>

የህጻናቱ ደም...!!! (ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ)

የህጻናቱ ደም…!!!

ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ 

ወለጋ ውስጥ ሰሞኑን 180 አማሮች በግፍ እንደተጨፈጨፉ እና ከእነርሱም ውስጥ 70 ዎቹ ህጻናት እንደሆኑ መረጃ ወጥቷል። የህጻናቱም ደም ሄሮድ እንደአረዳቸው የቤተልሄም ህጻናት ደም ወደ እግዚአብሄር ይጮሀል።
ባለፉት 27 ዓመታት በድፍን ኢትዮጵያ እንዲሁ በግፍ ስለአለቁት አማሮች እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን(ጋምቤላውያንን ጭምር) ተቆጥተን ብዙ ብለናል። የምንችለውንም አድርገናል።  እብድ ኢሌ የሀረር ኦሮሞዎችን ሲያፈናቅልም ጮኸናል።
ይህኛው ግን ከሁሉም የከፋ ነው። 70 ምስኪን  አቅም የለሽ ህጻናትን መግደል አንደኛ ፈሪነት ነው። ሁለተኛ ከአውሬ ማነስ ነው። ሶስተኛ አቅል የሚያዞር የዘር ጥላቻ ነው።  ሌላ ፍቺ የለውም።
ማንኛውም እውነተኛ የነጻነት ታጋይ ወይም ነጻ አውጪ ነኝ የሚል ኃይል ዓላማው በደለኛ የሚለውን መንግሥት ዒላማ አድርጎ፣ ህዝብን ተንከባክቦ እና አቅፎ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን ለመመስረት ነው። በተጨማሪም ፍትህን ለማንገሥ፣ የዜጎችን ደህንነት እና መብት ለማስከበር ይዋጋል።  በሀገር ላይ ሰላም እና የሀብት ክፍፍል የሚደረግበትን ዘዴ ይቀይሳል።
ግፍን ለማስቆም ለራሱ ምሎ ለዜጎች ሁሉ ዋስትና ያለው ህይወት ለማስገኘት የራሱን ህይወት ይሰዋል። ይህ እውነተኛ የነጻነት ታጋይ ተግባር ነው።
በእኛ ሀገር ውስጥ ያሉት ለነጻነት እንታገላለን  የሚሉት ግን እላይ የተጠቀሰውን በማድረግ ፈንታ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ኃይል ብቻ በመዋጋት ፈንታ፣ ሥራዬ ብለው  ህጻናትን ጨምሮ ንጹሀንን እና አቅም የለሽ ዜጋዎችን፣ በተለይም አማሮችን ማረድ ነው። ሽፍታ እንዳይባሉ ሽፍታ ክብር አለው። ሽፍታ ገንዘብ ይዘርፋል እንጂ ዘር ለይቶ፣ ሆነ ብሎ  ዘር አያጠፋም።
አውሬ እንዳይባሉ፣ አውሬ ሲርበው ሌላውን አውሬ ያጠቃል እንጂ ዘር ለማጥፋት ብሎ ሌላውን አውሬ አይገልም።  ከአውሬ ያነሱ ናቸው።
እነሱ ከቶውንም ከነጻነት ጋራ ምንም ግንኙነት የላቸውም። መንግሥት ካለ ይህን ተገንዝቦ በእነዚህ ከሽፍታ እና ከአውሬ በታች በሆኑ ደም አፍሳሾች ላይ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ግዴታው ነው። አለበለዛ ሀገሪቱ በደም አበላ እንዳትጥለቀለቅ ያሰጋታል።
Filed in: Amharic