የአሜሪካ ነገር፤ አንቺን ሲልሽ ሲልሽ…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
አሜሪካ ስንት ወንጀል፣ ሰቆቃ እና የመብት ጥሰት ሲፈጽም በኖረው የህውሃ አገዛዝ ላይ ያልጣለችውን ማዕቀብ ዛሬ በዚህ ደረጃ እርምጃ መውሰዷ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነቷን አያሳይም። ለነገሩ በአለም ላይ ከተካሄዱ ብዙ የዘር ተኮር ጭፍጨፉዎች ጀርባ አሜሪካ የተጫወተቻቸውን ሚናዎች በመጽሐፍ የተሰነደ ስለሆነ ማንበብ ይቻላል።
ይልቅስ በትግራይ ላይ ከተፈጸመው የመብት ጥሰት ጋር በማስታከክ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ለኢትዮጵያ የደገሰላት ሌላ ጣጣ ያለ መሆኑን ግን ይህ ማዕቀብ ያሳብቃል። አሜሪካ ከአገር ውስጥ ሌላ አገር የማዋለድ ብዙ ሚሽኖችን የፈጸመች አገር ነች። ከዪጎዝላቪያ እስከ ሱዳን፤ ብዙ አዳዲስ አገሮችን አዋልዳለች። ከትልቋ ሱዳን ውስጥ ደብቡ ሱዳንን፣ ከኢትዮጵያ ኤርትራን ያዋለደችው አሜሪካ ኢትዮጵያን ሁለተኛ ልጅ ለማዋለድ ያቆበቆበች ትመስላለች። እንዲህ ያለውን አደጋ በኤምባሲ ደጃፍ በሚደረጉ ሰልፎች እና ተቃውሞዎች ማስቆም አይቻልም። ጥንቃቄ በተሞላው የዲፕሎማስ ሥራ እና የፖለቲካ ውሳኔዎች እንጂ።
አሜሪካ በሰልፍ ከኢትዮጵያ ላይ እጅሽን አንሺ ስለተባለች አታነሳም፤ ጫኚም ስለተባለች አትጭንም። እራሷን ብቻ የምታደምጥ ጉልበተኛ አገር ነች። ብዙ አገራትን፤ ሶሪያ፣ የመንን፣ ሊቢያን፣ ኢራቅን እና ሌሎች አገራትን በጉልበት አፍርሳለች። ማንም አላስቆማትም። የኢራቅ ሕዝብ ከጦርነቱ በፊት ከሳዳም ጎን ቆሞ አሜሪካንን በሚያወግዙ ሰልፎች ባንዲራዋን እያቃጠለ ይራገም ነበር። እራሳችንን ለዛ አደጋ ላለማመቻቸን ጥበብ እና ጥንቃቄ የተሞላው ዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ሥራ ያስፈልጋል።