>

የወሮበሎችን አገዛዝ ፈጽሞ እምቢ ማለት ያስፈልጋል! (ከይኄይስ እውነቱ)

የወሮበሎችን አገዛዝ ፈጽሞ እምቢ ማለት ያስፈልጋል!

ከይኄይስ እውነቱ


አገራችን ኢትዮጵያ ምናልባት በ16ኛው ክ/ዘመን ከተነሡት የአሁኖቹ ዘረኞች ቅም አያቶች በኢትዮጵያችን ላይ ካሠፈኑት ገዳና ሞጋሳ ከተባለ ማንነት፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ቅርስ አውዳሚ የሽብርና የወረራ ሥርዓት ካልሆነ በቀር በታሪካችን እንዲህ ዓይነት ሀገረ መንግሥት ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሠራ፣ ወደር የማይገኝለት የጭካኔ፣ የጐሠኝነት፣ ኢትዮጵያ/አማራ እና ከተሜ ጠል፣ ድንቁርናን ከዕብደት ያስተባበረ የፈሪ ዱርዬዎች አገዛዝ ገጥሟት አያውቅም፡፡ እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ሽብርተኞች አሠማርቶ፣ የአገር መከላከያ የሌለውን የጦር መሣሪያና ሎጂስቲክስ አቅርቦ ሕፃናትን፣ እናቶችን ያውም ነፍሰ ጡሮችን፣ አረጋውያንን ያለምንም ዕዳ በደላቸው ማንነታቸውንና እምነታቸውን ብቻ መሠረት አድርጎ የዘር ፍጅት የሚፈጽም አረመኔያዊ የአገዛዝ ሥርዓት በ21ኛው ክ/ዘመን ለመኖሩ አልሰማንም፡፡ 

ከዚህ በኋላ ይህ ዕርቃኑን የወጣውንና ኢትዮጵያን በቁሙ ገሃነም ያደረጋትን የአውሬውን የዐቢይ አገዛዝ – ኢሕአዴግ/ብል(ጽ)ግና – ማንነት አልተረዳንም የሚል ካለ ብአዴን ከሚባለው ባርነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው የቁም ምዉታን ስብስብ ጋር የሚደምር ነው፡፡ 

በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ቢጨንቃቸው መንግሥትና ሥርዓት ያለ እየመሰላቸው ራሱ ሕዝብን አሸባሪና ሽብርተኞችን ደጋፊ ለሆነ ወሮበላ አገዛዝ አቤት ሲሉ እናስተውላለን፡፡ ዳኝነትን ከወንጀለኛው መፈለግ ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ነው? ሰውየው ከፍሬው ታውቋል፤ አሁን ደግሞ በንግግሩም ማስመሰል አቁሞ እየለየለት ነው፡፡ አነሣሣችን ተራ ‹‹ጫጫታ›› እንዳልሆነ በጽኑ ደዌ ለተያዘውና ሥልጣን ላሰከረው መምዕላይ በተግባር እናሳየዋለን፡፡ ዙሪያውን የከበቡት የጥፋት ዓላማው አጋሮች፣ ባንዳዎች፣ ሰብእናቸውን የሸጡ አድርባዮች፣ ሆድ አደሮችና ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች አንድ ሐሙስ የቀረውን የወንበዶች አገዛዝ በንጹሐን ደም ለማስቀጠል አይሁዳዊ ዱለታቸውን የሰርክ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ 

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአገርን ሰላምና ጸጥታ የሚያስከብር፣ የሕዝብን ደኅንነትና ዋስትና የሚያረጋግጥ እንዲሁም ዳር ድንበር የሚጠብቅና ከጠላት የሚታደግ፣ ኢትዮጵያዊ የፖሊስ ኃይል፣ የደኅንነት ተቋም እና የአገር መከላከያ ኃይል የለንም፡፡ ይህ በማዕከል ብቻ ሳይሆን በየክፍላተ ሀገሩም ያው ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝብ ሕይወት ደኅንነቱን፣ ርስት አገሩን ለወንበዶች መተው የለበትም፡፡ በማንነታቸውና በእምነታቸው ብቻ በከንቱ ደማቸው የፈሰሰ ወገኖቻችንን አደራ አለብን፡፡ የፈጣሪን ለፈጣሪ ትተን፣ እንደየ እምነታችንም በጸሎት እየተጋን፣ የወሮበሎች አገዛዝ እንጂ መንግሥት እንደሌለን በሚገባ ተገንዝበን፣ ራሳችንን አደራጅተን አጥፊውን ኃይል በማስወገድ የራሳችንን እና የአገራችንን ህልውና መታደጊያው ሰዓት እጅግ ዘገየ ከሚባል በቀር አሁን ነው፡፡ 

የዚህ አስተያየት ዋናው መልእክት በወሬ እንዳንፈታ ነው፡፡ አገዛዙ እና ግበረ በላዎቹ፣ ለግል ዓላማቸው የተቆጣጠሩት የሕዝብ ሜዲያዎች (ግልብጥ ሎሌዎቹን ዋልታ፣ ፋና እና ሪፖርተርን ጨምሮ) በማዕከልም ሆነ በየክፍላተ ሀገሩ ያሉት፤ በግል ሜዲያ ስም ባገር ውስጥና በውጭ የተቆጣጠሯቸውና ድርጎ የሚሰፍሩላቸው፤ እንዲሁም በየማኅበራዊው ሜዲያ ያሠማሯቸው ምንደኞች በሚያስተላልፉት መልእክት ሳንረበሽና ሳንሸበር፤ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ብቻ አስተማማኝ ከምንላቸው ምንጮች እየተከታተልን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ኢሕአዴግ የሚባለውን ቆሻሻ ድርጅት ከአገራችን ሳናስወግድ ከእንግዲህ እንቅልፍ ሊኖረን አይገባም፡፡ በቁሙ ሥጋ የለበሱ አጋንንቶች ናቸው አገራችንን የተቆጣጠሩት፡፡ ማናቸውንም መግለጫ ያውጡ፣ ሺህ ጊዜ አስቸኳይ ዓዋጅ ያውጁ፣ ትርጕም ስለሌው ‹ምርጫ› ያውሩ፣ ሕገ ወጥ ኃይላቸውንም አስታጥቀው ያሠማሩ አትረበሹ፣ አትደንግጡ፣ አትከፋፈሉ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከነሱ ይበልጣልና፡፡ ጆሮአችንን አንስጣቸው፡፡ እምቢኝ በቃን እንበል፡፡ የኛ ጭንቀት የሕዝብ ደኅንነት፣ የአገር አንድነትና ህልውና ነው፡፡ በቃን አንገፈገፈን!!! ብለን እውነትን ከያዝን በኅብረት ከተነሣን ማነው የሚቋቋመን፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን እንደሚሉት ‹‹ብዙ ሕዝብ እግዚአብሔር ነው››፡፡ አገዛዝ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፡፡ ሁላችንም በየአካባቢያችን ያለውን እንቅስቃሴ ነቅተን እንከታተል፡፡ 

የሃይማኖት አባቶች ያለምንም ፍርሃት ወጥታችሁ ለሕዝባችሁ መልእክት አስተላልፉ፡፡ በጣም ዘግይታችኋል፡፡ በተለይም የርትዕት ተዋሕዶ ቤክ፣ አገልጋዮቿና ምእመናን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት (በቅርቡ 3ዓመታት እጅግ በከፋ መልኩ) ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እውነተኛ አባቶች በልጅነት መንፈስ ተዉ ብንላችሁም ነጣቂ ተኩላዎችን በውስጣችሁ አቅፋችሁ ይዛችኋል፡፡ ጫናው ይገባናል፡፡ ሕዝባችንን አረመኔ አገዛዞችን አትታዘዙ እምቢ በሉ ስንል፣ እናንተ አዕይንተ እግዚአብሔር ከሆናችሁ፣ ለዓለም ምዉት ነን ካላችሁ የሰማያዊው መንግሥት እንደራሴዎች አባቶቻችን ደግሞ የላቀ ይጠበቃል፡፡ ዛሬ በዓላውያን ፊት እውነተኛ ምስክር ሆናችሁ ከክርስቶስ ባደራ የተቀበላችሁትን መንጋ ካልታደጋችሁ ነገ ምእመናንም፣ አገርም የአምልኮት ስፍራም አይኖረንም፡፡ ጸሎት/ምሕላ መልካም ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው አባቶችና እናቶች ጸሎት በቊዔት እንዳለው እናምናለን፡፡ ያ እንደተጠበቀ ሆኖ መንጋው ራሱን ከአውሬዎች እንዲከላከል የእረኝነት አለኝታነታችሁን በተግባር አሳዩ፡፡ 

መልእክቴን ከመቋጨቴ በፊት በብዙ መከራና ስቃይ ውስጥ ለምትገኘው የትግራይ ወገኔ በሰማይም በምድርም አደራ የምልህ የአረመኔው ዐቢይ አገዛዝ ፍላጎት የሰሜኑን ሕዝብ (በተለይ አማራና ትግሬውን አናክሶ) ከኢትዮጵያ አገሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ሙሉ ለሙሉ ለማኮላሸት ያለመ ነው፡፡ እንወቅበት፡፡ የመጠን ልዩነት ካልሆነ በቀር ያልተገፋ ያልተበደለ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ምሬቱ ሁሉም ዘንድ አለ፡፡ አማራው ማኅበረሰብ ጠላት ሆኗችሁ አያውቅም፡፡ እናንተም በሚገባ ታውቁታላችሁ፡፡ የሕወሓት ውላጆች መጫወቻ አንሁን፡፡ ኃይልና ጊዜ ሳናባክን ኅብረት ፈጥረን በኢትዮጵያ ባድማ ላይ ‹ኦሮሚያ› የሚባል ሕወሓት የፈጠረላቸውን የቅዠት ‹አገር› ለመመሥረት የሚባክኑትን የ16ኛው ክ/ዘመን ወራሪዎች ልጆችና ወራሾችን በሚገባቸው ቋንቋ ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ በገዛ አገርህ አትኖርም ዘርህን አጠፋለሁ የሚልን ኃይል በሰላማዊ ትግል እንግጠመው የሚል ረብ የለሽ የፖለቲካ ንግግር ለመስማት ጆሮ የለኝም፡፡ ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ በሕይወት የመኖር ዋስትናውን በኃይል ለመቀማት የሚመጣን ማንኛውንም አካል በኃይል የመመከት ተፈጥሮአዊ፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊም መብት አለው፡፡

እግዚአብሔር ፈቅዶ ከሰጠን ምድር የት እንሂድ? አገር ህልው ስትሆን ሁሉን እንደርስበታለን፡፡ መሬቱም የትም አይሄድ፡፡ ወደ አእምሮአችንና ኅሊናችን ከተመለስን ገበታው ለሁላችን ይበቃል፡፡ ሰላማችን ሲመለስ ቁጭ ብለን ተወቃቅሰን፣ ተወያይተን፣ ተመካክረን፣ ላለፈው ይቅር ተባብለን ሁላችን በእኩል የምንኖርባት አገር ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህ ጥሪ የነገድ/ጐሣ ልዩነት ሳይደረግ በአራቱም ማዕዝናት ለምንኖር ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን፣ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን ናት ብሎ ለሚያምን ለሚቀበል ኢትዮጵያዊ ወገኔ ሁሉ ይድረስ፡፡

Filed in: Amharic