>

ሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች (አምባቸው ደጀኔ- ከወልዲያ)

ሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


“እኔ አልዋሽም፤ ውሸት የሚባል ነገር አልወድም!” የሚል ሰው ካለ የመጀመሪያው ውሸታም እሱ ነው፡፡ ለበጎም ይሁን ለክፉ ሁላችንም እንዋሻለን – በዚህ አንወሻሽ፡፡ ማጋነንም ውሸት ነው፤ እውነትን ላለመናገር መታቀብም ውሸት ነው፤ ላለመዋሸት ዝምታን መምረጥም ውሸት ነው፤ የቅለት ክብደቱ ደረጃና ዓላማው ይለያይ እንጂ ሁላችንም እንዋሻለን፡፡ ውሸት ወይም ሀሰት የሕይወት አንዱ ቅመም ነው – ጠቃሚ ነው ማለቴ ግን አይደለም፡፡

አሁንም ቢሆን “ሰማይ ዝቅ፣ መሬት ከፍ ይላሉ እንጂ እኔ ዋሽቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም ቢሆን እመብርሃን ታጥፋኝ አልዋሽም” የሚለኝ ካለ መብቱ ነው፡፡ እኔ ግን ወደተነሳሁበት ጉዳይ ገባሁ፡፡ በነገራችን ላይ የሦስቱም የውሸት ደረጃ አንዱ ከሌላው ሳይበልጥ ተመሳሳይ ሚዛን በመርገጡ ሦስቱም አንደኛ ናቸው፡፡ ሌሎች ባለደረጃዎች ከአራተኛ ይቀጥላሉ፡፡

ውሸት ደረጃ አለው፡፡ ትልልቅ ውሸቶች አሉ – ሰውን ከሰው የሚያቆራርጡ፤ የሚያገዳድሉም ጭምር፡፡ ለጨዋታና ለፈገግታ ሲባል የሚሰነዘሩ ቆይቶ ግን እንዳስፈላጊነታቸው ሀሰት መሆናቸው የሚነገሩ ትንንሽ ውሸቶችም አሉ፡፡ በጓደኛሞች መካከል ብዙ እንተዛዘባለንና ስለውሸት ያለን ግንዛቤ የሚናቅ አይመስለኝም፡፡ ከትልልቅ ውሸታሞች መካከል ሦስቱን አሁንና ዛሬ በ2013 የትንሣኤ ዋዜማ ላይ ላስተዋውቃችሁ ነውና ተዘጋጁ፡፡ በሪከርድ ደረጃ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስን መዝገብ ያለተቀናቃኝ በተመሳሳይ ነጥብ በአንደኝነት የሚወጡትን ውሸታሞች ማለቴ ነው እንጂ ከደረጃ አራት ጀምሮ የሚሰደሩትን ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገራት ውሸታሞችን ካየን ዘርዝረን አንጨርሳቸውም፡፡ በተለይ በዚህ ባለንበት ዘመን ውሸት እንደፋሽን ሆኖ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አልሆነም፡፡ ሙስናም እንደዚሁ፡፡ ማንም ይሁን ማን፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣንም በለው የበታች ሠራተኛ ከመሬት እየተነሣ እንደጣቃ ሲቀደድ ማየት የዘመኑ አሳዛኝና አሳሳቢ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ተተኪው ትውልድም ይህን መረን የለቀቀ ዘመን አመጣሽ መጥፎ ልማድ እየተከተለ በመጥፋት ላይ ይገኛል፡፡ የማያሳፍረው እያሳፈረ፣ የሚያሳፍረው የልብ ልብ በመስጠት እያጀገነ ትውልድ ሲዘቅጥ በስፋት ይታያል – በሃይማኖቱም በዓለማዊውም፡፡

ውሸት ምን እንደሆነ ታውቁታላችሁና ስለምንነቱ መናገር አያስፈልገኝም፡፡ ዋሾነት ግን ከተፈጥሮ ባሕርይም፣ ከጤና መቃወስም፣ ከተጋቦትም፣ ከኅልውና ማስቀጠያነትም፣ ከቅጣትና ወቀሳ ማምለጫም፣ ከዐመልም (ከባሕርይ ጋር ይቀራረባል) ወዘተ. ጋር ይገናኛል፡፡ እኔ አሁን የምጠቅሳቸው ውሸታሞች ግና ይበልጡን ከጤንነት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ምን ማለቴ ነው – እነዚህን ዓይነት ሰዎች ካልዋሹ ይታመማሉ፤ ደጋግመው ካልወሻከቱ ህመማቸው ይጸናባቸውና ምናልባትም እስከሞት ሊደርሱ ይችላሉ – እነዚህን ሰዎች የጤና ሣይንሱ “Pathological liars” ይላቸዋል – መለስ ዜናዊም የዚህ ደዌ ተጠቂ ነበር፤ ምን እሱ ብቻ ሁሉም ሕወሓታውያን የዚሁ ልክፍት ሰለባዎች ናቸው፡፡ ልናዝንላቸው ይገባናል፡፡ ችግሩ በሥልጣን መሰላል እንደምንም ተንጠላጥለው ወደላይ ከወጡና ትልቁን ሀገርን የመምራት ቦታ ከያዙ የሚመሯትን ሀገር ድምጥማጧን እስከማጥፋት መድረሳቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ሀገራቱና ሕዝቦቻቸው ወዮላቸው! አንድ የሀገር መሪ ጨዋ ሲሆን የሚመራው ሕዝብም ጨዋ ይሆናል ተብሎ ይገመታልና የመሪ አመራረጥ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አለዚያ መሪው ዋሾ ዱርዬ፣ ተመሪውም ቀልማዳ ዱርዬ ይሆኑና ሀገሪቷ የለየላት የኳስ አበደች ሀገር ትሆናለች – ልክ እንደኛዋ፡፡

ከሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች ሁለቱ ከኢትዮጵያ ሲሆኑ አንዱ ከውጭ ሀገር ነው፡፡ ከውጪው ልጀምር፡፡ ኢራቃዊ ነው፡፡ በሣዳም ሁሤን አገዛዝ ዘመን ብቸኛው ክርስቲያን ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበር፡፡ አሊ ሀሰን አብድ አልማጂድ አል ቲክሪቲ ይባላል፡፡ በኩርዶች ላይ የኬሚካል የጦር መሣሪያ በመጠቀሙ ምክንያት ኢራቃውያን “ኬሚካል አሊ” በሚል ቅጽል ስም ይጠሩት ነበር፡፡ የአሜሪካ ጦር ባግዳድን እየከበበ ባለበት ወቅት ይህ ሰው “ባግዳድ የአሜሪካ መቀበሪያ ትሆናለች” እያለ ዓለምን በሣቅ ጦሽ ያደርግ የነበረ ሰው ነው፡፡ እውነቱን እኮ ያውቀዋል፡፡

ቀጣዩ ዋሾ የኛው ጉድ አቢይ አህመድ ነው፡፡ ክርስቶስ “አፌን በምሣሌ እከፍታለሁ” እንዳለ አቢይም “አፌን በሀሰት ንግግር እከፍታለሁ” ብሎ የሰባተኛነት ንጉሥነቱን የእናቱን ትንቢት ለማስፈጸም ቆርጦ ሳይነሣ አልቀረም፡፡ ሰውዬው ውሸታምነቱ ሳያንሰው የሚናገረው ሁሉ የትናንቱ ከዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ደቂቃ ንግግሩ ከሁለተኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሴከንዶች ንግግሩ ጋር እርስ በርስ ይጋጫል ወይም ይላተማል፡፡ ገራሚ ሰው ነው!!

ሦስተኛው አንደኛ ዋሾ የወያኔ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ነው፡፡ ይህም ሰው ልክ እንደ ኬሚካል አሊ “መቀሌ የወራሪው አቢይ ጦር መቀበሪያ ትሆናለች” በሚለው ንግግሩ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን ከአንዱ ጎሬው ውስጥ ሆኖ ብዙ የአማራ ልዩ ኃይሎችን በ10 ደቂቃ ውስጥ እንደደመሰሰና በርካታ የኤርትራ ክፍለ ጦሮችንም ከ20 ምናምን ታንኮች ጋር ድባቅ እንደመታ፣ በአሥር ሽዎች የሚቆጠሩ የጠላት ወታደሮችን እንደገደለና እንደማረከ እየተናገረ ነው – “ለአፍ አቀበት የለውም” መባሉ እንዴቱን ያህል ትክክል አባባል መሰላችሁ፡፡ 

እነዚህ ሦስት ውሸታሞች አእምሯቸው በተለዬ ሁኔታ ካልተመረመረና መንስኤው ካልታወቀ ጦሱ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ኅልውና ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከሀሰት ንግግር እግዜር ይጠብቀን!!

Filed in: Amharic