>

ጥቂት መዛግብታዊ እውነቶች ስለ ወልቃይት-ጸለምት… ነጠቃ! (አሰፋ ሀይሉ)

ጥቂት መዛግብታዊ እውነቶች ስለ ወልቃይት-ጸለምት… ነጠቃ!

አሰፋ ሀይሉ

— መሠሪው ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፣ የወያኔ ገደል ማሚቶ ማኒፌስቶ፣ እና የፕ/ር ገብሩ ታረቀ እማኝነት!

የብዙ የኢትዮጵያችንን ችግሮች ምንጮች ስናጣራ – የብዙ ችግሮቻችን ምንጮች ከውጪ የመጡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወያኔ ወልቃይት-ሁመራ-ፀለምትን እና ራያን የትግራይ ግዛት ተደርጎ መካለል አለበት ብሎ ያሳያት ዶናልድ ሌቪን የተባለ አሜሪካዊ ሶሺዮሎጂስት ነው፡፡
ይሄ ሰውዬ በእኛ ዘመን አቆጣጠር በ1957 ዓ.ም. (በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ1965) ላይ ባሳተመው «Wax and Gold» በሚል መጽሐፉ፣ አማራ የሚባል ሌሎቹን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በበላይነት ጨፍልቆ የሚገዛ ሕዝብ አለ በማለት፣ የጎንደር፣ የመንዝና የጎጃም አማራዎች (በማላውቀው ምክንያት ወሎን ይዘለዋል) እንዴት በታሪክ እንደተሳሰሩና፣ እንዴት እርስ በርስ በመመሣጠር (እና በመተባበር) የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ረግጠው ሲገዙ እንደኖሩ ለማሳየት ያልተጣጣረው ጥረት የለም፡፡
የአማራው ሥሪተ ሰብዕና በሀይልና ጉልበት ላይ የተመሠረተ ጦረኝነት እንደሆነም ደግሞ ደጋግሞ በመጽሐፉ ያሰፈረው ሃሳብ ነበር፡፡ ይህን ለመቀባባት ግን በተለይም በመንዝ ምድር ሄዶ የአማራውን ሕዝብ አኗኗርና ባህል፣ እንዲሁም የአማራውን ረዥም ዘውዳዊ ታሪኮች ጨምሮ በማካተት በመጽሐፍ አውጥቶታል፡፡
በዚህ መጽሐፉ ላይ ነበር ይሄው ዶናልድ ሌቪን በወቅቱ ኤርትራን ጭምር የሚያጠቃልለውን የኢትዮጵያ ካርታ በመጽሐፉ የመጀመሪያ ገጽ ላይ በማስፈር፣ እና ተከዜን ተጎራብተው የሚገኙት የወልቃይትና ሁመራ አካባቢዎች እንዲሁም በወሎ በኩል ያለው የራያ አካባቢ የትግርኛ ተናጋሪ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ካርታው ላይ በመሣል – እነዚህ አካባቢዎች የትግርኛ ተናጋሪዎች የሚኖሩባቸው ስለሆኑ፣ ለአስተዳደር ተገቢ የሚሆነው ትግርኛ ተናጋሪ ከሆነው ከትግራይ ጋር በአንድ አስተዳደር ስር ቢጠቃለሉ ነው – በማለት ማንም ያልጠየቀውንና የማያገባውን ከመጽሐፉ ዓላማ ጋር የማይገናኝ ሴራ በመጽሐፉ አስፍሮ ለዓለም አሳወቀ፡፡
ዶናልድ ሌቪን ይህን ያደረገው በ1957 ዓ.ም. ላይ ነው ብያለሁ፡፡ ግን ይሄ ሰውዬ በወቅቱ ቁልጭ ያለ የራሱ ታሪካዊ አስተዳደራዊ ካርታ ከነበራት ሀገራችን ላይ ለምን ትግርኛ ቋንቋን ብቻ መርጦ፣ ካርታ ሠርቶ ከትግራይ ጋር ለማካለል ተነሳ? የቋንቋ ክፍለሀገር እየሸነሸነ በመጽሐፉ ከነካርታው ስሎ እንዲያሳትም ማን ፈቀደለት? ምንስ አነሳሳው?
የሰውየው ዓላማ በትግርኛ ተናጋሪነት ቋንቋ ለቋንቋ የሚግባባን ሕዝብ በአንድ ላይ ቢተዳደር የተሻለ ነው ከሚል ቅን ሀሳብ የመነጨ ከነበረ፣ ለምን በወቅቱ የኢትዮጵያ ክፍለሀገር የነበረችውንና በትግርኛ የሚናገሩ ዜጎች ያሉባትን የኤርትራ ክፍለሀገርንስ አካባቢዎች በካርታው ላይ ከትግራይ ጋር ደባልቆ አላካተታቸውም? በተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪነት የወቅቱን ክፍለ ሀገሮች (‹‹ጠቅላይ ግዛቶች››) ካካለለ ላይቀር – ለምንስ በነካ እጁ በኦሮምኛ ወይም በጉራጌኛ ወይም በሌላ ተመሣሣይ ቋንቋ የሚናገሩትንስ በካርታው ላይ ለምን አንድ ላይ ስሎ አላሰፈራቸውም? ለምን ትግርኛን ብቻ መረጠ?
የሰውየውን ምክንያትና ተልዕኮ ማወቅ ባልችልም፣ ስለ ሰውየው መሠሪ ሃሳብ ብዙ ነጥቦችን ማንሳት ግን እችላለሁ፡፡ አንዱን ማስረጃዬን እጠቅሳለሁ፡፡ ሰውየው በአማራው ላይ ያደረበትን ጥላቻ ያወቅኩት ቀደም ብዬ ለዩኒቨርሲቲ ጥናት ጽሑፌ ይረዳኝ ዘንድ በኢትዮጵያውያን የሞራል ሰብዕና ላይ የተሠሩ ጥናቶችን በማፈላልግበት በ90ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ በዓለማቀፍ ጆርናል ላይ በታተመው በዚያ የዶናልድ ሌቪን ጥናት ላይ አማራውን የሚገልጽባቸው ቃላት እጅግ አስደንግጠውኝ ነበር፡፡
በጆርናሉ ውስጥ ሌቪን አማራን አረመኔ ቅኝ ገዢ በማስመሰል የገለጸባቸውን 19 (አስራ ዘጠኝ) ቅጽል ስሞች ቆጥሬ ለታሪክ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ ከእነዚያ ሌቪን አማራውን ከገለጸባቸው የጥላቻ ቃላት መካከል ‹‹ኮሎኒያሊስት››፣ ‹‹ዲክታተር››፣ ‹‹ሰብጁጌተር››፣ ‹‹ሄጄሞኒክ››፣ ‹‹ሩለር››፣ ‹‹ባርባሪክ››፣ ‹‹ሜርሲለስ››፣ ‹‹ፓራሳይቲክ››፣ ወዘተ. የሚሉ ቃላት ይገኙባቸው ነበር፡፡
ሰውየው በአማራ ላይ ሥር የሰደደ ጥላቻ እንዳለው ስመለከት ገርሞኝ ነበር በጣም፡፡ ከምን የመነጨ እንደሆነ ተመራምሬ ልደርስበት ስላልቻልኩ፣ ከጆርናሉ መሐል የተወሰኑ ሀሳቦችን ብቻ ወስጄ ሌላውን ጣልኩት፡፡ (ያ ሌቪን ጆርናል በምንጭነት ያገለገለበት ያልታተመ ጥናቴ አሁንም በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተመጻሕፍት ውስጥ ይገኛል፡፡)
በበኩሌ ለመጀመሪያ ጊዜ የወልቃይት ሁመራ ፀለምትን እና የራያን አካባቢዎች ከትግራይ ክፍለሀገር ጋር በትግርኛ ተናጋሪነት ሰበብ አንድ ላይ በማጣመር በካርታ በማስቀመጥ የመጀመሪያ ሰው ያጋጠመኝ ያ ዶናልድ ሌቪን የተባለ አሜሪካዊ ጊንጥ ነው፡፡ የጊንጡን ታሪክ ለመረዳት እንደቻልኩት – ወደ ኢትዮጵያ የሶሽዮሎጂ ጥናት ለማድረግ ሲመጣ – በለብ ለብ ‹‹ልዩ ፕሮግራም›› በሚሰኝ እንግዳ የሆነ የትምህርት አሰጣጥ ዘዬ፣ በተካለበ ፍጥነት የዶክትሬት ዲግሪውን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከመጀመሪያ ዲግሪ ተነስቶ ማስተርስና ዶክትሬቱን እንዲቀበል ተደርጎ ነው የመጣው፡፡
ታሪኩን ካልቀየሩት፣ ለሚፈልግ፣ አሁንም ስለ ሰውየው በቂ ፍለጋ በማድረግ ይህንኑ ማረጋገጥ ይችላል፡፡ በግሌ እንደማስበው ግን ሰውየው በምሁር አምሳል ወደ ሀገራችን የመጣው ያንኑ በመጽሐፉ አሳትሞ ያሳየንን እኩይ ተልዕኮ አንግቦ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው አንዳንድ የአማራ ልሂቃን ይሄንን ሰውዬ ጭራሽ የአማራን ታሪክ ለዓለም አሳወቀልን በሚል ዋዋቴ ‹‹አባ ሊበን›› የሚል ሀበሻዊ ስም ሰጥተው ሲያንቆለጳጵሱት ተመልክቼ አንገቴን በሀፍረት ደፍቼያለሁ፡፡ ወያኔዎቹ ግን ሥልጣን ከያዙ በኋላ በክብር እንግድነት በመንግሥት ደረጃ ግብዣ ልከው ከአሜሪካ ካስመጡት በኋላ፣ ለሰውየው የክብር ዶክትሬትና የብሔራዊ ጀግና ሜዳሊያ ሸልመውታል፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየው ሰውየው ለወያኔዎች ታላቅ ውለታ የዋለላቸው መሆኑን ነው፡፡ የአማራ ሸላሚ ነሆለሎቹ ይሄንን አይተው እንኳ ስለሰውየው ያላቸውን አድናቆት ደግመው የፈተሹት አይመስለኝም፡፡ ይህን ያልኩት የዛሬ ሶስት ዓመት የሰውየውን መጽሐፍ ከነካርታው አስደግፌ የወያኔ የሁመራ ይገባኛል ጥያቄ ከዚህ ሰውዬ እኩይ ሥራ የመነጨ መሆኑን ሳስረዳ፣ ብዙ የአማራ ልሂቅ ተቃውሞኝ ነበርና ነው፡፡
ለማንኛውም ይሄ ሰውዬ መጽሐፉን ካሳተመ ከ 10 (ወይም ከ11) ዓመት በኋላ ነው ወያኔ በማኒፌስቶዋ ላይ ‹‹አማራው የትግራይን ህዝብ ጨቁኖ ታሪካችንንም ነጥቆ ባህሉን በላያችን ላይ በግድ በመጫን እየገዛን ነው›› በማለት ‹‹ይሄን መንግሥታዊ መመሪያ የሆነ የአማራ አገዛዝና ጭቆና እስክናስወግድ ድረስ የአማራን ሕዝብ ሠላም እንነሳዋለን›› የሚል አማራውን በጠላትነት የሚፈርጅ አስቂኝ መግለጫ ያወጣቸው፡፡
ወያኔ በቀጥታ ዶናልድ ሌቪን በመጽሐፉ በካርታ ሥሎ ያተመውን ቃል በቃል በመኮረጅ (ወይም እንደ ፎቶግራፍ በማንሳት) ለመጀመሪያ ጊዜ የትግራይ ግዛት ‹‹በምዕራብ በኩል ወልቃይትንና ፀለምትን ያጠቃልላል›› የሚል አዋጅ የያዘ የ1968 ዓ.ም የተ.ሓ.ኅ.ት. ማኒፌስቶዋን ያሳተመችውም ዶናልድ ሌቪን በ‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ›› (ሰምና ወርቅ) ካተመላት ከ10 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡
ወያኔ የዶናልድ ሌቪንን ቃል እንደ ገደል ማሚቶ አንድም ሳታስቀር በማሰተጋባት፣ አማራውን ጨቋኝ ጠላቷ አድርጋ፣ የወልቃይትና ፀለምትን የአማራ ታሪካዊ አስተዳደራዊ ግዛት፣ ዓይኗን አፍጥጣ የትግራይ ታሪካዊ ግዛቴ ነው ብላ በማኒፌስቶዋ ካተመች ከ20 (ከሃያ) ዓመታት በኋላ ደግሞ – የኢትዮጵያ መንግሥት ለመሆን በቃችና – በምኞት ያለመችውን ግዛት የጸገዴ አርማጭሆን አካባቢ ሁሉ ቦጭቃ ጨማምራበት – ከአማራው (ከጎንደር እና ከወሎ) ላይ በጉልበት ነጥቃ ወደ ቀዳማይ ክልል ትግራይ (ወደ ክልል-1) አካለለችው፡፡ እና ‹‹ምዕራባዊ ትግራይ›› የሚል የዳቦ ስም አወጣችለት፡፡ ከላይ እንዳልኩት – መሠሪውን የሀሳብ አፍላቂዋን – ዶናልድ ሌቪንን – ከሀገሩ አስጠርታ – በብሔራዊ ጀግና ክብር ሸልማ ሸኘችው፡፡
ድርቅና ሲበዛ መታመምን ያመለክታል፡፡ እኔ አሣፍ መሆኔን እያወቅኩት፣ አይደለሁም አብርሃ ነኝ ብዬ ድርቅ ካልኩ፣ ነገሩ ከድርቅና ያልፍና ወደ አዕምሮ ህመም ደረጃ ከፍ ይላል፡፡ የወያኔዎችም ድርቅና እንደዚያ ወደ ህመምተኝነት ደረጃ የተጠጋጋ ድርቅና ነው፡፡ የጎንደርና የትግራይ ህዝብ (ሁለቱም ሕዝቦች) ሑመራ-ወልቃይት-ፀለምት-ራያ ለዘመናት የኖረ የአማራ ታሪካዊ ርስት መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ቀሪውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ነው፡፡
በጎንደር የታተሙ የሑመራ ነዋሪ መታቂያ ካርዶ እስካሁን ማህተማቸው ሳይደርቅ በነዋሪዎች እጅ መኖራቸውን፣ ከብዙ በአካባቢዎቹ ይኖሩ ከነበሩ ወዳጆቼ በዓይኔ በብረቱ አይቼ ያረጋገጥኩት ሀቅ ነው፡፡ እና የሰው መሬት ነጥቆ የምን ድርቅና ነው? አንዳንዴ የወያኔዎቹ ናዚ ሽማግሌዎች፣ ጤነኛ አይመስሉኝም፡፡ ደረቆች ብቻ አይደሉም፡፡ ዓይነ ደረቆች ብቻም አይደሉም፡፡ ከእውነታው ጋር እጅግ የተጣሉ፣ ‹‹ዲሉዥናል› አጥፍቶ ጠፊ ቀውሶችም ናቸው ማለት ነው፡፡
ከወያኔ የተስፋፊነትና የግዛት ነጠቃ ህልሞች ውስጥ በጣም የሚያስቀኝ በ1968 ማኒፌስቶዋ ወልቃይትና ፀለምትን የትግራይ ታሪካዊ ግዛቶች ናቸው የሚል ዶናልድ-ሌቪን-ወለድ ጉምዠታዋን ስትለቀልቅ፣ አብራ የትግራይ ግዛቶች ናቸው ብላ ያሰፈረቻቸውን ቦታዎች ሳስባቸው ነው፡፡
ወልቃይት ፀለምትን የትግራይ ግዛቶች ብላ ማወጇ በጣም ያስቀኛል ብያለሁ፡፡ የወያኔ ሽማግሌዎችን ጤንነት ከሚያጠራጥሩኝ ነገሮች መሐል ሌላኛው ደግሞ በዚሁ የ1968 ዓም ማኒፌስቷቸው ላይ አፋርም የትግራይ ግዛት ነው፣ ኩናማም የትግራይ ግዛት ነው፣ ሳሆም የትግራይ ግዛት ነው፣ አገውም የትግራይ ግዛት ነው ብለው የጨመሩትና በተለይ ከዝርዝሩ በኋላ ‹‹ወ.ዘ.ተ.›› (ይቀጥላል) ብለው ያስቀመጡት ነገር ነው፡፡
እንዴ? በታሪክ እኮ እንደነዚህ ዓይነት እውነታውና ህልሙ የተምታታበት ‹‹ዲሉዥናል›› ስብስብ ተደራጅቶና ታጥቆም፣ መንግሥት እስከመሆን ደርሶ ታይቶም አያውቅ እኮ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ፡፡ በፍጹም፡፡ አንዳንዴ ይሄ ነገራቸው ከማሳቅም አልፎ ያሳቅቀኛል፡፡ ምክንያቱም የፈጸሙት ተራ ጆክ አይደለም፡፡ የእብደት ህልማቸውን፣ በንጹሃን ዜጎች ደም ነው መሬት ላይ አውርደው የቆመሩት፡፡
አፋርን ለራሳቸው ሳይሆንላቸው ሲቀር፣ ከወሎ ላይ ገነጠሉና ‹‹አፋር›› ክልልን መሰረቱ፡፡ ግን ጊዜ ባይቀድማቸው ኖሮ ውስጥ ውስጡን እፍፍ እያሉ አብርደውና ተዘጋጅተው እንዳለሙት አፋርንም ወደ ትግራይ ሊጠቀልሏት አቆብቁበው ነበር፡፡ ኩናማና ሳሆን ሻዕቢያ ነጠቀቻቸው፡፡ ወያኔዎች በማኒፌስቷቸው ‹‹አገው›› የኛ ነው የሚሉት፣ እስከ የሃ ድረስ ለመዝለቅ አስበው ይሁን፣ ወይስ የኤርትራ አገው ነን የሚሉትን ‹‹ቢለኖችን›› ሽቅብ ሄደው ለመጠቅለል አስበው ይሁን ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡
ብቻ ግን እነዚህ እንኩቶ ቀውሶች፣ የትግራይን ህዝብ፣ በአሉሽ-አሉሽ ከንቱ ጉምዠታቸው እሣት ረመጥ ውስጥ ከትተው፣ ለ40 ዓመት ደሙን ሲያፈሱትና ሲያስፈስሱት ኖሩ፡፡ እግዜር የሥራቸውን ይስጣቸው! ከምንም በላይ በራሱ በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍ ነው የፈጸሙበት! አሁንም ደሞ ባሩዳቸውን እያጨሱለት ነው!
ኢትዮጵያውያንን ግራና ቀኝ አባልታ ደማችንን ማፍሰስና ማስፈሰስ የማይደክማት አሜሪካም፣ አማራ ከወልቃይት ሁመራ ጸለምት (‹‹ከምዕራብ ትግራይ››) ይውጣ የሚል መግለጫዋን አውጥታላቸዋለች፡፡ እንግዲህ አልሰሜን ውሻ ሶስቴ ይነክሰዋል የሚባለው ሊፈጸም ነው በትግሬዎች ላይ፡፡ ሶስተኛውን ዙር የወያኔ ደም ርጭት መርሃ-ግብር እውን ለማድረግ የሚነሳለት የትግራይ ወጣት ይገኝ እንደሆነ በጽሞና የምናየው ነው፡፡
በጣም የሚገርመኝ አንድ የአውሮፓውያን አባባል አለ፡፡ ‹‹ሁልጊዜ እውነቱን ከተናገርክ፣ ሁሌ የውሸት ታሪክ መፍጠርም፣ የፈጠርከውን ውሸት እየረሳኸው መሳሳትም አይጠበቅብህም›› የሚል፡፡ እውነቱን የሚናገር ሰው ሁሌ ያንኑ ነው የሚደጋግመው፡፡ ውሸትን እየፈጠረ የሚያወራ ግን – አንዳንዴ በመሐል ሳት ይለውና እውነቱ ያመልጠዋል፡፡
የወያኔው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በ‹‹ሞደርን አፍሪካ ጥናት ጆርናል›› ቮልዩም 40፣ ቁጥር 3 ላይ በእኛ 1994 ዓ.ም. ላይ (በግሪጎሪያን 2002) ያሳተመው የወያኔዎችን የጦር ገድል የሚያወራ የጥናት ጽሑፍ አውጥቶ ነበር፡፡ በግሌ ‹‹ገድለ-ወያኔ›› ብዬ የጠራሁትን ይህን በ Cambridge University Press የታተመ ጥናቱን እርሱ ግን “From Lash to Red Star: The Pitfalls of Counter-Insurgency in Ethiopia, 1980-82” የሚል ርዕስ ነው የሰጠው፡፡ ያው አንዳንዴ የምትፈልገውን ነገር፣ ከማትፈልገው ነገር ውስጥ ስለምታገኝ፣ ሁሉንም ነገር ማንበብ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው – በሚለው መርህ – ካነበብኩት ቆየሁ፡፡
የጥናት ጽሑፉ ከኦጋዴኑ የላሽ ዘመቻ እስከ ሰሜኑ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሰለፋቸውን ሠራዊቶችና የተከተለውን የውጊያ ታክቲኮች በማውሳት፣ የወያኔ ተጋዳላዮች እንዴት 140 ሺኅ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ጦር የሻዕቢያ አጋዥ በመሆን ብትንትኑን እንዳወጡት በጀብዱ የተሞሉ ተዛማጅ ስታቲስቲካዊ አኀዞችን ያቀርባል፡፡
ጥናቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በዚህ ጥናቱ – የቀይ ኮከብ ጥሪ የታወጀው በሶስት ክፍላተ ሀገሮች መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ እነዚህም የቀይ ኮከብ ሶስት የዘመቻ ታርጌቶች ፡- የሻዕቢያ መደበቂያ የሆነው የኤርትራ በረሃ፣ ወያኔን የደበቀው የትግራይ በረሃ፣ እና ኢዲዩንና ኢህአፓን የደበቀው የጎንደር ምድር መሆናቸውን ይናገራል፡፡
በመሆኑም ይህ የገብሩ ታረቀ ጥናት በአንድ በኩል የወያኔዎቹን ‹‹ደርግ (መንግሥቱ ኃይለማርያም) ከኢትዮጵያ ህዝብ ነጥሎ በትግሬዎች ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት እንዳወጀባቸው›› በማስመሰል – እንደ እነርሱ በውሸትና ዲሉዥን የቀወሱ ዘረኛ ‹‹ምሁሮቻቸውን›› በማሰለፍ ለዓለም የሚቀላምዱትን ዝባዝንኬ ብኩንነት የሚያጋልጥ ጥናት ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን በዚህ የጥናት ጽሑፉ ገብሩ ታረቀ ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ – ብዕሩን ሳት እያለው (ወይም ለአፍታም ሳት ሳይለው) ሁመራ የጎንደር አካል እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ ይጽፋል፡፡ በአንዱ ገጽ ላይ “Humara (Gondar)” – ‹‹ሑመራ (ጎንደር)›› – በማለት ሑመራን የጎንደር አካል አድርጎ በቅንፍ የገለጸበትን ገጽ አያይዤያታለሁ፡፡ እውነት ተደብቆ አይቀርም፡፡ እውነት ሳት ብሎም ይወጣል፡፡ ስለ እውነት እንነጋገርና እውነተኛ መፍትሄ እንፈልግ፡፡ ውሸትን ሺህ ጊዜ ቢደጋግሙት፣ እውነት አይሆንም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic