>
5:18 pm - Wednesday June 15, 6416

ለአማራው ህዝብ የተደገሰለት ....! (አሰፋ ሀይሉ)

ለአማራው ህዝብ የተደገሰለት ….!

አሰፋ ሀይሉ
 
ይህ የቁርጥ ቀን መድረስ ዜና ነው! 
ጆሮ ያለው ይስማ! 

የኢዜማ ፓርቲ የቅርብ ተባባሪና ደጋፊ መሆኑን የማውቀው የጥንቱ የሎውስኩል ወዳጄ ተክለሚካኤል አበበ፣ ወልቃይት ሁመራን በተመለከተ የሰጠው አስተያየት፣ ደጋግሜ ስለው የቆየሁትን የአብይ አህመድንና የኢዜማን ጋብቻ ዓላማና ግብ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦልኛል፡፡ ተክለሚካኤል በዚህ አስተያየቱ፡- ‹‹የአማራ ልዩ ሀይል ከምእራብ ትግራይ መልቀቅ.. በግድ መፈጸም ያለበት ጉዳይ ነው›› ይልና፣ ‹‹አለበለዚያ›› ግን ‹‹ወልቃይት ጠገዴን.. በዘላቂነት እሥኪወሠን በፌዴራል መንግሥቱ ማሥተዳደር›› ዓይነተኛ አማራጭ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡
ይቀጥልና ‹‹የምእራብ ትግራይ መነጠቅ›› ብሎ ድርጊቱን ንጥቂያ በሚል ቃል በመሰየም ‹‹የኢትዮጵያን ሕግጋት ይጥሣል›› በማለት – የአሜሪካውን መግለጫ በመደገፍ ኤርትራንም የአማራ ክልል ሀይሎችንም የሚያወግዝ አስተያየቱን ያስቀምጣል፡፡ በመጨረሻ የሰጠው አስተያየት ሁሉንም ያጠቃልለዋል፡- ከላይ ‹‹በግድ መፈጸም ያለበት ጉዳይ ነው›› የሚለውን ‹‹የአማራ ልዩ ሀይል ከምእራብ ትግራይ መልቀቅ›› በተለመከተ፣ ‹‹መጪው ምርጫ ወሳኝ ነው›› በማለት ይደመድማል፡፡
ወሳኝነቱን ሲያስረዳ ደግሞ የአማራን ልዩ ሀይል ከምእራብ ትግራይ በግድ የማስወጣቱን ተግባር ለመፈጸም ‹‹ለመጪው መንግሥት አቅም ይሰጠዋል›› ስለዚህ መጪውን የአማራን ልዩ ሀይል (እና የኤርትራን ጦር ‹‹ከምእራብ ትግራይ››) በግድ የሚያስወጣውን መንግሥት ‹‹እንምረጥ፣ እናስመርጥ፣ እና አገሪቱንም ከችግር እናውጣ፡፡›› ሲል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በአካል ካገኘሁት ቢያንስ 20 ዓመት የተቆጠሩትን የጥንቱን የካምፓስ ወዳጄን ተክለሚካኤልን በዚህ ደረጃ ወርዶ ፀረ-አማራ አቋሙን እንዲህ በይፋ ያራምዳል የሚል ግምት ኖሮኝ አያውቅም ነበር በእውነት፡፡ ያሳዝናል፡፡ በመሠረቱ ማንም ሰው የመሰለውን አስተያየትና አቋም ማራመድ መብቶ መሆኑን መናገር አይጠበቅብኝም፡፡ እኔም አስተያየቴን እየሰጠሁ ያለሁት በተመሳሳይ ምክንያት ነውና፡፡
በሌላ በኩል ግን በዚህ አጋጣሚ ተክለሚካኤልን ምንም ሽፍንፍንና ክንብንብ ስለሌለው ግልጽ አስተያየቱ እጅግ ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ ምክንያቱም ደግሜ ደጋግሜ የአማራውን ሕዝብ ከአብይና ከኦሮሙማው ደባ፣ ከኢዜማ የጠላትነት ተግባር ደጋግሜ ሳስጠነቅቅ የቆየሁትን ሀሳብ እንዲህ ፊት ለፊት አውጥቶ በማስቀመጥ፣ መረዳቴ ትክክል እንደሆነ ስላረጋገጠልኝ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እኔም ራሴ በግሌ አብይ አህመድ በትግራይ ላይ ጦርነት ሲከፍት የአማራውን አብሮ መሰለፍ ወዲያውና ያለምነብም ማስተባበል ስቃወም እንደነበር ይታወቃል፡፡ የእኔ ተቃውሞ ምክንያት ግን የኦሮሙማውን የተረኛ ገዢነት ዕቅድና ሸፍጥ ስለገባኝና፣ አብይ አህመድንና በሁሉ ነገር በወያኔ አምሳል ተጠፍጥፎ የተሰራውን ኦህዴድንና ሰዎቹን አምኖ የአማራው ልጅ ጦርነት ውስጥ ከገባ በኋላ፣ ደሙን በበረሃ ዘርቶም፣ ከጎረቤቱ ጋር ደም ተቃብቶም፣ የሚገባበትን እጅግ አደገኛ አጣብቂኝና ደም መፋሰስ በመረዳት ነበር፡፡
በወቅቱ ‹‹ዛሬ ከመከላከያ ጎን እቆማለሁ ያላችሁ ሰዎች፣ ነገ አብይ አህመድ አማራው ላይ ጦሩን ሲያዘምት ከመከላከያው ጎን ትቆማላችሁ ወይ?›› ብዬ ስጠይቅ፣ ለምን እንዲህ አልክ ብሎ አስተውሎ ከመጠየቅ ይልቅ፣ ሟርት ተናጋሪና የወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች አፍቃሪ አድርጎ የኮነነኝ የፌስቡክ ተሰላፊ ብዛት ይገርም ነበር፡፡
ደግሜ ደጋግሜ ላሳደገኝና በስሜ፣ በአምሳሌ፣ በሁለመናዬ ከነሰብዕናዬ ቀርጾ ከማህጸኑ ላወጣኝ ለአማራው ህዝቤ የተናገርኩትን ማስጠንቀቂያ ይኸው ጊዜ እውነት መሆኑን እያሳየን ነው፡፡ አሁን በተጻራሪ መደብ ላይ በቆምነው በወንድሜ ተክለሚካኤል የተነገረውን ይህንኑ ሃሳብ በአሜሪካም በኩል ሳይመጣም ደጋግሜ መናገሬ ይታወቃል፡፡ ከመከራ የሚመከር፣ ከቃልና ዕውቀት አይመከር ሆኖ ታለፈ፡፡
አሁን እዚህ ደርሰናል፡፡ በአሜሪካ አንደበት የተደገሰልን እየተነገረን ነው፡፡ ከኢዜማው ደጋፊ ከተክለሚካኤል አፍ በአስተያየት መልክ እየተነገረን ነው፡፡ እስከዛሬም አንሰማ ብለን እንጂ ተናግረውት የጨረሱት ቢሆንም፣ ነገና ከነገ ወዲያ በግልጽ ከእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና፣ ከእነ አብይ አህመድና የኦሮሙማ ጭፍሮቹ አንደበት በአማራ ላይ የታወጀውን ሰልፍ የምንሰማበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ የማያውቅ ደደብ ሁን ብሎ ፈጣሪ የረገመው ፍጡር ብቻ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
‹‹ተኩላውን ሲያስቡ፣ በትሩን ያዘጋጁለታል›› ይላሉ ሩሲያኖች፡፡ አማራው ወገኔ ሰምተሃል፡፡ ዛሬ ንቃና ለነገህ ተዘጋጅ፡፡ ምከርና የሚሆነውን ጠብቅ፡፡ ፈጣሪ ከእውነት ጋር ነው፡፡ ፈጣሪ ከእኛ ጋር እንደሚሆን እምነቴ የፀና ነው፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic