አብን፣ ባልደራስ፣ እናት፣ ትዴፓ እና ኢዜማ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተፈጸመ ያለውን ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ በተመለከተ በራስ አምባ ሆቴል በጋራ የሰጡት መግለጫ፤
በአገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የቀጠለው የጥላቻ ትርክት ኢትዮጵያዊ ርዕያችንና አንድነታችን እንዲናጋ በማድረግ አገራችንን ለከፍተኛ የማኅበረ-ፖለቲካ ምስቅልቅል ዳርጓት ይገኛል፡፡
በትሕነግ መራሹ የኢሕአዴግ መንግስት ሥርዓት ዘመን በአገራችንና በሕዝቧ ላይ ዘግናኝ አፈናና ሰቆቃ ሲፈጸም እንደቆየ ይታወቃል፡፡ በመላው የአገራችን ሕዝብና በዴሞክራሲ ኃይሎች የተባበረ ትግል አማካኝነት የጭቆና ሥርዓቱ ግንባር ቀደም ዘዋሪ የነበሩት ስብስቦች ከማዕከላዊ የስልጣን መንበራቸው እንዲገፉ በማድረግ አዲስ የለውጥ ተስፋ ለመፈንጠቅ አስችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአገራችን የፖለቲካ ችግር ስር የሰደዱ የትርክትና የመዋቅር መሰረቶች ያሉት በመሆኑና በአጠቃላይ ሥርዓት ሰራሽ በመሆናቸው አገራዊ የበጎ ኃይሎች አሰላለፍን በማጠናከር፤ ሁሉን አካታች የሆነ የብሔራዊ ውይይትና ድርድር መድረክ በመፍጠር፤ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ፍትኃዊ አማካይ ላይ በመድረስ ዘላቂ እልባት ማምጣት ይገባል የሚል አቋም ስናራምድ ቆይተናል፡፡
በተለይም የአገራችን ሕዝብ ከባድ መስዋእትነት የጠየቀውን ሁለገብ የጸረ-ጭቆና ትግል ሲያካሂድ የቆየው አገራችንን ወደ ተሟላ የሰላም፤ የዴሞክራሲና የፍትኅ ምዕራፍ ለማሸጋገር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ዜግነት እና የዜጎች መሰረታዊ መብቶች በአገራችን የማኅበራዊ፤ የፖለቲካና የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የተሟላ እውቅና እንዲያገኙ በማስቻል ዘላቂ ፍትኅን፤ እኩልነትን እና ዴሞክራሲን እውን ማድረግ እንደሚገባ በተደጋጋሚ አሳስበናል፡፡
ለአገራዊ ስኬታችን መሰረት የሆኑት የሕዝብ አንድነት፤ ወንድማማችነት፤ ሰላምና የሕግ የበላይነት መስፈን ጉዳይ የነገ ስራ ሳይባል በቁርጠኝነት ተቀናጅተን በፍጥነት ማረጋገጥ አለብን በሚል መልዕክታችንን ስንገልጽ ነበር፡፡ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር ካልተቻለ የምንመኛቸውን አገራዊ ግቦች ማሳካት እንደማንችል፤ የፖለቲካችን መሰረት የሆኑትን የአገርና የሕዝብ አንድነትን ለማስጠበቅ አዳጋች እንደሚሆን ይታወቃል፡፡
በዚህ ረገድ በባለፉት ሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ በርካታ ዜጎች የማንነትና የእምነት ተኮር ጥቃቶች ሰለባ ተደርገው ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ተፈናቅለዋል፡፡ ዘርና እምነት ተኮር የሆኑ ጥቃቶች መበራከት፤ አድማሳቸውን እያሰፉ በበርካታ የአገራችን ክፍሎች መዛመት፤ በክልሎችና በፌዴራል መንግስቱ በኩል ከሚታየው ጉልህ ቸልተኝነት ጋር ተዳብለው ሲታዩ ችግሩ ግንባር ቀደም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመሆን በቅቷል፡፡
በተለይ የጥፋት ፖለቲካ ተዋንያን የሆኑ ጽንፈኛ ስብስቦች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያራምዱትን የጥላቻ ትርከት ተከትለው በሚፈጸሙ ተከታታይ ዘር ተኮር ጥቃቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ተረጋግጧል፡፡ ጥቃቶቹን ለማስቆም የሚደረገው መንግስታዊና አገራዊ ጥረት ፍጹም የማይመጥንና በቂ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ በተለይ እየተፈጸሙ ያሉት ጥቃቶች በርካታና ተደጋጋሚ መሆናቸው፤ በመንግስት በኩል ከሚታየው ለከት የለሽ ዳተኝነት በተጨማሪ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ጭምር በጥቃቶቹ መሳተፋቸው ስጋቱንና አደጋውን ውስብስብ እንዳደረገው ለመግለጽ እንፈልጋል፡፡ በዚህ ሕዝብ አገት ነባራዊ ፖለቲካ ላይ ተመስርተን የአገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ርዕይ እውን ማድረግ እንደማይቻል ያለንን ስጋት በግልጽ ማሳወቅ እንሻለን፡፡
ስለሆነም፡-
የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በንቃት ለመጠበቅ፤ የአገራችንን አንድነት ለማጎልበትና ዘላቂነቷን ለማረጋገጥ እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጽናት በጋራ ግንባር ቀደም ሆነን እንደምንሰለፍ እያረጋገጥን፤
1. በአገራችን ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና በአጠቃላይ መጤ ተብለው በተፈረጁ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን።
2. የፌዴራሉ መንግስትና የክልሎቹ መንግስታት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው እናሳስባለን።
3. የችግሩን ግዝፈትና መደጋገም እንዲሁም በአገራችን አንድነትና ደኅንነት ላይ የደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘላቂ እልባት የመስጠቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕዝብ ተወካዬች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
4. የዚህ መግለጫ አካል የሆን ፓርቲዎችም ችግሩ የአገር አንድነት እና ደኅንነት ላይ የተጋረጠው አደጋ አስቸኳይ መፍትኼ እንደሚያሻው በማመን የመፍትኼ አካል ለመሆን እና የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናችንን እንገልፃለን።
5. በመንግስት በኩል እስካሁን በተፈፀሙት ጥቃቶች ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አመራሮች ሆነው የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በጥቃቱ የተሳተፉትን በሚመለከት በፍጥነት ተገቢው የማጣራት ሥራ እንዲሰራና በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ እናሳስባለን።
6. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ አሰላለፎች ውስጥ ተካትተው ዘርና እምነት ተኮር ጥቃቶችን የሚፈፅሙ አካላትን ለማውገዝ፣ ለማጋለጥ እና ለመከላከል ብሎም ለማሸነፍና በሕግ ጥላ ስር ለማዋል በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7. በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የምትኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአማራ ሕዝብ ላይ በጥላቻ ኃይሎች እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለማውገዝ፣ ለማጋለጥና ለፍርድ ለማቅረብ ያለምንም ልዩነት በጋራ እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
8. በተፈፀሙባቸው ጥቃቶች ምክንያት ደጋፊ ወገኖቻቸውን ላጡና በጅምላ ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁት ወገኖቻችን በአስቸኳይ የነፍስ አድንና የመልሶ ማቋቋም የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢና በቤኒሻንጉል ክልል በተፈፀሙት ዘር ተኮር ጥቃቶች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ነፍስ ይማር እያልን፣ የተለያዩ ጉዳቶች ለደረሰባቸው ወገኖች ማገገምን እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።
በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ዘርን፣ እምነትን እና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት አድርገው ከሚከሰቱ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች መጠበቅ ይገባቸዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ)
እናት ፓርቲ
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ!