>

ዐብይ አሕመድና ያላሳሰባቸው የድንጋይ ናዳ...!!! (እስክንድር ነጋ፤ የህሊና እስረኛ ቃሊቲ፤ አዲስ አበባ)

ዐብይ አሕመድና ያላሳሰባቸው የድንጋይ ናዳ…!!!

(እስክንድር ነጋ፤ የህሊና እስረኛ ቃሊቲ፤ አዲስ አበባ)


 

ከማኪያቬሊ እስከ ርካብና መንበር
ምርጫ 2013 ወዴት እየሄደ ነው? ጠቅላይ ሚንስትሩ በቢሯቸው በሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ‹‹ከዘንድሮው ምርጫ በኋላ የድንጋይ ናዳ ይኖራል ብዬ አልሰጋም›› የሚል አስተያየት ጣል አድርገወል፡፡ ስጋቱ ለምን እንደሌላቸው ሲያስረዱንም ‹‹የዘንድሮውን ምርጫ ከ1997ቱ ምርጫ ጋር አታወዳድሩት፣ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው›› ብለውናል፡፡
በሌላ በኩል የድንጋይ ውርወራ ቢኖር እንኳን በከተሞች ዙሪያ ይወሰናል ተብሎ ስለሚታሰብ ከፀጥታ ሃይሉ አቅም በላይ እንደማይሆን ከገለፁበት ቃና (tone of his speech) እንድንረዳ ተደርገናል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ሰላሙን ሁላችንም እንፈልገዋለን፡፡ ሥራ ስለሚበዛባቸው የሰሞኑን የማይናማር ዜና (ወታደራዊ መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ማስቆም አልቻለም) የተከታተሉ አይመስለኝም፡፡ በወታደራዊ አቅማቸው መተማመን ችግር የለውም፡፡ በወታደር መመካት ግን የውድቀት መንገድ ነው፡፡ የሚመካ በእግዚዓብሔር ብቻ ይመካ፡፡
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኮሎኔል ዐብይ በሃይል እንደሚያምኑ በ‹እርካብና መንበር› በፅሐፋቸው አስቀድመው ነግረውናል፡፡ ችግር ሲያጋጥማቸው ከአንዴም፤ ሁለቴ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በወታደር ዩኒፎርም ባየኋቸው ቁጥር ወደ ‹እርካብና መንበር› መፅሐፋቸው እሮጣለሁ፡፡ በዚህ መፅሐፋቸው የአመራር ጥበብን ከማኪያቬሊ (Makiavelian) መማር እንደሚገባ ይገልፃሉ፡፡
ማኪያቬሊ ስለ አመራር ጥበብ ያለው ግንዛቤ በአንድ ዓረፍተ ነገር ሲገለፅ ‹‹አንድ መሪ ከመፈቀር ይልቅ ቢፈራ ይሻለዋል›› የሚል ነው፡፡ ስለ አተገባበሩ ሲገልፅም ‹‹ዱላና ዳቦን እያፈራረቁ ሕዝብን መምራት ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡ ሕዝብ አልታዘዝ ሲል በዱላ መመታት እንዳለበት፤ መሪውን ሲታዘዝ ደግሞ ዳቦ ሊሰጠው ይገባል የሚል አስተምህሮ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ማኬያቬሊ ይህን ሃሳቡን የከተተበትን ‹ዘ ፕሪንስ- The Prince› የተባለችውን ቀጭን መፅሐፍ ለማንበብ በተደጋጋሚ ሞክሬ አንዴም እንኳን ልጨርሰው አልቻልኩም፡፡ ድክመቱ የእኔ ነው፡፡ መፅሐፉን እኔ አነበብኩትም፤ አላነበብኩትም ከዓለም ታላላቅ ቅርሶች ተርታ ይመደባል፡፡ ብዙ ቁም ነገሮች አሉት፡፡ ሃሳቡ ለእኛ ዘመን ባይሆን እንኳን ብዙ የአውሮፓ ነገስታት እና መሪዎች ከራስጌያቸው አይለያቸውም ነበር፡፡ በታሪክ ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡
በእኛ ዘመን ግን ነገሮች ተለዋውጠው አንድ ሰው የማኪያቬሊ ተከታይ ከተባለ ‹‹ሸረኛ፣ ተንኮለኛ፣ አምባገነን›› ሆኗል እንደማለት ነው፡፡ ባለንበት የዴሞክራሲ ዘመን ማኪያቬሊ በፖለቲከኞች አንደበት ወይም ፅሁፍ ውስጥ አይጠቀስም፡፡ ከተጠቀሰም በአሉታዊ ገፅታው ብቻ ነው፡፡ ይህ እውነታ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደፊት በሚያስነብቡን መፅሐፋቸው ግምት ውስጥ ያስገቡታል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሂደቱ ሲገመገም
ወደ ምርጫውና ድንጋይ ውርወራው እንመለስ፡፡ አስብ አሁን ያለው የምርጫ ዝግጅት እንዴት ይገመገማል? ከሁሉ አስቀድሞ የምርጫ ቦርድ የሚያደርገው ዝግጅት አለ፡፡ ከዝግጅት አኳያ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንዳለ ከቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አንደበት ሰምተናል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 250 ሺህ አካባቢ የምርጫ አስፈፃሚዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ 75 ሺህ ያህሉ አስተማማኝ በሚባል ደረጃ ዝግጅት አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነገሮች በጥሩ ከሄዱ ተጨማሪ 75 ሺህ አስፈፃሚዎች እስከ ምርጫው ዕለት ይዘጋጃሉ፡፡ ሁለቱ ተደማምረው 150 ሺህ ገደማ ይሆናሉ፡፡ ሒሳቡ አይከብድም፡፡ መቶ ሺህ የምርጫ አስፈፃሚዎች ጎድለው ነው የዘንድሮውን ምርጫ የምናደርገው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ‹‹ባለን የሰው ኃይል ምርጫውን እናደርጋለን›› ብለውናል ብርቱካን፡፡
ይህ ክፍተት ባለበት ሁኔታ ምርጫውን ምድረግ ይመከራል ወይ? ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉን ምርጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ ሀገራዊም፤ ዓለም አቀፋዊም ጉዳዮች አይፈቅዱም፡፡ በያዝነው ዓመት በበርካታ ሀገራት ምርጫ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያም የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ በሌላ በኩል ሙሉ የምርጫ አስፈፃሚዎች በሌሉበት ሁኔታ ተዓማኒ ምርጫ ማድረግ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ተጨባጭ ምልክቶች እየታዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በመላ ሀገሪቱ ከተሰራጩት የምርጫ ቁሳቁሶች መካከል (ማህተሞች፣ ቅፆች ወዘተ) በተወሰኑት ላይ የዝርፊያ ሙከራ መደረጉን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አብስረዋል፡፡ በቂ የምርጫ አስፈፃሚዎች አለመኖራቸው እንዲ ዓይነት ሙከራዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ በተለይ ወሳኝ በሆነው የቆጠራ ጊዜ፤
ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት የዘንድሮው ምርጫ በብዙ መልኩ ከ1997ቱ ጋር ባይመሳሰል እንኳን ቆጠራው ተዓማኒ ካልሆነ በውጤቱ አንድ ይሆናሉ፡፡ ማለትም በምርጫ 97 ያየነውን የድንጋይ ናዳ በምርጫ 2013ም የማስተናገዳችን ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጡንቻ ናዳውን ቶሎ ሊያስቆም ይችል ይሆናል፡፡ እንዳይከሰት አድርገን ሁሉንም ቀዳዳ መድፈን ግን አይቻልም፡፡ የድንጋይ ውርወራውን ፈፅሞ እንዳይከሰት ማድረግ የሚቻለው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ብቻ ነው፡፡ ዝግጅቱ ላይ ግን መሰረታዊ ችግር ከወዲሁ እያየን ነው፡፡
ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? ብርቱካን አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ የክልል መስተዳድሮች የሚተባበሩ ከሆነ የአስፈፃሚዎችን ቁጥር በአጭር ጊዜ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ መስተዳድሮቹ ቢተባበሩም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አይቀረፍም፡፡ ብዙ ቀዳዳዎች ግን ሊደፈኑ ይችላሉ፡፡ የእነዚያ ቀዳዳዎች መደፈን በድንጋይ ናዳ መኖርና አለመኖር መካከል ሚዛን የሚደፋ ሊሆን ይችላል፡፡
አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚፈልጉት ምንድን ነው? ድፍን ባለ መልኩ ምንም ዓይነት ድንጋይ ውርወራ እንዳይነሳ ይፈልጋሉ ብለን ካሰብን እንሳሳታለን፡፡ ውርወራውን ሊፈልጉት ይችላሉ፡፡ የማኪያቬሊ ተማሪ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎችን በማኪያቬሊ መነፅር እንያቸው፡፡
ይቀጥላል . . .
Filed in: Amharic