>
5:26 pm - Wednesday September 17, 6504

የጎሳ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ፣ የጋረጠው ብሔራዊ አደጋ! ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የጎሳ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ፣ የጋረጠው ብሔራዊ አደጋ!

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ የታሪክ መታጠፊያ ላይ የምትገኝ ሀገር ሆናለች፡፡ ምእራባውያን የምጣኔ ሀብት እርዳታ አንሰጥም፣ወይም እናዘገያለን በማለት ያስፈራራሉ፡፡ የዲፕሎማቲክ ጫና በመፍጠር የሐገሪቱን ሉአላዊነት ይፈታተናሉ፡፡ ግብጽና ሱዳን በበኩላቸው  ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ላይ የውሃ ሙሌትን ለማሰናከል የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይምሱት ስር የለም፡፡

ይሄም ብቻ አይደለም በታቀደ እና ድንገተኛ በሚመስል መልኩ  ከውጭ ሀይሎች፣ በተለይም ከታሪካዊ ጠላቶቻችን አኳያ ሀገሪቱን ለመጉዳት የሚሰነዘረው ጥቃት ለሀገሪቱ መረጋጋት የሚበጅ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት፣ ድርጅታዊ አቅም የተሸመደመደ ቢሆንም፣ወይም የህውሃት ድርጅታ አቅም አከትሞለታል ቢባልም፣ የትግራይ ሚሊሻ ጦር ደፈጣ ተዋጊዎች ጥቃት ማድረስ ካላቆሙ፣ የትግራይ ወጣቶች እናዳያኮርፉ መንግስት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከተሳነው( ለወጣቶች፣ የትምህርትና ስራ እድል በማመቻቸት ሊሆን ይችላል፣ የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት ወዘተ የወጣቶች ልብ እንዳይሸፍት ማድረግ ይቻላል፡፡) የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሊዶል ይቻለዋል፡፡ በውጤቱም በትግራይ የሚደረገው የፖለቲካ ሽግግር ጥርጣሬ ውስጥ ይዶላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በትግራይ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በእጅጉ ያስቸግራል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወለጋ፣ ቤኒሻንጉል እና በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ የንጹሃን ኢትዮጵያዊ ዜጎች በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጆች መገደል የኢትዮጵያውያንን ልብ ያሻክራል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ለዘመናት የነበረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የህይወት መስተጋብር ወዘተ ወዘተ በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ በህዝብ መሃከል ውጥረትን ይፈጥራል፡፡ የደቀቀውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ አፈር ድሜ ያስግተዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የአፋር እና ሶማሌ ኢትዮጵያዊ ወንድማማቾች መሃከል በድንበር ይገባኛል ምክንያት ጎራ ለይተው የሚያደርጉት ፍልሚያ ለኢትዮጵያ አንድነት ቡግንጅ (ጠንቅ) ነው፡፡

6ኛው ሀገር አቀፍ የምርጫ ውድድር በፍጥነት እየቀረበ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሀገሪቱ ምርጫውን በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ የተዘጋች አትመስልም፡፡እንደ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ከሆነ አሁን ድረስ ( ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሚያዚያ 9 ቀን 2013 ዓ.ም.) መራጩ ህዝብ የሚበጀውን ለመምረጥ በነቂስ ወጥቶ አልተመዘገበም፡፡ የሰለጠነ መንግስት ለማቆም ብቸኛው አማራጭ ፍትሃዊ፣ርትአዊ፣ አለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው የምርጫ ውድድር ላይ የሚቀርቡ የህዝብ ወኪሎችን መምረጥ ሆኖ ሳለ ህዝቡ ለመምረጥ በበቂ ቁጥር አልተመዘገበም መባሉ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ከ10 ቀናት በታች ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የመራጩ ህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ለመመረጥ የተመዘገበው ቁጥር ደግሞ የቀነሰው በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር በመሆኑ እጅጉን አስደንጋጭ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በጸጥታ ችግር ምክንያት በብዙ የሐገሪቱ ክፍል የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመራጮች የምዝገባ ጣቢያዎች አሁን ድረስ አልተከፈቱም ( እስከ ሚያዚያ 9 ቀን 2013 ዓ.ም.)

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ለመፍታት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ካቃታት፣ ኢትዮጵያውያን ርሰበርሳችን  የምንጋጭ ከሆነ፣ በፍጥነት አንድነታችንን መጠበቅ ካልሆነልን፣ ከተፋፈልን ለውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥቃት መጋለጣችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መደርደር ቢቻልም የኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት እንዲላላ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አርብቶ አደሮች ለዘመናት አልፎ አልፎ በግጦሽ ሳርና ውሃ መሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚጋጩ ቢሆንም፡፡ በአሁኑ ዘመን በህዘብ መሃከል በየግዜው ግጭቶች የሚቀፈቀፉት በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ በባህሪው አፋጀሽኝ ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናስታውሰው በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እምነት ወይም ተስፋ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት እንደ ሰም አቅልጠው፣እንደ ብረት ቀጥቅጠው የገዙት የሕውሃት የፖለቲካ ዘዋሪዎች ከማእከላዊ መንግስት ስልጣናቸው ገሸሽ ካሉ በኋላ በኢትዮጵውያን መሃከል መልካም ግንኙነት ሊፈጠር እንደሚችል፣ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት ግዜው አሁን ነው ተብሎ፣ተዚሞ ነበር፡፡ የነበረው የፖለቲካ ለውጥ ራሱ የአንድነት ታምቡር የሚመታ ይመስል ነበር፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ካስከበሩ፣ከጠበቁ አስደናቂ ውጤት እንደሚያመጡ በታሪካቸው ብዙ ቦታ ላይ ደማቅ እና አንጸባራቂ ድል ስላስመዘገቡ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል አለምን ባስደመመ መልኩ፣ምእራባውያን ነጮች፣ በተለይም ቅኝ ገዢ ሀገራት መሪዎችና የነጭ ትምክህተኞች ለማመን እና መቀበል  ባዳገታቸው ሁኔታ ፋሺስት ጣሊያንን በአድዋ ጦርነት ድል የመታነው የውስጥ አንድነታችንን ለማስከበር በመቻላችን ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዶክተር አብይ የስልጣን አክሊል በደፉ ማግስት በተለይም በውጭ ሀገር የመጀመሪያ ጉዞአቸው ላይ ስለ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ በአደባባይ በመናገራቸው፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና በብዙ መልኩ በመግለጻቸው ኢትዮጵያውያን በደስታ ስሜት ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ የዶክተር አብይ ሁነኛ ሸሪክ ወይም የትግል አጋር የነበሩት  አቶ ለማ መገርሳ  ‹‹ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ›› የሚል ዲስኩር በአደባባይ በመናገራቸው ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን በስሜት ሰክረው ነበር፡፡ በሌላ በኩል በለውጡ ዋዜማና መባቻ ላይ ‹‹ የኦሮሞው ደም ደሜ ነው›› የሚሉ ኢትዮጵያውያን  በተለይም በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የሚኖሩ ወጣቶችና አዛውንቶች በነቂስ አደባባይ ላይ በመውጣተቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ቦግ ብሎም ነበር፡፡  በአጭሩ ሀገሪቱም ከብዙ አመታት በኋላ የራሷን ታሪክ ያገኘች መስሎ ታይቶም ነበር፡፡ ነበር ልበል ዛሬ የነበረው አንዳልነበረ በሚገኝበት አሳፋሪና የጭንቅ ግዜ ላይ በመድረሳችን፡፡

ምን ስህተት ተሰራ ?

በማናቸውም የፖለቲካ ሽግግር ላይ ውጣውረድ የማይቀር ክስተት ነው፡፡ በተለይም ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገው ጉዞ በርከጃታ መሰናክሎች እንደሚገጥሙት ለማወቅ የፖለቲካ ምሁርነትን አይጠይቅም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅጉን የተለየ ነው፡፡ እንደ ብዙ የፖለቲካ አዋቂዎች የጥናት ወረቀት ውጤት ከሆነ በኢትዮጵያ የለውጥ ዋዜማ ላይ በስልጣን ኮርቻ ላይ የሚፈናጠጡ ቡድኖች በስልጣን ዘመናቸው ጥቂት አመታት ውስጥ የሕዝብ ድጋፍ ይቸራቸዋል፡፡ መጨረሻቸው ግን አያምርም፡፡ ሀገሪቱን በደም አባላ አጥበው ከስልጣናቸው ይወገዳሉ፡፡ ደርግ በስልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ አመታት ውስጥ  በመሃልና በዳር ሀገራት ከባድ ተቃውሞና ጦርነት ቢከፈትበትም ህዝባዊ ቅቡልነት ግን ነበረው፡፡ መሬት ላራሹና የከተማ ትርፍ ቤት አዋጅ በርካታ የህግ ክፍተት ቢታይባቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ አስገኝተውለት ነበር፡፡ የተስፋፊውን ዚያድ ባሬ ጦር ያሸነፈው ህዝባዊ ድጋፍ ስለነበረው ነው፡፡ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝም ቢሆን ከደደቢት በረሃ ተነስቶ ምኒሊክ ቤተመንግስት የገባው በታሪካዊ ጠላቶቻችን እና በአንዳንድ ምእራባውያን ሀገራት የሎጄስቲክ ድጋፍ ብቻ አልነበርም፡፡ ለመጨረሻው ድሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ አልተለየውም፡፡ በደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ የተማረረው ህዝብ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖረው ገበሬ ከደርግ የባሰ አይመጣም በሚል 

የዋህነትና ስሜታዊነት በሩን ለወያኔ ወለል አድርጎ ከፍቶለታል፡፡ደርግም ሆነ ወያኔ ግን መጨረሻቸው አላማረም፡፡በሁለቱም አገዛዞች በኢትዮጵያ ጦርነት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብም ከችጋር ሳይገላግሉ፣ታሪካዊ ውድቀታቸውን ተግተው ከፖለቲካው አደባባይ ተሸቀንጥረው ወድቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዛሬ ሶስት አመት በፊት ስልጣን ላይ የወጡት ዶክተር አብይ እና መንግስታቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ክብርና ሙገሳ ተችሯቸው እንደነበር ምንም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ የወያኔ ጎሰኛ እና ግፈኛ አገዛዝ ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑ ከተወገደ በኋላ የሀገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ ሊቆም እንደሚችል፣ በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር በይበልጥ ስር ሊሰድ እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ተስፋን ጭሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ዛሬ ከሶስት አመት በኋላ የሐገሪቱ ሰላም አስተማማኝ መሆን አልቻለም፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍል የህዝብ ዋይታ ገኗል፡፡ የሚሰማው ሁሉ አቅልን የሚያሳጣ እና ከባድ ሀዘን ላይ የሚጥል ነው፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል እንዲሉ ከእብድ ውሻ የከፉ መሳሪያ አንጋቾች የንጹሃንን ዜጎች ህይወት ስለመቅጠፋቸው፣ የሰላማዊ ዜጎችን መኖሪያ ቤቶች ስለማቃጠላቸው፣ ንብረቶችን ስለመዝረፋቸው ወዘተ ወዘተ ሰርክ አዲስ የሚሰማ አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ሊመጣ ስለመቻሉ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ማን ነው ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ ፡፡ በእኔ በኩል ወቀሳዬን የአንበሳውን ድርሻ ማለቴ ነው፡፡ ለፖለቲካ ስርአቱና ከወያኔ ኢህአዲግ ለተወረሱ ችግሮች እሰጣለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሙሉበሙሉ ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር የፖለቲካ ስርአቱን ሙሉበሙሉ ተጠያቂ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሪቱ የሚበጀውን መንገድ ባለመከተሉ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ ስንቶቻችን ነን የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን የምንገኘው ?መልሱን ለአንባቢው ትቼዋለሁ፡፡ ለአብነት ያህል ባለፉት ሶስት አመታት የተገኘው የፖለቲካ ለውጥ በትክክለኛው ሀዲድ ላይ እንዲጓዝ የብዙዎቻችን አስተዋጽኦ ምን ነበር ? በነገራችን ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች እንደሄሱት ከሆነ የፖለቲካ ሽግግሩ የተያዘበትን መንገድ ይተቻሉ፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ

1.በቀድሞው ኢህአዲግ ዛሬ ብልጽግና ያሉ ወይም የነበሩ የለውጡ አራማጆች የፖለቲካ ለውጥን በተመለከተ ግልጽ የሆነ እረጅም እቅድ ለማውጣት የሚጠበቅባቸውን አልሰሩም ወይም ለመስራ ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ እነርሱ ትኩረት ሰጥተው የነበረው ጎለተው ታይተው ለነበሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍትህ እጦት፣አደገኛ ምዝበራ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ስለተፈጸሙ ግብረስይልን ወዘተ በማጋለጥ ላይ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የሜቴክ የስራ ሃላፊዎች ለፍርድ ማቅረብ፣ ግብረሰይል ይፈጸምበት የነበረውን የዝነኛውን ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ መዝጋት፣ለአመታት የታሰሩ ፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ወዘተ ወዘተ መፍቀድ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለፖለቲካ ሽግግር ለሚረዱ ቁምነገሮች ትኩረት አልሰጡትም፡፡ በውስጣቸው እና ከፓርቲያቸው ውጭ ለሚገጥማቸው ተቃውሞ በግዜው ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ከራሰቸው ፓርቲ ውስጥም ሆነ ከውጭ ለሚገጥማቸው ተቃውሞ የሰጡት ግምት አናሳ ነበር፡፡

2.በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሸን ወይም ቀውስ ለመቆጣጠር ግልጽ የሆነ እቅድ ባለመኖሩ ምክንያት በተለይም የጎሳ ፖለቲከኞች የሚፈጥሩትን አደጋ በግዜው መቆጣጠር የተቻለ አይመስለኝም፡፡ ለአብነት ያህል በሀገሪቱ የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተደራጁ ኢመደበኛ የወጣቶች ስብስብ ወይም ቡድኖች የፈጸሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ማስታወስ ይበቃል፡፡

3.በተመሳሳይ መልኩ ከትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ጋር ቁጭ ብሎ ለመነጋገር፣በርን ለሰላማዊ ውይይት ክፍት ለማድረግ፣ በሰለጠነ መንገድ ለመነጋገር ከመንግስት አኳያ ሆደ ሰፊ መሆን አልተቻለም ነበር፡፡ ወይም ሰፊ እቅድ የተያዘ አይመስለኝም፡፡ ወደ ጦርነት ሳይገባ ቅደመ ንግግር ቢጀመር አሁን የተከሰተው ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አይከሰትም ብዬ አስባለሁ፡፡ ጦርነት የእግር ኳስ አይነት ጨዋታ ባለመሆኑ ክቡር የሰውን ልጅ ህይወት ይቀጥፋል፣ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ተንከራታች ያደርጋል፣ ለዘመናት የተገነቡ መዋእለ ንዋዮችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ያፈራርሳል፡፡ለዚህም ነው ሀገራት ወደ ጦርነት ውስጥ ከመዶላቸው በፊት ደግመው ደጋግመው የሚያስቡት፡፡ በእኔ እድሜ ብቻ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት( ዛሬ ሩሲያ ተክታታለች)፣ የተባበረችው አሜሪካ የቃላት ጦርነት ከገጠሙ አርባ አመት አለፋቸው፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱም የኑክሌር ባለቤት የሆኑ ሀገራት ፊትለፊት ጦርነት አልገጠሙም፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት በአፍጋኒስታን ምድር ሙጃሂድንን በመደገፍ፣የተባበረችው አሜሪካ ደግሞ ታሊባንን በማስታጠቅ( ኋላ መልሶ የአሜሪካ ጠላት ሆኗል) የእጅ አዙር ጦርነት አድርገዋል፡፡ በአጭሩ አሜሪካኖችም ሆኑ ሩሲያዎች የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ስለተረዱ በሰሜን ኮሪያና ኢራን ጉዳይ ላይ ይጨቃጨቃሉ እንጂ ወደ ለየለት ጦርነት አይገቡም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት ቤቱን በሰራባቸው ሀገራት ደግሞ የጦርነት ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በትግራይ ሰፍኖ የነበረው ሰላም እና ጸጥታ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ባለመስፈኑ ምክንያት በሌሎች የሐገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጽእኖ ስለመኖሩ እሙን ነበር፡፡

በትግራይ ምድር የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮችና የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ሚሊሻዎች ጦርነት ከመግጠማቸው በፊት በክልሉ ሰላምና ጸጥታ በመስፈኑ ምክንያት የልብ ልብ የተሰማቸው የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች፣ በፌዴራሊስት ጭንብል ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ሞክረው ነበር፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች፣በቤኒሻጉል ክልሎች ለተከሰቱ አለመረጋጋቶች እጃቸው እንደነበረበት መንግስት ሲከሳቸው ይሰማል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ረብሻ ልባቸውን ያሳበጣቸው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በስራቸው ያለው ሚሊሻ ጦር በትግራይ በነበረው የሰሜን እዝ ጦር ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ኖቬምበር 3 2020 ጥቃት ከፍተዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ደመና ሆኖ ይኖራል፡፡

በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና ጸጥታ  በቅጡ ማስከበር ቢሆንለት ኖሮ ፣ የህዳር 3 2020 ( እ.ኤ.አ. ) ድርጊት ሊፈጸም አይችልም ነበር፡፡ በቀሪው የሀገሪቱ ክፍል ሰላም እና ዴሞክራሲ፣ እንዲሁም ነጻነት ምሉሄበኩልሄ ቢሆን ኖሮ፣ የትግራይ ተወላጆችም የነጻነት፣ ዴሞክራሲ ጥያቄ ለትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ያቀርቡ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ በምላሹ ደግሞ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ሳይወድ በግድ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ይዘጋጅ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ሲባል ግን በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የፖለቲካ ነጻነት አልነበረም ማለቴ አይደለም፡፡ ከትግራይ ክልል በብዙ መልኩ የተሻለ የፖለቲካ ለውጥ ታይቷል፡፡ የዲሞክራቲክ ተቋማት ግንባታው ግን ምሉሄበኩልሄ መሆን አልተቻለውም፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሚያካሂዳዊ ጦርነት ህጋዊ፣ የፖለቲካ ህጋዊነት ያለው መሆኑ ቢታወቅም በብዙዎች ዘንድ በተጋሩ ዘንድ ፊታቸው ላይ ድቅን  የሚለው የሚከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ነው፡፡ ስለሆነም የትግራይ ህዝብ የፌዴራሉን መንግስት ወታደሮች እንደ ነጻ አውጪ እንዲመለከታቸው በርካታ ስራዎች መከናወን አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ የፌዴራሉን መንግስት ወታደሮች እንደ ወራሪ እንዳይመለከታቸው ሰላማዊ አመራጮችም ጎን ለጎን መካሄድ የግድ ይላል፡፡

በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ጥናት ውጤት ከሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ሀገሪቱ ለገጠማት የሰላምና ጸጥታ ችግር ዝቅተኛ ግምት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲናገሩ እንደተደመጠው ከሆነ በየቦታው የሰላምና ጸጥታ ስጋት የተከሰተው በዋነኝነት ምክንያቱ በቅርቡ የፖለቲካ ነጻነት እውን በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት የፖለቲካ ነጻነት እውን በመሆኑ ወደ ሀገር ቤት የገቡ አንዳንድ የፖለቲካ ሀይሎች ለሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ሁነኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በነገራችን ላይ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚከሰቱ ግጭቶች ተጠያቂዎቹ ስለ ዴሚክራሲያዊ ሂደት ምንም እውቀት የሌላቸው ተራ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚከሰቱ የርስበርስ ግጭቶች፣ ሰላምና አለመረጋጋት ተጠያቂዎቹ ወይም ዋነኛ የግጭት አቀጣጣዮች ረዥምና ስትራቴጂክ ፖለቲካዊ አላማ ወይም ግብ  ያላቸው ( ያነገቡ)  አክራሪ የጎሳ ብሔርተኞች በስውር የሚደግፏቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን የውጭ ሀይሎች ናቸው፡፡ ጊዜው አሁን ነው በማለት እናት ኢትዮጵያን ሰላም ነስተዋታል፡፡ እረፍትም አሳጥተዋታል፡፡

አረ ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ይሆን ? (Where do we go from here?)

የጎሳ ፖለቲካ በማናቸውም ስፍራ፣በማንኛውም ቦታ አደገኛ ነው፡፡ለሀገር ህልውና አይጠቅምም፡፡አንድን ሀገር ሰላም የሚነሳ ነው፡፡የህዝብን ዋይታ ያባብሳል፡፡ዘውትር የህዝብ ኑሮ (ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው፡፡) የቆቅ ኑሮ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ትውልድን ያደናግራል፡፡ በትውልድ መሃከል ፍቅርና አንድነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡በዜጎች መሃከል የባቢሎን ግንብ ይገነባል፡፡ ለዚህም ነው በዚች ምድር ላይ የሚገኙ ሀገራት ሁሉ (  ድህነት ቤቱን ከሰራባት ኢትዮጵያ በቀር) የጎሳ ፖለቲካን አያስፈልገንም በማለት ወደ ታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ አሽቀንጥረው የጣሉት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘውግ ፖለቲካ አኳያ ለመደራጀት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖራቸውም (በጎሳ  የመደራጀት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) በጎሳ ፖለቲካ መደራጀት እርባና የለውም፡፡ አንዱን ከሌላኛው ሳያበላልጡ፣ሁሉም የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ለአንድ ሀገር መጥፎ ምሳሌ ናቸው፡፡ ለአንዲት ሀገር መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮች የመፍትሔው አካል ሳይሆኑ፣ የችግሩ ማእከል ናቸው፡፡ እነርሱ ምንግዜም ቢሆን በችግር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ አክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች ለሀገሪቱ አንድነትና አለመረጋጋት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሌሎች የዲሞክራሲ እና ነጻነት ምሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ በሀገራችን ገቢራዊ አለመሆን ወዘተ ወዘተ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአንድ የጎሳ ክልል ሰላም ከሌላ ኢትዮጵያ ሰላም ማግኘት አትችልም፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ያደረጉ ሽምቅ ተዋጊዎች ባሉበት ሀገር ሰላም እና ጸጥታ ህልም መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ባደረጉ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ታጣቂዎች በወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች ለአብነት ያህል በሰሜን ሸዋ ኤፍራታና ግድም ወረዳ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይ የኦነግ ሸኔ በመባል የሚጠራው የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት በየግዜው የሚፈጽመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማቆሚያው የጥ እንደሆነ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የብልጽግና ፓርቲ ወይም በብልጽግና ፓርቲ የኦህዲድ ንኡስ ፓርቲ ኦነግ ሸኔ የተሰኘው ታጣቂ የጎሳ ቡድን የሚፈጽመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሰረታዊ በሆነ መልኩ መከላከል ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ታላቅ ስጋት ውስጥ የዶለ( የከተተ) ይመስለኛል፡፡ በእኔ አስተያየት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ሁሉ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ ሊኖራቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ከኢትዮጵያ አንድነት አኳያ የብልጽግና አባል ፓርቲ አባላት ሁሉ አንድአምሳል፣አንድ አካል መሆን ቢያቅታቸው፣ በሰለጠነ መንገድ ተቀራርበው፣ቁጭ ብለው በሰከነ መንፈስ ከተነጋገሩ በኋላ በቅድሚያ ለኢትዮጵያ አንድነት መተባበር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የእነርሱ መተባበር አክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመፈጸማቸው በፊት ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል፡፡

አክራሪ ብሔርተኞች በሐገሪቱ አንድነት፣ ሰላም እና መረጋጋት ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፣ መንግስት በፍጥነት፣ በውስጡ ተሰግስገዋል የሚባሉ አክራሪ ብሔርተኞችን ማወቅ፣ መለየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

በእኔ አስተሳሰብ ዶክተር አብይ አህመድ እና መንግስታቸው ከሌሎች የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅቶች በበለጠ ሀገሪቱ ከተደቀነባት ብሔራዊ አደጋ እንድትወጣ ዛሬም ቢሆን ታሪክ እድሉን የሰጣቸው ይመስለኛል፡፡ከተጠቀሙበት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ድግሞ ታላቅ ሃሳብ ስላላቸው ወይም ምርጥ የአመራር ችሎታ ስላላቸው አይመስለኝም፡፡ ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ያላቸውን መልካም ራእይና ምኞት እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሌሎችም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የሚበጅ ፖሊሲ ሊኖራቸው ይችላል ብዬም አስባለሁ፡፡ የዶክተር አብይ መንግስት ኢትዮጵያ ከተደቀነባት ብሔራዊ አደጋ ሊታደጓት እድሉ አላቸው ያልኩበትን ምክንያት አንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፤-

  1. ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ የታሪክ መታጠፊያ ዶክተር አብይ የብልጽግና ፓርቲ መሪ ናቸው፣የኢትዮጵያም ጠቅላይ ሚነሰትር ናቸው፡፡ ስለሆነም የሎጂስቲክ አቅርቦት እና የተቋማት ቁጥጥር፣ እንዲሁም የጸጥታው መዋቅር የበላይ ሃላፊ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ወደ መልካም ጎዳና እንድትጓዝ ይረዳል፡፡
  2. ዶክተር አብይና መንግስታቸው ኢትዮጵያ ከጎሳ ፖለቲካ ወደ ዜግነት ፖለቲካ እንድትሸጋገር ሚዛናዊ መሆን ይቻላቸዋል
  3. ምንም አንኳን ኢትዮጵያን ከጎሳ ፖለቲካ ለመገላገል ያለው እድል ጠባብ ቢሆንም ፣ የመንግስታቸው ውሳኔ ለመስጠት መዘግየት ሀገሪቱን ለውጪ ሀገራት ጥቃት ሊያጋልጣት ይቻለዋል፡፡ ስለሆነም መንግስታቸው በሰለጠነ መንገድ የጎሳ ፖለቲካ ስለሚመክንበት መንገድ ከኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ ጋር መመካከር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ፓርላማ ( የህዝብ ተወካዮች ስብሰባ) ላይ ተገኝተው ንግግር ያቀረቡት ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት ከሆነ ‹‹ ኢትዮጵያ አንደነቷ ሲናጋ ›› ማየት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራቸው እንድትከፋፈል ፍላጎታቸው እንዳልሆነም በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲናጋ አይፈልጉም፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም እንዲከበር ምኞታቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ በመጨረሻዋ ደቂቃ የአንድ ሰው መስእዋትነት ሀገሪቱን ማዳን አይችልም፡፡ የአንድን ሀገር አንድነት እና ሰላም ለማስከበር ግልጽ የሆነ እቅድና ቁርጠኛ አመራርን ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን ይሄንኑ ገቢራዊ ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ያላችን አንድ ሀገር ናት፡፡ የተወለድነው፣ የምንማረው፣ ሰርተን የምባላው፣የምናድገው፣ በመጨረሻም ከዚች አለም በሞት ስንለይ የምንቀበረውም በዚችው ውድ ሀገራችን አፈር ውስጥ ነው፡፡ ስለሆነም ለሀገራችን ህልውና እና አንድነት የሚበጅ የፖለቲካ መስመር እንድንከተል የመንግስት ወይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ብቻ  አይደለም ሀላፊነቱ የኢትዮጵያውያን ዜጎችም ጭምር ነው፡፡ሰላም፡፡

Filed in: Amharic