አማራ ቢሆን ኑሮ….!!!
አሳዬ ደርቤ
➺የወሎ አማራ የከሚሴ ኦሮሞዎች ላይ ጥቃት ሊያደርስ ቢዘምት ኑሮ…
➺ሕጻናትና ሴቶች በየቀኑ የሚጨፈጨፉበት የወለጋ ዞን አማራ ክልል ውስጥ ቢሆን ኑሮ…
➺አዴፓ የሚባል ደካማ ድርጅት አገር ተረክቦ ብሔሮችን ለመጨፍለቅና ኢትዮጵያን ለማድቀቅ ሲንቀሳቀስ መመልከት ብንችል ኑሮ….
➺መተከል ላይ ቀይ እየተባሉ የተገደሉት አማራና አገዎች ‹‹ጥቁር›› ብለው በጅምላ ቢገድሉ ኑሮ…
➺አዴፓ ኦዴፓን ሲሆን፣ አብን ደግሞ ኦነግ ሸኔን የሚወክል ሽፍታ ሁኖ በጥቅሻ እየተግባቡ ንጹሐንን ሲቀጥፉ ብናይ ኑሮ…
➺አዴፓ የህውሓትን ሤረኝነትና እብሪተኝነት ወርሶ፣ መከላከያን ወግቶ በወልቃይትና በራያ በኩል ትግራይን ሲወጋ ብናይ ኑሮ…
➺በውጭ አገር የሚኖሩ የአብን እና የአዴፓ ደጋፊዎች ከኦነግ ሸኔ/ ከህውሓት ቡችሎች ጋር ገጥመው ኢትዮጵያን ወይም ደግሞ አንዱን ብሔር ‹‹ዳውን ዳውን›› ሲሉ ብንሰማ ኑሮ…
➺የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጉርሳቸው ቆጥበው የሰሩትን ኮንዶሚንየም የተከፋፈሉት አማራዎች ቢሆኑ ኑሮ….
➺‹‹ተከብቤያለሁ›› የሚለውን የእስክንድርን ፖስት የሰሙ ደጋፊዎቹ በመንጋ ተደራጅተው ሰው ሲገድሉና ንብረት ሲያቃጥሉ ብናይ ኑሮ…
➺ደሴ ወይም ጎንደር የተወለደው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን ለማገልገል ሲሞክር የአማራ ኤሊትና አክቲቪስት ‹‹የእኛ ብቻ ሁን›› ወይም ደግሞ ‹‹እኛ እንዲንወድህ ለእንትና ብሔር ያለህን ጥላቻ አሳየን›› እያሉ ሲጎትቱት ብንታዘብ ኑሮ…
➺የሃይማኖት ክፍፍል እያስተናገደ በሚገኘው የአማራ ክልል ውስጥ የተደራጁ ፓርቲዎች ሌላ ክልል እየገቡ በሃይማኖት ለመከፋፈልና ለማገዳደል ሲጥሩ ብንታዘብ ኑሮ….
➺በብሔርተኞች የተሞላው የአማራ ክልል በዜግነቱና በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውን የኦሮሚያ (የትግራይ) ክልል ‹‹ጨፍላቂ እና አሃዳዊ›› እያለ ሲፈርጅ ብንሰማ ኑሮ…
➺እንደ አጠቃላይ ብሔር ብሔረሰቦች ፈረቃ አውጥተው የሚዘምቱበት የአማራ ክልል እራሱን በመከላከልና “አትግደሉኝ” በማለት ፈንታ ወደ ሌሎች እየዘመተ የሚገድል ቢሆን ኑሮ…
.
.
ለኢትዮጵያ ያለኝን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ለአማራ ያለኝን ጥላቻም አሳይህ ነበር፡፡ በትዊተርም በለው በጦር ግንባር ከጎንህ ተሰልፌ አማራ ላይ ስዘምት ታገኘኝ ነበር፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሁሉ ግፍ በእኛ ላይ ሲፈጸምብን በፈገግታ የሚመለከተው ዘረኛ ሁሉ ስንገደል እልልታችንን በማቅለጥ ፈንታ ተቃውሟችንን በመግለፃችን ዘረኞች ይለናል። የሞት ጽዋችንን ያለ ምንም ጩኸት እንጎነጭ ዘንዳ ያመቻቸናል።