደረግበት በካራማራ ላይ እንደነበር አቶ አደፍርስ በጽሁፋቸው ላይ ጠቅሰውታል።በዚህ ኮሌጅ የሚማሩ የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች ለመስክ ልምምዱ ካራማራ ሲመጡ የ10ኛ ሜ/ብርጌድን ይጎበኙ እንደነበር በኢትዮጵያ የጦር ሀይል ታሪክ ባተኮሮ መጽሐፍት ላይ ተጽፎ ይገኛል።( በተለይም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ስለነበረው ሰራዊት በሚተርኩት የታሪክ መጽሐፍት ላይ ፍንተው ብሎ ይገኛል፡፡) የብርጌዱ አመራሮችም ካራማራ ለመከላከል ውጊያ ያለውን ጠቀሜታ በተዘዋዋሪ መንገድ ይገነዘባሉ። አደፍርስ አክለው እንዳብራሩት ከሆነ፣ይህ ለረጂም ጊዜ ልምምድ ሲደረግበት የነበረው ካራማራ እውነተኛው የሶማሊያ ማጥቃት ሲዘነዘር የመከላከያ ምሽግ አልተቆፈረም፤ ጦሩም በዚህ ቁልፍ ቦታ ላይ የመከላከል ውጊያ አላደረገም። ለምን? የመቶ ሚሊዮን ህዝብ ጥያቄ ነው።

ካራማራ ላይ መከላከያ ያልተያዘበትን ሁኔታ ከማንሳት በፊት ሠራዊቱ የነበረበትን ቁመና ማጤኑ ሁኔታዎችን በስፋት ለመገንዘብ ያስችላል። በሀገራችን አብዮት ፈንድቶ በሠራዊቱ ውስጥ ከሻለቃ በላይ ማዕረግ የነበራቸው ልምድ ያካበቱ መኮንኖች የዘውድ ሥርዓት ደጋፊ፤ አድሃሪ ተብለው በጡረታ ከሠራዊቱ የተገለሉበት ወቅት ነበር። አዲሶቹ የሠራዊቱ ወጣት መሪዎች ልምድ የሚጎላቸው ቢሆንም ለአብዮቱ በነበራቸው ታማኝነት እየተመዘኑ ቁልፍ የአዣዥነት ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል። ዘመናይ የሆነ የአሜሪካን ታንክ፤ ብረት ለበስና ጸረ-ታንክ መሣሪያዎች የታጠቀውና በሶማሊያ ጦር ይፈራ የነበረው ጂጂጋ ላይ የነበረው 10ኛ ሜ/ብርጌድ፤ በመሃል አገር የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም፤ ለቤተ መንግሥት ጠበቃ ወዘተ ለማዋል እየተቆነጠረ በመላኩ የብርጌዱ ኃይል ተመናምኗል። ሶማሊያም ከነበራት የኃይል ሚዛን የበላይነት በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ምቹ ጊዜ መሆኑን ተገንዝባ ነው ማጥቃት የሰነዘረችው።( አደፍርስ) ከአቶ አደፍርስ ሃሳብ እንደምንረዳወ ሀገራን ኢትዮጵያ የተማሩ ልጆች እያሏት ሀገራቸውን ማገልገል እንዳችሉ በአገዛዞች በመከልከላቸው የተነሳ ሀገሪቱ ለበርካታ ግዜያት ለአደጋ መዳረጓን ነው፡፡ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በሙያቸው ሀገራቸውን እንዳያገለግሉ ገሸሽ ሲደረጉ የሚደርሰው አደጋ የከፋ ነው፡፡ ከድላችን እንደምንማረው ሁሉ ከውድቀታችንም መማር የሰውነት ባህሪ ነው፡፤

ሶማሊያ “የታላቋን ሶማሊያ“ ሕልም እውን ለማድረግ የምሥራቁን ጎራ ተቀላቅላ በሶቪየት ሕብረትና በሌሎች ሶሻሊስት አገሮች ዕርዳታ የመከላከያ ሠራዊቷን ገንብታለች። ሠራዊቷ በሦስት ዕዞች የተዋቀረ ነበረ። 26ኛው ዕዝ በሰሜን ሶማሊያ ሐርጌሣ ላይ፤ 21ኛው ዕዝ በማዕከላዊ ሶማሊያ ዱስመረብ ላይና 60ኛው ዕዝ በደቡብ ሶማሊያ ባይደዋ ላይ ነበሩ። ለግንዛቤ እንዲረዳ አንድ ዕዝ፦ 2 እግረኛ ክ/ጦሮች፤ 1 ሜ/ክፍለ ጦር፤ 1 ታንክ ብርጌድ፤ 1 መድፈኛ ብርጌድና 1 አየር መቃወሚያ ብርጌድ ይዞ የተዋቀረ ነበረ። ከላይ ከተጠቀሱት ዕዞች ሌላ 54ኛና 43ኛ የተባሉ በሰው ኃይልና በትጥቅ ያልተሟሉ ለውስጥ ጥበቃ ሞቃዲሾ አካባቢ ነበሩ። በምስራቅ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ድንበር አስከባሪ ሆኖ የኖረው አምበሳው 3ኛ እግረኛ ክ/ጦር ሲሆን በግንባሩ 26ኛና 21ኛ ዕዞች ተሠልፈዋል። በ 1 ክ/ጦርና በ 2 ዕዞች መካከል የነበረው የኃይል ሚዛን ለማንም ግልጽ ይመስለኛል። 

የሶማሊያ መከላከያ ኢትዮጵያን በመደበኛ ሠራዊት ለማጥቃት ሦስት ምዕራፍ ያለው ዕቅድ ነድፎ እንደነበር በታሪክ ተጠቅሷል። በምዕራፍ አንድ- በ21ኛው ዕዝ ዋርደር፤ ቀብሪደሃር፤ጎዴንና ደጋሐቡርን አጥቅቶ መያዝ። በምዕራፍ ሁለት- በ26ኛው ዕዝ ጂጂጋ፤ ደሬዳዋና ሐረርን መያዝ። በምዕራፍ ሦስት- በ21ኛና በ26ኛ ዕዞች በጋራ አዋሽ ላይ መከላከያ መያዝ ነበሩ። የዚያድ ባሬ ሠራዊት በመጀመሪያ የውጊያ ምዕራፉ ኦጋዴን ውስጥ የወገን ጦር ሠፍሮባቸው በነበሩት ገላዲን፤ ዋርደር፤ቀብሪደሐር፤ ጎዴና ደጋሃቡር ወዘተ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1969 ዓ/ም ማጥቃት ሠንዝሮ የሶማሊያ ሠራዊት ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም በነበረው የኃይል የበላይነት ተጠቅሞ ሁሉንም ቦታዎች አስለቅቆ በቁጥጥሩ ሥር አዋለ። የዕቅዱን ምዕራፍ ሁለት ተግባራዊ ለማድረግ 26ኛው ዕዝ ሙሉ ኃይሉን ይዞ ጂጂጋንና ድሬዳዋን ለመያዝ ተንቀሳቀሰ።ጂጂጋ ላይ የነበረው ኃይሉ የተመናመነው 10ኛ ሜ/ብርጌድ፤ ለማጠናከር የተላከው 92ኛ ሕዝባዊ ሠራዊትና ከደጋሐቡር አፈግፍጎ የመጣ ጦር የጂጂጋን ከተማ ለመታደግ ቆርጦ ተነሳ።

ውጊያን በድል ለመወጣት በሞያው የተካኑና የረጂም ጊዜ ልምድ ያካበቱ የበሰሉ የጦር መሪዎች ለድል ወሳኞች መሆናቸውን ከተደረጉ ጦርነቶች መገንዘብ ይቻላል። በሀገራችን በሰሜኑም ሆነ በምስራቁ በተደረጉ ውጊያዎች ሽንፈቱ በአብዛኛው የአመራር ስህተት ነበር። በጂጂጋውም ግንባር ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል። በጂጂጋ አካባቢ የነበረው ጦር አዛዥ ወይም የበላይ አስተባባሪ የደርግ አባል ከምዕራፍ አንድ የሶማሊያ ጥቃት በኋላ ተከታዩ ተጠቂ ጂጂጋ ላይ ያለ ጦር መሆኑንና የኃይል ሚዛን ልዩነት መኖሩን ተገንዝቦ መቋቋም የሚቻልበትንና ውጊያውም የሚያደርሰውን ጉዳት መጠን መቀነስ የሚያስችል ዕቅድ መንደፍ ነበረበት፤ ሆኖም ወቅቱ የአንድ ሰው ዕዝ መሆኑ ቀርቶ በደቦ የሚወሰንበት የውዥምብር ጊዜ ስለነበረ ዕቅድ ነድፎ ማስፈጸም የሚቻልበት አልነበረም፤ ቢሆን ኖሮ ሁለት ነገሮች መደረግ ነበረባቸው፦

አንደኛ – የጂጂጋን ከተማ ለመከላከል በግንባር ጠንካራ የመከላከያ ምሽግ ማዘጋጀት፤ በዚህ ምሽግ ጠላትን ማገድ ካልተቻለ ወደኋላ አፈግፍጎ መከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ መከላከያ በሆነው ካራማራ ላይ ጠንካራ ምሽግ ማዘጋጀትና ጦሩን ማለማመድ፤( አደፍርስ)

ሁለት- የሶማሊያ ጦር የኃይል የበላይነት ግምት ውስጥ በማስገባት ሜዳ ላይ ያለችውን የጂጂጋን ከተማ ሊይዝ እንደሚችል ታሳቢ አድርጎ፤ ውጊያው በጂጂጋ ኗሪ ሕዝብና በጦሩ ቤተሰብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የከተማውን ሕዝብ በቅድሚያ ማውጣት የሚቻልበትን ዘዴ አቅዶ መተግበር። 

ሁለቱም አልተደረጉም። የተደረገው ምንዲነው፦

10ኛ ሜ/ብርጌድ የጂጂጋን ከተማ የውስጥና የዙሪያ ጥበቃ ለማጠናከር ለመጣው 90ኛ ሕዝባዊ ሠራዊት አስረክቦ፤ ያለውን የሰውና መሣሪያ በሦስት ከፍሎ በሦስት አቅጣጫ ለመከላከል በቶጎውጫሌ አቅጣጫ በአሮሬሳ ከረብታ፤ በቀብሪበያህ መንገድና በተፈሪ በር አቅጣጫ ከአሮሬሳ ኮረብታ ሰሜን 20 k/ሜትር ላይ ቀብረቢያን በምትባል መንደር አጠገብ መከላከያ ቦታ ያዘ። 

የጦሩ ቤተሰብና የከተማው ሕዝብ ከተማውን ለቀው ለመውጣት ቢሞክሩ አብዮታዊ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን ለጦሩም ሆነ ለከተማው ሕዝብ በይፋ ግንባሩን ከሚያስተባብሩ የደርግ አባላት መልዕክት ተላለፈ።

የጂጂጋ መከላከያ አያያዝ በጥልቀት ሳይሆን በስፋት ስለነበረ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም ጠላትን ማቆም ግን አልተቻለም፤ የመጀመሪያው መከላከያ ሲሰበር ሌላ የመከላከያ ምሽግ ወይም ተተኪ የሚሆን ተጠባባቂ ኃይል ባለመኖሩ ጦሩ አፈግፍጎ ወደ ጂጂጋ ከተማ አመራ በከተማው ውስጥ እንዳይወጣ ተከልክሎ የነበረው ኗሪና የጦሩ ቤተሰብ አፈግፍጎ ከመጣው ጦር ጋር ድብልቅልቁ በወጣ መልኩ ዕዝና ቁጥጥር በሌለበት ከተማውን እየለቀቀ መውጣት ጀመረ። ይህ ሁኔታ ለሶማሊያ መድፎች የተመቻቸ ዒላማ እንዲሆኑ አደረገ። ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። ተሸንፎ የሚያፈገፍግ ጦርና ግድብ የሰበረ ውሃ የሚያቆመው የለም እንደሚባለው ጦሩ ካራማራ ላይ ቆም ብሎ ለመከላከል ሳይሞክር ማለፊያ በሩን በፈንጂ ሳያጥር ወይም መሰናክል ሳያስቀምጥ መስከረም 3 ቀን 1970 ካራማራን አልፎ ወደ ሐረር አቅጣጫ ጉዞውን ቀጠለ።

የሶማሊያ ጦር መሪዎች ካራማራን ለመያዝ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንከፍልበታለን ብለው ያሰቡትን በቀላሉ ስለያዙ ከፍተኛ የሆነ ደስታ ተሰማቸው። የሚያፈገፍገውን የኢትዮጵያ ጦር መከተል አቁመው ሁለት ቀን ሙሉ በካራማራ ላይ የድል ፈንጠዝያ አደረጉ። የኢትዮጵያ ጦር ካራማራ ላይ መከላከያ ባለመያዙ ለፈጸመው ስህተት ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈለ ሁሉ የሶማሊያ ጦርም ተመሳሳይ ስህተት ሠራ። የሚያፈግፍገውን የኢትዮጵያ ጦር ሚዛኑን እንደሳተ ፋታ ሳይሰጥ እግር በእግር እየተከተለ ቢያጠቃ ኖሮ ሐረርን ከመያዝ የሚያግደው ኃይል አልነበረም። ፈንጠዝያ የተደረገባቸው ሁለት ቀናት ለኢትዮጵያ ጦር ወርቃማ ጊዜ ሆኑ፤ ቆሬ ላይ የመከላከያ ቦታ ለመያዝ አስቻሉ። የሶማሊያ ጦር ከድሉ ፈንጠዝያ በኋላ ማጥቃቱን ሲቀጥል ቆሬ ላይ ምን ገጠመው? በሌላ ርዕስና በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል። 

የኢትዮጵያ ጦር በመልሶ ማጥቃት የጂጂጋን ከተማን የካቲት 26 ቀን 1970 መልሶ መያዝ ችሏል። ከተማው የተያዘበትንና የሶማሊያ ጦር ተመቶ ከኢትዮጵያ መሬት ጠቅሎ የወጣበትን የካራማራ ድል በማለት በየዓመቱ ይታወሳል። ከላይ እንደተገለጸው ጂጂጋን ለመከላከል በግንባር በተደረገው ውጊያ ሲፋለሙም ሆነ በማፈግፈጉ ሂደት መስዋዕት የሆኑ በርካታ ወገኖቻችንም መታሰብ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም ካራማራ በድሉ ብቻ ሳይሆን ውድቀቱም መታሰብ አለበት። የወያኔ አገዛዝ ደርግን በጦርነት ማሸነፉን ነገረን ስለደረሰበት ውድቀት በጥልቀት አልነገረንም ነበር፡፡ ወይም ከደርግ ውድቀት ለመማር መንፈሳዊ ወኔ ከድቶት ነበር፡፡ ከሃያ አመት በፊት የኢትዮ ኢርትራ ጦርነት ምክንያትና ውጤት በተመለከተ በዝርዝር፣ በእውነት መሰረት ላይ ሆኖ አጋዛዙ አልነገረንም ነበር፡፡ ከሁለት አመት በፊት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ተፈራርመው መልካም ጎረቤት ለመሆን በቁ የተባለው መልካም ዜና ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሁለቱም ሀገራት ህዝብና መሪዎች ካለፈው ስህተት መማር የታሪክ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር መሃከል ያለው ግጭት መነሻ ምክንያቶች በባለሙያዎች ተጠንቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነቱ መነገር ያለበት ይመስለኛል፡፡ በእሳት ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ የምትቅበዘበዘውን ግብጽና ሸሪኮቿን ሴራ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ተለዋዋጭ ባህሪ የምታሳየውን የተባበረችው አሜሪካን ጨምሮ ታላቋ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ጭምር ኢትዮጵያ ሀገራችንን አንገት ለማስደፋት የሚያደርጉትን ሴራ ምክንያትነት ለኢትዮጵያ ህዝብ በእውነት መሰረት ላይ ቆመው እውነተኛ መረጃ ማቅረብ ከመንፈሰ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ይጠበቃል፡፡ ግዴታቸውም ይመስለኛል፡፡ የተባበረችው አሜሪካን ሴራ ብቻ መመርመር ትምህርት ይሰጠናል፡፡ በ1954 ዓ.ም. የእነ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይና ወንድማቸውን ግርማሜ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ያከሸፈችው አሜሪካ ነበረች፡፡ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሀገሪቱ በወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ላይ በምትገኝበት ግዜ ሁሉ የአሜሪካ ፍላጎት ፣ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ አያውቅም፡፡ ለምን ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል በመንሳቷ ምክንያት ቂም ከቋጠሩት አንደኛዋ ሀገር መሆኗን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ለማናቸውም ኢትዮጵያውያን ከድላችን ባሻግር ከውድቀታችን እንድንማር ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡

 

ኮሎኔል ካርዶስ ቪያ ቪሴንሲያ በምስራቅ ኢትዮጵያ ጀብዱ የፈጸመ ኩባዊ ጀግና

 

ይህ ዛሬ ታሪኩን በወፍ በረር የማስቃኛቸሁ ግለሰብ በአለም አቀፍ የሶሻሊስት ሀገራት ትብብር መንፈስ መሰረት ለኢትዮጵያ ሀገራችን ደሙን ሊያፈስላት፣ አጥንቱን ሊከሰክስላት ወደ ኢትዮጵያ ምድር መጥቶ የነበረ፣ በትውልድና በዜግነት ኩባዊ የሆነው የጦር መኮንን ኮሎኔል ካርዶስ ቪያ ቪሴንስያ ይባላል ።

አገራችን በቀቢፀ ተስፋው የታላቋ ሶማሊያ ግንባታ ቅዠት በዚያድ ወታደሮች መላው ሐረረጌና ከፊል ባሌና ሲዳሞ ክፍለሃገሮች (በግዜው አጠራር) ለ8 ወራቶች ላላነሰ ጊዜ ( ከሐምሌ ወር መግቢያ 1969 እስከ መጋቢት ወር መጀመሪያ 1970 ዓም ) ተደፍራና ተወራ በነበረች ጊዜ በወጣትነት ዕድሜው በመቶ አለቅነት ማዕረግ ከወገን ጦር ጎን ተሰልፎ ዓለም አቀፍ ግዳጁን የተወጣ ጀግና ነው ።

በጦር ሜዳ ፍልሚያ ላይም ምርኮ ሆኖ በበረሃማው ሶማሊያ እስር ቤቶችም ከጦር ሜዳ አጋሮቹ ከሆኑት ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ጋራም ከአሥር ዓመታት በላይ መከራን ተቀብሏል ። 

ምናልባትም የተቀበለው ፍዳ ከኛም ወታደሮች በላይም ሊሆን ይችላል ።

ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ ሁለቱ መንግሥታት የምርኮኛ መለዋወጥ ስምምነት ሲያደርጉም ከምርኮው ቀንበር ተላቋል ። እንደወጣ አልቀረም ። 

ምድራችንን ዳግም ረግጧታል ። ከሦስት ዓሥሮችም በኋላ በሕይወት ካሉት ጀግኖቻችን ጋርም ዝክር ለማድረግም ዳግም መምጣቱን ተመለከትኩ ። 

እንደ መርሐ ብሔርና ብሔራዊ በዐል 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶ ብንቀበለውም በወደድኩኝ ። 

ቀይ ምንጣፍም ተመኘሁለት ። 

ኮሎኔል ሆይ !

ክብርም ማዕረግም ላንተ ይሁን እልሃለሁ ።

የጦርነቱን ወላፈንና እሣቱን ፣ ጭንቀቱንና ፍጅቱን ፣ የወደቁትን በማሰብ ሃዘኑን ጭምር ሁሉ በህጻንነት ዕድሜዬ በውን ስላየሁት ለጀግኖች ያለኝ ክብር ከተራ ዜጎች በላይ ነው ። 

ብዙ ጀግኖች ረግፈዋል ። 

አካልም አጉድለዋል ።

በየሆስፒታሉም በተለያየ ደረጃ የቆሰሉትን ለመጠየቅም ተሰልፈናል ። ትናንት ከነትጥቃቸውና እንግታቸው በረሃ አጥቁሯቸው በፂም የሞሉ ፊቶችና ቅጠልያ ለብሰው ደፋ ቀና ሲሉ ያየናቸው እንደ ወጡ ቀርተው ወፍ ሳይጮህ በጠዋት መርዷቸውን ሰምተናል ።

መንደሩንም የሃዘን ደመና ወሮት ጭር ብሎም አስተውለናል ። 

ደረት የሚደቁ እናቶችና ጎረቤቶች፣ ዕንባቸው በጉንጫቸው ላይ ደርቆ የነጣ ቦይም የሰራ ህፃናቶችም አባብለናል ። 

የነገንም ሳናውቅ በሥጋትም ለበርካታ ወራቶች ዕንቅልፍም አጥተናል ።

የወደቁትን መታሰቢያ ዕለት ተስካራቸውንም ለማውጣት ባሕላችንና ዕምነታችነ ያስገደደንን ሁሉ ፈፅመናል ።

አቤቶም ብለን ፀሎት አድርሰናል ።

በመከራው ምን ያልሆነው አለ?

ጦር ሜዳ ወርጄ ተዋግቼ አላውቅም፡፡  በመሳሪያ ትግልም የማምን ሰው አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን የሀገራቸው ድንበር በውጭ ወራሪ ሀይሎች ሲደፈር ጨረቄን ማቄን ሳይሉ ለውድ ሀገራቸው ህይወታቸውን ቤዛ አድረገው ላለፉ ጀግኖች፣ አካላቸው ለቆሰለ ወታደሮች ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው  የሚፈልጉትን  መሪ ሲመርጡ ማየት ግን  ምኞቴና ፍላጎቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዛን ዘመን ሠፈር በመጠበቅ ከታጠቁት ጋርም ሌሎች የመንደር ወጣቶች ጨምሮ በርካታ ምሽቶች በምሽግ ማሳለፍ ግድ ይል ነበር። ወታደሮች ወደ ጦር ሜዳ ሲዘምቱ ለጦር ሜዳ ቅርብ በሆኑ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችና ጎልማሶች፣ አዛውንቶች ጭምር አካባቢያቸውን በንቃት ይጠብቁ ነበር፡፡

በጣምራ ጦር በተሰኘው መጽሀፍ ላይ እንደተጠቀሰው ግምባር ቀደሟ የጦር ሜዳ ሠፈሯ ሐረር ሐማሬሣ  ነበረች። 

ዛሬ የቀድሞው ሠራዊት ታሪክ ማዕከላነቷን ( ከሠራዊት መኖሪያና ሥልጠና ሥፍራነቷን እስከ ጦር ግምባርነቷን ) ደብዛዋን ለማጥፋት ጠላቶቿ ባይተኙላትም ዛሬም ከነዋሪዎቿ ጋር አለች ። 

እርሷም አልሞተችም ። 

እኔም አልሞትኩም ። 

የመድፉና የሞርተሩ ወዳጅ እነ  ሻምበል ታምሩ ዓየለ፣ መድፈኛው አስር አለቃ ዘውዱ ድረሪሳ፣ በኦጋዴን በረሃ መስእዋት ሆኖ ያለፈው የመቶ አለቃ ነጋሽ ድርሪሳ እና ሌሎች ያልተዘመረላቸው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሌትም ቀንም በማዘዣ ሠፈር እና ምሽግ ውስጥ ነበርና ውሏቸው ፣ ቤተሰባቸውን በምሽት የሚጠብቅ አልነበረም፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ  ተገቢው ሥልጠና ያለውም፣ የሌለውም  ሽጉጥም፣ ዱላም ያለው ማታ ማታ ጠላት ጥሶ ቢመጣና አደጋ ላይ ሲወድቁ ለመከላከል ሽጉጥ ወይም ዱላ በማዘጋጀት የመንፈስ ዝግጅት ነበራቸው፡፡ በተለይም በምስራቅ ኢትዮጵያ ሃማሬሳና ካራማራ አካባቢ የነበረው የወታደሩ ቤተሰብ ህይወት ይህን ይመስል ነበር በግዜው፡፡ ጥሎ መውደቅም ይቻላል።

ያንዬ መላው ሐረርጌ ግዛት ጥይት ሳይጮህ የሚውልበት ጊዜ የለም ። 

የሠርጎ ገቦቹ ማሞ ቂሎ ጠመንጃ ተኩስ ድምፅ ጆሮዬ ላይ አሁንም አለ ። ቂው ጋ ! ቂው ጋ !

በአንድ ጠዋትም አንድ ጀብራሬ ወታደር የታጠቀው ሽጉጥ በእጁ ላይ የባረቀችበትንና የሸተተኝ የባሩዱ ሽታና ቀኑን ሙሉ በጆሮዬ ግንዴ ላይ ጬኸቷ የፈጠረብኝን ስሜት ታሪክም ፅፌ ለወዳጆቼም አስነብቤአለሁ ። 

የገረመውም ገርሞታል ። 

የጀብራሬው ወታደር ሽጉጥ የባረቀችው ለእኔና የልጅነት ባልንጀሮቼ ካሱና ጩኒ ደስታ ከረሜላና አረንቻታ ከእነ ሼህ ድልገባ ሱቅ ሊገዛል እንደቆመ ነበር፡፡ ያ/ ወታደር፡፡ ኢትዮጵዊ መሆኑን ነበር የማውቀው፡፡ አያውቀኝም፡፡ ያንዬ በእኛ የህጻንነት ዘመን፣ ትልቅ ሰው ፣ በተለይም ለመለዮ ለባሹ ታላቅ አክብሮት ነበረን፡፡ የኢትዮጵያው ወታደር በየትም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ህጻናትን እንደራሱ ልጅ የሚቆጥርበት ዘመን ነበር፡፡ በጣም ረጅም ዘመን እንዳይመስላችሁ፡፡ የምተርከው የዛሬ ሰላስምንት አመት የስምንት አመት ልጅ በነበርኩበት ግዜ በአይምሮዬ ተቀርጾ የቀረውን እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ አሁን ወደ ኮሎኔል ካርዶስ ቪያ ቪሴንስያ አጭር ታሪክ ልወሰዳችሁ ።

 

የተከበርክና የተወደድክ ኮሎኔል ሆይ !

ለአንተም ኢትዮጵያ ሁለተኛ አገርህ ነች ። 

በተመቸህ ጊዜ ግባባትና የጦር ሜዳ ጓዶችህ ጋር ተጋድሎህን ዝከርባት ። 

በፈለከው ጊዜ ደግሞ በሠላም ውጣ ። 

እኛም አንተንም ጓዶችህን እንወድሃችኋለን ። 

እንደ ባሕላችንም ሁላችሁንም ግዳጃችሁን የተወጣችሁትን እናከብርችኋለን ።

ስለከፈልከው መስዋዕት ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ያስታውሳሉ ።

ውቅያኖሶችና አኀጉሮች አቋርጣችሁ በክፉ ቀኖች ከጎናችን በመሰለፋችሁ አንተንም ሆነ ሌሎች ጓዶችህ የከፈሉትን መስዋዕትነት ኢትዮጵያዊያኖቹ በሕይወታቸው እስካሉ ድረስ ፈፅሞም አይረሱም ።

ከዚህ ሰው ታሪክና ማስታወሻ ጥቂት መማር ያቃታቸው በምድሯ በቅለውና አድገው ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ የሚጎነጉኑ ርካሽ የፖለቲካ ቁማርተኞችና የእንግዴ ልጆቿ ሁሉ የሞት ምች ይምታቸው ።

አገሬ ኢትዮጵያን በክፉ የሚያስቧትን ጡት ነካሾች በመላው 

ለኢትዮጵያ ግዛት አንድነት ባለማወላወል ቤቴን፣ ትዳሬን ፣ ልጆቼን ሳይሉ በሁሉም አቅጣጫ የተሰውት ዐርበኛ ልጇቿ ዐፅም ይፋረዳቸው ።

እናመሰግናለን ኮሎኔል ካርዶሶ ቪያ ቪሴንሲያ !

ቪቫ ኮሎኔል !

ዋንታ ናሜራ ዋኺራ ዋንታ ናሜራ፣

ዋንታ ናሜራ ዋኺራ ዋንታ ናሜራ፡፡

 

በትክክል ብዬው እንደሆን አላውቅም ልታረም !

Filed in: Amharic